Biography Catagories

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ዘሪቱ ከበደ

 

ዘሪቱ ከበደ ወልደጊዮርጊስ

ድምጻዊት፤ የዘፈን ግጥም ደራሲና አዘጋጅ፤ የማህበረሰብ ተቆርቋሪ

 

 

ዘሪቱ ከበደ“ኦ ምን አለፋኝ መልሱ ከጠፋኝ፣ እርሱ አይሳሳት ሁሉም በምክንያት፣ የኔም አይን አይቷል እርሱ ያበራው፣ ሰሪ አይበልጥም ወይ ኦ ከተሰራው፡፡”

የኔም አይን አይቷል የሚል የዘፈን ስንኝ


ገና በልጅነት እድሜየ ነው፡፡ ከሙዚቃ ጋር በፍቅር የወደቅሁት፡፡ የተወለድኩትም ሆነ ያደግሁት በአዲስ አበባ ሲሆን የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት በጥብቅ ቤተሰብ ቁጥጥር ውስጥ ነበር፡፡ አባቴ የኪነ-ሕንፃ ባለሙያ ነበር፡፡ እናቴ ደግሞ የቤት እመቤት ነበረች፡፡ ተገዳ ሳይሆን መርጣ፡፡ ሁለት ታናናሽ እህቶች ያሉኝ ሲሀን፣ አባቴ ከመጀመሪያው ትዳሩና ከቀድሞው የፍቅር ግንኙነቱ የወለዳቸው ሌሎች ታላላቅ እህቶችም አሉኝ፡፡ ወላጆቼ በትምህርት አስፈላጊነት ላይ የማያውላውል አቋም ነበራቸው፡፡ ጊዜዬን የማሳልፈው፣ ቤት ውስጥ አልያም ትምህርት ቤት ብቻ ነበር፡፡ የሚመስለኝ፡፡ ከጥናት ውጭ ሌላ ነገር እንድሰራ አምብዛም አይፈቀድልኝም፡፡ ነፃነት የማገኘው አያቶቼ ቤት ስሄድ ብቻ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ሰፊ ገጽታ እንድገነዘብ ያስቻሉኝ አያቶቼ፣ አርአያዎቼ ናቸው፡፡

ወላጆቼ ግሩም የሙዚቃ አፍቃሪዎች ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያዊያንና የሌሎች አገራት ከያኒያን የሙዚቃ የሙዚቃ ስብስቡንም አያሰሰኩ ሳዳምጥ፣ ከድንቅ ከያኒያን ከአዘፋፈን ስልቶችና ከድምጽ ቅላፄዎች ጋር መተዋወቅ ቻልኩ፡፡ በእነዚህ ስብስቦች አማካኝነት ነው፡፡ በውስጤ የነበረውን ድምፃዊ የመሆን ፍላጎት በወጉ ማጤን የቻልኩት፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ መዝፈን ጀመርኩ፡፡ ከዚያም የራሴን የዘፈን ግጥሞች መፃፍ ቀጠልኩ፡፡ ይሁም ሆኖ ግን ማህበረሰቡ ዘፈንን እንደሙያ እንደማይቆጥረው አውቅ ስለነበር፣ በውስጤ የታመቀውን ዘፋን የመሆን ጽኑ ፍላጎንንና ሕልሜን፣ ለማንም ሰው ትንፍሽ አላልኩም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአባባይ የዘፈንኩት፣ የወላጆች ቀን በዓል ላይ የስምንተኛን ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር፡፡ በወቅቱ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች የሙዚቃ ባንድ ታጅቤ ያነቀንኩትን ዘፈን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት ወላጆቼ፣ በችሎታዬ ኩራት ተሰምቷቸው ነበር፡፡ በተለይ እናቴ የፍላጎቴ ሙዚቃ እንደሆነ ስለገባት፣ ሙዚቀኛ የመሆን ህልሜንና በመስኩ ርቄ የመጓዝ ውሳኔዬን ደገፈችልኝ፡፡ አባቴ ግን ነገሩን በዚያ መንገድ አላየውምና ጊዜዬንና እምቅ አቅሜን በከንቱ እያባከንኩ ነበር የመሰለው፡፡ አሳዛኙ ነገር ገና በሙዚቃ ገፍቼ ሳልሄድና ስኬታማ መሆኔን ሳያይ የ16 ዓመት ልጅ ሆኜ አባቴ በሞት ተለየኝ፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ ግን፣ እንደ ቀድሞው የመዝፈን ዕድል አላገኘሁም፡፡ ትምህርት ቤቱ “ዓለማዊ ዘፈን” በሚጠራው ሙዚቃዎች ላይ፣ ጥብቅ አቋም ነበረውና አብዛኛውን ጊዜዬን ሙዚቃ ለማድመጥና የዘፈን ግጥሞችን ለመፃፍ አዋልኩት፡፡ በዚህ ወቅት የፃፍኳቸው አንዳንዶቹ ግጥሞች፣ የኋላ ኋላም በመጀመሪያው አልበሜ ውስጥ የመካተት ዕድል አግኝተዋል፡፡

ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ፣ ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር መዝፈን ጀመርኩ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትያትር የማጥናት ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ሆኖም አልተሳካልኝም፡፡ በሱ ፋንታ የንግድ ትምህርት እንዳጠና በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተመደብኩኝ፡፡ ሕልሜ ግን ይሄ አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ እንደምንም ለመማር መጣሬ አልቀረም፡፡ ያውም ከአዲስ አበባ አዳማ እየተመላለስኩ፡፡ አዳማ ትምህርቴን እከታተልና፣ ከባንዱ ጋር ለመጫወት ደግሞ ተመልሼ ወደ አዲስ አበባ እመጣ ነበር፡፡ ሆኖ ከስድስት ወር በላይ መዝለቅ አልቻልኩም፡፡ ትምህርቱን አቋርጬ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ከልቤ በምወዳችው የሙዚቃና የፊልም ሙያዎች ላይ ለመሰማራት ወሰንኩ፡፡ ወዲያው በትወናና በፊልም ጽሁፍ ለመሰልጠን አርት አካዳሚ ገባሁ፡፡ የሙዚቃ ትምህርትም በግሌ መውሰድ ጀመርኩ፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር፣ ሰዎች የራሴን አልበም እንዳወጣ ያበረታቱኝ የጀመሩት፡፡ ለመሞከር የምችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፡፡ የሚል ስሜት ስለነበረኝ ገፋሁበት፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ቀን ከሌት ሰርቼ ያዘጋጀሁትን የመጀመሪያ አልበሜን፣ ዘሪቱ” በሚል ስያሜ በ1997 ዓ.ም ለአድማጭ ጆሮ አደረስኩ፡፡ የሙዚቃ ስብስቡ የያኔውን ማንነቴን በቅጡ ያንፀባርቃል፡፡ ዘፋኞቹ ከሕይወቴና ከኑሮዬ የተቀዱ ከእለት ተዕለት ሕይወቴና ገጠመኞቼ የተወለዱ ናቸው፡፡ አልበሜ እንደወጣ፣ ከመቅጽበት ስሜ በመላ አገሪቱ ታወቀ ዘፈኖቼ በየመንገዱ፣ በየቤቱና በየምግብ ቤቱ ሲደመጥ መስማት፣ አልበም፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የምር ቦታ ለማግኘት መቻሌን ማመን አቃተኝ፡፡

ብዙም ሳልቆይ፣ በመላው ኢትዮጵያ “ጎዞ ዘሪቱ” የተሰኘ የሙዚቃ ጉዞ ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ በከያኒነት የተቀበሏችሁና የሚወዷችሁ በየትኛውም ሥፍራ ያሉ ሰዎች ሁሉ፣ እንዲህ በኮንሰርት መልክ በአካል አግኝተው ሊያዩዋችሁ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃን እንደ ትርፍ ማግኛ ሥራ መስራት ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ እናም ዝግጅቱን ለማሳካት ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ነበረብኝ፡፡ በተመልካቾች ላይ ከፈጠረው የእርካታ ስሜት አንፃር ሲታይ፣ ሙዚቃ ጉዞው ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ዝግጅቴን እንዳጠናቀቅሁ ደግሞ፣ ሙዚቃዬን ይዤ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ተጉዣለሁ፡፡

