Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ለ‹‹ናፍቆትና ፍቅር›› አልበምህ ግጥም ማን ሰጠህ?

ናፍቆትና ፍቅር›› ስሜት ሲደመር ትምህርት

 

Image result for ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ

 

ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ ተጫዋችና ቅን እንደሆነ በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ይመሰክሩለታል፡፡ ባለፈው ሐሙስ በአዲሱ አልበም ዙሪያ ቃለምልልስ  ሳደርግለት በሳቅና በፈገግታ በሀዘን እየተመላለሰ ነበር ሃሳቡን የገለፀው፡፡ የመጀመሪያ አልበሙ ከወጣ ከሰባት ዓመት በኋላ ሰሞኑን ለአድማጭ ጆሮ የደረሰውን አልበሙን ‹‹ናፍቆትና ፍቅር›› ብሎታል፡፡ በቃለምልልሱ ወቅት ሞባይሉ ስራ አልፈታም፤ ስለ አልበሙ አስተያየት፣ አድናቆት የሚሰጡ አድማጮች ሲደውሉለት ነበር፡፡ ሚካኤል በላይነህ በህይወቱ እና በሙያው ዙሪያ ከጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው

 

ለቀረበለት ጥያቄዎች የሰጠውን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል፡

እንዴት ወደ ሙዚቃ ሕይወት መጣህ?

የተወለድኩት አዲስ አበባ ሲሆን የልጅነት ዘመኔን ያሳለፍኩት ኮተቤ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴ ወንድራድ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጥቁር አንበሳ ነበር የተማርኩት፡፡ በባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪክ ሲቲ በአድቫንስድ ዲፕሎማ፤ ከዛም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቼ ፖለቲካል ሳይንስ አጠናሁ፡፡

 

በቤተሰብ ውስጥ እህቴም ወንድሜም ጥሩ ሙዚቃ አድማጮች ነበርን፤ ከሙዚቃ ጋር አብሬ ነበር የኖርኩት፡፡ በቤት ውስጥ የሙዚቃው ፍቅር ስላለን አንዱ የከፈተውን አንዱ ይሰማዋል፡፡ ብዙ ጊዜም የምንሰማው የውጭ ሙዚቃዎችን ነበር፡፡

 

የሀገር ውስጥ ሙዚቃ አንሰማም እያልኩኝ ሳይሆን አብዝተን ግን የውጭ ሙዚቃ አንሰማ ነበር፡፡ በልጅነቴም ሆነ እስከ ተወሰነ የዕድሜ ጊዜዬ (ኮሌጅ እስከገባሁበት ጊዜ) ድረስ ‹‹ሙዚቀኛ እሆናለሁ›› ብዬ አስቤም አላውቅ፤ የሙዚቀኛ ሰፈርም ሄጄ አላውቅም/ሳቅ/ ሰዎች በቤተክርስቲያን ውስጥ በሙዚቃና በድምፅ አድገው እንደሚመጡት አይነት ሆኜ አይደለም እዚህ የደረስኩት፡፡ አስበውና የነበረው ሜዲካል ዶክተር መሆን ነበር፡፡ ሙዚቃን ስከተል ኖርኩ ማለት ባልችልም ከኮሌጅ በኋላ ግን ሙዚቃን መከተል ጀመርኩ፡፡

 

ኮሌጅ ስጨርስ ሙዚቃን እማራለሁ ብዬ አሰብኩ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ የመንግስት ስራ አገኘሁ፡፡ የመንግስት ሣራ ከጀመርኩ በኋላ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ገባሁ፡፡ የሙዚቃ ችሎታ እንዳለኝ የገባኝ ያን ጊዜ ነው፡፡ ለቤተሰብ አራተኛ (የመጨረሻ ልጅ) ነኝ፡፡ ነገር ግን በእኔ ውስጥ ያለው የሙዚቃ ስሜት በእነሱም አድጐ እንደእኔ እንደዚህ ባይወጣም ሙዚቃን ይወዳሉ፡፡

 

ከኮሌጅ ተመርቀህ ስትወጣ ስራ አገኘህ፤ ደሞዝህ ስንት ነበር?

 

አዎ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ የመንግስት መስሪያ ቤት ስራ ተቀጥሬ አራት አመት ሰርቻለሁ፡፡

 

አድቫንስ ዲፕሎማ ነበር ያለኝ፤ 420 ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡

 

ለቤተሰብህ ስንተኛ ልጅ ነህ? ሙዚቃ ስታደንቁ የነበራችሁት ወንድሞችህና እህትህ የአንተን ሞያ ተከተሉ፤ የልጅነት ህልምህ የነበረው የሜዲካል ዶክተርነት ጉዳይ ቀረ ማለት ነው?

