Biography Catagories

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ካፒቴን አምሳለ ጓሉ እንደኛነው

 

ካፒቴን አምሳለ ጓሉ እንደኛነው

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የንገደኞች አውሮፕላን ዋና አብራሪ

Captain Amsale“የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ት/ቤት የመግቢያ ፈተናን ወስጃለሁ፡፡ ሆኖም ሳላልፍ ቀረሁ አብዛኞቹ በመጀመሪያ ሙከራቸው ይወድቁ ነበር፡፡ በእርግጥ በመግቢያ ፈተናው መውደቄ ተስፋ አለመቁረጥንና የበለጠ መጣርን አስተምሮኛል፡፡

 

በበረራ መማረክ የጀመርኩት ልጆች ሳለን አባቴ እኔና እህቶቼን ወደ አየር ማረፊያ እየወሰደ አውሮፕላን ሲያርፍና ሲነሳ ያሳየን በነበረበት ወቅት ነው፡፡ አባቴ አውሮፕላኑን የሚያሳየን የአብራሪነት ፍላጎት እንዲቀሰቀስብን አስቦ አይመስለኝም፡፡ በእኔ ልብ ውስጥ የአብራሪነት ፍላጎት ያደረው ግን በዛ ጊዜ ነበር፡፡ ግዙፎቹ አውሮፕላኖች ሰማዩን እየሰነጠቁ ሲከንፉ በደስታ ተጥለቅልቀን መመልከታችን፣አባታችንን ሳይከነክነው እንደማይቀር አስባለው፡፡ አባታችን ሁላችንም እንደየፍላጎታችን እንድጓዝ ከማበረታታት ችላ ያለበት ጊዜ ባይኖርም፣ ያ የየሳምንቱ የአየር ማረፊያው ጉብኝታችን እንዴት የበኩር ልጅ የዕድሜ ልክ ሕይወትና ሙያ ሊሆን እንዲቻል አሁንም ድረስ ይገርመዋል፡፡

የተወለድኩት በ1969 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ነበር፡፡ አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቼ፣ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ ደህና ገቢ የነበራቸውን ወላጆቼን በአርአያነት እየተመለከትኩ ነው ያደግሁት፡፡ አባትና እናቴ በራሴ እንድተማመንና ህልሜን ለማሳካት እንድጣጣር ያበረታቱኝ ነበር፡፡ ሴት በመሆንሽ ገደብሽ እዚህ ድረስ ነው” ቢለውኝ አያውቁም፡፡ ያደግሁበት ማህበረሰብም፣ ለዛሬ ማንነቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እያንዳንዱ የማህበረሰቡ አባል እንደራሱ ልጅ ነበር የሚያየኝ፡፡ የእለተ እለት እድገቴን ከመከታተልም ባሻገር በትምህርት በርትቼ እንደገፋ ያበረታቱኝ ነበር፡፡ አብራሪ የመሆን ፍላጎቴን ሁሉም ያውቁ ስለነበር የማያደንቀኝ አልነበረም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ፣ ሁለት ታንዛኒያውያን ;(አንድ ወንድና አንድ ሴት) የበረራ ሰልጣኞች እኛም ሰፈር ይኖሩ ነበር፡፡ እናም በዩኒፎርማቸው ተማርኬ ፈዝዤ እመለከታቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

የሶስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ቤተሰቦቼ ወደ አዲስ አበባ ስለመጡ የመጀመሪያው ደረጃ ትምህርቴን በአሳይ የሕዝብ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተልኩ፡፡ በ1987 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ገብቼ ስነ ሕንፃ አርክቴክቸር) ትምህርት መማር ጀመርኩ፡፡ እንዲያውም ሆኖ ግን የልጅነት ሕልሜ አልዘነጋሁትም ነበር፡፡ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመግቢያ ፈተናን ወስጄ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተፈታኞች በመጀመሪያ ሙከራቸው ይወድቁ ነበር፡፡ አለም ሳላልፍ ቀረሁ፡፡ በእርግጥ በመግቢያ ፈተናው መውደቄ ተስፋ አለመቁረጥንና የበለጠ መጣርን አስተምሮኛል፡፡ የሥነ-ሕንፃ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ የመግቢያ ፈተናን በድጋሚ ወሰድኩና አለፍኩ፡፡

ክፋቱ ግን አስቸጋሪ ሰዓት ላይ ሆነብኝ፡፡ የበረራ ስልጠናው በሚጀመርበት በመጋቢት ወር 1992 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነበር፡፡ እናም ለዓመታት የለፋሁበትን ትምህርተ ገደል እንደመክተት ሆነብኝ፡፡ የማታ ማታ ግን በሐምሌ 1992 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ስልጠናውን እንድጀምር ተፈቀደልኝ፡፡

ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደውን ስልጠና አጠናቅቄ በአብራሪነት የተመረቅሁት በሕዳር 1994 ዓ.ም ሲሆን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ተኩል በዘለቀው የሥራ ዘመኔም በረዳት አብራሪነት ለ4 ሺህ 475 ሰዓታት አውሮፕላኖችን አብርሪያለሁ፡፡ ከዚያም ለተለያዩ ፈተናዎች ምዘናዎችና ግምገማዎች በኋላ እድገት ተሰጥቶኝ በዋና አብራሪነት (የካፒቴን) ስልጠና ጀመርኩኝ፡፡ አስፈላጊውን የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና እንዳጠናቀቅሁም ከመጀመሪያ በራሪዬ ከሰባት ዓመት ተኩል በኋላ 2002 ዓ.ም ካፒቴን ሆንኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከአንድ ሺችሉ ህ በላይ ሰዓታት አብርሬአለሁ፡፡

እናንተም ወንዶች የገነኑበት ሙያ ውስጥ ገብታችሁ ልትገኙበት እንደምትችሉ አትጠራጠሩ፡፡ ለምን አውሮፕላን አብራሪነት አሊያም ጠቅላይ ሚኒስትርነት አይሆንም ምንም የማይቻል ነገር የለም፡፡

 የሰለጠንኩትም ሆነ የሰራሁት በበርካታ ዓይነት አውሮፕላኖች ነው፡፡ ከእነሱም መካከል ፎከር 50፣ ዳሽ 8 Q -400፣ ቦይንግ 757 እና 767 ይገኙበታል፡፡

Captain Amsale

 

እኔ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት አብራሪ አይደለሁም፡፡ የመጀመሪያዋ አብራሪ (1925) ሙሉ እመቤት እምሩ ሲሆኑ እሳቸውን ተከትልም በ1950ዎቹ አመታት አሰገደች አባተ ሁለተኛዋ ሴት አብራሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከዚያም ሌሎች ሶስት ሴቶች አብራሪ ከሆኑ በኋላ እኔ ስድስተኛዋ አብራሪ የሆንኩት፡፡ ነገር ግን ለካፒቴንነት ማዕረግ የሚያበቃውን ሙሉ ስልጠናና መመዘኛ ወሰዶ በማጠናቀቅ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አብራሪ የሆንኩት ግን እኔ ነኝ፡፡ የሚያኮራኝ የመጀመሪያዋ ሴት ካፒቴን መሆኔ ሳይሆን አሰልቺውንና እልህ አስጨራሹን የሥልጠናና ግምገማ ሂደት በስኬት ተወጥቼ፣ የሙያየ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ መቻሌ ነው፡፡ እምደሚመስለኝ ስኬታማ ለመሆን ያገዘኝ በራሴ ላይ ያለኝ እምነትና ተስፋ አለመቁረጤ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በጣት የሚቆጠሩ ሴት አብራሪዎች ለመኖራቸው በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ አብዛኛው ሰው አብራሪነትን እንደወንድ ሥራ አድርጎ መቁጠሩ፣ ሌላው ደግሞ ለአብራሪነት የሚጠየቀው የቁመት መስፈርት 1.7 ሜትር ሲሆን ብዙዎቹ እህቶቻችን ደግሞ ያን ያህል ረዥም አለመሆናቸው ይመስለኛል፡፡ ፆታዬ ምንም ዓይነት መሰናክል ጋርጦብኝ ያውቃልን ብዬ አላስብም፡፡ አምዳምድ ፆታ እድልዎና አሉታዊ አስተያየቶች ቢደርስብኝ በጄ ብዬ ስለማልቀበልና እንደቁምነገር ስለማልቆጥራቸው አስጨንቀውኝ አያውቁም፡፡ ሕብረተሰብ በሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር አይለወጥም፣ ነገር ግን የራስን አመለካከት የአስተሳሰብ ዘይቤ መለወጥ ይቻላል፡፡ እናም በጥንካሬና በትጋት በመበርታት ሕልምን ከግብ ማድረስ ይቻላል፡፡  ፈተና በገጠመኝ ጊዜ ከፆታዬ ጋር አላገናኘውም፡፡ ይልቁንም በሙያና በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙና መታለፍ ያለባቸው ፈተናዎች እንደሆነ አድርጌ ነው የማሳስባቸው፡፡

ትልቁ ፈተናዬ የነበረው ልጆቼን ማሳደግ ነው፡፡ ሙያው በአጠቃላይ መፈናፈኛ የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው ከቤተሰቦቼ እንድለይ ያስገድደኛል፡፡ አንዳንዴ ከቤት ውጭ አንድ ሳምንት የማሳለፍ ጊዜ አለ፡፡ ነገር ግን ጥሎ አይጥልም እንዲሉ ጠንካራ ድጋፍ የሚያደርግልኝ ባለቤት ሰጥቶኛል፡፡ በአየር መንገዱ ደንብ መሰረት ፣ ሴት ነፍሰ ጡር ስትሆን በረራ እንታቆም ትገደዳለች፡፡ እኔም በእርግዝናዬ ወቅት የጀማሪ አብራሪዎች መምህር በመሆን ሰርቻለሁ፡፡ ታዲያ ከረዥም እረፍት በኃላ ወደ በረራ ሥራ ስመለስ ብቃቴን ማደስና አውሮፕላን በሚመስለው የመለማመጃ ጣቢያ ሲሙሌተር ላይ እንደገና መሰልጠን ይጠበቅብኛል፡፡

አሁን የልጅነት ሕልሜን ማሳካት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፡፡ ወደፊት በሞያዬ ቦይንግ 777 እና 787 የመሳሰሉትን ትላልቅ አውሮፕላኖች በካፒቴንነት ለማብረር እሻለሁ፣ በቤተሰባዊ ሕይወቴ ደግሞ ልጆቼ አድገውና ስኬታማ ሆነው ለማየት እመኛለሁ፡፡ በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሕይወት ታሪኬን፣ ተመክሮዬንና ስኬቴን በማጋራት ለማህበረሰቡ የድርሻዬን አስተዋጽኦ ለማበርከት እሞክራለሁ፡፡ እንደ አንድ ውጤታማ፣ ብቁና በሌሎች አቅም የምትሆን ሴት፣ አዲሱን ትውልድ በተለይ ደግሞ ልጃገረዶችን ለማበረታታት እንዲሁም ጥሩ አርአያ ለመሆን እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መንፈስ አነቃቂ ተናጋሪ ለመሆንም እሻለሁ፡፡ እነዚህን  ለእኔ ትልቅ የመንፈስ እርካታ ያጎናፅፈኛል፡፡

ህልሜ በአገሬ ሕዝቦች መካከል ህብር ተፈጥሮ ማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በልዩ የበለፀገ ታሪኳ፣ባህሏና፣ ቅርሷ፣ እንድትታወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወንዶችም ሴቶቹም ያለሙትን ለማሳካት እኩል መብትና እድል አግኝተው ማየትም እሻለሁ፡፡ ሴቶች የተሻለ ዕድል፣ የተሸለ ሕይወትና የተሸለ ገቢ አግኝተው እንዲሁም ከጥገኝነት ተላቀው እንደማይ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በዛሬው ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያድጉ ልጃገረዶችና ወጣቶች ሴቶች የምለግሳቸው ምክር እንዲህ የሚል ነው፣ ፍላጎታችሁን በቅጡ ለይታችሁ በማወቅ ተግታችሁ ሥሩ፣ በልጅነት እድሜያችሁ ትምህርትን የሙጥን ብላችሁ እስከመጨረሻው በትኩረት ግፉበት፣ የምትወዱት ሥራ ላይ አተኩራችሁ ሁለመናችሁን በመስጠትና በቁርጠኝነት ተግታችሁ ሥሩ በምንም ነገር ቢሆን ተስፋ አትቁረጡ፣ እናንተም ወንዶች የተገነኑበት ሙያ ውስጥ ገብታችሁ ልትገኑበት እንደምትችሉ አትጠራጠሩ፡፡ አውሮፕላን አብራሪነትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትርነትም ቢሆን የማይቻል ነገር የለምና፡፡