Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

 መስቀል በጉራጌ

 

 

 

በወርሐ ጽጌ አደይን ተከትሎ በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት የሚከበረው የመስቀል በዓል በተለይ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ አለው። መስቀል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ባህላዊ ገፅታው ብዙዎችን ይስባል። ይማርካል። ህብረ ብሔራዊነቱም እንዲሁ።

የመስቀል በዓል መከበር ከጀመረ በርካታ ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይነገርለታል። በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ደምቆና አሸብርቆ የሚከበር መሆኑም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል (UNESCO) ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል።

 

 

 

የመስቀል በዓል አከባበር እንደየአካባቢው ይለያያል። በጉራጌ፣ በከንባታ በዶርዜና መሰል ብሔሮች በዓሉ የተለየ ትኩረት ስለሚሰጠው ከሌሎች በዓላት ለየት ተደርጎ ይከበራል። በእዚህ ጽሑፍም በጉራጌ ባህል የመስቀል በዓል እንዴት እንደሚከበር ላስቃኛችሁ ወደድሁ። በጉራጌ ባህል የመስቀል በዓል መከበር የሚጀምረው መስከረም በገባ በ13ኛው ቀን። ከአገር ውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው የብሔሩ ተወላጅ እንዲሁም ሌሎች የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉ ሳይደርስ ለበዓሉ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮችን በመግዛት ይዘጋጃሉ።

የብሔሩ ተወላጆች የመስቀል በዓልን ለማክበር ከያሉበት ወድትውልድ አገራቸው የሚያቀኑት ቀደም ብለው ነው። ለመስቀል በዓል አገሩ ያልገባ የብሔሩ ተወላጅ ካለ «ሞቷል» ተብሎ ስለሚታመን እንደምንም ብሎ በዓሉን ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማሳለፍ የተለመደ ነው።

 

ለበዓሉ አገር ቤት የገባም የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶችን በመፈጸም እስከ መስከረም 21 ቀን ድረስ ይቆያል። በየዕለቱ የሚከናወኑት እነዚህ ባህላዊ ሥርዓቶች የተለያየ ስያሜ አላቸው። ከመስከረም አስራ ሁለት እስከ አስራ ስምንት ድረስ ያሉት ቀናት የራሳቸው የሆነ ስያሜ፣ ትርጓሜና ሥርዓት አላቸው።

 

መስከረም 13 «ወልቀን» ተብሎ ሲጠራ ትርጓሜውም የሴቶች ቀን በመባል ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ሴቶች ጎመንና ዓይብን በማዘጋጀት በሶዶ ጉራጌ አጠራር ደዋወሸት የሚባለውን ማባያ ቆጮ ተጠቅመው አጠቃላይ ቤተሰቡ ተሰባስቦ ይመገባል። ይህን የሚመገቡት የቤተሰቡ አባላት በየራሳቸው በተዘጋጀላቸው «ጣባ» አማካኝነት ነው። ጣባዎቹ ተሰቅለው ከተቀመጡበት ለመስቀል በዓል ብቻ የሚወርዱ ሲሆን፤ በቤተሰቡ ልክና በየስማቸው የተዘጋጁ ናቸው። ተለይቶ የማይሰጠው ባልናሚስት ለሆኑ ብቻ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።

 

መስከረም 14 ደግሞ «ደንጌሳት» በመባል ሲጠራ ዕለቱ የልጆች ወይም የሕፃናት ቀን ይባላል። ይኸውም ልጆች በትንሹ በሰፈር አካባቢ ደመራ ደምረው የሚጫወቱበት ቀን ነው። ደመራው ካለቀም በኋላ አባቶችና እናቶች ይመርቃሉ። በዚህ ቀንም እንደመጀመሪያው ሁሉ በቤት ውስጥ ጅባ እና እንጮት ተነጥፎ ደዋወሸት ይሰጣል።

 

