ስቴፈን ሀውኪንግ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

 

የዓለማችን ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ ስቴፈን ሀውኪንግ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቤተሰቦቻቸው አስታወቁ።እንደ ቤተሰቦቹ ገለፃ፥ ስቴፈን ሀውኪንግ ዛሬ ማለዳ ላይ በቤታቸው እያሉ አርፈዋል።“በጣም የምንወደው አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል” ሲሉም የስቴፈን ሀውኪንግ ልጆች ተናግረዋል።

 

የፌዚክስ ሊቅ የሆኑት እንግሊዛዊው ስቴፈን ሀውኪንግ “ብላክ ሆልስ” እና “ሪላቲቪቲ” በሚባሉ የፊዚክስ ስራዎቻቸው የሚታወቁ ሲሆን፥ “ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ታይም” የሚለውን ጨምሮ በርከት ያሉ የሳይንስ መጻህፍቶችንም ጽፈዋል።ስቴፈን የ22 ዓመት ወጣት እያሉ ባጋጠማቸው የነርቭ ህመም ያለ ድጋፍ ሰጪ መሳሪያ መናገርም ሆነ መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቆይተዋል።

ስቴፈን ሀውኪንክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 8 1942 ላይ ነበር በእንግሊዟ ኦክስፎርድ የተወለዱት።እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1959 በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በተፈጥሮ ሳይንስ ያጠኑት ሀውኪንግ፥ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከካንብሪጅ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል;። በፈረንጆቹ 1963 “ሞቶር ኔውሮን” በተባለ የነርቭ በሽታ የተጠቁት ስቴፈን በወቅቱም ከዚህ በኋላ በህይወት የሚኖሩት 2 ዓመት ብቻ ነው ተብለው ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1988 ያሳተሙት “ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ታይም” የሚለው መጽሃፋቸውም በዓለም ዙሪያ በ10 ሚሊየን ኮፒ መሸጡ ይታወሳል።

 

Source:Fanabc.com