 

ሜዲካል ዶ/ር እንዳልሆን ያደረገኝ ዘጠነኛ ክፍል ሆኜ ትርፍ አንጀት ላስወጣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኛሁ፡፡ ያን ጊዜ ነው ሆስፒታልን ጠልቼ የወጣሁት፡፡ ጐበዝ ተማሪ ነበርኩ፡፡ የት/ቤት ጓደኞቼን ሳገኝ “ኢንጂነር ትሆናለህ ብለን ስንጠብቅህ እንዲህ ሆነህ አረፍከው” ይሉኛል፡፡ የራሴ አለቃ ነኝ፤ ደስ የሚለኝን ነገር ነው የማደርገው፡፡

 

ደስ ባለኝ ሰዓት ነው ከእንቅልፌ የምነቃው…ብዙ ነገሩ ቀላል እንዳይመስልሽ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ፖለቲካል ሳይንስ ደስ ብሎኝ ፈልጌ ነው ያጠናሁት፡፡ እንደውም ይቆጨኛል ሳይንስ ነው የተማርኩት፤ አርት ነበር መማር ያለብኝ፡፡ ምክንያቱም ጂኦግራፊና ሂስትሪ ላይ በጣም ጐበዝ ነበርኩ …የአየር ንብረት ሁኔታ መከታተል ደስ ይለኛል፡፡

 

ፖለቲካል ሳይንስ ያጠናኸው ለምንድን ነው፤ ፖለቲከኛ የመሆን ሃሳብ ነበረህ?

 

ፖለቲካ ሳይንስ ያጠናሁት ፖለቲከኛም ሲያወራ ምን ሊል ፈልጐ ነው…ማለትሽ አይቀርም፡፡ ሙሉበሙሉ ባታውቂም እንኳን ግምት ትወስጃለሽ፡፡ እናም ስለ ዓለም፣ ስለ ሀገር…… ሁኔታ ብዙ ነገሮች እንድታውቂ ያግዛሻል፡፡ የድህረ ምረቃ ት/ቤት ልገባ ሃሳቡ ነበረኝ፡፡ በሙዚቃውም ላይ ጥሩ ጥሩ ፍንጮች በራሴ ላይ ማየት ስጀምር፣ ከዚያም ብዙ ጊዜ ዜማ ስለምሰራ የበለጠ ሞያውን እያሳደጉ ቴክኒካሊም እየተገነዘብኩ ከስሜት ጋር ስሠራ ትምህርቱን ትቼ ሙዚቃው ላ አተኮርኩ፡፡

 

የዛሬ ሶስት ዓመት በበርክሌ ዩኒቨርስቲ የወሰድኩት የሙዚቃ ትምህርት  የሶስት ወር ኮርስ ነበር፡፡ አሁን የሆነ ነገር ውስጤ እንዳለ ገብቶኛል፡፡

 

ያንንም የበለጠ ለመግለጽ ከውስጤ ጋር እንድነጋገር፣ በሙዚቃ ስሜት እንዳወራ፤ የምሠራው ነገር ምክንያታዊ እንዲሆን….. እስከ አሁን ስሜት ነው የሚመራኝ፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ስሜት ሲደመር ትምህርት ሲሆን የበለጠ የዳበረ አቅም ይኖራል፡፡ ፒያኖ እሞክራለሁ፤ ያንን ያንን ማሳደግ ነው የያዝኩት፡፡

 

በሙዚቃ ትምህርት ራሴን እያሳደግሁ ነው ብለሃል ከዚህ በፊት የሰራኸውን ስራ አሁን ላይ ሆነህ ስታየው ‹‹ይህቺን እንደዚህ አድርጌ ሰርቻት ቢሆን›› የምትለው አለህ?

