Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ደመግቡዋ አርቲስት አልጋነሽ ታሪኩ «ወይራዬ»

 

Image result for አርቲስት አልጋነሽ ታሪኩ

 

በኪነ ጥበቡ ሥራ ላይ መሳተፍ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ከ1958 እስከ 1989 ዓ.ም በተወዛዋዥነት፣ በአልባሳት ዝግጅትና ስብስብ ኃላፊነት እንዲሁም በከፍተኛ የውዝዋዜ አዘጋጅነት አገልግላለች። ከ1989እስከ 2001ዓ.ም በተዋናይነት በዚሁ ቦታ ማገልገሏ ይነገርላታል። አርቲስቷ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በጡረታ ብትገለልም አሁን ድረስ በተለያዩ ፊልሞች እና ቴአትሮች ላይ በተዋናይነት እንዲሁም ለአዲስ ዓመት እና ለተለያዩ ዝግጅቶች በተጋባዥነት፣ በአስተዋዋቂነትና በባህላዊ እንዲሁም ዘመናዊ ውዝዋዜ ሥራዎች እያገለገለች ትገኛለች።

በዘርፉ በርካታ የሙያው ሰዎችን አፍርታለች። በውዝዋዜ ሥራዋ የተለያዩ የውጭ አገራትን ያየችው ይህች ታላቅ አርቲስት፤ በአለባበስ የአገሯን ባህል በማስተዋወቅ ትታወቃለች። አርቲስቷ በርካታ ዓመታትን በቴአትር ቤት አሳልፋለች። በውዝዋዜም ቢሆን ማንም የሚያህላት አልነበረም። በዚህም «የመድረኩ እንዝርት» በሚል ቅጽል ስም ይጠሯት ነበር። የዛሬ እንግዳዬን አርቲስት አልጋነሽ ታሪኩን።

እንግዳዬን ያገኘኋቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል የአርቲስቷን የሃምሳ ዓመታት ሥራዎች በሚዘከርበት ወቅት ነበር። መቼም አርቲስት አንቱ ሲባል አይወድምና አንቺ በሚል መጻፌን ከድፍረት አትቁጠሩብኝና ከዚህ በኋላ ላለው ገለጻዬ «አንቺ» እያልኩ እጓዛለሁ።

በወቅቱ ለዚህች ጥበበኛ የተዘረፈው ቅኔ፣ የተዘመረው ዝማሬና እርሷ ለአገር ጥበብ እድገት ያበረከተችው አስተዋፅኦ በስፋት ቀርቧል። ከውልደቷ አሁን እስካለችበት ሕይወቷ ያለው ታሪኳም እንዲሁ ሲተረክ ነበር። እናም እኔም ከቀረቡት መረጃዎች በተጨማሪ ባለታሪኳን አነጋግሬ ያገኘሁትን የሕይወት ተሞክሮ እነሆ ተማሩበት ልላችሁ ወደድሁ።

 

በጎጃም ክፍለ ሀገር ውስጥ ሞጣ ከተማ «ሰዴ ጊዮርጊስ» በምትባል ትንሽ መንደር ከአባቷ አቶ ታሪኩ እጅጉና ከእናቷ ወይዘሮ ጥሩነሽ ጌታሁን ሚያዝያ 19 ቀን 1942 ዓ.ም ተወለደች። ዕድሜዋም ለትምህርት ሲደርስ በትውልድ መንደሯ እስከ ሦስተኛ ክፍል ትምህርቷን ተከታተለች። በወቅቱ በተወለደችበት አካባቢ ሴት ልጅ ትዳር መያዟ እንጂ መማሯ ያለው ጠቀሜታ እምብዛም ትኩረት የሚሰጠው ባለመሆኑ ቤተሰቦቿ ገና በጨቅላ ዕድሜዋ ከአዲስ አበባ ለመጣ ሰው እንዲንከባከባትና የራሱ እንዲያደርጋት ፈቅደው ዳሯት። የትዳር አጋሯም ወደ አዲስ አበባ ይዘዋት በመሄድ አብረው መኖር ይጀምራሉ። በዚያም ታዳጊዋ አልጋነሽ ለትምህርት በነበራት ጉጉት ከዛሬ ነገ ትምህርት ያስገባኝ ይሆን እያለች ብታስብም ባለቤቷ ትምህርቷን እንድትከታተል ዕድሉን ስላላመቻቸላት በመበሳጨት ወደ ተወለደችበት አካባቢ በመመለስ ከቤተሰቦቿ ጋር መኖር ጀመረች።

