Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሂሳብ ሊቃውንት ዘንድ አንድ ሰው በህይወት እያለ ተረ

አንድ ሰው ነበር ኢርዶስ የሚሉት

 

Image result for ኢርዶስን

 

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሂሳብ ሊቃውንት ዘንድ አንድ ሰው በህይወት እያለ ተረት እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ ከሞተ በኋላ ደግሞ ብሶበታል – ፖል ኢርዶስ፡፡

ኢርዶስን ከአስር ዓመታት በላይ ተከታትሎ በህይወት ታሪኩ ላይ የሚያጠነጥን ‘The Man Who Only Love Numbers’ የሚል መጽሐፍ የጻፈው ፖል ሆፍማን መጽሐፉ ባለ ከፍተኛ ሽያጭ (Best-Seller) ሆኖለታል።

ለመሆኑ ፖል ኢርዶስ ማነው ?

እርግጥ ነው የ20ኛው ክፍለ ዘመን ወደር የለሽ የሂሳብ ሊቅነቱን ማንም አይጠራጠርም፡፡ እንዲያውም በርካታ የሂሳብ የምርምር ወረቀቶችን በመጻፍ እስከዛሬ ከነበሩት የሂሳብ ሊቃውንት – ታላቁ ‘ዮለር’ን ጨምሮ – ማንም አይስተካከለውም ነበር የሚባለው፡፡

በዓለም አቀፍ የሂሳብ ሊቃውንት አምባ አንድ የሂሳብ ሊቅ 50 ያህል የምርምር ወረቀቶችን ካሳተመ “ኦ!….እሱኮ ታላቅ የሂሳብ ሊቅ ነው’”ይባላል፡፡ ኢርዶሳችን ግን ስንት የምርምር ወረቀቶችን አሳተመ ? ከ1500 በላይ፡፡

በሁሉም የአለማችን ክፍል ያሉ የሂሳብ ሊቃውንት የኢርዶስ ስም ሲነሳ የሚታወሳቸው ግን ሌላ ነገር ነው። ኢርዶስ የሂሳብ ተንከራታች ነበር፣ የሂሳብ መንፈሳዊ ተጓዥ። ከሂሳብ ውጪ አንዳችም ህይወት ያልነበረው ሰው !

እርግጥ ነው ዓለማችን በሂሳብ ፍቅር የተለከፉ በርካቶችን ታዝባለች። ግን ማነው እንደ ኢርዶስ በቀን እስከ 19 ሰዓት ያህል ሂሳብ የሚሰራ? ሂሳብ ማለት ውበት ካልሆነ ውበት አላውቅም የሚለው ኢርዶስ ከሂሳብና ከሂሳብ ሊቃውንት አምባ ውጪ አንዳችም ህይወት አልነበረው፡፡ ኢርዶስ ሚስት፣ ልጆች፣ ቤትም ሆነ ቋሚ ስራ አልነበረው፡፡

ከ20ዎቹ ዓመታቱ አንስቶ የሂሳብ ኮንፈረንስ ሊከታተል በሄደበት በድንገተኛ የልብ ህመም እስከሞተበት እስከ 83 ዓመቱ ኢርዶስ ዘመኑን ያሳለፈው በሁለት ነገር ነው ማለት ይቻላል – አንድ፣ ሂሳብ ሲሰራ….ሁለት፣ ሲዞር፡፡ የሂሳብ ሴሚናር አለበት የተባለ የዓለም ክፍል ወይም ዩኒቨርሲቲ ኢርዶስ ይጠፋል ማለት ዘበት ነው፡፡

ወዳጆቹ ኢርዶስን ለማግኘት ሲፈልጉ መጀመሪያ በዓለም ዙሪያ ኢርዶስን ሊመስጥ የሚችል የሂሳብ ኮንፈረንስ ያለበት ሀገር ያጣራሉ፡፡ ከዛ ኮንፈረንሱ በሚካሄድበት ዩኒቨርሲቲ ባሉ በግምት አምስት በሚሆኑ የሂሳብ ሊቃውንት አድራሻ ደብዳቤ ይልካሉ፡፡ ያለ ጥርጥር አንዱ – ኢርዶስ ይደርሰዋል፡፡

