Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

የግጭት አፈታት ሳይኮሎጂ

 

የግጭት አፈታት ሳይኮሎጂ

 

 Image result for aggression in people

ግጭት ጥልቅ ውስጣዊ ስሜቶች አደባባይ ላይ ወጥተው እንዲሰጡ ያደርግል፡፡ በዚህ ጊዜ በእውናችን ቀርቶ በህልማችን እንኳን አልመን የማናውቀውን ነገር ራሳችንም ሌሎችም ሲያደርጉ አስተውለን ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለመስማት የሚከብድ ወንጀል ፈጸመው ወዳጅ ዘመዶቻቸው ስለእነዚሁ ሰዎች ጠባይ ሲጠየቁ “እሱ እኮ ሰውም ቀና ብሎ አይመለከት፣ ታላቁን አክባሪ፤ አንገት ደፊ ወዘተ ነበር” ሲሉ ይደመጣል፡፡ እንደተባለውም እነዚህ ሰዎች ሰው አክባሪ፣ ካልደረሱባቸው ሰው ላይ የማይደርሱ ይሆናሉ፡፡ መስካሪዎቹ ፊት ለፊት ያዩትን ነው የመሰከሩት፡፡ ነገር ግን እነዚህ መስካሪዎች አይተውት የማያውቁት አጥፊ ስሜት እነዚህ ሰዎች ውስጥ ይኖራል፤ ተመልካች ይቅርና ባለቤቱም ራሱ አያውቀው ይሆናል፤ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ፡፡ይህ ማለት ግን በስሜት ተገፋፍተን በፈጸምነው ድርጊት ተጠያቂ አንሆንም ማለትም አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ስሜቶቻችንም የገዛ ራሳችን ንብረት እንጂ የማንም አይደሉም፡፡

ግጭት የሚያስከትለውን ውድመት የበዛ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት ከመፈጠሩ በፊት ለመከላከልም ሆነ ከተፈጠረ በኋላ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ዕውቀት እና ክህሎት እጦት ነው፡፡ በትንሽ በትልቁ ብስጭት የሚሉ ሰዎችን ታውቁ ይሆናል፤ ለምን ቀና ብላችሁ በሙሉ ዓይናችሁ ተመለከታችሁኝ ብለው ችግር የሚፈጥሩ እና ችግር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በምዕራቡ ዓለም ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ‹ንዴትን መቆጣጠር› የሚችሉበት የተለየ ስልጠና ቁጭ ብለው እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ግጭትን መከላከልም ሆነ መፍታት በስልጠና ሊደረጅ የሚችል ችሎታ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ግጭትን ለመከላከል እና ለመፍታት የሚረዱ ነጥቦችን እንዳስሳለን፡፡

1. ስናዳምጥ ‹ጥቃትን› አናዳምጥ

ጥቃት እየተፈጸመብን ነው ብለን ከአሰብን አጸፋዊ መልስ ለመስጠት አናቅማማም፡፡ ክፉ ደግ መነጋገር ደግሞ ምክንያታዊ ውይይት ድራሹ እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡ በተለይ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ማንኛውም ዓይነት ንግግር ሲደረግ ‹ይህ ሰው በትክክል ምን እያለ ነው?›፣ ‹ምን ዓይነት መረጃ ነው በመተላለፍ ላይ የሚገኘው?›፣ ‹ምንድነው የተከፋበት ምክንያት? ለምን ተቆጣ? ለምን ክፉ ተናገረ?› ወዘተ በማለት በስሜት ታጅበው ከሚፈሱት ቃላት ጀርባ ያለውን መልዕክት ለይቶ ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ ይህንን ከአደረግን ራስን ለመከላከል ከፍ ሲልም መልሶ ወደ ጥቃት ወደ መሰንዘሩ ከመኬዱ በፊት መግባባት እንዲነግስ ያደርጋል፡፡