አዲስ አበባን የለመደችው አልጋነሽ በገጠሩ አካባቢ መኖር ግን አልቻለችም ነበር። በተለይ ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት የሚያስገባት ሰው በማጣቷ ተመልሳ ወደ አዲስ አበባ መጣችና ከአክስቷ ጋር መኖር ጀመረች። ይሁን እንጂ ለትምህርት ያላትን ፍላጎት ተረድቶ ወደ ትምህርት ቤት የሚያስገባት ሰው በዚህም ቢሆን አልተገኘም። ከዚያ ሌላ አማራጭ መፈለጉን ተያያዘችው፡፡ እረፍት አልባዋ ታዳጊ አልጋነሽ በወቅቱ የተጠቀመችው አማራጭ ቤት ተከራይታ ብቻዋን መኖር ነበር። ሆኖም ግን የምትማርበትም ሆነ የቤት ኪራይ የምትከፍለው ገንዘብ ስለሌላት ዘመዶቿ እየረዷት ቴዎድሮስ አደባባይ ተረት ሰፈር አካባቢ ተከራይታ ለጥቂት ጊዜ ቆየች። የቤተሰብን እጅ መጠበቅ ያንገበግባልና ሌላ አማራጭ ማፈላለጉን ቀጠለች። ከዚያም «ሳይደግስ አይጣላም» እንዲሉ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት ወይም በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለመቀጠር የሚያስችል አጋጣሚ ተፈጠረላት።

በሥራዋ የተሻለ ደሞዝ በማግኘቷም ቤት በመቀየር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ 8 ካዛንቺስ አካባቢ ሁለተኛ ቤቷን ተከራየች። በእኔ የደረሰ በሌላ አይድረስ በማለትም ወንድሞቿን እና እህቶቿን ከገጠር በማስመጣት አስተምራ ሁለቱ ወንድሞቿን ዶክተር አንዱን ደግሞ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ለማድረስ በቃች። ልጆቿንም ቢሆን አስተምራ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በዲግሪ እንዲመረቁ አድርጋለች።

አልጋነሽ ያቋረጠችውን የቀለም ትምህርት አዲስ አበባ ምሥራቅ ጎህ ትምህርት ቤት በማታው ክፍለ ጊዜ እየተከታተለች በልጅነቷ ያጣችውን ትምህርት በራሷ ጥረት ለመቀጠል ችላለች። በ1977 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዳ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ተዘዋውራለች፡፡ ሆኖም ግን ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ትምህርቷን እንዳትቀጥል የሚያደርጉ በርካታ መሰናክሎች ገጥመዋታል። በዚህም ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገዳለች። ይሁንና ከዓመታት በኋላ ትምህርቷን እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተምራ አጠናቃለች።

ቆይታ በቀድሞ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት

እንደሚታወቀው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት የኢትጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ትውፊታዊ የትወና ጥበባትን በማጥናት፣ በማበልጸግ፣ በማስተዋወቅና ተደራሽ በማድረግ ለመልካም ገጽታ ግንባታ ማዋልን ዓላማው አድርጎ የተለያዩ ባለሙያዎችን በስሩ በመያዝ በአገራችን ኪነ ጥበብ ታሪክ ሰፊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ነው። አርቲስቷም በዚህ ቴአትር ቤት ለመቀጠር የበቃችው ይህንኑ ተግባር ለመከወን ነበር። ስለዚህም ታኅሣሥ 8/1958 ዓ.ም በዚህ ቴአትር ቤት የአርቲስትነት ሙያዋን «ሀ» ብላ ጀመረች።

በእርግጥ ዘመኑ የባሕላዊ ውዝዋዜ ጥበብ ያልዳበ ረበት፣ ሴት ልጅ መድረክ ላይ መውጣት እንደ ነውር የሚቆጠርበትና ከማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ፈተና የሆነበት ነበር። ይህቺ ሴት ግን የጊዜውን አስተሳሰብ ወደ ጎን በመተው ካደገችበት አካባቢ ያገኘችውን ልምድ ይዛ ወደ መድረክ ብቅ ያለችው በ16 ዓመት ዕድሜዋ ነበር። ለዚህም ደግሞ የበቃችው የእራሷ ብርታት እንግዳ ሆኖ የሌሎች የጥበቡ ባለሙያዎች እገዛ ታክሎበት እንደሆነ ስለርሷ የቀረበው መረጃ ያስረዳል። በተለይ ወደ ቴአትር ቤቱ እንድትገባ ካደረጓት መካከል በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት የሙዚቃ ባለሙያ የነበሩት አቶ ጌታቸው ደጀኔ ናቸው። በወቅቱም አርቲስቷ ወደ ኪነጥበቡ ዓለም ብትመጣ ምን ያህል ውጤታማ እንደምትሆን በተደጋጋሚ በማግባባት ወደ ሙያው እንድትገባ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በዚህም አርቲስት አልጋነሽ በቴአትር ቤቱ የሚሰጠውን ፈተና በመውሰድ ጥሩ ውጤት አምጥታ በተወዛዋዥነት ልትቀጠር ችላለች።

