Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

አርቲስት አስናቀች ወርቁ

 

Image result for አርቲስት አስናቀች ወርቁ

 

አስናቀች ወርቁ የኢትዮጵያን የኪነ ጥበብ ኅዋ ካደመቁት ከዋክብት ከእነጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ዘነበች ታደሰ እና ሌሎችም ጋር በመሆን የማይረሱ ሥራዎቿን ትታልን አልፋለች። በአብዛኛው የምትታወቀው ራሷን በክራሯ እያጀበች በምትጫወተው መንፈሥን ሠራቂ ዘፈኖቿ ቢሆንም፤ አስናቀች መጀመሪያ ሙያዋን የጀመረችው በተዋናይነትና በተወዛዋዥነት ነበር።

በ1944 ዓ.ም. እና 45 በማዘጋጃ ቤት ቴያትር ”የፍቅር ጮራ” እና ”እኔና ክፋቴ” የተሰኙትን ተውኔቶች አከታትላ በመጫወት በህዝብ ዘንድ ዕውቅናን አትርፋለች። በዚያን ሴቶች ከማጀት ወጥተው ከወንዶች እኩል በሥራ ዓለም መሳተፋቸው ብርቅ በሆነበት ዘመን፤ ለሁሉም አዲስ በነበረው የቴያትር መድረክ አንዲት ውብ ወጣት ሴት መታየቷ የባሰውን አስገርሟል። አስናቀች በቅርቡ በሰጠቸው አንድ ቃለምልልስ፤ ውብ ገላዋን በከፊል የሚያሳዩ ቀለል ያሉ የመድረክ አልባሶቿንና በሰዎች ላይ ያሳደሩትን ስሜት በምልሰት በማስታወስ ”ያኔ’ኮ ምን ጉደኛ ነች ነበር የተባልኩት” ብላለች።

በ1926 ዓ.ም. አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ተወልዳ እዚያው ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው ያረፈችው - አስናቀች።

እንደማንኛውም አድናቂዋ ዘፈኖቹዋን ከመውደዴ ሌላ በተለያየ አጋጣሚ አግኝቻት ደግነቷን፣ ትህትናዋን፣ ጨዋታና ቀልዷን ለማየት ችያለሁ።

በ1982 ዓ.ም. ላይ ሪቨር የሚባል የፈረንሣይ የፊልም ፕሮዳክሽን ኩባንያ ”ፈረንጅ” የሚል ፊልም ለመቅረፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። ለተዋናይነት ከመረጣቸው መካከል ታዋቂዋ ዘፋኝ ወይዘሮ ንጋቷ ከልካይና አስናቀች ወርቁ ነበሩበት። ቀረፃው የሚካሄደው ሐረር በተለምዶ የራምቦ ቤት እየተባለ የሚጠራው ቦታ ስለነበር፤ ሁላችንም ወደዚያው ተጓዝን።

የእኔ ሥራ በአማርኛ የሚጫወቱት ተዋንያን ፈረንሣይኛና እንግሊዝኛ ተናጋሪ ከሆኑት ጋር በቋንቋ እየተግባቡ እንዲሠሩ በትርጉምና በሌላም ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበር።

አስናቀች ቀደም ብሎ የተሰጣትን ቃለ ተውኔቷን ድሮ አጥንታ ጨርሳለች። ያኔ ዕድሜዋ ከሃምሳው የዘለለ ቢሆንም የረዥም ዘመን ልምዷ የተመደበላትን ክፍለ ትያትር ያለ አንዳች ችግር በቃሏ አጥንታ ለመያዝ አስችሏታል። ስለዚህም በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሌሎች ተዋንያን ሲያጠኑ እሷ ካረፍንበት የሐረር ራስ ሆቴል በረንዳ ላይ አረፍ ትልና ስላለፈ ታሪኳ ስጠይቃት እየመለሰችልኝ በቀልድ የታጀበ ለዛ ያለውን ጨዋታዋን ታመጣለች። ስለእነ አሰፋ አባተ፣ ሽሽግ ቸኮልና ወደ ኤርትራ ሄዶ ሻዕቢያን ከመቀላቀሉ በፊት የሥራ ባልደረባዋ ስለነበረው በረከት መንግሥተ አብ የነበራትን ትዝታ አካፍላኛለች። ”አሰፋ አባተ ድምፀ መልካም ብቻ ሳይሆን ፀባየ ሸጋም ነበር። እሱ ሲዘፍን ሁላችንም ፀጥ ነው። ወደር የለውማ። ማን ይስተካከለዋል? አሟሟቱ ብቻ ምስጢር ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናል” አለችኝ።

 

”ምን ሆኖ ነው የሞተው?”