 

አለ….. ብዙ አለ፡፡ የሙዚቃ ስራ ላይ አንዱ ከአንዱ እየተቀባበለ የሚሠራበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚያይበት አንግል ዜማ ይለያያል፡፡ እኛ አገር ከኮፒራይት ጋር የተሳሳተ አመለካከት አለ እንጂ በውጭ አንድ ሰው የሌላውን ስራ ሲሰራ በአግባቡ አስፈቅዶ በአግባቡ ነው የሚሠራው፡፡ እኛ ግን ‹‹ለምን ሠራው? ፍራሽ አዳሽ›› እንላለን፡፡  ደስ ባለው መንገድ ነው የሚሠራው፡፡ ዜማውን እሱ ያየበት መንገድ አለ፡፡ እኔም እንደዛ ነው በራሴ ስራዎች ውስጥ ያየሁት፡፡ አሁን ባይሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መልሼ እንደምሠራቸው አስባለሁ፡፡

 

በግል ከሰራኸው ውጭ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን የሠራኸው ለየት ያለ ሥራ (ሙዚቃ) አለህ?

 

አዎ፡፡ ‹‹መለያ ቀለሜ›› በሚል ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር የሠራሁት አልበም ገጣሚው ጌትነት እንየው ነበር፤ የመጀመሪያው “አንተ ጐዳና” የሚለው አልበሜ ከመውጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት የተሠራ ነው፡፡ ቀረፃው ፈረንሳይ ሀገር ነው፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ ግን አልቀረበም ነበር፡፡

 

ነገር ግን ከሰው ጋር በደንብ የተዋወቅሁበት የምለው “ማፍቀር ነው መሠልጠን” በሚለው የነቢይ መኮንን ግጥም፣ ዜማው የኔ  በሆነው “ማለባበስ ይቅር” በሚለው ዘፈን ነው፡፡ ከህዝብ ጋር በደንብ ያስተዋወቀኝ ይሄ ይመስለኛል፡፡

 

‹‹መለያ ቀለሜ›› ለሀገር ውስጥ ገበያ ለምን አልተሸጠም? ብዙዎች ጥሩ ስራ መሆኑን ሲናገሩ እሰማለሁ…?

 

ያደከመኝም ያከሠረኝም ስራ ነው፡፡ ከኪሴ ገንዘብ አውጥቼ ነበር የሠራሁት፡፡

 

ጀርመኖችና ፈረንሳዮች ለሆነ ፕሮጀክት መርጠውት ከተቀረፀ በኋላ አንዳንድ ያልተመቸ ነገር ገጠመውና ተቋረጠ፡፡

 

በሃገር ውስጥ አከፋፋይ ሳይኖረው ቀረ፡፡ በጣም የተለየ ነበር፤ ፒያኖ ሆኖ ቮካል ነበር፡፡

 

ሶስት ዘፈን ላይ ቼሎና ቫዮሊን አለው፡፡ አራቱ ዜማ የግርማ ይፍራሸዋ ነው፡፡

 

ከመጀመሪያው ካሴትህ በኋላ በሀገርና በውጭ ሀገር ኮንሰርቶችን አቅርበሃል?

 

የመጀመሪያ አልበሜ ታዋቂ እየሆነ የመጣው ቀስ በቀስ ነው፡፡ ከዛም ሁለተኛውን አልበሜን ለማገዣ ወዲያው ልሠራለት ነበረ፡፡ ግን ነገሮች እንደፈለግሁት አልሆኑልኝም፡፡ በሀገር ውስጥ ብዙ መድረኮችን ሰርቻለሁ፤ በእርግጥ የኑሮ መንገዶች አቅጣጫቸው ይገርማል፡፡

 

ህይወት እንዴት ነው?

 

አሁን መልካም ነው፡፡ ከባድ ጊዜ ነበረኝ አልፌዋለሁ፤ ከእግዜር ጋር፡፡ አስተሳሰቤ ላይ መሠረታዊ የሆኑ የህይወት ለውጦች እንዳደርግ አስገድዶኛል፡፡ ሞትን እንዳልፈራው፤ የልቤን እንድከተልና ዛሬን እንድደሰት አድርጐኛል፡፡ የህሊና ነፃነት እዉነተኛ ነፃነት እንደሆነ ስለተረዳሁ ከሠዎች ጋር በመጥፎ ነገር እንድገናኝ አልፈልግም፡፡ እየሠሩ መኖር እንዴት ደስ የሚል ጥቅም እንዳለው በደንብ አይቼበታለሁ፡፡ አሁን በሌላ የአስተሳሰብ ጥግ ላይ ነኝ፡፡

 

‹‹ናፍቆትና ፍቅር›› የሚለው አልበምህ በቅርብ ቀን ተብሎ ቢተዋወቅም ሳይወጣ ከቆየ በኋላ ነው ሊረሳ ሲል የወጣው....