አርቲስት አልጋነሽ ሥራዋን እንደጀመረች ከኃላፊዎቿና ከአሰልጣኞቿ እንድትሰራ የሚሰጣትን በልጅ ጭንቅላቷ በፍጥነት በመያዝ ሥራዎቿን መድረክ ላይ ማቅረብ የጀመረችው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር። እንዲያውም በቴአትር ቤቱ በተቀጠረች ሦስት ወር ሳይሞላት በጥቁሮች ኪነ ጥበባዊ ፌስቴቫል ላይ ለመሳተፍ ወደ ሴኔጋል ለመጓዝ የቻለችና የአገሯን ባህል ለማስተዋወቅ ዕድሉን አግኝታለች።

የውዝዋዜ አምባሳደሯ-አልጋነሽ

አገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ የየብሔረሰቡ መገለጫዎች የሆኑ ምት እና ስልት ያላቸው የውዝዋዜ ዓይነቶች አሏት። እነዚህም ውዝዋዜዎች እንደየአካባቢው በተለያየ አልባሳት፣ ጌጣጌጥና ቁሳቁስ የሚታጀቡ ናቸው። ይህ የአንድ አገር መገለጫ የሆነው ባህላዊ ውዝዋዜ ጥበብ መሠረታዊ ይዘቱን ሳይለቅ፣ የኅብረተሰቡን ውክልና ሳያጣ እንዲያድግ እና ለትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በሙያው ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለሙያው የሚሰጡት ክብር ወሳኝ ነው። ስለዚህም አርቲስት አልጋነሽ ይህንን ሁሉ ተግባር በማሟላት ዓለምን ለማስደመም የበቃች እንደሆነች ስለእርሷ የቀረበው መረጃ ያስረዳል።

አርቲስት አልጋነሽ በኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ጥበብ ውስጥ ከገባች ጀምሮ ሙያዋን እያሻሻለችና ለሙያው ትልቅ ክብርን እየሰጠች ባህሉ አገራዊ ይዘቱን እንዳይለቅ ከሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን ሙያው አሁን ካለበት ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት የጥበብ ሰዎች መካከል ትጠቀሳለች። አንድ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር በቅብብሎሽ የሚያስተላልፋቸው እጅግ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ መካከልም አንዱና ዋነኛው ማኅበረሰቡ በአክብሮት የተቀበላቸውን ባህላዊ ክንዋኔዎች ሳይበርዙ ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ መቻል ነው። በመሆኑም ባለታሪኳ በውዝዋዜው ዘርፍ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ስናይ ሥራዎቿን በአገራችን በሚገኙ ጠቅላይ ግዛቶች በአሁኑ ወቅት ክልል በመባል የሚጠሩት የአገራችን ክፍሎች በመዘዋወር አንዱ ብሔረሰብ የሌላውን ብሔረሰብ ባህል እንዲያውቅ በማድረግ የጎላ ሚናን ተጫውታለች።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ባህል ለተለያዩ አገሮች ለማስተዋወቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይም ያገኘችውን ዕድል በመጠቀም የአገራችንን ባህል በማስተዋወቅ የድርሻዋን በመወጣት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል የበኩሏን ድርሻ የተወጣች ሴት ነች። በነበራትም ሙያዊ ብቃት በየጊዜው ከሌሎች የሙያ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን ለበርካታ አገሮች የአገሯን ባህል አስተዋውቃለች። ይህንን ተግባር ከፈጸመችባቸው አገራት መካከልም በአህጉራችን አፍሪካ ሴኔጋል፣ ሱዳን፣ አልጀሪያ፣ ናይጀሪያ እና ኬንያ፤ ከአውሮፓ እንግሊዝ፣ ስፔን፣ ጀርመን ሲሆኑ፤ ከሰሜን አሜሪካ ካናዳ ከመካከለኛው አሜሪካ ሜክሲኮ፣ ኩባ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ የመን ይጠቀሳሉ። አርቲስት አልጋነሽ እርሷ ከሌሎች ያገኘችውን እውቀት ለተተኪዎች በመስጠት የሙያ ቅብብሎሹ እንዲቀጥል ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። ካላት የረዥም ጊዜ ልምድ እንዲካፈሉ ለማስቻል የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና በሥነ-ምግባርም እንዲታነጹ በመምከር አሁን ላይ ታዋቂ የሆኑትን ወጣት የውዝዋዜ ባለሙያዎች በመደገፍና በማገዝ የምትታወቅ መሆኗን በርካታ የሥራ ባልደረቦቿ የመሰከሩት ነው።