”ቀን ደህና ውሎ ወደማታ ላይ ሆዴን አመመኝ አለ አሉ። ጠዋት ለሞት በቃ። የምግብ መመረዝ ነው የተባለው። ምቀኞች መድኃኒት አጠጥተውት ነው ተባለ። እውነቱ ምን እንደሆነ ማን ያውቃል?” አለች በትዝታ ነጉዳ።

”ሽሽግ ቸኮልንስ አብረሻት ሠርተሻል?”

”ወይ ጉድ! የዛሬ ልጆች ደግሞ ሽሽግን ታውቋታላችሁ? አንቺስ ጉደኛ ነሽ ልጄ። ሽሽግማ መጀመሪያ ’እንዲያው ዘራፌዋ’ን መድረክ ላይ የተጫወተች ነች። በኋላ ማሪቱ ለገሠ የተጫወተችውን ባህላዊ ዘፈን። ሌሎችም እንዲሁ ተጫውተውታል። ሽሽግ ግን ስትዘፍነው በዚያ በድምፅዋ ምን ብዬ ልንገርሽ ከጥፍር ነው የምትነቀንቀው። ...”

አንዳንዴ ከራት በኋላ ሁሉም በረንዳው ላይ ተሰብስቦ ሲዝናና፤ አስናቀች ምንግዜም የማይለያት ክራሯን ይዛ ታንጎራጉራለች። እሷ ስትዘፍን ሠራተኛ ሥራውን አቋርጦ፣ እግር የጣለው የሆቴሉ ደንበኛ የመጣበትን ትቶ፣ ... ሁሉም ይከባታል። ፈረንጆቹ ተዋንያንና የፊልሙ ሠራተኞቹ ሳይቀሩ ያንን ውብ ድምጧን ለመስማት በዙሪያዋ ይሰበሰባሉ። የፊልሙ መሪ ተዋናይ የነበረው ዕውቁ እንግሊዛዊ ተዋናይና የፊልም አዘጋጅ ቲም ሮዝ[1] በአድናቆት ከሚያዳምጧት አንዱ ነበር። ትዝ እንደሚለኝ ሥራ በዝቶበት በሰዓቱ ከአልመጣ ቦታ ይዘንለት እንድንጠብቀው ይጠይቃል።

 

ቲም ሮዝ, Tim Roth”አቤት አቤት ማለት ምን ማለት ነው?” አለኝ አንድ ቀን አጠገቤ ቆሞ ሲያደምጣት ቆየና።

”መደነቅን ወይም ጠንካራ ስሜትን የምንገልፅበት ቃል ነው”

”እና እየደገመች አቤት አቤት ስትል የምን ስሜትን ነው የምትገልጠው?”

”ቲም እየውልህ። አስናቀች የምትዘፍነው ስለ ፍቅር ብቻ ነው። ከፍቅር ድርና ማግ የተሠራች ነች”

”ይሄንን ለመረዳት እውነቴን ነው የምልሽ አማርኛ መናገር አያስፈልገኝም። እያት! ... እያት እስቲ ዓይኗ፣ ፊቷ ላይ የምታነቢው ሁሉም እኮ ይነግርሻል! በጣም የምትገርም አርቲስት ናት” አለ ቲም በፍፁም አድናቆት ተውጦ።

ከዚያ በኋላ አስናቀችን በድጋሚ ያገኘሁዋት እ.ኤ.አ. በ1998 ከበላይነሽ አመዴ፣ ከተስፋዬ ገሠሠ እንዲሁም ከሌሎች አርቲስቶች ጋር በመሆን ፓሪስ የመጣች ግዜ ነበር። ያኔ ከተጫወተቻቸው የማይረሱ ዘፈኖቿ መሃል ”ጤናዬዋ ለኔ” የሚለው ትዝ ይለኛል።

አስናቀች ትታልን ከሄደቻቸው በርካታ ተደናቂ ሥራዎቿ ሌላ በተለይ የማደንቅላት ውብ የሆነ አለባበሷንና የፋሽን ግንዛቤዋን ነው። ከሆሊዉድ ኮኮብ ተዋንያን በምንም የማያንሱ አስገራሚ ፎቶዎቿ ሽቅርቅርነቷን ይመሰክራሉ። አስናቀች ወርቁ የምንኮራባት ዕንቁ አርቲስታችን ነበረች።

ምንጭ፡- ሮዳስ ቅጽ 2,2002 ዓ.ም