2. ደመ ነፍሳዊ ግፊት አደብ እንዲገዛ ማድረግ

የምንፈልገው እንዳልተሟላ፣ ፍትህ እንደጎደለ፣ ውሸት እንደከበረ፣ መስማት የማንፈልገው ጥያቄ እንደቀረበ ወዘተ ስናስብ እጥፍ ድርቡን መልሳችሁ አከናንቡ የሚል ውስጣዊ ደመ ነፍሳዊ ግፊት ይቀሰቀሳል፡፡ እስከ ዶቃ ማሰሪያው፣ አፍንጫው ድረስ፣ ልክ ልኩን ወዘተ ነገረው ዓይነት ፈሊጣዊ አገላለጾቻችን ‹ክፉ ነገርን ልክ የለሽ በሆነ ክፍት መመከትን› እንደምናበረታታ ፍንጭ የሚሰጡ ናቸው፡፡ አጥቂ ምክንያታዊ ይሁንም አይሁንም፣ ደግ ይሁንም አይሁንም አበጀህ የማለት፣ እንደ ጀግና ከፍ አድርጎ የመመልከት ባህል ሊወገድ ይገባል፡፡

በግጭት ወቅት ‹እንዲህ በል፣ እንዲያ በል፣ የት አባቱ ወዘተ› ዓይነት ውስጣችን የሚፈሉ የደመ ነፍስ ግፊቶችን ማቀዛቀዝ ግጭትን ለመፍታት ይረዳል፡፡ ደመ ነፍሳዊ ምሪትን ከአስቆምን በኋላ ተረጋግቶ በማሰብ መናገር የምንፈልገውን ‹እኔ› በማለት መናገርም እንዲሁ ይመከራል፡፡ ለምሳሌ፣ በቤት ውስጥ የትዳር አጋር ስራ አላግዝ ብሎ አስቸግሮ ከሆነ ‹አንተ ድሮም ሰነፍ ነህ፣ ምንትስ ነህ› ከማለት ይልቅ ‹እኔ ስራ ካላገዝከኝ/ካላገዝሽኝ ቅር ይለኛል፤ ተጋግዘን ልንሰራ ይገባል፤ ይኼ እኮ የጋራ ህይወት ነው› ማለት ግጭት ላይ አርቆ ማጠሪያ ስልት ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ውስጣችን አሉታዊ ስሜት ሲጸነስ እንደመጣልን ከመናገር እንቆጠብ፡፡ ‹ከአፍ የወጣ አፋፍ› አይደል ከነአባባሉስ፡፡ ንግግር የፈሰሰ ውሃ ነው፡፡ እንደ ደራሽ ውሃ ፈሶ ያለ የሌለውን ጠራርጎ ከሄደ በኋላ ሁኔታዎችን ወደ ነበሩበት መመለስ ፈታኝ ነው፡፡ ስለሆነም ንግግር ሲያደርጉ ማመዛዘን እንዲሁም ከአንደበታችን የሚወጡ ቃላት ግጭቱ ላይ ሄደው ሲያርፍ የቤንዚን ነው ወይስ የውሃ ሚና የሚጫወቱት የሚለውን ቀድሞ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

3. የሰዎችን በጎ ጎን ማነጋገር

100 % አጥፊ፣ ምንም ነገር የማይገባው፤ ውስጡ እንጥፍጣፊ መልካምነት የሌለው ወዘተ ሰው አይኖርም፡፡ የትኛውም ሰው መልካም ማንነት የማንነቱ አካል ነው፡፡ እርስ በእርስ ስንነጋገር አንዳችን የአንዳችንን ይህንን መልካም ጎን ለማነጋገር ጥረት እናድርግ፡፡ ‹ጅኒ› ገለመሌ የሚል አጓጉል ፍረጃ ውስጥ ሳንገባ መልአኩን ማንነት እናወያየው፡፡የሰው የእምነቱ መነሻ ስረ መሰረት የአንድም ይሁን የብዙ የሰው ልጅ ፍቅር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ ድፍን ያለ ‹ነጭ› አለያም ደግሞ ድፍን ያለ ‹ጥቁር› ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ፈረንጆቹ እንዲህ ዓይነቱን ጠርዘኛ አመለካከት ‹‹either/or thinking›› ይሉታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ራስንም ሆነ ሌሎችን አውዳሚ ነው፡፡ ከ‹ሰይጣን› ሌላ ሙሉ ለሙሉ ‹ሰይጣን› የሆነ ፍጥረት የለም፡፡