በቴአትር እና በፊልም ተዋናይነት

አርቲስት አልጋነሽ በቴአትሩ ዘርፍ መሳተፍ የጀመረችው በውዝዋዜ ሥራዋ ላይ በተደራቢነት እየሰራች ሳለ ነው። በዚህም ደግሞ የተዋናይነት ደረጃ እድገት ለማግኘት በቅታለች። አልጋነሽ ተዋናይ ሆና ሥራዋን የጀመረችው ነሐሴ 12/1989 ዓ.ም ሲሆን፤ ከ16 በላይ የመድረክ እና 6 የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በተዋናይነት እንዲሁም በ4 ቴአትሮች በአስተባባሪነት ሰርታለች። ወደ ፊልሙ ዘርፍ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ከ11 በላይ የፊልም ሥራዎች ላይ ተሳትፋለች። በቴአትሩ ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራችው የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ድርሰት የሆነውን «ሦስት ለአንድ» የተሰኘ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ነበር።

በመቀጠልም በሙሉጌታ መክብብ ተተርጉሞ በጌታቸው ደባልቄ የተዘጋጀው «የከተማው ባላገር» ላይ እንደ እናት፤ በሐዲስ አንተነህ ተተርጉሞ በፍራንዝ ዜልቬከር በተዘጋጀው «ስስታሙ መንጠቆ» ፣ በደራሲ ከበደ ሚካኤል ተጽፎ በፍራንስ ዜልቬከር የተዘጋጀው «አኒባል»፣ የወጋየሁ ንጋቱ ድርሰት የሆነውን «በእንቅልፍ ልብ» ላይ በተዋናይነትና በአስተባባሪነት ሰርታለች። የጸጋዬ ገብረመድህን ድርሰት በሆኑት «ሀሁ በስድስት ወር» ላይ እንደ ራብተኞች «እናት አለም ጠኑ» ላይ ደግሞ እንደ ጉልት ቸርቻሪ «ኦቴሎ» ላይ እንደ ዴዝዲሞና ሆና ሰርታለች።

በግርማቸው ተክለሃይማኖት ድርሰት «ቴዎድሮስ» ላይ የቴጌዋ ጠባቂ በመሆን፣ በኤልያስ ደጀኔ ተተርጉሞ በአለማየሁ ታደሰ በተዘጋጀው «ይግባኝ» ላይ እንደ ዳኛ፤ የአበባው አስራት እና የዳግማዊ ፈይሳ ድርሰት በሆነው በአበበ አዲስ በተዘጋጀው «የባላገር ፍቅር» ላይ እንደ እናት ሆና በመሪ ተዋናይነት እና በአስተባባሪነት ተውናለች። የጌታቸው ደባልቄ ድርሰትና ዝግጅት በሆነው «ያስቀመጡት ወንደላጤ» ላይ እንደ ቡና ቤት አሻሻጭ፤ በአሰፋ ገብረማርያም ተተርጉሞ በዓለሙ ገብረአብ በተዘጋጀው «ዋናው ተቆጣጣሪ» ላይ የአናን ገጸ ባህሪ በመላበስም ተጫውታለች። የጫን ያለው ወልደጊዮርጊስ እና ቴዎድሮስ ተሰማ ትርጉም ሥራ በሆነው ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት ዓለሙ ባዘጋጀው «ዋዜማ» ላይም ቢሆን እንደ ቤተ መንግሥት ሰዎች በመሆን ሰርታለች።

በተስፋዬ ገብረማርያም አዘጋጅነት የተሰራው «አዳብና» ላይ፣ የአለማየሁ ታደሰ ትርጉም ሥራ የሆነውና በሻሼወርቅ በየነ በተዘጋጀው «ደመነፍስ» ላይ አስተባባሪ በመሆን ሰርታለች። በአቶ ጫንያለው ወልደጊዮርጊስ ተደርሶ በአቶ ዳግማዊ ፈይሳ በተዘጋጀውና በጉራጌ ባህል ውስጥ የነበረውን የሴቶች መብት ጥያቄ በማንሳት የማይረሳውን ገድል የፈጸመችው የጉራጌዋ ጀግና ውርዶት ላይ በሚያጠነጥነው «የቃቄውርዶት» በተሰኘ ሙዚቃዊ ቴአትር እንደ የቃቂውርዶት እናት በመሆን የሰራቻቸው ሥራዎች ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ።