 

በጠ/ሚኒስትራችን ህልፈት ብሔራዊ ሀዘን ነበረ እኮ! ሃምሌ አጋማሽ ላይ ነበር በየአዲስ አበባ ጐዳናዎች ላይ ‹‹በቅርብ ቀን›› ተብሎ የተለጠፈው… በአንድ ወር ጊዜ ሊወጣ ነበር የታሰበው፡፡

 

ይገርምሻል አሁን እንደውም የኩኩ ሰብስቤ አልበም ሊቀድም ነበር፡፡

 

ከ7 ዓመት በኋላ ሰሞኑን በተለቀቀው በሁለተኛው አልበምህ ላይ በርካታ ውስብስብ ችግሮችን እንዳለፍክ ገልፀሃል፡፡ ስለ እነዛ ውስብስብ ችግሮች ልትነግረኝ ትችላለህ?

 

የመጀመሪያው አልበሜ በ1997 ዓ.ም ነበር የወጣው፡፡ በ2002 ዓ.ም ደግሞ ይህን ሁለተኛ አልበሜን ላወጣ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ ከዛም በ2004 ዓ.ም. አዲሱ ጠ/ሚ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ቃለ መሃላ በፈፀሙ ቀን የእኔም አልበም በዛው እለት ነበር የተለቀቀው፤ መገጣጠሙ ገርሞኛል፡፡ እኔ ምርጫና ፖለቲካ እየተከተልኩ ነበር የማወጣው (ሳቅ)

 

የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ስለሆንክ ይሆን?

 

(ሳቅ) ያስኬዳል፡፡ በ2002 ዓ.ም “ናፍቆትና ፍቅር” የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሜን እየሰራሁ እያለ ባለቤቴ አረፈች፡፡ የቅርብ ሰው ከአጠገብ ሲጠፋ ይከብዳል፡፡ የቀድሞ ባለቤቴ… የሞት መንገድ ላይ መሆኗን ያወቅሁት በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው … የአንጀት ካንሠር ነበር … /ረጅም ትንፋሽ/ ሰው ተሰባሪ ነው … ሰዎች በሰው ላይ ክፉ ነገር ሲያደርጉ እንዴት ያሳዝነኛል መሠለሽ … ከዛ የሃዘን ስሜት ለመውጣት ረጅም ሰዓትና ጊዜ ወሰደብኝ፡፡ አሁን ያ ሁሉ አልፎ  ጥሩ ልጅ ስለአገኘሁ አግባቻለሁ፤ በ2004 ዓ.ም. ሐምሌ 8 ቀን፡፡ ያለፍኩበት መንገድ መጥፎ ሆኖም ስላለፈው ማውራትሽ አይቀርም፤ ጥሩና ሰፊ ልብ ያላት ሴት ማግኘት መታደል ነው፡፡ በአዲሱ አልበሜ መታሰቢያነቱን ለቀድሞ ባለቤቴ (ሚሚ መንገሻ) በማድረግ ስም ሳስቀምጥ ምንም፤ ተፅዕኖ አልነበረብኝም፤ በስምምነት ነው፡፡ አሁን ከምንም በላይ የእምነትን ዋጋና ጥቅም አግኝቻለሁ፡፡ …

 

‹‹አዲሱን›› አልበምህን ለመስራት፤ ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?

 

የወሰደብኝ አንድ አመት ነው፡፡ ባሰብኩት ጊዜ ጨረስኩኝ፤ ከእግዚአብሔር ጋር፡፡ የ2004 ዓ.ም መሪ ቃሌ የነበረው፡፡ “To get things done by any possible means”  (ባለኝ ነገር ሁሉ ስራዬን ማከናወን እንደማለት ነው) ባለፈው ዓመት ነው የጀመርኩት፡፡ በየዓመቱ በአዲስ የህይወት መሪ ቃሎች አስቀምጣለሁ፡፡  “thinking out of box” (“ከተለመደው አስተሳሰብ መውጣት) በሚል

 

ለ‹‹ናፍቆትና ፍቅር›› አልበምህ ግጥም ማን ሰጠህ?