በአንዱ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ኮንፈረንስ ሲካሄድ አዘጋጆቹ ኢርዶስን ለመጥራት አያሳስባቸውም፡፡ ለነገሩ እንጥራውስ ቢሉ በየትኛው አድራሻ ሊጠሩት – እሱ እንደሁ ቋሚ አድራሻ የለው፡፡ ለነገሩ እሱ ራሱ የሂሳብ ኮንፈረንስ ያለበትን አነፍንፎ ከች ይላል እንጂ፡፡

ለሳምንት ወይም ለሁለት ሳምንት ያህል ካረፈበት በአንዱ የዓለማችን ክፍል ካለ የሂሳብ ሊቅ ቤት ተነስቶ፣ ብዙዎቹ የዓለማችን ታላላቅ የሂሳብ ሊቃውንት የሚያውቋትን በዓለም ላይ ያሉትን ጥቂት ንብረቶቹን – ጥቂት ልብሶቹንና የሒሳብ መስሪያ ወረቀቶቹን የሚይዝባትን ያረጀች ቦርሳ ይዞ፣ ከተፍ ! ከዚያም ወደ ሂሳብ ሴሚናሩ አዳራሽ ወይም ወደ መጣበት ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ትምህርት ክፍል ያቀናና ያቺን ሁሉም የሚያውቋትን መፈክሩን የሃንጋሪያዊ ዘይቤ ባለው እንግሊዝኛ ያውጃል ‘My Mind is Open’ (አንጎሌ ክፍት ነው፡፡) አሁን ሂሳብ መስራት እንችላለን ነው ነገሩ፡፡

አብዛኞቹ ታላላቅ የሂሳብ ሊቃውንት ለብቻቸው መሽገው ነው ከሂሳብ እንቆቅልሾች (Problems) ጋ የተፋለሙት፡፡ ለኢርዶስ ግን ሂሳብ ከምንም በላይ ማህበራዊ ጉዳይ ነው – ሰብዓዊ መስተጋብር። ለዚህም ነው ከ1500 በላይ ከሚሆኑ የምርምር ስራዎቹ አብዛኞቹን ከ500 በላይ ከሆኑ የሂሳብ ሊቃውንትጋ በጥምረት የሰራው፡፡ ከሂሳብ ውጭ አንዳችም ዓለም ለሌለውና በተጠራበት የእራት ግብዣ ላይ ስለ ሂሳብ የሚያወራው ሰው ካጠ እዛው የእራት ጠረጴዛው ላይ ሊተኛ የሚችለው ኢርዶስ የሂሳብ ሴሚናሮችና የሂሳብ ሊቃውንት ስብስብ ብቸኛዎቹ ከሰው የመቀላቀያ ምክንያቶቹ ነበሩ፡፡