ከቴሌቪዥን ድራማዎች የአለልኝ መኳንንት ድርሰት «አንተዋወቅም» ላይ እንደ እናት፤ የጥላሁን ዘውገ ድርሰት «የሕሊና ችሎት» ላይ እንደ ሰካራም፤ የአስቴር በዳኔ ድርሰት በሆነው «ሕሊና» ላይ እንደ ሀብታም ሴት፤ «ገበና» ላይ እንደ አክስት በመሆን፤ የብስራት ገመቹ ድርስት የሆነው «ዋዜማ» ላይ እንደ እናት በመሆን እንደተጫወተች አርቲስት አልጋነሽ ታሪኩን በሚዘክረው መድረክ ላይ የቀረበው መረጃ ያትታል። በፊልም ኢንዱስትሪውም ውስጥ ያላት ተሳትፎን መረጃው እንደሚያስረዳው፤ የመጀመሪያ ሥራዋ በአብርሃም ቀናው ተደርሶ በትዕግስት ባዩ የተዘጋጀውን «ባይተዋር» የተሰኘውን ፊልም የእናት ገጸ ባህሪን ወክላ መጫወቷን መረጃው ያትታል።

በመቀጠልም ቴዎድሮስ ተሾመ ባዘጋጀው «አዳም» በተሰኘው ፊልም ላይም እንዲሁ የእናት ገጸ ባሕሪ በመላበስ የሰራች ሲሆን፤ የቴዎድሮስ ተሾመ ድርሰት የሆነው «ቀይ ስህተት» ላይም እንደ አክስት፤ በሠራዊት ፍቅሬ ተደርሶ በሮማን አየለ የተዘጋጀው «ሰካራሙ ፖስታ» ላይም እንደ ሀብታሟ ሴት በመሆን ተውናለች። በቴዎድሮስ ተሾመ ተደርሶ በቢንያም ወርቁ የተዘጋጀው «ውበት ለፈተና» እንዲሁም በአሳልፈው ታምሬ ተደርሶ በቢንያም ወርቁ የተዘጋጀው «አልዓዛር» ላይ እንደ እናት ሆና ተጫውታለች። የአስቴር በዳኔ ድርሰትና ዝግጀት በሆነው «ፍርቱና» ላይ እንደ ሀብታም ሴት፤ የቴዎድሮስ ተሾመ ድርሰት የሆነው «ስሌት» ላይ እናት በመሆን የተጫወተች ሲሆን ሌሎች ፊልሞች ላይም በስፋት ተውናለች።

በማስታወቂያ ዘርፉ

አርቲስት አልጋነሽ ከፊልም ሥራዎቿ በተጨማሪ በቴሌቪዥን የማስታወቂያ ሥራዎች እና በሙዚቃ ክሊፕ ሥራዎች ላይ ትሳተፋለች። ለአብነት ያህል በአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ በተዘጋጀው «ቮልቮ» እና «ላቀች ምድጃ»፣ «የአየር መንገድ» ማስታወቂያ፣ በአቶ ተስፋዬ ማሞ በተዘጋጀው «ጉድሞርኒንግ ሻይ» በረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ የተዘጋጀው «አንበሳ ሻይ ቅጠል» ላይ የሰራቻቸው የማስታወቂያ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። በሙዚቃ ክሊፕ ላይ ከተሳተፈችባቸው መካከል ደግሞ በኪሩቤል አስፋው የተዘጋጀው እና አብዱኪያር ያዜመው «የከዳማ እናቱን» ይጠቀሳል።