4. ለሰዎች ስሜት ቦታ እንስጥ

ስሜቶቻችን ጠቋሚ ምልክት ናቸው፡፡ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ስሜት ደንታ ቢስ መሆን ተገቢ አይደለም፡፡ የሰዎችን ስሜት መረዳት የተፈጠረው ግጭቱ መንስኤ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይረዳል፡፡ ችግር ችግር ሆኖ የሚዘልቀው መንስኤው እስኪታወቅ ድረስ ነው፡፡ የራስንም ሆነ የሌላውን ስሜት አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ግን ግጭትን ይወልዳል፤ ያባብሳልም፡፡ ‹ዶርማንት› የሚባል የእሳተ ገሞራ ዓይነት አለ፡፡ መገለጫው ውሎ አድሮ አንድ ይደርሳል ብለን ሳናስበው የደረስንበት ቀን ላይ መፈንዳት ነው፡፡ ያኔ ታዲያ እዚያ አካባቢ ያለን ምንም ነገር አያደርጋችሁ፡፡ የነበረውን እንዳልነበረ ይሆናል፡፡ ሰሚ ጆሮ ተነፍጎ የከረመ ስሜትም እንዲሁ ቋት ሲሞላ አንድ ቀን ያፈነውን ክዳን አሽቀንጥሮ ሲወጣ ብዙ ሳይሰባብር አይበርድም፡፡ ‹አይመጣምን ትተሸ ይመጣልን አስቢ› ትልቅ ቁም ነገር አዘል መልዕክት ነው፡፡ በእንቁላል ዕድሜ ላይ የሚገኙ ስሜቶችን ስራዬ ብሎ መስማት፣ ቦታ መስጠት እና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከሰማይ በታች ማድረግ የሚቻለውን ነገር ሁሉ ማድረግ ግጭትን በሩቅ ያስቀራል፤ ድንገት ቢቀሰቀስ እንኳን ያለ ብዙ ኪሰራ ይቀዘቅዛል፡፡ ሳይኮሎጂቶች ቅጣትን የማያበረታቱት ለዚህ ነው ለጊዜው ቀጪ ዱላውን ጨብጦ ዙሪያቸው ሲገኝ ልጆች ታዛዥ እንዲሆኑ ያደርጋል እንጂ ዘላቂ የሆነ የጠባይ ለውጥ ግን ጨርሶ አያመጣም፡፡ ስለዚህ በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ ግጭትን አስቀድሞ ለመከላከልም ሆነ አንድ ጊዜ ከተፈጠረ በኋላ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለማረጋጋት ለሰዎች ስሜት ቦታ መስጠት፣ እንደተረዳናቸው ማስረዳት፣ ቁስላቸው እንደተሰማን መግለጽ ይመከራል፡፡

5. መስማት እና መስማማት መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ

የተጋጨን ሰው ቅሬታውን መስማታችንን ማወቅ አለበት፡፡ የሰው ልጅ አለመግባባት ሲፈጠር ቀዳሚ ፍላጎቱ መሰማት ነው፡፡ መስማማት ቀጥሎ የሚመጣ ሌላ ሂደት ነው፡፡ በቂ ጊዜ ሰጥተን ሰምተናል ማለት በተባለው ሁሉ ተስማምተናል ማለት አይደለም፡፡ በሁሉ ነገርም መስማማት አይቻልም፡፡ መደማመጥ ግን ቁልፍ ሚና ሊጫወት እና በቀላሉ ልንተገብረው የምንችለው የግጭት መፍቻ መመሪያ ነው፡፡ ከሁሉ በፊት ምንአልባትም ከሁሉ በላይም አቁሳዩ ጥይት አድማጭ ማጣት ነው፡፡ ሰውን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍ ክብረ ነክ ድርጊት ነው፤ ንቀት ነው፤ ‹ምን ታመጣላችሁ?›፣ ‹የራሳችሁ ጉዳይ› ወዘተ ማለት ነው፡፡ እነዚህ የአመለካከከት እና ድርጊት መስመሮች በራሳቸው ግጭትን ይቀሰቅሳሉም፤ ያባብሳሉም፡፡ አንድን ሰው እህ ብሎ መስማት፣ ሃሳቡን በሚገባ እንዲገልጽ ዕድል መስጠት፣ እየተባለ ያለውን ፍሬ ነገር በገዛ ራስ ትርጉምና ፍረጃ ሳይጀቡኑ ለመረዳት ጥረት ማድረግ፣ ሳይኮሎጂስቶች ‹‹already listening›› የሚሉት አለ (የሚመልሱትን መልስ እያውጠነጠኑ መስማት ማለት ነው)፣ እንደዚህ ካለው የማይበጅ የህሊና ድምጽን ዝም አሰኝቶ የሌላውን ህሊና የቅሬታ ድምጽ መስማት ግጭትን ይቀንሳል፤ ይፈታልም፡፡ ተደማመጥን ማለት ተስማማን ማለት አይደለም፤ ሰሚ ጆሮ መስጠት መሸነፍ አይደለም፡፡ መደማመጥ እስካለ ድረስ በአልተስማሙበት ጉዳይ ላይም በልዩነት መስማማት ይቻላል፤ ‹ላለመስማማት መስማማት› እንዲሉ፡፡

6. ስናዳምጥ አስሬ ጣልቃ እየገባን አስተያየት አንስጥ

ይኼም እንዲሁ ለንግግር አድራጊው ያለንን ዝቅተኛ ክብር አስረጂ ነው፡፡ የሚከባበሩ ሰዎች ግጭት ውስጥ የሚገቡበት ዕድል አነስተኛ ነው፡፡ አይበለውና ግጭት ቢነሳ እንኳን  በሰለጠነ መንገድ መፍታት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ አንድ ከዚህ በፊት በሌላ አንድ ጽሑፌ ላይ ያነሳሁት ገጠመኝ አለኝ፡፡ እዚህ ጋርም ቢነሳ አስተማሪነቱ የጎላ ሊሆን ስለሚችል ደግሜ ላንሳው፡፡ በነጋ በጠባ አንድንዴ አገር ጉድ እስኪል ድረስ የሚጣሉ ጥንዶች ቤት በአንድ አጋጣሚ ተገኘሁና አንድ ርዕሰ ጉዳይ ተነስቶ ሃሳብ መቀያየር ጀመርን፤ ይመስለኛል ክርክር ቢጤም ነው፡፡ ሚስት ሃሳቧን ሳትጨርስ ባል ደጋግሞ ያቋርጣል፡፡ ሚስት ታዲያ መሃል ላይ ወደ እኔ አንገቷን አዙራ በቅሬታ ድምጽ ‹ተመልከተው አያዳምጠኝም እኮ› አለችኝ፡፡ ቅሬታዋ ‹ለምን በእኔ ሃሳብ አልተስማማም› አይደለም፡፡ ቅሬታዋ ‹ለምን ስናገር አታዳምጠኝም› ነው፡፡ ስንወያይ ሃሳብ የማስጨረስ ልምድ ይኑረን፡፡ ማንም ‹ዓመት› አያወራም፡፡ የቤተሰብ ውይይት ይባልናም በመመገቢያ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበን የወላጅን የትዕዛዝ ዝርዝር የመስማት ትዕግስት እንዲኖረን እንጂ የራሳችንን ሃሳብ እንድንገልጽ አንበረታታም፡፡ አምባገነኖችን በዚህ መልኩ ነው በየቤቱ የምንፈጥራቸው፡፡ ሳይደመጥ ያደገ ልጅ ነገ አድማጭ መሪ የሚሆንበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡ በተቋማት ውስጥም ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ ውይይት ማለት በአንድ አቅጣጫ ብቻ ከአሰሪ ወደ ሰራተኛ የሚዥጎደጎድ ምክር ይመስለናል፡፡ ሃሳብን ማስጨረስ ይልቁንም ‹እንዲህ ለማለት ፈልገህ ነው ወይ?› የሚል ጥያቄ በንግግር መጨረሻ በመጠየቅ በትክክል የተባለውን ለመረዳት መጣር፣ ስንነጋገር ከተናጋሪ ጋር ቀጥታ የዓይን ግንኙነት ማድረግ፣ በየመሃሉ ‹አሃ› ማለት ወዘተ ተናጋሪ እየተደመጠ እንደሆነ ስለሚያስገነዝበው መከባበር የሰፈነበት አየር እንዲኖር ያደርጋል፤ መከባበር ወደ መስማማት የማይወስድበትም ምንም ምክንያት የለም፡፡

7. ግምታችንን ገልጸን ግምታችን ስህተት ከሆነ ለመታረም ፈቃደኛ መሆን

‹ግምቶች ብዙ ጊዜ ከእውነታ የራቁ ናቸው› ይላል አንድ ወዳጄ፡፡ ለእውነት የቆመ ሰው ‹ከአፈርኩ አይመልሰኝ› ከሚል ድርቅና የጸዳ ነው፡፡ ‹በዚህ ሰዓት ነበር አይደል ቤት የገባኸው?› ብለን ‹አይደለም፤ በዚህ ሰዓት ነው› የሚል የተለየ መልስ ከተሰጠን፣ ማረጋገጥም ከቻልን ሃሳባችንን እንቀይር፡፡ አንድ ጊዜ የተናገሩትን ላለመሻር በስህተት ላይ ስህተትን እየከመሩ የመሄድ አዚማችን ራስን እያረሙ፣ ወደ እውነት እየተቃረቡ፣ ከእውነት ጋር በእውነት እየተመሩ ከመኖር ይልቅ ሚዛን ይደፋል፡፡ በታሪክም በአመክንዮም ስህተት ስህተትን አርሞ አያውቅም፡፡ ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም፡፡ መሳሳትን ማመን የመንፈስ ከፍታ ነው፡፡ ራስን ማረም ትልቅነት ነው፡፡ ‹ይቅርታ አድርጉልኝ› ማለት ህይወት ውድድር ነው ብለን ብናምን እንኳን በልጦ መገኘት ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ለመታረም ፈቃደኛ ያለመሆን ድርቅና ያጠቃናል፡፡ ይኼንን የስነ ልቡናችንን ጎን አፍርሶ መስራት ጠቃሚ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አንድ አባ ወራ ከሚስቱ ጋር ተጋጭቶ ለማስማማት ጥረት በምናደርግበት ወቅት ‹እኔ ምንም ስህተት የለብኝም፤ 100 % ልክ ነኝ› የሚል መልስ ይሰጠናል፡፡ የሰው ልጅ በዚህ ደረጃ ልክ ሆኖ አያውቅም፤ ወደፊትም የሚሆን አይመስለኝም፡፡ የዚህ አባ ወራ ምላሽ ‹ስህተትን ማመን ሞት ነው› የሚል የጸና እምነት እንዳለን፣ ድርቅናችን ጥጉ የት ድረስ እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡

8. ውስብስብ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመረዳት እንትጋ

አለማወቅ የብዙ ችግር ምንጭ ነው፡፡ ማወቅ ትዕግስትን፣ ጥረትን፣ ተነሳሽትን ወዘተ ይጠይቃል፡፡ ድምዳሜ ላይ ከመድረሳችን በፊት የግጭቱን ቀስቃሽ መንስኤዎች ለመረዳት መጓጓት ግጭትን በመፍታት ሂደት ውስጥ ገንቢ ሚና ይጫወታል፡፡

9. ‹ገንቢ ውይይት ማድረግ ይቻላል› የሚል እምነት ይኑረን

የአትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የ‹ይቻላል› መርህ በግጭት አፈታት ውስጥም ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ አስቀድሞ ‹መግባባት አይቻልም› የሚል እምነት ውስጣችንን ከሞላው ለመግባባት ምንም ጥረት አናደርግም፡፡ ጥረት ብናደርግ እንኳን ለይስሙላ ይሆናል፡፡ የተዘጋ የአይቻልም አስተሳሰብ ወደ መቻል የሚወስዱንን መንገዶች ለመስራት መፈንቀል ያለብንን ድንጋይ በሙሉ እንዳንፈነቅል ጋሬጣ ይሆንብናል፡፡ ከአንጀት ካለቀሱ እንባ መቼም ቢሆን አይገድም፡፡

