የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ወደ ውጭ በቀጥታ መላክ የሚችሉበትን ስምምነት ፈጸሙ

 

በአዲሱ የቡና ንግድ አዋጅ መሠረት አቅራቢና ላኪዎች በጋራ እንዲሠሩ ባስቀመጠው ሥርዓት በመጠቀም፣ የደቡብ ቡና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር ከመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በገባው ስምምነት መሠረት ቡናን በቀጥታ መላክ የሚችልበትን ዕድል አስጠብቋል፡፡

ስምምነቱ ማክሰኞ፣ መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በተፈረመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የስምምነቱ ዓላማ ቡና አቅራቢዎች ከላኪዎች ጋር በመሆን ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የሚያበረታታ የአሠራር ሥርዓትን ለማስፈን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አቅራቢዎች ከአምራቾች ያሰባሰቡትን ቡና በቀጥታ ወደ ውጭ ለመላክ ይቸገሩ እንደነበር የቡና አቅራቢዎቹ አማካሪ አቶ ብሩክ ቢተው ገልጸዋል፡፡ ከቡና አላላክ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ሲታይ የቆየውን የገበያ ችግር አዲሱ አዋጁ በመቅረፉ፣ የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች እንደ አቅራቢ፣ ኮርፖሬሽኑም እንደ ገዥ በመሆን ቀጥተኛ የንግድ ትስስር የፈጠሩበት የመጀመርያው የግብይት ስምምነት ሆኗል፡፡

 

የጋራ ስምምነቱ ተፈጻሚ በሚሆንበት ወቅት፣ በንግድ ሠንሰለቱ ውስጥ የሚታዩ አለመተማመኖችን እንደሚያስቀር ተነግሯል፡፡ የንግድ ሥርዓቱን በማቀላጠፍ፣ የገበያውን መርኅ በጋራ ለመወሰን የሚያስችል፣ ጥራት ያለውና ጥሩ ዋጋ የሚያስገኝ ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ብቻም ሳይሆን የገዥውን ፍላጎት በማሟላት በዘላቂነት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ስምምነቱ ዕድሉን እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

የደቡብ ቡና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንደገለጹት፣ 30 ሚሊዮን ሕዝብ የሚተዳደርበት የቡና ምርት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በነበረው የቡና ግብይት ችግር ሳቢያ፣ አርሶ አደሩ፣ አቅራቢው፣ ላኪውና አገሪቱ  ከቡና ሊያገኙ የሚገባቸውን ጥቅም ሲያሳጣ ቆይቷል ብለዋል፡፡

 

በተወሳሰበው የግብይት ሥርዓት ሳቢያ ከፍተኛ ኪሳራ ሲደርስ ከመቆየቱ በተጨማሪ፣ የቡና ግብይቱም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲፈጸም የሚያስገድድ ሕግ እየተተገበረ በመቆየቱ፣ አቅራቢዎችን የሚያስተናግድ አማራጭ የወጪ ገበያ ዕድል ዝግ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በአዲሱ የቡና አዋጅ ግን አማራጭ የገበያ ዕድል በመፈጠሩ ሳቢያ፣ አቅራቢዎችም ቡናን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በስምምነቱ መሠረትም በአማራጭ ገበያ ዕድል ቡናን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩ ታምኖበታል፡፡

 

አዲሱ አዋጅ አቅራቢና ላኪው ተደራድረው እንዲገበያዩ ስለሚያስችል፣  የአቅራቢና የላኪ የትስስር ስምምነቱን ‹‹በፍላጎታችን ወደ ኮርፖሬሽኑ በመሔድ በድርድር የፈጸምነው ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከአቅራቢዎች በተጓዳኝ ለአምራቾችም ጠቀሜታው እንደሚጎላ አብራርተዋል፡፡ በኦርጋኒክ ሠርተፊኬት፣ በትሬሲቢሊቲ አሠራር ቡናን እንደልብ የመሸጥ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቅሰዋል፡፡የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ከበደ፣ በቡና ዘርፍ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እንደተከናወኑ ጠቅሰው፣ ወደ ሪፎርሙ የተገባበት ምክንያትም በነባሩ የግብይት ችግሮች ሳቢያ የሚፈለገውን ያህል ቡና ወደ ውጭ በመላክ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ ነው፡፡

 

ጥራት ያለው የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የመጀመርያውን የቀጥተኛ የንግድ ትስስር ከአቅራቢዎች በቀረበ ጥሪ መሠረት በተለይ ገዥዎቻችን የሚጠይቁትን መሥፈርት ማሟላት የሚቻልባቸው መንገዶችን ስለሚያመቻች፣ ከማኅበሩ ጋር ለመሥራት ስምምነት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ከስምምነቱ በፊትም ቢሆን፣ የቡና ማሳዎች ድረስ በመሔድ የምርት ይዞታውን እንደተመለከቱ የገለጹት አቶ መንግሥቱ፣ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻም ሳትሆን፣ በዓለም ከሚጠቀሱ ከ80 በላይ ቡና አምራች አገሮች ኢትዮጵያ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ከፍተኛ የቡና አምራች ከሚባሉት ቀዳሚ ተርታ ብትሠለፍም፣ ከቡና የወጪ ንግድ አኳያ ግን ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች፡፡

 

የቡና ምርት መጠንን በመጨመር በቂ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ዕድል ለመፍጠር፣ የልዩ ጣዕም ወይም የስፔሻሊቲ ቡናዎችን በብዛት በማቅረብ ሌሎች አገሮችን በመወዳደር አስተማማኝ አቅርቦት መፍጠር የሚቻልበትን አካሔድ አዲሱ ስምምነት እንደሚፈጥር አቶ መንግሥቱ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተመሠረተበት አንዱ ዓላማ ከአርሶ አደሩ ጋር መሥራትን የሚያካትት በመሆኑ፣ ከዚሁ ዓላማ በመነሳት ስምምነት መደረጉ ተጠቅሷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ2009 ዓ.ም. 8.5 ሚሊዮን ኩንታል እህል፣ ቡና፣ የፍጆታ ዕቃዎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ በ8.82 ቢሊዮን ብር ለመግዛት አቅዶ የ5,891,081 ኩንታል ምርት በ6.67 ቢሊዮን ብር በመግዛት የዕቅዱን 69 በመቶ በመጠንና የ76 በመቶ በዋጋ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በ2009 ዓ.ም. በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ 7.60 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የ8,57 ኩንታል እህል፣ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የፍጆታ ዕቃዎች እንዲሁም የግዥና የማማከር አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ፣ 6.31 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የ7.8 ሚሊዮን ኩንታል ምርትና አገልግሎት በመሸጥ የዕቅዱን 92 በመቶ በመጠን እንዲሁም የ83 በመቶ የዋጋ ክንውን አስመዝግቧል፡፡

 

በ2009 ዓ.ም. 897.90 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 236.71 ሺሕ ኩንታል ቡና፣ የቅባት እህል፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ውጭ አገር በመላክ 39.97 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ዓምና ከወጪ ንግድ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በ2008 ዓ.ም. ከነበረው አፈጻጸም አኳያ ሲነጻጸር፣ የ42 በመቶ ዕድገት ማሳየቱም ተጠቅሷል፡፡

 

የደቡብ ቡና አጣቢዎች አበጣሪና አቅራቢዎች የዘርፉ ማኅበር በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺሕ በላይ አባላትን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው፡፡ የቡና ግብይት ሪፎርምን ተከትሎ ለወጣው አዲስ አዋጅና አሠራር በሐሳብ አፍላቂነትም ይጠቀሳል፡፡ 

 

Source: www.ethiopianreporter.com/article/8624