Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ውጥረትን እና ጭንቀትን ድብርት በመቀነስ እረፍት እና እፎይታን፣ ጤናና ደ

 

ውጥረትን እና ጭንቀትን ድብርት በመቀነስ እረፍት እና እፎይታን፣ ጤናና ደስታን እንዴት ማብዛት ይቻላል?

 

 Image result for ጭንቀት

 

ያለልዩነት ሁሉም ሰው በአንድም ሆነ በሌላ ጊዜ በልዩ ልዩ ምክንያት ውጥረት/ጭንቀት ውስጥ ራሱን ሊያገኝ ይችላል፡፡ ውጥረት በልኩ ሲሆን የሚያተጋ እና የሚያነቃ ቢሆንም ልኩን አልፎ ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ረዘም ላለ ጊዜ ሕይወታችን ውስጥ ሲቆይ ለልዩ ልዩ የአእምሮ እና አካል የጤና ችግር አጋልጦ ይሰጠናል፡፡ አስከ 70 በመቶ የሚደርሱ ታካሚዎች ሀኪም ጋር የሚመላለሱበት ዓብይ ምክንያት ከውጥረት ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ነው፡፡

ስር የሰደደ ውጥረት ከሞላ ጎደል ሁሉንም የአካላችንን ስርዐት ይረብሻል፡፡ የደም ግፊትን መጠን ያንራል፤ በሽታ የመከላከል አቅምን ዝቅ ያደርጋል፤ ለድንገተኛ የልብ ህመም (heart attack) እና ምት (stroke) የሚኖረንን ተጋላጭነት ይጨምራል፤ እርጅናን ያፋጥናል ወዘተ፡፡ ሌላው ቀርቶ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ውጥረት የአንጎልን አነዋወር እና አሰራርን በመቀያየር ለከፋ ጭንቀት እና ድብርት ለመሳሰሉ የአእምሮ ጤና መቃወሶች አጋልጦ ይሰጣል፡፡

በዕለት ተዕለት ህይወታችሁ ውስጥ የሚፈጠሩ የውጥረት ምንጮችን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር ይረዳሉ የምንላቸውን 10 ስልቶችን እናስነብባችሁ፡-

ፋታ

በየቀኑ መጠነኛ ፋታ የምታገኙበት ጊዜ ይኑራችሁ፡፡ በዚህ የፋታ ሰዐታችሁ ታዲያ ከየትኛውም አይነት ሀላፊነት እና ተግባር ራሳችሁን ነፃ በማድረግ አእምሮአችሁንም ሆነ አካላችሁን ለማሳረፍ ሙከራ አድርጉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ቴሌቪዥን፣ ራዲዬ፣ አይፓድ፣ ኮምፒውተር፣ ስልክ የመሳሰሉትን ነገሮች እንኳ በዚህ የፋታ ጊዜያችሁ በመዝጋት ውጥረትን ቢያንስ ቢያንስ ረገብ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡

እስኪ ይሁና!

አንድ አንድ የውጥረት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ልንለውጣቸውም ሆነ ልንወጣቸው አንችል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፣ ከልብዎ የሚወዱት ወዳጅዎ በሞት ከዚህ ዓለም ቢለይ ወዳጅዎን ከሞት የሚመልሱበት መላ አይኖርም፤ አልያም ደግሞ በህክምና የማይድን ህመም ቢያጋጥምዎ ያሉበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መቀየር አይችሉ ይሆናል፡፡ ታዲያ፣ እነዚህን የውጥረት ምንጮች ማድረቂያ አንዱ ስልት ነባራዊ ሁኔታውን አገናዝቦ “እስኪ ይሁና!” ብሎ መቀበል ነው፡፡ “ለምን እንዲህ እና እንዲያ ሆነ?”፣ “እንደው ጌታዬ ምን ብበድልህ ነው?”፣ “እውነት የልህማ!” ወዘተ ዓይነት ቅሬታዎችና ምሬቶች ውጥረትን ያባብሱ ይሆናል እንጂ አይቀንሱም፡፡ ስለዚህ፣ ልንለውጥ የማንችለውን ነገር ዘወትር ከመጋፋት ይልቅ እስኪ ይሁና ብሎ መቀበል ውጥረቱን ያረግባል፡፡ ለምሳሌ፣ የካንሰር ታማሚ ቢሆኑ እና ነጋ ጠባ እንደው አምላኬ ምን ብበድልህ ነው የሚል ምሬት ውስጥ ቢገቡ፤ በአንድ በኩል ህመሙ የሚፈጥረው ውጥረት አለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለምን የሚለው መልስ አልባ ጥያቄዎ የሚፈጥረው ሌላ ውጥረት አለ፡፡ ስለዚህ፣ መለወጥ የማይችሉትን ይህንን እውነታ መቀበል ቢችሉ ቢያንስ ቢያንስ እርሶ የፈጠሩትን፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነብዎትን ሁለተኛውን ተጨማሪ ውጥረት ይቀንሳሉ፡፡