 

መስፍን ወ/ተንሳይ የሚባል አዲስ ልጅ ነው፤ አገር ወዳድ እና ጐበዝ ልጅ ነው፡፡ ሌላ ወጣት ዳዊት ተስፋዬ፣ ቴዎድሮስ ፀጋዬም ሰጥተውኛል፡፡ እንዴት መልካም ሰዎች መሰሉሽ፡፡ ጥሩ አመለካከት እርብሽብሽ ካለው አመለካከት የራቁ ልባቸው ደስ የሚል ልጆች ናቸው፡፡ ስራቸውም እጅግ ብቃት አለው፡፡ የሠዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታን “ስወድሽ” የሚለውን ግጥምም በአልበሜ ውስጥ አካትቼዋለሁ፡፡

 

በመጀመሪያው አልበምህ ላይ በመፅሃፍ ታትመው ከወጡ የጌትነት እንየው ግጥሞች አንዱን ወስደህ ዘፍነህ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታን ዘፍነሃል…እንዴት መረጥከው?

 

የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥም የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ሬዲዮ ላይ ነበር የሰማሁት፡፡ ሱራፌል ወንድሙ ሲያነበው ሰማሁትና ወዲያው ደውዬ በጣም ደስ ይላል ይሄንን ግጥም ስጠኝ ስለው፣ መጽሐፍ ላይ እኮ አለ “መንገድ ስጡኝ” የሚለው የገብረ ክርስቶስ ደስታ የግጥም መድበል ላይ አለኝ፡፡ ከእርሱ ተውሼ አነበብኩት፡፡ በጣም ደሳስ የሚሉ ግጥሞች ነበሩት፡፡ ለጊዜው ለነበረኝ ስሜት “ስወድሽን” የሚያክልልኝ ግጥም አላገኘሁም፡፡

 

ወዲያው ዜማ ሠራሁለት፡፡ ይህንኑ ዜማ ማለት ነው፡፡ ያን ከሠራሁት በኋላ ግጥሙን ገብረክርስቶስ ደስታ በሬድዮ ሲያነበው ሰማሁት፡፡ እናም ደስ አለኝ፡፡ ገብረ ክርስቶስ በጣም ልዩ ነው ለእኔ፤ የስዕል ስራዎቹንም ሳይ የበለጠ ተደነቅሁ፡፡ በግጥሙ ውስጥ በርግጥ አንዳንድ ያልገቡኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እኔ ለዘፈን በሚመች መልኩ አድርጌ ከላይ ወደታች አመሰቃቅዬ ሰራሁት፡፡

 

አንዳንድ ባለሙያዎች ስወድሽ ግጥም አንተ የሰራኸው የገብረ ክርስቶስን… ዜማ አደብዝዞታል ይላሉ?

 

ሲጀመር ዜማ አልነበረውም፡፡ በእርግጥ ገጣሚው ሲያነበው የራሱ ዜማ አለው፡፡ እያንዳንዱ ገጣሚ ሲያነበው ሌላ ዜማ ይሰጠዋል፡፡ አሁን ከገብረክርስቶስ ጋር ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም፡፡

 

አይደለም የዜማውን ስሜት ግጥሙንም ወረቀት ላይ ነው ያየሁት…እኔ የተሰማኝን ዘፍኛለሁ፡፡ …እኔ የተሰማኝ ይሄ ነው፤  ሲወዳት …ውዴ እወድሻለሁ ሲላት ነው የማውቀው፡፡

 

ለእኔ ከአልበሙ ውስጥ የምወደው ዘፈን እሱ ነው፤ ጥሩ ሙዚቃና ጥሩ ዜማ አለው፡፡ ይህንን አስተያየት የሰጡ ሰዎች በአእምሮዋቸው ዜማ እየሰሩለት ነበር ማለት ነው፡፡ በወጣ በአምስት ቀን ውስጥ በዩቲዩብ፣ ድሬ ቲዩብ ከ15ሺ  በላይ ጊዜ ተሰምቷል…በርካታ ኮሜንቶች አሉ፡፡

 

ዜማውን እንደ ዜማ፣ ግጥሙንም እንደ ግጥም፣ ሙዚቃውንም እንደ ሙዚቃ የሰሙ ሰዎች የሰጡት ስሜት ነው የሚመስለኝ፡፡ ይኼንን ያህል የእኔን ስሜት ተጋርተዋል ማለት ነው፡፡

 

እንዲደመጥ ያደረገው ግጥሙ እንጂ፤ ዜማው (ሙዚቃው) አይደለም የሚሉ ወኖች አሉ?