የሙዚቃ ሥራዬ በአንድ ዘርፍ እንዲመደብ ወይም እንዲፈረጅ አልፈልግም፡፡ ሙዚቃዬን የሕይወቴና የገጠመኞቼ ነፀብራቅ እንደመሆኑ፣ በአንድ የተወሰነ ዘውግ ወይም ዘይቤ አልመድበውም፡፡ አልበሜ ከወጣ በኋላ፣ ከበርካታ የሙዚቃ ቡድኖች ከያኒያን ጋር በመተባበር ዘፈኖች ለማሳተምም ባሻገር፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሙዚቃ ሥራዎችን አቅርቤአለሁ፡፡ እስካሁን በተለያዩ የሙዚቃ ዘይቤዎች ከሮክ እስከ ፋንክ፣ ከአኩስቲክ እስከ ጃዝ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ አሁን ምናልባት ለሁለተኛ አልበሜ ዝግጁ ሳልሆን አልቀርም፡፡ ይሄኛውም ስብስብ የእስከዛሬውን የሙዚቃ ጉዞዬን የሚያንፀባርቅ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ፣ ከልቤ ወደምወደው የፊልም ሙያ ገብቻለሁ፡፡ በልጅነቴ በፊልሞች ላይ የመስራት ትልቅ ህልም ነበረኝ፡፡ እንደውም ራሴ በፈጠርከት ምናባዊ የፊልም ድርጅት ውስጥ፣ ራሴን በተዋናይነት እመርጥ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከሆሊላንድ አርት አካዳሚ ጓደኞቼ ጋር በቅርቡ አንድ ፊል ሰርተን ለእይታ አብቅተናል፡፡ በውስጧ ያለውን እምቅ ኃይል ለማግኘት በጉዞ ላይ ስላለች ልጃገረድ የሚተርከውና “ቀሚስ የለበሱ እለት” የተሰኘው ይህ ፊልም፣ ስለጀግንነትና ፈተናዎችን ተጋፍጦ ስለማሸነፍ የሚያሳይ ሲሆን፣ ልጃገረዶቸች አቅማችን አውጥተው እንዲጠቀሙበት ያበረታታቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በትወና ሙያን በጀመርኩበት በዚህ ፊልም ላይ  በአቀናባሪነትና የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ በመጫወትም ተሳትፌአለሁ፡፡ ወደ ፊትም ፉልም በመፃፍና በማዘጋጀት መቀጠል እሻለሁ፡፡ ወደ ፊት ፊልሞችን ለማዘጋጀት እሞክራለሁ፡፡

ከቀድሞም ጀምሮ ለሕብረሰብ የመቆርቆር ጠንካራ ቁርጠኝነት ነበረኝ፡፡ ወገንን ለማገልገል አምናለሁ፡፡ መርዳት የምችልምበት አጋጣሚ ባገኘሁ ጊዜ ሁሉ ሰዎችን ከመርዳት ወደ ኋላ አልልም፡፡ በመዲናዋ አረንጓዴያማ አካባቢዎች በማደጌ ፣ ለዛፎችና ተፈጥሮ በእለት ተእለት ሕይወታችን ለምትለግሰን ውበት ከፍተና አድናቆት አለኝ፡፡ ይሄ ነው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢንሺየቲቭ ፈር ቀዳጅ ያደረገኝ፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ ዓላማ፣ ለአከባቢ እንክብካቤ ማድረግ ስላለው ፋይዳ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን፣ ከእውቁ ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህና ከጋዜጠኛ መሀመድ ካሳ ጋር በመተባበር ነው የተሳተፍኩት፡፡ አረንጓዴ ኢትዮጵያ ሕብረሰተቡ ዛፍ የመትከልና የመንከባከብ ባህል እንዲያዳብር ለማበረታታት ያለመ “ሙዚቃ” ለአረንጓዴነት” የተሰኘ ኮንሰርት በ2002 ዓ.ም አቀርቧል፡፡ እኔ በግሌ ዛፎችን እወዳለሁ፡፡ ለሁላችንም ግን እነዚህ ዛፎች በብዛት ያስፈልጉናል፡፡

እንደ ብሪቲሽ ካውንስል የአየር ንብረት ተወካይነቴ፣ አርቴፊሻል” የሚል ዜማ ሰርቼ አቀንቅኛለሁ፡፡ ዜማው በቴክኖሎጂ የበላይነትና በዘመኑ ጥድፊያ የተሞላበት ሕይወት ሳበቢያ ለተፈጥሮና ለሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ እውነታዎች ጊዜ ማጣታችንን የሚሞግት ሲሆን፣ ሕብረተሰቡን ከተጫነበት የድንዛዜ ስሜት ለማንቃት የተዘጋጀ ነው፡፡ ተሳትፎዬ በአከባቢ ጥበቃ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሕብረተሰቡ በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በሚደረጉ ማህበራዊ ቅስቀሳዎች ላይም ሥሰራ ቆይቻለሁ፡፡ የዩኒሴፍ ተወካይ በመሆንም፣ ለሕፃናት የእናት ጡትን ብቻ መመገብ ስላለው ፋይዳ አስተዋውቃለሁ፡፡  የሰዎች ኑሮ እንዲቀየር በማገዝ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እስከቻልኩ ድረስ፣ ሁል ጊዜም በእንዲህ አይነቶቱ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ተስታን ያጎናጽፈኛል፡፡