ዘና ማለት

በየዕለቱ ዘና ሊያደርገን የሚችል አንድ ነገር ማድረግ መቻል ውጥረትን መቀነሻ ፍቱን መላ ነው፡፡ መጫወት፣ መደነስ፣ ሙዚቃ መስማት ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ምንም ይሁን ምን በየዕለቱ አንድ ዘና የሚያደርጋችሁን ነገር ማድረግ ውጥረትን ለመቀነስም ሆነ ለመቆጣጠር በእጅጉ ይረዳል፡፡ የሚያስደስታችሁን ነገር በየጊዜው ባደረጋችሁ ቁጥር ለምትሰሩትም ስራ የሚኖራችሁ ፍቅር እንዲሁ ተያይዞ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ስጡ ይሰጣችሁማል!

ይህ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወርቃማ ጥቅሶች መካከል አንዱ ነው፡፡ መስጠት ለ”መጽደቅ” ብቻ ሳይሆን ጤናን ለመጠበቅም ይረዳል፤ በሽታ የመከላከል አቅማችንን ከፍ ያደርጋል፤ ህይወታችን በትርጉም የተሞላና በዓላማ የታጠረ እንዲሆን ያግዛል፡፡ ስለዚህ፣ ያላችሁን ማንኛውንም ነገር ጊዜም ሆነ ገንዘብ እንደየአቅማችሁ እና ነባራዊ ሁኔታችሁ ስጡ፣ በምትኩ ከውጥረት ነፃ የሆነ ህይወት ይሰጣችኋል፡፡ አንድ አንዶቻችሁ እዚህ ጋር “እኔ ራሴ እርዳታ የምፈልግ ሰው ነኝ፡፡ ምን ኖሮኝ ነው የምሰጠው? ራስ ሳይጠና…፡፡” ትሉ ይሆናል፡፡ ጊዜን መስጠት፣ ጉልበትን መለገስ፣ አከባቢን ፅዱና አረንጓዴ ማድረግ ወዘተ በነፃ ራስ ሳይጠናም በዙሪያችን ለሚገኙ ሰዎች ልናበረክት ከምንችለው ብዙ ነገር መካከል ጥቂቱ ነው፡፡ እና ነገሩ “ከአንጀት ካለቀሱ” ነውና እንዲያው ለሌሎች ብቻ ብለን ሳይሆን ለራሳችንም አሰብ አድርገን መስጠትን ባህላችን እናድርግ፡፡

ወሲብ

የቨርጂኒያው ሳይኮሎጂ ሙያ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጄምስ ኮን ከሚያፈቅሩት ሰው ጋር አዘውትሮ ወሲብ መፈፀም ቢታመሙ ቶሎ ለመዳን፣ በህመም እና በሽታ የመያዝ እድላችንን ለማጥበብ እንዲሁም ረጅም እድሜ ለመኖር ያስችላል ይላሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሚወዱት ሰው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የእግር ጉዞ ማድረግ እንኳን ውጥረትን በእጅጉ እንደሚቀንስ የጥናት ውጤታችን ያሳያል ብለዋል እኚሁ ሳይኮሎጂስት፡፡

ይቅር ብያለሁ!

ቂምና በቀልን መቋጠር የሚያስከፍለው ዋጋ የትዬለሌ ነው፡፡ ውስጣችን ቂምና ቅሬታ ሲያዝል ሰውነታችን ይዝላል፣ አእምሮአችን አሰራሩ ይዛነፋል፣ አካላችን ጤንነቱ ይጓደላል፡፡ ሚቺጋን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተደረገ ጥናት ይቅርታ ማድረግ ከጤናማ አእምሮና አካል ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው አረጋግÚል፡፡ “ይቅር ብያለሁ!” የሚሉ ሰዎች “በመቃብሬ ላይ…!” ከሚሉ ሰዎች ይልቅ በአካልም ሆነ በአእምሮ ይበልጥ ጤነኛ ናቸው፡፡ “በደለን” የምንለውን ሰው ሳይሆን የገዛ ራሳችንን ለመጥቀም ዛሬ ነገ ሳንል ይቅርታ ማድረግን እንለማመድ፡፡

ፅሞና

በብዛት የምስራቃዊኑ ባህል ነው፡፡ በተለይ የአእምሮ ጤንነትን በመጠበቅ ረገድ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ፅሞና በእንግሊዝኛ “ሜዲቴሽን” ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ አንዱ ጠቀሜታው ውጥረትን መቀነስ ነው፡፡ በቀን ለአንድ ወይም ሁለት ጊዜ ለሀያ ደቂቃ ያህል “ሜዲቴሽን” መስራት በርካታ ጠቃሜታ ያስገኛል፡፡ ፅሞና ማለት አንድ ስዕል ላይ ወይም አንዳች ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ አእምሮ ውጥረት የፈጠሩበትን ነገሮች እንዲዘነጋና እንዲረጋጋ የማድረግ ስልት ነው፡፡ አስሩን እየፈተለ ውጥርጥር ያለን አእምሮ ፅሞና ረጋ ያደርጋል፡፡

ኑ ጓደኞቼ…!