ኢርዶስ ትውልዱ ሀንጋሪ ነው – አንደኛው የዓለም ጦርነት አውሮፖን ሊያምስ አንድ ዓመት ሲቀረው በ1913 ተወለደ፡፡ ወላጆቹ የሁለተኛ ደረጃ የሂሳብ መምህራን የነበሩ አይሁዶች ናቸው፡፡ ኢርዶስ በተወለደበት ሰሞን ሁለቱም እህቶቹ በ‘ስካርሌት ፌቨር’ መቀጠፋቸው የኢርዶስን ወላጆች በብቸኛ ልጃቸው በኢርዶስ ላይ ሙጥኝ እንዲሉ አድርጓቸዋል። ጭራሽ የኢርዶስ አባት በግዞት ወደ ሳይቤሪያ መወሰዱ አኑካ የሚላት እናቱ ሙሉ ህይወቷን ለህፃኑ ኢርዶስ እንድትሰጥ አደረጋት፡፡ ተላላፊ በሽታ ፍራቻ ኢርዶስ ሁለተኛ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ የተማረው ቤት ውሰጥ ነው፡፡ በፍጹም ምሁራዊ ክባቤ ውስጥ ያደገው ኢርዶስ በሶስት ዓመቱ በሺ ቤት ያሉ ቁጥሮችን በጭንቅላቱ ማባዛት፣ ቤት የሚመጡ እንግዶችን እድሜ እየጠየቀ እስከ ዛሬ የኖሩትን በሰከንድ አስልቶ መናገረ ጀመረ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ሲገባ ደግሞ በዝነኛው የሃንጋሪ የተማዎች የሂሳብ መጽሄት ላይ የሚወጡ የውድድር ጥያቄዎች ቀንደኛ መላሽ ሆነ፡፡ አደገኛ የሂሳብ ሰው መሆኑ በጀው እንጂ በወቅቱ በነበረው ፀረ-ሴማዊነት ሳቢያ ኢርዶስ ዩኒቨርሲቲ መግባት ባልቻለ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ቡዳፔስት ያለው ትልቁ ዩኒቨርሲቲ ገባና በ21 ዓመቱ በሂሳብ Ph. Dውን ያዘ፡፡ ወቅቱ ፀረ-ሴማዊነት ዕጅጉን የተስፋፋበት ዘመን ስለነበር ለድህረ-ዶክትሬት ጥናት ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ዕድል ሲሰጠው ሳያቅማማ ወደ እንግሊዝ አገር አቀና፡፡

ኢርዶስ ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ እንደገባ አንድ ቀን ያልጠበቀው ችግር ገጠመው፡፡ የሻይ ሰዓት ነው። ለተማሪዎች ዳቦና ቅቤ ቀርቧል፡፡ ተማሪዎች ዳቦው ላይ ቅቤ እየቀቡ ይበላሉ፡፡ ኢርዶስ ደነገጠ፡፡ እስከዛሬ ዳቦ ላይ ቅቤ ቀብታ የምታበላው እናቱ አኑካ ነበረች፡፡ ዳቦ ላይ ቅቤ የሚቀባበትን ጥበብ ደግሞ ፈጽሞ አያውቅም፡፡ ኢርዶስ አፈረ፡፡ ….ግን እንደምንም ሞከርኩት – ብዙም ከባድ አይደለም ይላል ኢርዶስ፡፡ በ83 ዓመት የህይወት ዘመኑ ከሂሳብ ውጪ አንዳችም ይህ ነው የሚባል ሙያ ያልነበረው ኢርዶስ ከሂሳብ ሊቃውንት ጓደኞቹ ጋ ጨዋታ ተነስቶ ስለ ምግብ ማብሰል ችሎታቸው ሲጨዋወቱ፣ ‘እኔ እንኳን…ይላል ኢርዶስ….እስከ ዛሬ ሞክሬው ባላውቅም እንቁላል መቀቀል የሚያቅተኝ አይመስለኝም፡፡’