 በቅርቡ ደግሞ “ተረት ተረት” የተሰኘ ሌላ ፕሮጀክት ጀምሬያለሁ፡፡ በዚህ ፕሮጀክት፣ ለኢትዮጵያ ሕፃናት የሚሆኑ ታሪኮችን አሰባስበን በመፃፍ ለማሳተም ያቀድን ሲሆን፣ በመጪው ዓመት ለንባብ እንደሚበቃ ተስፋ አለን፡፡

 ባለትዳርና የልጆች እናት እንደመሆኔ ለቤተሰብ ሕይወት በእጅጉ እጨነቃለሁ፡፡ ቤተሰባዊ ሕይወቴንና ሙያዬን አመጣጥኜ ለመምራትም እጥራለሁ፡፡ ባለቤቴ  ላካቸው መንግስቱ ወርቁ ይባላል፡፡ ሶስት ወርቅ የሆኑ ልጆችም አሉኝ ክርስቲያን፣ መንግስቱና ፀሎት ብለናቸዋል፡፡ በሕይወት ዘመኔ ስህተቶችን ሰርቻለሁ፣ አደገኛ ሁኔታዎችንም ተጋፍጫለሁ፡፡ ከእነዚህ ተሞክሮዎች ብዙ ከመማሬ ባሻገር የተሸለ ሰውም እድርገውኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በሚስትነትና በእናትነት የሴትነት ሚናዬን ለመወጣት ስሞክር ያገኘሁት እውቅና  ይበልጣል፡፡

አብዛኛው ብርታት የማገኝ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባለኝ ቁርኝት ነው፡፡ በየትኛው ኃይማኖታዊ ተቋም አባል ያልሆንኩ ክርስቲያን ነኝ፡፡ ስለዚህ በጠንካራ እምነቴ ነው የምመራው፡፡ እስካሁን ባለው ሕይወቴ፣ ታላቁ ስኬቴ የምለውን አዕምሮአዊ (“ውስጣዊ) ሰላም ለመቀዳጃ ችያለሁ፡፡ ለእኔ ይሄ ከየትኛው ዲግሪ፣ ሽልማት ገንዘብና እውቅና ሊገኝ የማይችል ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ የአዕምሮ ሰላምና የመንፈስ እርካታ ማግኘት የሚቻለው፣ ከእግዚአብሔር ጋር በሚፈጠር እውነተኛ ግንኙነት ብቻ ነውና፡፡

ሁላችንም እኛ ብቻ እናሳካው ዘንድ ለታጨ አንድ የተለየ አላማ ታስበን መፈጠራችንን ማወቅ ይገባናል፡፡ እኔ ከዚህ ዓይነቱ ነፃነትን የሚያቀዳጅ እውቀት ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ጥላቻ የሚባል ነገር ፈጽሞ አያስፈልግም በጀግንነት፣ በቅንነትና፣ በትሁትነት አምናለሁ፡፡ ፈጽሞ የማያረጅ ብቸኛ ግንኙነት መሰረቱ እግዚአብሔር ነውና ከሁሉም በላይ በእሱ አምናለሁ፡፡

በዙሪያ የማያቸው ነገሮች ሁሉ መነቃቃትን ይፈጥሩልኛል፡፡ እስካሁን ድረስ በሕይወትና ሙያዬን የመራሁበት መንገድም ያኮራኛል፡፡ ሕልሜን ተከትዬ የመጓዝና አዳዲስ ፈተናዎችን የመጋፈጥ ችሎታን ያጎናጽፉኝ ጥሩ ቀልብና ስሜት ናቸው፡፡ ሕይወት በቀጣይ ወዴት እንደምታመራኝ አላውቅም፡፡ በእርግጠኝነት የማውቀው ከአሁን በኋላ ሌሎች ብዙ ፊልሞችና የሙዚቃ አልበሞች እንደማበረክት እንዲሁም በጣም ብዙ በሚባሉ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደምሳተፍ ነው፡፡

 

“ሁላችንም፣ እኛ ብቻ እናሳካው ዘንድ ለታጨ አንድ የተለየ ዓላማ ታስበን መፈጠራችንን ማወቅ ይገባናል፡፡ እኔ፣ ከዚህ ዓይነቱ ነፃነትን የሚያቀዳጅ እውቀት ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡”