Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት በ19ኛው መቶ ዘመን በነገሡት በዳግማዊ ምኒልክ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ማን ነው?

 

በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት በ19ኛው መቶ ዘመን በነገሡት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአሁን ዘመን ዳግማዊ ምኒልክ ተብሎ የሚጠራውና ዘመናት የተሻገረው ተቋም መቋቋሙ ይወሳል፡፡ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስ አገላለጽ ሌሎች የታሪክ ምሁራንም ይጋሩታል፡፡ በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ድርሳን አገላለጽም፣ የመደበኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ለመስፋፋት እንደ አንድ ዐቢይ ክስተት የሚቆጠረው ድርጊት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተከናወነው በንጉሠ ነገሥቱ ስም የሚታወቀው ትምህርት ቤት በ1900 ዓ.ም. መከፈቱ ነው፡፡

‹‹የዘመናዊ ትምህርት›› ፍላጎት እያደገ መምጣት የጀመረው በ19ኛው መቶ ዓመት መሆኑን ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮፓና ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ ዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የታሪኩ ድርሳን ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ ነባሩ የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት የሚጀምረው ግን በዘመነ አክሱም ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ መሆኑም ይገለጻል፡፡ የተለያዩ ጸሐፍትና የሥነ ትምህርት ምሁራን ነባሩን የትምህርት ሥርዓት ባህላዊ የትምህርት ሥርዓት፣ የቤተክህነት ትምህርት ቢሉትም ደስታ በርሀ ስብሐቱ በአንድ ጥናታቸው እንዳመለከቱት፣ ነባሩ የትምህርት ሥርዓት ‹‹የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት›› መባል አለበት ይላሉ፡፡›› ለዚህም ማገናዘቢያቸው እስከ 20ኛው መቶ ዓመት መባቻ ድረስ የኢትዮጵያ ትምህርት በተማከለ ወይም ባልተማከለ መልኩ በተለያዩ አካላትና ተቋማት አስተዳደርና ሥር መከናወኑ ነው፡፡

በ19ኛው መቶ ዓመት መገባደጃ ከዘመናዊነት ጋር የተያያዙ ባቡር፣ ሆስፒታል፣ ባንክ፣ መኪና ወዘተ. በኢትዮጵያ መከሰትን ተከትሎ ከውጭ አገሮች ጋር ከተፈጠረው ግንኙነት አኳያ ዘመነ ምኒልክ ብዙ ትሩፋቶችን አስገኝቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ ትምህርት ቤት መከፈቱ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ አራት ኪሎ እሪበከንቱ አፋፍ ላይ በአሁን ጊዜ በኮንዶሚኒየሞች መካከል ተሰንጎ በሚገኘው የቀድሞው የንጉሠ ነገሥቱ አማካሪ የሙሴ ኤልግ መኖርያ ቤት በነበረው ትምህርት ቤቱ መከፈቱ ይታወቃል፡፡ የትምህርት ዓይነቱም አማርኛ፣ ግእዝ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዓረቢኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ሒሳብ፣ ሳይንስና ስፖርትን የያዘ ነበር፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ልጁን የማያስተምር ወላጅ ሀብቱ እንደሚወረስ እስከ ማወጅ የደረሱት የመማር ፍላጎት ውስን በመሆኑ መኳንንቱ አሽከሮቻቸውን እንዲያስተምሩ ማዘዛቸውም ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

108 ዓመታት ያስቆጠረውን ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ጅማሪ አንድ ማዕዘን ሆኖ እየተወሳ እየተጻፈ የሚገኘው፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት የበቀለው ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ከመቋቋሙ ከስድሳ ሦስት ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ 903 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዓዲግራት ከተማ (ትግራይ) አካባቢ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

መሰንበቻውን ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅቶት በነበረው ዓውደ ጥናት ላይ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያቀረቡት አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት የተከፈተው ታኅሣሥ 1 ቀን 1837 ዓ.ም. ዓዲግራት ከተማ ዳርቻ በሚገኝ ጎልዓ መሆኑን ትምህርት ቤቱንና ዓሊቴናን በሚመለከት የተዘጋጁ ሰነዶችን በማጣቀስ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አምስት መምህራን የያዘውና በፋዘር ቢያንቸሪ በሚመራው የጎልዓ ትምህርት ቤት ሥራውን የጀመረው በ13 ወንድ ተማሪዎች ነበር፡፡ ይሰጥ የነበረው የትምህርት ዓይነትም ግእዝ፣ አማርኛ፣ ላቲን፣ ቲኦሎጂና ሥነ ቅርፅ ሲሆን፣ የማስተማሪያ ቋንቋው በአብዛኛው አማርኛ እንደነበረ የቀድሞው የፅንሰታ ትምህርት ቤት ምክትል ዳይሬክተርና መምህር የአሁኑ የዓሊቴና ቅድስት ማርያም ካቶሊካዊ ገዳም አስተዳዳሪው አባ ኃይለ ሓጎስ ያደረጉት ጥናት ያሳያል፡፡