ኢርዶስ ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ እያለ የጀመረው የመንከራተት አባዜ ህይወቱን ሙሉ ተከትሎታል፡፡ በዚህ አመሉ ሳቢያ ለኢርዶስ ቋሚ የዩኒቨርሲቲ የማስተማር ስራ ሊሰጠው የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ ለነገሩ እሱስ ቢሆን መች በጄ ብሎ ! በዚህ ምክንያት የኢርዶስ የገቢ ምንጭ በአብዛኛው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በጊዜያዊነት የሚሰጣቸው ሌክቸሮችና የጓደኞቹ ኪስ ነበር፡፡ 1952 ላይ ግን ለኢርዶስ የሚመች ስራ ኖትረዳም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተገኘለት ወይም ተፈጠረለት፡፡ ይኸውም መቀመጫውን ኖትረዳም ዩኒቨርሲቲ አድርጎ ባሻው ጊዜ የፈለገው አገር እንደልቡ እየሄደ የሂሳብ ሴሚናር የሚካፈልበትን ነፃነት የሚያጎናጽፍ፡፡ ይህን ዓይነት ነፃነት ማግኘት በማስተማር ኃላፊነቶች ውጥረት ሳቢያ ለብዙ ፕሮፌሰሮች የማይታሰብ ነው፡፡ ለኢርዶስ ግን ተቻለ፡፡ ግን ምን ያደርጋል…ኢርዶስ ይህን በረከት ብዙም ሳይቋደስ አንድ ችግር ተፈጠረ፡፡ በወቅቱ በሴናተር ማካርቲ የተቀጣጠለው አሜሪካንን ከኮሚኒስት ርዝራዦች ማጥራት የተባለው ዘመቻ ኢርዶስን አንዱ ኢላማ አደረገው፡፡

ምክኒያት ?

በኮሚኒስት ሀንጋሪ ካለችው እናቱጋና በኮሚኒስት ቻይና ካለው የሂሳብ ሊቅ ሁዋን ጋ ደብዳቤ መላላኩ ! በቃ ይኸው ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢርዶስ ለሁዋን የላካቸው አብዛኞቹ ደብዳቤዎች….

“ውድ ሁዋን….X እና yን ኢንቲጀሮች ናቸው ብለን ብንወስድ….” የሚሉ ዓይነት ቢሆኑም አጣሪ ኮምሽኑ ግን ኢርዶስን ክፉኛ ነው የጠረጠረው፡፡ እናም የአጣሪ ኮምሽኑ አባል ኢርዶስ ቢሮ ድረስ መጥቶ ኢርዶስን መረመረው፡፡

“ለመሆኑ ስለማርክስ ምን ታስባለህ ?” ጠየቀ መርማሪው፡፡

“ምንም አላስብም፡፡ እንደምታውቀው ማቲማቲሺያን ነኝ – የማርክስን ስራ ለመገምገም ብቁ ነኝ ብዬ አላስብም፡፡ ቢሆንም ግን ሰውየው ከባድ ጭንቅላት ሳይኖረው አይቀርም፡፡”አበቃ፡፡ በዚሁ ኢርዶስ አሜሪካንን ለቅቆ ከወጣ የመመለሻ ቪዛ እንማይሰጠው ተነገረው፡፡ እንደተለመደው ደግሞ አንዱ አገር አንድ የሒሳብ ሴሚናር ሊካሄድ ነው፡፡ ምንም ሳያመነታ ሄደ፡፡ለመመለስ ሲያመለክት አትገባም ተባለ፡፡ ከአስር ያህል ዓመታት በኋላ እገዳው አስኪነሳለት ድረስ ሒሳብ ባለበት ቦታ ሁሉ ዓለምን ሲያዳርስ – የሂሳብ በረከቱን ሲረጭ አሜሪካንን ግን አልረገጠም፡፡ በመሆኑም ለአስር ዓመታት ያህል ኢርዶስን አጠገባቸው ማግኘት ያልቻሉ አሜሪካውያን የሒሳብ ሊቃውንት ለረጅም ጊዜያት ያህል የአሜሪካንን ሒሳብ ድብርት ተጭኖት ነበር ይላሉ፡፡

ኢርዶስ አንዲት መሳጭ ሒሳባዊ ሃሳብ ብልጭ ካለችበት ሃሳቢቱን ለማጋራት በየትኛውም ሰዓት ይሁን የትኛውም የዓለም ክፍል ያለ የሒሳብ ሊቅ ጋ ይደውላል፡፡ አንዴ አንዲት አስደናቂ ሒሳባዊ ዘዴ ተከሰተችለትና በሌላ የዓለም ክፍል ወዳለ የሂሳብ ሊቅ ጋ ሊደውል ስልክ አነሳ፣ “ኢርዶስ፣ እንዴት በዚህ ሰዓት ሰው ቤት ስልክ ትደውላለህ። አሁንኮ’ የምትደውልለት ሰውዬጋ ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ነው” አሉት ጓደኞቹ በተቃውሞ፡፡ “አውቃለሁ…” አለ ኢርዶስ ስልኩን እየደወለ፣ “ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ከሆነ በእርግጠኝነት ከቤቱ የትም ሊሄድ አይችልም ማለት ነው፡፡”