የአርቲስቷ አርአያዎች

አርቲስቷ በሙያዋ እንድትገፋና ውጤታማ እንድትሆን ያገዟትና አርአያ የሆኗት የመጀመሪያው ሙያተኛ አርቲስት አውላቸው ደጀኔ ናቸው። ብዙ ሙያተኞችን የፈጠሩና እርሷንም የውዝዋዜ ዓይነቶችን፣ አለባበስን፣ የባህል አልባሳትን እንዴት መያዝ እንዳለባትና ለዛሬው ማንነቷ እንድትበቃ ያደረጓት በመሆናቸው ሁሌም ትኮራባቸዋለች። ከእርሳቸው በተጨማሪም በርካታ የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች በምክርም በሙያም ያገዟትም እንዳሉ ትናገራለች። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል አስናቀች ወርቁ፣ ደስታ ገብሬ፣ ታደለ ታምራት፣ መርዓዊ ስጦት፣ ሰይፈ አርአያ፣ ጀንበሬ በላይ እና ሌሎችም ለደረሰችበት ደረጃ ያበረከቱላት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ከአንድ ሰው ስኬት በስተጀርባ ሌሎች ግለሰቦች መኖራቸው እሙን ነውና ለእርሷም ሕይወት መለወጥ ምክንያት ናቸው የምትላቸውን ማለትም ከጎኗ ሳይለዩ በማበረታታትና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እገዛ በማድረግ የደገፏትን ሰዎች አመስግናለች። እነርሱም ወንድሟ ኮሎኔል ሊቁ አለሙ፣ የአፍሪካ ክሊኒክ ባለቤት አቶ ብርሃኔ ገብረጊዮርጊስ እና የላንድ ማርክ ሆስፒታል ባለቤት ፕሮፌሰር ከበደ ወሌና አብራው የምትሰራ ሲስተር ጌጤ በሕይወቷ ውስጥ ባለውለታዎቿ መሆናቸውን ትናገራለች።

የአርቲስቷ ቤተሰባዊ ሕይወት

አርቲስት አልጋነሽ ከልጅነት ባሏ ውጪ በሕግ ያገባችው ባል አልነበረም። ነገር ግን ሦስት ሴት ልጆችን ከተለያዩ ሰዎች ወልዳለች። የመጀመሪያዋ አትክልት ታደሰ ትባላለች። ዩኒቲ ኮሌጅ በሆቴል ማኔጅመንት ተመርቃለች። በአሁኑ ሰዓት ኑሮዋን አሜሪካን አገር አድርጋ ከትዳር አጋሯ ጋር ትኖራለች። ሁለተኛዋ ደግሞ መሃቡባ ከበደ የምትባል ስትሆን፣ በፖለቲካል ሳይንስ ተመርቃለች። በአሁኑ ወቅት አየር መንገድ በሆስተስነት እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናትም ነች። ሌላዋ እየሩሳሌም መሸሻ ትባላለች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ ግቢ በማኔጅመንት ትምህርት ተመርቃለች። በአሁን ወቅት ወደ ንግዱ ዓለም በመግባት የራሷን ሥራ እየሰራች ከእናቷ ጋር ትኖራለች።

በሥራ ዓለም ባሳለፉት ጊዜያት «ይህን አላደረኩም» ብላ የምትቆጭበት ነገር እንደሌለ የምትናገረው አርቲስት አልጋነሽ፤ በጊዜዋ መሆን የሚገባትን ሆናለች። ወጣትነቷን በሚገባ በጥበቡ ዓለም አሳልፋለች። መቼም «ዕድሜን እንደማቱሳላ ያርዝምልህ» ብለው እንደሚመርቁት አባቶች ዕድሜዋ በርክቶላት ለጡረታ ስትደርስ ከቤቱ ብትገለልም አሁንም ለጥበብ አለሁ ማለቷን አልተወችም።

የሙያ አጋሮቿ ስለ አርቲስቷ ምን ይላሉ?

በዝክረ አርቲስት አልጋነሽ ከቀረቡ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ስለ እርሷ የሙያ አጋሮቿ ምን ይላሉ የሚለው አንዱ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አርቲስት ትዕግስት ባዩ «አልጋዬ ለጥበቡ ያላት ፍቅር ሙሉ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ሁሌ በመስራት የምታምን፣ ሰርታ የማትጠግብ፣ ጠንካራ፣ ለሙያዋና ለብሔራዊ ቴአትር ልዩ ቦታ ያላት ናት። በዚህም በውዝዋዜውም ሆነ በተዋናይነት ሙያዋ ምሳሌ በመሆን ለጥበቡ ዕድገት ሁሌም የምትጥር ነች። በማህበራዊ ኑሮዋም ለችግርም ለደስታም ቀድማ የምትደርስ፣ ሰው መርዳት የምትወድ፣ በፍቅር የተሞላች የፍቅር ሰው ነች» በማለት ትገልጻለች።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተወዛዋዥ ኤልሳቤጥ ማሞም «ለዛሬው የእኛ ማንነት መምጣት የእነ አልጋዬ መስዋዕትነት ውጤት ነው። በላባቸው ብቻ ሳይሆን በደማቸውም ጭምር ነው ሙያውን ጠብቀው ያቆዩልን። አልጋዬ ከገንዘብ በላይ ለያዘችው ሙያ እድገት ትኩረት ትሰጣለች። ባህሉም ተጠብቆ እንዲቆይ ከማድረግ አንጻር ብዙ አሳውቃናለች። በተለይ አለባበስ ላይ እርሷ ካለች በጣሙን እንጠነቀቃለን። ይህ ደግሞ ለማንኛውም ባህል ልዩ ትኩረት እንድንሰጥ አድርጎናል» በማለት ምስክርነቷን ሰጥታለች።

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ «አልጋነሽ ሥርዓት አክባሪ በመሆኗ እና ሙያዋን በማክበሯ ጥሩ ፍሬ ማፍራት ችላለች። ስኬታማ የመሆኗም ምስጢር ይሄው ነው። ምሳሌ የምትሆን ለምሳሌነት የምትበቃ ሴት ነች። ሁሉን አሟልቶ የሰጣት ነች» በማለት ለሙያው ያላትን ብቃት መስክርውላታል። አርቲስት ታደለ ታምራት በበኩሉ «አልጋነሽ ወደ ውዝዋዜ ክፍል ከመጣች ጀምሮ ከኃላፊያችን አውላቸው ደጀኔ እና ከእኔም የሚሰጣትን ሥልጠና በፍጥነት የመያዝ ችሎታዋ ከሌሎቹ ለየት የሚያደርጋት ባህሪዋ ነበር። ሥራ ወዳድ ናት። ለምሳ እንኳን የማትወጣበት ጊዜ ነበር። በሥራዋ ላይ ኃላፊነትን መውሰድ የምትወድ፣ ማንንም የማትጠብቅ የምታውቀውን ለሌሎች በመስጠት የምትታወቅ፣ ለባህሏ የምትቆረቆር፣ በራሷ ተነሳሽነት የተሻለ ሥራ ለመስራት ጥረት የምታደርግ፣ የሥራ ባልደረቦቿን በማስተባበርና በጋራ በማጥናት ጥበቡን ለማሳደግ የጎላ ሚናን የምትጫወት ጠንካራ ሴት ናት»።

ወይዘሮ ጤናዬ ኃብተገብርኤል «አልጋነሽ ስትፈጠር ሁሉን አሟልቶ የፈጠራት ቆንጆ፣ ደግ፣ ግርማሞገስ ያላት ተቸገርኩ ላላት ማንም ሳያውቅባት ችግሩን መፍታት የምትችል እንዲሁም አንድ ጥሩ ነገር ለመግዛት ስትፈልግ የምትመርጥበትን ዓይነት ናት» በማለት ገልጸዋታል። አርቲስት መርዓዊ ስጦትም፤ አልጋነሽ ሙያውን ለማሳደግ ባላት ተነሳሽነት ከራሷ ገንዘብ አውጥታ አልባሳትን በመግዛት ሥራውን ለማሳመር የምትጥር ሁለገብ የሆነች ድንቅ እና ብርቅ አርቲስት መሆኗን መስክረዋል።

አርቲስት አልጋነሽ የሰራቻቻውን ውዝዋዜዎች፣ ቴአትሮች፣ ፊልሞችና ማስታወቂያዎች በተመለከተ ከአብዛኛው ሰው ልምድ ውጭ በተለየ መልኩ በፎቶ የተደገፈ ማድረጓ ከሌሎች አርቲስቶች ለየት ያደርጋታል። ለዚህም ደግሞ በሄደችበትና በተወነች ቁጥር ፎቶ ትነሳለች። በውዝዋዜው ዘርፍ አብረዋት ይሰሩ የነበሩ የሥራ ባልደረቦቿ ለሥራ ያላትን ፍቅርና ጥንካሬ በማየት «ወይራዬ» በሚል ቅጽል ስም ይጠሯት እንደነበር በወቅቱ ስለእርሷ የቀረበው ታሪክ ያትታል። አርቲስት አልጋነሽ በብሔራዊ ቴአትር ለ43 ዓመት ማገልገሏን፣ በ2001 ዓ.ም በጡረታ ከሥራዋ የተገለለች መሆኗንና አሁንም በሙያዋ አገሯን እና ወገኗን ባላት እውቀት በማገልገል ላይ የምትገኝ እንደሆነም የቀረበው መረጃ ያስረዳል።