‹‹ጎልዓ በሪ ዘመናዊ ትምህርቲ›› በሚል ርእስ በፀጋይ ሐድሽ የቀረበው ጽሑፍም ይህንኑ ሐሳብ ያጠናክራል፡፡

የጎልዓው ትምህርት ቤት ባጋጠመው ችግር ምክንያት የማስተማር ሥራውን ከአራት ዓመት ማለፍ አልቻለም፡፡ በጥቅምት 1841 ዓ.ም. ወደ ዓሊቴና መዛወሩንና በወቅቱም በአስተማሪነት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ብፁዕ አባ ገብረ ሚካኤል፣ አባ ወልደ ገብርኤልና አባ ወልደ ኪሮስ ይሠሩ እንደነበር ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡

የዓሊቴናው ትምህርት ቤት ከውጣ ውረድ አላመለጠም፡፡ በ1844 ዓ.ም. ባጋጠመው የእሳት ቃጠሎ ከደረሰበት ውድመት አገግሞ ለመነሳት ዓመታት ወስዶበታል፡፡

በሦስት ኢትዮጵያውያንና በሁለት አውሮፓውያን ካህናት አማካይነት ማስተማሩን ሲቀጥል በወቅቱ የሚሰጡ ትምህርቶች ግእዝ፣ አማርኛ፣ ላቲን፣ አርቲሜቲክ (ሒሳብ)፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ፍልስፍናና ቴኦሎጂ ሆኖ የመማርያ ቋንቋው አማርኛ ሲሆን፣ የ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የመማሪያ ቋንቋው ትግርኛንም ጨምሮ ነበር፡፡

በዓድዋ ጦርነት (1888 ዓ.ም.) ዋዜማ ወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ዓዲግራትን በመያዙና ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የመጡት ካህናት በመባረራቸው ትምህርት ቤቱ በ1887 ዓ.ም. ከተዘጋ በኋላ ተመልሶ የተከፈተው ሦስት ዓመት ቆይቶ ነበረ፡፡ የትምህርት ዓይነቶቹም ከቀደሙት ጋር ቢመሳሰልም የፈረንሣይኛ ቋንቋን ግን አክሏል፡፡ የተማሪዎች ቁጥርም 32 ደርሷል፡፡ በአቶ ፀጋይ ሓድሽ አገላለጽ፣ ዓሊቴና ከጎልዓ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት የቀጠለባት ቦታ ሆና ቆይታለች፡፡

በ1481 ዓ.ም. ቫቲካንን ለመሳለምና የሐዋርያቱን ጴጥሮስና ጳውሎስ መቃብር ለማየት በኢየሩሳሌም በኩል ወደ ሮማ (ቫቲካን) የተጓዙትን ኢትዮጵያውያን የተመለከቱት ፖፕ ሲኪስቱስ አራተኛ፣ ጥቁር አፍሪካውያን ለንግደት (ለመሳለም) በዘመኑ በነበረው አስቸጋሪ መንገድ ወደሮም መጓዛቸውንና መንፈሳዊነታቸውን በማድነቅ ለሌላው ዓለም ሕዝብ ያላደረጉትን በቫቲካን ውስጥ የእንግዳ ማረፊያ በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር አጠገብ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ቦታው ከ400 ዓመታት በላይ የግእዝ ፊደልና ቋንቋን ሊጡርጊያን (ሊተርጂ) ሲጠናበትና የተለያዩ ጽሑፎች ሲዘጋጁበት ነበር፡፡ በ1912 ዓ.ም. በነበሩት ፖፕ በነዲክቶስ 15ኛ አማካይነት ወደ ዘመናዊ ኮሌጅ በማደጉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ለስኮላርሺፕ ይጓዙ ነበር፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ተማሪዎች መካከል ዶ/ር አባ ሐጎስ ፍሡሕ በሮማ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ በኡርባኒያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ፒኤችዲ ያገኙ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በዓሊቴና ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ከሸዋ፣ ጎንደር፣ ደሴ ከትምህርት ማዕዱ ለመቋደስ ይጓዙ የነበሩት ጥቂት አልነበሩም፡፡ ለምሳሌም የአዲስ አበባ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት አቡነ አስራተ ማርያም የምሩ፣ በዓሊቴና ‹‹ብሽፋረው›› በሚል መጠርያ የሚታወቁትና ብዙ መጻሕፍት ያሳተሙት የጎንደሩ አባ ገብረ ሚካኤል መኰንን ይጠቀሳሉ፡፡  

በጎልዓ ከ171 ዓመታት በፊት የተጀመረው ዘመናዊ ትምህርት መንፈሳዊና ዓለማዊን ያስተባበረ መሆኑን በሚያወሱት አቶ ፀጋይ አገላለጽ፣ በዓለማዊውም ሆነ በሃይማኖታዊ ትምህርቱ ቦታው ያፈራቸው ምሁራን ለአገር ያበረከቱት አስተዋጽዖ ባግባቡ መሰነድ ያስፈልጋል፡፡

ረዥም ዕድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገርለትን ዘመናዊ ትምህርት ቤት በተመለከተ በዓሊቴና ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ የቀረበው ጥናት የሚሞግት ወይም የሚያጠናክር ሊቀርብበትም ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ታኅሣሥ 1 ቀን 1837 ዓ.ም. (ዲሴምበር 10 ቀን 1844) በጎልዓ (ዓዲግራት) ተከፍቷል፤›› ብሎ ዕውቅና መሰጠቱን የጠቆሙት አቶ ፀጋይ፣ የጎልዓን ታሪክም በማጉላት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶች የሚጎበኙት ቦታ እንዲሆን ማድረግም ይገባል ይላሉ፡፡

 

ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