10. ግጭቱ እንዲባባስ እያደረግን ከሆነ ከድርጊታችን እንቆጠብ

ባልና ሚስት ፍቅራቸው ሳይጠፋ አንድ ጣሪያ ስር አብረው የሚኖሩት አንዱ እሳት ሲሆን ሌላኛው አፈር ከሆነ ብቻ ነው ፡፡ እሳትን በእሳት ማጥፋት ፈጽሞ አይቻልም፡፡

11. ጥፋቱ የማን እንደሆነ ሳይሆን መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅ መሞከር

ጣት መጠቆም የረባ ለውጥ አያመጣም፡፡ ኮሽ ሲል ተወንጃይ ፍላጋ መሯሯጥ ዘላቂ ለውጥ አያመጣም፡፡ ማውገዝ ረጅም መንገድ አያስኬድም፡፡ መወነጃጀል ግጭትን መፍታት የማይችል ቀሽም ስትራቴጂ ነው፡፡ ግጭት ሲቀሰቀስ ጥፋተኛውን ሳይሆን መንስኤውን ለማወቅ መጣር ግጭቱ ዳግም እንዳይፈጠርም ሆነ አንድ ጊዜ ከተፈጠረ በኋላም እንዲበርድ ለማድረግ ያግዛል፡፡ እውነቱን ለመናገር በየትኛውም ዓይነት ግጭት ውስጥ ሁሉም ወገን የሚጫወተው ሚና ይኖራል፡፡ ስለዚህ ‹ይኼ ግጭት እንዲቀሰቀስ እንዲሁም እንዲባባስ ምን ዓይነት ሚና ተጫውቻለሁ?› ብሎ ራስን መጠየቅ እና የራስን ቤት ከሁሉ በፊት መፈተሽ ግጭትን ይከላከላል፤ ያበርዳልም፡፡

12. ስምምነትን ግልጽ ማድረግ

በግልጽ ያልተቀመጡ ስምምነቶች ዛሬም ሆነ ነገ ግጭት እንዲፈጠር በር መክፈታቸው አይቀርም፡፡ ፍላጎትን በቀጥታ በመናገር ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን አማራጭ ተግባራዊ የሚያደርግ፣ ዳግመኛ ለጥል መጋበዝ እንዳይመጣ የሚያደርግ ግልጽ ስምምነት ላይ መድረስ ብልህነት ነው፡፡ በግለሰቦች ሌላው ቀርቶ በባለ ትዳሮች መካከል እንኳን በተደጋጋሚ ቅራኔ የሚፈጥሩ ጉዳዮች ካሉ በሚገባ ከተነጋገሩ በኋላ የመፍትሄ ስምምነቱን በወረቀት ጭምር አስፍሮ ማስቀመጥ ወደፊት ግጭት ሊፈጠር የሚችልበትን ዕድል ይቀንሳል፡፡ ሰው ሊረሳ፣ ቃሉን ሊያጥፍ፣ ፍላጎቱ ሊለወጥ ወዘተ ይችላል፡፡

13. ግጭት ወደፊትም ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ እና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ

ዛሬ ተነጋግረን የፈታነው ጉዳይ ነገም ሌላ ቁጥር አንድ አወዛጋቢ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ሊል ይችላል፡፡ በጥንዶች መካከል ዛሬ ተስማምተንበታል የሚሉት ጉዳይ ነገ ሰላምን ከቤታቸው ገፍትሮ ሊያስወጣ ይችላል፡፡ ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም የተቋጨ ግጭት እንደ አዲስ ሊያገረሽ እንደሚችል ማሰብ፣ የቅድመ መከላከል ስራ መስራት እንዲሁም ገፍቶ መጥቶ ግጭቱ ሲፈጠርም የበዛ ጥፋት እና ውድመት ሳይደርስ መርገብ የሚቻልበትን ስልት መንደፍ ይመከራል፡፡ ትላንት ያደናቀፍን ድንጋይ ዛሬም መልሶ ሊያደናቅፈን አይገባም፤ ቢቻል በቀላሉ አስቀድሞ መገመት የሚቻለውን ይቅርና በቀላሉ ለማይገመተውም ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ይገባል፡፡ ቸር እንሰንብት!

ምንጭ፡-.zepsychologist