 

አፌን ሞልቼ የምነግርሽ ገብረክርስቶስን እንደ አዲስ ማስተዋወቅ አለብን፡፡ ምን አልባት አንቺ በስነጽሑፍና በጋዜጠኝነት …ስራዎች አካባቢ ስለሆንሽ የሚታወቅ መሰለሽ እንጂ የ45 ዓመት ሰው ገብረክርስቶስን ታውቀዋለህ ብትይው አያውቀውም፡፡ እኔ ብዙ ሰው ጠይቄያለሁ፡፡ “የሚስለው ሰውዬ ነው…ስወድሽ የሚለው” “ከበደ ሚካኤል ግጥም ነው” በሚል በመደናገር ስሜት አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡ ‹‹ስወድሽ›› የሚለውን ‹‹ሶስተኛውን›› ሙዚቃ የሚሉ አሉ…እና የሆነ ሰፈር ላይ ስንሆን የእነሱ ሰፈር አስተሳሰብ የሌላው ሰፈር አስተሳሰብ ይመስላቸዋል፡፡ ገብረ ክርስቶስ፤ የእርሱ ማንነት፣ ስራው፣ ስዕሉ ተቋርጣል፤ አልተላለፍም ለትውልዱ፡፡ ግጥም ገጣሚ እንዳመጣው ለዘፈን አይሆንም፡፡

 

ኮምብኔሽኑ ጥሩ ነው፡፡ ሙዚቃ ስትሰሚ ግጥሙን ብቻ ልትወጅ አትችይም፡፡ ግጥሙን ወደሽው ዜማውና የድምፃዊው ድምፅ ሙዚቃውን አላሰማ ካለሽ ምን ታደርጊዋለሽ፡፡

 

የግጥም አድናቂ ነህ? ግጥም ታነባለህ?

 

ጥሩ አንባቢ ከሚባሉት ውስጥ ላልመደብ እችላለሁ፡፡ ማንበብ ደስ ይለኛል፡፡ ካልሽስ በዘፈን ውስጥ ጥሩ ግጥም አድማጭ አልነበርኩም፡፡ በዘፈን ውስጥ ባለፍኩ ቁጥር ግን ቦታው እየገባኝ እየመሰጠኝ ስለመጣ ነው፡፡

 

“መለያ ቀለሜ”ን ከጌትነት እንየው ጋር ስሰራ በጣም አስቸግረው ነበር፡፡ ገጣሚ ማለት… እያንዳንዱ ቃል ለራሱ ሚዛን አላትና አንዷ ቃል ስትጐልበት የቁስል ያህል ነው ህመሙ የሚሠማው፡፡ ያንን ስሜት ብዙ አላውቀውም ነበር፤ አስቸግረው ነበር፡፡ በ”ናፍቆትና ፍቅር” አልበሜ ግጥም የፃፉትም ልጆች በፍፁም የዘፈን ግጥም ገጣሚዎች አይደሉም፤ ገጣሚዎች ናቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ ከገጣሚዎች ነው የወሰድኩት ማለት እችላለሁ፡፡

 

ግጥሙንም ሲጽፉት ዜማ በራሳቸው አስበው ካልሆነ በስተቀር…የኔን ዜማ ሰምተው በዛ ተንተርሰው አይደለም፡፡ ስሜታቸው ላይ ነው የተፃፈው፡፡ ከዘፈናቸው ውስጥ አንቺ የሌለሽበት፣ ትመጪ እንደሁ፣ አፋጀሽኝ…የሚሉት በዘፈን ፎርም የተሠሩ አይደሉም፤ እኔ ነኝ በዘፈን ፎርም ያመጣሁት፡፡

 

አንተ ግጥም ትጽፋለህ?

 

የምጽፍ ይመስለኛል…እስከ አሁን አልፃፍኩም፡፡ ግን የሚመጡልኝን ስራዎች አስተካካዬ እሰራቸዋለሁ፡፡ ገብረ ክርስቶስ ያንን ዕድል አልሰጠኝም፡፡

 

አልበሙን ለምን ‹‹ናፍቆትና ፍቅር›› ብለህ ሰየምከው? ምን ናፍቆህ ነው…

 

የአልበሙን ስሜት ስትሰሚው …ናፍቆት አለው ፍቅር አለው፡፡ ስለዚህ ርዕስ እንስጠው ተባብለን ስንዘጋጅ ይሄን አልነው፡፡ ምን ልትይ እንደፈለግሽ ጠርጥሬሻለሁ…(ሳቅ) ከግጥሞቹ ውስጥ እኔ ያሰብኩት አለ፤ ገጣሚዎቹ  ያሰቡት ግጥምም አለ…በአልበሙ የተካተቱት ዘፈኖች በሙሉ በናፍቆትና ፍቅር ዙሪያ ናቸው፡፡

 

ከዘፈን ግጥሞችህ ውስጥ የአንተን ስሜት ተከትሎ አንተ በፈለከው መንገድ የተፃፈ ግጥም አለ ማለት ነው?

 

አዎ አለ፡፡ ‹‹ትመጪ እንደሁ›› የሚለው ለምሳሌ ዜማውም ግጥሙም ያችን ቃል ይዞ መጣ…ለቴዲ ሳመክረው…ከየት ዳውን ሎድ እንዳደረገው አላውቅም (ሳቅ) በፍጥነት በ4 ቀን ውስጥ ጽፎ አመጣልኝ፡፡ ዜማ ስታይሉና አሬንጅመንቱ…ጥሩ ለዛ ያለው ነው፡፡ ሌላው የቅጽበት ስሜቶች አለ አይደለ…? ለምሳሌ ‹‹አንቺ የሌለሽ ጊዜ›› የሚለው ዓይነት፡፡ በመጀመሪያው አልበሜ “አንተ ጐዳና…”እንደተጠቀምኩበት መጣሪያ የህይወቴ መንገድ አይነት፡፡

 

ሞቅ ሞቅ ካሉ ዘፈኖች ይልቅ ቀዝቀዝ ያሉና ወደ ትዝታ የሚያደሉ ዘፈኖች ታበዛለህ?

 

አዎ፡፡ በዚህኛው አልበሜ እንደሱ ላደርግ ሞክሬ ነበር…ግን እስከ አሁንም ያለፍኩበት መንገዱ ይሁን ምን አላውቅም ውስጤን ያዝ አደረገኝ፡፡ ግን እኮ ሞቅ ሞቅ ያሉም አሉት እኮ…ያው ግን ድምፄ ሶፍት ስለሆነ የጆሮ አደጋ አያደርስም (ሳቅ)

 

ከሀገራችን ሙዚቀኞች ጋር ህብረት የለውም ትባላለህ፤ የራስህ ምክንያቶች አሉ?

 

(ሳቅ) ብዙ ጊዜ እኔ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እነሳለሁ፡፡ ብዙ ድምፃዊያን ጠዋት 12 ሰዓት ይተኛሉ፡፡ ካለኝ ልምድም ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት በላይ ቆይቼበት የማውቀው የስራ ልምድ የለኝም፡፡ ስጨርስ ቤቴ ነው የምገባው፣ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት እንኳን ብተኛ በጠዋት አንድ እና ሁለት ሰዓት እነሳለሁ፡፡ ጠዋትን በጣም ነው የምወደው፡፡ የመጣሁበትና ያለፍኩበት ባክ ግራውንድ ነው፡፡

 

ከሙዚቃው ውጭ በርካታ የማውቃቸው ሰዎች አሉ፡፡

 

እንደነገርኩሽ እንደ ቢሮ ሰዓት በጠዋት ተነስቼ መስራት ይሻለኛል፡፡ ዜማ ሲሰሩ ብዙ ጊዜ ፍራሽ ላይ ሆነው ነው የሚሠሩት፤ እስቲ እኔስ ይመጣልኛል ብዬ አንድ ቀን ቁጭ አልኩ፡፡

 

ስራው ቀርቶ ለመቀመጥ ለመመቻቸት ጊዜውን ፈጀሁት፡፡ የቢሮ ወንበር አለኝ ቁጭ ብዬ… ኪቦርድ አለኝ፡፡ በዛ ሁኔታ ነው ስራዬን የምሰራው፡፡ በሀዘን በደስታ የምንገናኝ በርካታ ጓደኞች አሉኝ የምወዳቸው፡፡

 

ብዙ ቀልዶችና ጨዋታዎች አሉ እዛ ሰፈር፡፡ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፋለሁ፡፡

 

በአልበምህ ዙሪያ ከአዲካ ጋር ምን አቅዳችኋል?

 

በዚህ ቀን ብዬ ባልነግርሽም በቅርብ ቀን በአገር ውስጥም በውጭም ኮንሰርቶችን እንሠራለን የሚል እቅድ አለን፡፡

 

ከአዲሱ አልበምህ ለአንባቢ የምትጋብዘው?

 

(ሳቅ) ሁሉንም እወደዋለሁ፡፡ ሁሉም ዘፈን ራሱን ችሎ የሚቆም ነው፡፡ አንዱ አንዱን የሚደግፈው አይደለም፡፡ ይህን ጥያቄ እንደምጠየቅ አውቃለሁ፤ ለመልሱ ስል “ስወድሽ” የሚለውን ሙዚቃ ስሙልኝ፡፡

 

በመጨረሻ የምትለው ካለ…

 

አልበሙ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በኢሜል፣ በስልክ፣ በአካልም ገንቢ አስተያየት ለሰጡኝ ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ አዲካ ኮሚዩኒኬሽን ኤንድ ኢቨንት ኦርጋናይዜሽንን አመሰግናለሁ፡፡

 

ቴዲ አፍሮ ወደ ትዳር ለመግባት ወስኖ በዚህ ሳምንት ተሞሽሯል፡፡ ትዳር ለመመስረት መወሰን በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ እንኳን ደስ ያለህ ውድ የሞያ ጓደኛዬ፡፡

 

ለነበረን ጊዜ በጣም እናመሰግናለን፡፡

 

 

 

ትመጪ እንደሁ

 

ትመጪ እንደሁ እያልኩ፣ ሌት ተቀን ናፋቂ

 

ሰርክ የማይታክተኝ አለሁሽ ጠባቂ

 

ፍቅር ተደግፌ፣ ቃል ኪዳን ታቅፌ

 

ትመጪ እንደሁ እያልኩ፣ ክፍት ነው ደጃፌ

 

አትቀርም እላለሁ፣ በመላ በጥበብ

 

ምን ቀን እየገፋ፣ እድሜዬን ብታለብ

 

ቆፈን ቢገርፈኝም፣ ጥበቃዬ በዝቶ

 

እኔ ግን እዛው ነኝ፣ አላጐደልኩ ከቶ

 

ትመጪ እንደሁ - ትመጪ እንደሁ

 

አለሁ እኔ፡፡ ሳላጐድል በፍቅር እንዳለሁ

 

ትመጪ እንደሁ - ትመጪ እንደሁ

 

አለሁ እኔ፣ በፍቅር አለሁኝ እንዳለሁ

 

በናፍቆትሽ እሳት፣ ነድጄ ሳልከስም

 

ባይንሽ በጠረንሽ፣ መልሼ እንዳገግም

 

ሳዜም እኖራለሁ፣ ፀሎት ስደጋግም

 

ካለሁበት ድረስ፣ እግርሽ እንዲረዝም

 

 

 

ልምጣ ያልሽ እንደሆን፣ ቀና ነው ጎዳናው

 

ልቤ ተመላልሶ፣ ደልድሎታልና

 

ምኞት የማይደክመው፣ ልቤ ልበ ብርቱ

 

ትዝታም አይደለ፣ ተስፋ ነው ቅኝቱ

 

ትመጪ እንደሁ… ትመጪ እንደሁ

 

አለሁ እኔ፤ ሳላጐድል፣ በፍቅር እንዳለሁ

 

ትመጪ እንደሁ - ትመጪ እንደሁ

 

አለሁ እኔ፣ በፍቅር አለሁኝ እንዳለሁ

 

ገጣሚ ቴዎድሮስ ፀጋዬ

 

ዜማ ሚካኤል በላይነህ

 

‹‹መለያ ቀለሜ›› በሚል ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር የሠራሁት አልበም ገጣሚው ጌትነት እንየው ነበር፤ የመጀመሪያው “አንተ ጐዳና” የሚለው አልበሜ ከመውጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት የተሠራ ነው፡፡ ቀረፃው ፈረንሳይ ሀገር ነው፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ ግን አልቀረበም ነበር፡፡ ነገር ግን ከሰው ጋር በደንብ የተዋወቅሁበት የምለው “ማፍቀር ነው መሠልጠን” በሚለው የነቢይ መኮንን ግጥም፣ ዜማው የኔ  በሆነው “ማለባበስ ይቅር” በሚለው ዘፈን ነው፡፡ ከህዝብ ጋር በደንብ ያስተዋወቀኝ ይሄ ይመስለኛል፡፡

 

የመጀመሪያው አልበሜ በ1997 ዓ.ም ነበር የወጣው፡፡ በ2002 ዓ.ም ደግሞ ይህን ሁለተኛ አልበሜን ላወጣ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ ከዛም በ2004 ዓ.ም.  ነበር የተለቀቀው፤ ፡፡

 

ምንጭ፡-አዲስ አድማስ ጋዜጣ