መስከረም 15 «ጨርቆስ» በመባል የሚጠራ ሲሆን፤ የዕርድ ቀን በመባልም ይነገራል። ዕለቱ ዕርድ የሚፈጸምበት በመሆኑ የሚታረደው በሬ ሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ ሽማግሌዎች ስለአገር ሰላምና በዓሉን በተመለከተ እያነሱ ይመርቃሉ። መልካም ምኞታቸውንም ይገልጻሉ። የቤተሰቡ አባላትም ሦስት ጊዜ «ኬር ይሁን» በማለት ምርቃቱን ይቀበላሉ። ትርጉሙ «ሰላም ይሁን» ማለት ነው። በእዚህ ባህላዊ በሥነሥርዓት ላይ እንዲመርቁ የሚጋበዙት ሴቶች ወይም ወንዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ለማሳረጊያነት የሚሆነውን ምርቃት ሁሌም የሚመርቀው ወንድ እንጂ ሴት አይሆንም። ይህ ሥርዓት በምርቃትም ሴቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ያሳያል። ዕለቱ አንዳንድ ጊዜም የጥሬ ሥጋ ቀን በመባል ይጠራል። ምክንያቱ ደግሞ በዕለቱ የሚበላው ጥሬ ሥጋ በመሆኑ ነው። ዕርዱ በግል ወይም በጋራ ሊከናወን ይችላል። በዕርድ ክፍፍል ወቅት የታረደውን በመከፋፈል ለሚስኪኖች እንዲደርስ ይደረጋል።

 

መስከረም16 «የብርንዶ ወይም የክትፎ ቀን» ይባላል። የጉራጌን ባህላዊ የአመጋገብ ሥርዓትን ከሚያመላክቱ መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የክትፎ አመጋገብ ሥርዓት ነው። ቀኑ ለየት ያለና ትኩረት የሚሰጠው ዕለት ሲሆን፤ በዚህ ቀን ትልቁ ደመራ የሚደመርበት ሲሆን፤ ጎረምሳና ልጃገረዶች በባህላዊ ጭፈራ የሚተያዩበት ቀንም እንደሆነ ይነገራል።

 

መስከረም17 «ከሰል» በመባል የሚጠራ ሲሆን፤ በዚህ ቀን ሁሉም የቤተሰብ አባላት ደመራው ወደተደመረበት ቦታ በመሄድ ከሰሉን እየረገጡ የሚሻገሩበትና ዘመኑ መልካም ዘመን እንዲሆንላቸው የሚማጸኑበት እንደሆነም የብሔሩ ተወላጆች ይናገራሉ። ከሰል መጥፎው ወይም ጥሩ ያልነበረው ነገር የጠፋበትና ብርሃን የታየበት ዕለት ማብሰሪያ ተደርጎ ይታሰባል። ከዚያም ባሻገር የአዲስ ዓመት መግቢያና የዘመን መለወጫ ዕለትም በመሆኑ ሁሉም የራሱን ዕቅድ ይዞ ለመልካም ነገር የሚነሳበትም ነው ይላሉ።

 

ከመስከረም 18 እስከ መስከረም መጨረሻ ያሉት ቀናት ደግሞ «አዳምና» ወይም «የገበያ ላይ ጨዋታ» በመባል ይታወቃሉ። በእነዚህ ቀናት ልጃገረዶችም ሆኑ ጐረምሶች በነፃነት ይጫወታሉ። ጨዋታውም የሚፈጸመው ገበያ ባለበት ሁሉ እየተዘዋወሩ ሲሆን፤ በተለይ ከሌሎች ቦታዎች የመጡ ወንዶች ለወደፊት ሚስት የምትሆናቸውን ሴት የሚመርጡበትና ሴቷም ብትሆን የምትታጭበት ጊዜ ነው።

«ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ» እንደሚባለው ሁሉ በእነዚህ ቀናት ልጃገረዶቹም ሆኑ ወንዶቹ አሸብርቀው ይታያሉ። የጉራጌ ወንድ ሊያገባ ከፈለገ አዳምና ይጨፍርና በእዚያው ለራሱ የምትሆነውን ሚስት ያጫል።

ምንጭ ፡-ማህደረ ደቡብ