ሒሳብ ሲሰራ ቡና መጠጣት የሚያዘወትረው ኢርዶስ የሒሳብ ሊቅ ማለት ቡናን ወደ ሒሳብ የሚለውጥ ማሽን ነው ሲል ይኮምካል፡፡ በ1971 (ያኔ ኢርዶስ 58 ዓመቱ ነው፡፡) እንደጉድ የሚወዳት እናቱ አኑካ ስትሞት ክፉኛ ነበር የተሰበረው። ሀዘኑን ለመርሳት በቀን 19 ሰዓት ያህል ሒሳብ መስራት የጀመረውም ያኔ ነው፡፡ በሃዘኑ ሳቢያ ያጋጠመውን ድብርት ለማሸነፍ አምፊታሚን የተባለ አነቃቂ መድሃኒት መጠቀም ጀመረ፡፡ የሱሰኝነት አደጋው ያሳሰበው ጓደኛው ለኢርዶስ የውድድር ሃሳብ አቀረበለት – ለአንደ ወር አምፊታሚን ካልተጠቀመ 500 ዶላር ሊሰጠው፡፡ ኢርዶስ ለአንድ ወር ያህል አምፊታሚን ሳይጠቀም ውድድሩን አሸነፈ፡፡ የ500 ዶላሩን ቼክ ከጓደኛው እየተቀበለ እንዲህ አለው ‘….ከሒሳብ ውጪ ሌላ ሱስ እንደሌለብኝ ያረጋገጥኩልህ ይመስለኛል፡፡ ችግሩ ግን አምፊታሚን ባለመውሰዴ ሳቢያ ሒሳብ በአንድ ወር ያህል ወደኋላ ቀርቷል፡፡’ኢርዶስ በቅርብ ጓደኞቹ ዘንድ በስፋት የሚታወቅ የራሱ የሆነ መዝገበ ቃላት ነበረው፡፡ በዚሁ መዝገበ ቃላቱ መሰረት አንድ የሒሳብ ሊቅ ሒሳብ መስራት ካቆመ ወይም ለሒሳባዊ ውበቱና ጥራቱ ብቻ ከሚጠናው ‘Pure Mathematics’ ወጥቶ ሒሳብ ጥቅም ላይ ወደ ሚውልባቸው ምህንድስና ወይም ወደ ሌላ ተዛማጅ ዘርፎች ከገባ ያ ሰው ሞቷል ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሒሳብ በጣም ጎበዝ የነበረ ልጅ ነበር፡፡ ይህ ልጅ በኢርዶስ እርዳታ በ13 ዓመቱ የሒሳብ የምርምር ወረቀት ሁሉ ጽፏል፡፡ አንድ ቀን ኢርዶስ እያዘነ፣ ‘ያ ጎበዙ የሂሳብ ተማሪ…..በለጋ ዕድሜው በ17 ዓመቱ ተቀጨ’ አለ፡፡ ጓደኞቹ በድንጋጤ ክው ብለው፣ ‘ምን ሆኖ ሞተ ?’ ሲሉ ጠየቁ፡፡ ‘ሂሳብን ትቶ ኢንጅነሪንግ ገባ።’