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ስሜታዊ ውጥረትን የመቋቋም ችሎታቸው ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበት አንድ ምክንያት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ከጓደኞቻቸው ጋር ጥብቅ ቅርርብ እና ጓደኝነት ስለሚመሰርቱ ነው፡፡ ስለዚህ፣ በስራም ሆነ በሌላ ጉዳይ አእምሮ ውጥር ሲል ባልንጃራን/ጓደኛን አግኝቶ የሆድ የሆድን ማውራት “እፎይ” ለማለት ይረዳል፡፡

ሙዚቃ

ውጥረት ሲበዛብዎት ሙዚቃ ማዳመጥም ሆነ ከድምፃዊው ጋር አብሮ ማንጎራጎር ቀላል የማይባል መረጋጋትን እና መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ የአሜሪካ ሳይኮሎጂ ባለሙያዎች ማኅበር ቅርብ ጊዜ በአከናወነው ጥናት መሰረት እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ሙዚቃ ውጥረትን የሚያረግቡበት ቁጥር አንድ መሳሪያቸው እንደሆነ ደርሶበታል፡፡

ሺህ አመት አይኖር!

ሕይወትን በሁሉም መስክ ቀለል ሊያደርጉ የሚችሉ ቁም ነገሮችን ማከናወን የዋዛ ውጥረት መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ስልት አይደለም፡፡ በተቻለ መጠን ሕይወትን ቀልጣፋ እና ቀላል የሚያደርጉ አማራጮችን አፈላልጎ መገልገል ብልህነት ነው፡፡ ሺህ አመት አይኖር! ለምሳሌ፣ የሚኖሩበት አከባቢ እምብዛም ከመስሪያ ቤትዎ የማይርቅ ከሆነ ከታክሲ ግፊያ እና ሰልፍ ይሉት ልፊያ ዳኑ ማለት ነው፡፡ ታክሲም ላያስፈልግዎት ይችላል፡፡ ሁለትና ሶስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዘ አድርገው ቤትዎ ቢገቡ ወጪም ውጥረትም ቀነሱ ማለት ነው፡፡ የቪዛ ካርድ ተጠቃሚ ቢሆኑ ገንዘብ ለማውጣት በፈለጉ ቁጥር የስራ ቀንና ሰዐት መጠበቅም ይሁን መሰለፍ አያስፈልግዎትም፡፡ ምግብ ቤትዎ አብስለው ቢመገቡ በመስተንግዶና ምግብ ንፅህና ጉድለት እንዲሁም በዋጋ ንረት መጎዳት ምክንያት ለሚደርሰብዎት ቅሬታ መላ ዘየዱ ማለት ነው፡፡ የምግብ ዝግጅት ቢማሩ የምግብ ችሎታዎ እና እውቀትዎን ከፍ በማድረግ በጣት ከሚቆጠሩ አማራጮች በመውጣት ጣት የሚያስቆረጥሙ ብዙ ምግቦችን አዘጋጅተው ጊዜ፣ ጤናና ደስታ ያተርፋሉ፡፡ ብቻ በሁሉም መስክ በተቻለ መጠን የዕለት ተዕለት ሕይወትን ቀላልና ቀልጣፋ የሚያደርጉ እርምጃዎችን መውሰድ ውጥረትን ቀንሶ ጤናና ለመጨመር ይረዳል፡፡

በመጨረሻ፣ ውጥረትን መቀነስ የሚለውን ሀሳብ ከላይ እስከታች ይዘን መዝለቃችን ውጥረት ጨርሶ አያስፈልግም ለማለት እንዳልሆነ አንባቢ ይገንዘብልኝ፡፡ ልክ የሌለው ውጥረት እርግጥ ነው አይበጅም፡፡ በልክ የሆነ ውጥረት ግን አስፈላጊ ነው፡፡ ስራ ያሰራል፤ በሽታ መከላከያ ህዋሶቻችን እንኳ ንቁ እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ መቆጣጠርም ሆነ መከላከል የሚያስፈልገው ከልክ በላይ ሆኖ እረፍት እና እፎይታ፣ ጤናና ደስታ የነሳን ውጥረት ነው፡፡

 

ምንጭ፡- ሜዲካል መጽሄት ግንቦት 2008