Quick Links

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የ2008 , የ300 ሺሕ ብር ፈጣሪዎች

 

የአይሲቲ ልቀት ማዕከል የ300 ሺሕ ብር ሽልማት የሚያቀዳጃቸው ፈጣሪዎች ይጠበቃሉ

የአይሲቲ ልቀት ማዕከል የ300 ሺሕ ብር ሽልማት የሚያቀዳጃቸው ፈጣሪዎች ይጠበቃሉ

ከተመሠረተ ስድስት ዓመታት ያስቆጠረው የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኔኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ልቀት ማዕከል፣ ለአምስተኛ ዙር በሚያካሂደው የፈጠራ ውድድር ወቅት ለስድስት አሸናፊዎች 300 ሺሕ ብር ሽልማት አሰናድቷል፡፡የልቀት ማዕከሉ በምርምር፣ በማማከር፣ በሥልጠና እንዲሁም በተለያዩ አይሲቲ ነክ ቴክኖሎጂዎች ላይ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ መብራህቱ፣ ከእነዚህ ሥራዎቹ ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው በሶፍትዌር ማበልጸግ መስክ ወጣቶች የሚያደረጉትን ተሳትፎ ማገዝ እንደሆነ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

 

በመሆኑም ላለፉት አምስት ዙሮች በተለያዩ የአይሲቲ የፈጠራ ውጤቶች የተሳተፉ ወጣቶች ልዩ ልዩ ሶፍትዌሮችን በማበልጸግ ያላቸውን ችሎታ እንዲያሳዩ መድረክ ሆኖ አገልግሏል፡፡ አጋዥ የትምህርት ማስተማሪያ ሶፍትዌር፣ የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ የሚጠቁሙ ልዩ ልዩ አፕልኬሽኖች፣ የደኅንነት ማስጠበቂያ ሶፍትዌሮች፣ የልብ ምትን ጤንነት የሚከታተል ሶፍትዌርን ጨምሮ በርካታ የአይሲቲ ውጤቶች በወጣቶቹ እየተሠሩ መጥተዋል፡፡  ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር ወቅት አሸናፊ ከነበሩት አንዱ በወንድምና እህት የተሠራው ኤሌክትሮ ካርዲዮግራፍ (ኢኬጂ ወይም ኢሲጂ) ይገኝበታል፡፡ አብሳላት ሠራዊት በተባለችው፣ በሙያዋ የሕክምና ባለሙያ በሆነችው ወጣትና በኤሌክትሪካል ምሕንድስና ዘርፍ በሰለጠው ወንድሟ ወጣት መላዕከ ሠራዊት የተሠራው ይህ መሣሪያ ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ሥጋቶች የሚጠቁም ነው፡፡

ሁለቱ እህትና ወንድም መሣሪያውንና ሶፍትዌሩን በመሥራት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከሦስቱ ዋና ዋና ገዳይ በሽታዎች ሁለቱ ከልብ ሕመም ጋር የተያያዙ መሆናቸውንና ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ ቴክኖሎጂውን አሻሽለው በመሥራት ወጣቶቹ ቴክኖሎጂውን ወደፊት ገበያ ላይ በብዛት ተመርቶ ሊቀርብ የሚችልበትን ዘዴ በመፈተሽ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡በዘንድሮ ዓመትም ከተወዳደሩት መካከል ስድስት አሸናፊዎች ከወዲሁ ተለይተው፣ ነሐሴ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ወቅት ይፋ እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም በሴቶች ብቻ ምድብ እንዲሁም በጠቅላላው ምድብ ተለይተው ከተወዳደሩ የአይሲ ፈጣሪዎች መካከል አንደኛ የሚወጡ ሁለቱ እንዳንዳቸው 75 ሺሕ ብር እንደሚሸለሙ ማዕከሉ አስታውቋል፡፡ ሁለተኛ የሚወጡት እያንዳንዳቸው 50 ሺሕ ብር ሲሸለሙ፣ ሦስተኛ ደረጃን የሚያገኙት 25 ሺሕ እንደሚሸለሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

ምንም እንኳ አገሪቱ የአይሲቲ ፈጣሪ ወጣቶች አቅም በየጊዜው ዕድገት እየታበት፣ የሚያመነጯቸውም የፈጠራ ሐሳቦች እየተራቀቁ ቢመጡም አሁንም ድረስ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች የደረሰቡት ደረጃ ለመድረስ መንገዱ የትዬለሌ መራቁ እየታየ ነው፡፡ በርካታ ወጣቶች የሚፈጥሯቸውን ሶፍትዌሮች የሚሸጡባቸው የኢንተርኔት ገበያዎች አለመኖራቸው፣ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥልቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ወዲህ አለመፈጠራቸው ለዘርፉ መዳከም ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ይደባሉ፡፡

Source: The Ethiopian Reporter ,06 Aug, 2016