በኢርዶስ መዝገበ ቃላት እግዚአብሔር ማለት ታላቁ ፋሽስት ነው ይላል – እንደ ቀልድ፡፡ ‘ካልሲዎቼን፣ መነጽሬንና የሃንጋሪ ፓስፖርቴን የሚደብቅብኝ እሱ እንደሆነ አውቃለሁ የሚለው ኢርዶስ ….ከሁሉ ከሁሉ ግን ታላቁ ፋሽስት እግዚአብሔር ዘንድ አንድ ትልቅ መጽሀፍ አለ’ ይላል፡፡ ይህ መጽሀፍ በሂሳብ ዓለም ያሉ ሒሳባዊ ቴረሞችና ውብ የማረጋገጫ ዘዴዎቻቸው (Proofs) ያሉበት ነው፡፡ እኛ ሒሳብ ወዳዶች አንድን የሂሳብ ጥያቄ (Problem) ለመስራት አበሳችንን ስናይ ፋሽስቱ የመጽሀፉን ገጽ ገልጦ በጨረፍታ ያሳየንና ዝግት ያደርገዋል። እኛ ደግሞ ያቺ ያየናት ብልጭ ትልብንና ከመጽሀፉ ገፆች ያላየነውን ለማግኘት አበሳችንን እናያለን – ኦ ፋሽስቱ’ ይላል ኢርዶስ፡፡

‘በእግዚአብሔር ላታምኑ ትችላለችሁ የሚለው ኢርዶስ፣ በመጽሀፉ ግን ማመን አለባችሁ’ ባይ ነው፡፡ አንድ ሒሳባዊ ቁምነገር ውብ በሆነ መልኩ ከተረጋገጠ፣ “ኦ ይሄ በቀጥታ ከመጽሀፉ የተገኘ ነው” ይላል ኢርዶስ በአድናቆት፡፡ ፖል ኢርዶስ እንዲህ እንዲህ እያለ ተዓምረኛ የሒሳብ ችሎታውንና ምንግዜም የማይረሳ አነቃቂ ማንነቱን እንደያዘ በዓለም የሒሳብ ሊቃውንት አምባ የዕውቀት በረከቱን እንደረጨ በ1996 ፖላንድ – ዋርሶ ውስጥ የሒሳብ ኮንፈረንስ ሊካፈል በሄደበት አረፈ፡፡

ለነገሩ እንኳ በኢርዶስ መዝገበ ቃላት መሰረት ‘መሞት’ ማለት ‘ለቅቆ መሄድ’ ማለት ነው፡፡ እናም በ83 ዓመቱ በለጋ የማወቅ ፍላጎት እንደጦዘ ድንገት ‘ለቅቆ ሄደ፡’ እሱንኳ መሞት የሚፈልገው እንዲህ አልነበረም፡፡ ኢርዶስ መሞት የምፈልገው ይላል ‘አንዲት ከፋሽስቱ መጽሀፍ በቀጥታ የመጣች ድንቅ የሒሳብ ሌክቸር ሰጥቼ ሳበቃ…..አንዱ እጁን አውጥቶ፣ ስለአጠቃላዩ ሁኔታስ ምን ትላለህ….’ ብሎ ሲጠይቅ፣

“መልሱን ለቀጣዩ ትውልድ ትቻለሁ…”ብዬ…እዛው መፈጠም’ ይላል፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ ከነገ ወዲያ ሊሞት እንደዛሬ አንዱን የምርምር ወረቀቱን ጽፎ ጨርሷል፡፡ በቀጣዩ ቀን እኔ ነኝ ያለ ምርጥ ሌክቸሩን በሂሳብ ኮንፈረንሱ ላይ አቀረበ፡፡ በልብ ህመም ድንገት ሲሞት ከአንዱ የሂሳብ ጥያቄ ጋር ግብግብ ገጥሞ ነበር፡፡ ኪሱ ውስጥ በቀጣይ ዩቲኒያ ውስጥ ወደሚካሄድ የሒሳብ ኮንፈረንስ የምትወስደው የአውሮፕላን ትኬት ነበረች፡፡

ፖል ኢርዶስ…. ፡፡

 

ምንጭ :  ZePsychologist