አርቲስቷ ከዚህ ባለፈ በሙያዋ እገዛ እንድታደርግ በተለያዩ አካላት በተጠየቀችበት ጊዜም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በተጠራችበት ሥፍራ በመገኘት ሥራዋን በታማኝነት ትሰራለች። ትብብር ከተጠየቀችባቸውና ካከናወነቻቸው ተግባራት የመጀመሪያው የአይዶል ውድድር ላይ በባሕላዊ ውዝውዜ ዳኝነት ላይ ተሳትፋለች፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የዘመን መለወጫ እንዲሁም ለገና፣ ለፋሲካ በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይም ተሳትፎዋ የላቀ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 40ኛው እና 50ኛውን ዓመት ሲያከብርም በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ተሳታፊም ነበረች።

በተጨማሪም 60ኛውን ዓመት ለማክበር በሚዘጋጅበት ወቅትም ቢሆን በኮሚቴ ውስጥ በመግባት ተሳትፎዋ አልተለየም። አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሚተላለፈው የእሁድ መዝናኛ ላይ ወይም «ዋዜማ» ድራማ ላይ የእናት ገጸ ባህሪን በመላበስ እየተጫወተች ትገኛለች። ወደፊትም ቢሆን ይህ ሥራዋ ሳይቋረጥ እንደምትቀጥልበት ነው በቆይታችን ያወጋችኝ። ከዚህች ሁለገብ የኪነ ጥበብ ሰው በርካታ ጥበባዊ ተመክሮዎችን መቅሰም ይቻላል።

ምክር ለአዲሱ ትውልድ

አርቲስቷ የአገሯን ባህል ጠብቃ ለተተኪዎች በማስተላለፍ የተጫወተችው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። በመሆኑም አዲሱ ትውልድ ከዚህች ለትውልድ አርአያ መሆን ከቻለች ሴት ምን ይማራል? በማለት በዕለቱ ከታደሙ አርቲስቶች መካከል የተወሰኑትን ለማነጋገር ችያለሁ። ከእነዚህም መካከል አርቲስት ተስፋዬ አበበ «ፋዘር» በመጀመሪያ ያነጋገርኳቸው ሲሆኑ፤ እርሳቸውም ስለ አርቲስቷ እንዲህ ይላሉ። «አዲሱ ትውልድ ከእሷ ለመማር ፈቃደኛ ቢሆን ሀቀኝነትን፣ የአገር ፍቅር እና ባህሉ እንዳይበላሽና እንዳይጠፋ ተከላካይ መሆንን ይማራል። የሥራ ባህሪዋን፣ ሥነ ሥርዓቷን፣ ሰው አክባሪነቷን፣ መካሪነቷን እና ባህሉን ጠብቆ ለሌሎች የማስተላለፍ ብቃቷን ይወርሳል። ልቦና ሰጥቷቸው ከተቀበሉ ከአልጋነሽ የሚማሩ ካሉ ለጥበቡ ታማኝ መሆንን፣ በሥነ-ምግባር የታነጸ መሆንን፣ ራስን መጠበቅን፣ ልበ ንጹህ መሆንን ይማራሉም» ብለዋል።

ሌላዋ ስለ አርቲስቷ የገለጸችው አርቲስት ብዙነሽ ቅጣው እንዲህ ትላለች «ሰዎችን በመርዳት፣ በማጽናናት ብሎም ንብረቷን አሳልፋ በመስጠት የምታግዝ ነች። ለአብነት እንኳን ባነሳ በሥራ ላይ እያለን አንድ አርቲስት ቢታመም የእርሷን መኪና እንደ አምቡላንስ እንዲጠቀም ይደረጋል። የጥበብ ሥራን ሲሰሩ ላመሹም ቢሆን መኪናዋ መሸኛ ነው» ትላለች። ታዲያ የሥራ ባልደረቦቿ ይህንን ያህል ካሉ እርሷስ አዲስ ትውልድ ከእርሷ ምን መውሰድ ይኖርበታል ትል ይሆን? ከእርሷ አንደበት እንስማ።

«አዲሱ ትውልድ ከእኛ መማር ያለበት በእኛ ዘመን እንደነበረው የአንድ ብሔረሰብ ውዝዋዜ ለመስራት የብሔረሰቡ አጨፋፈር፣ አለባበስ፣ አጋጌጥ በማጥናት ጥናት እንዲደረግ ይሰጣል። ከዚያም አጥንተን ስንጨርስ የብሔረሰቡ ተወላጅ እንዲመጣ ተደርጎ ትክክለኛነቱ ይረጋገጥና ለመድረክ ይበቃል። አሁን ግን ይህ ነገር ያለ አይመስለኝም። ባህሉ ከጊዜው ጋር ሊያድግ ይችላል። ነገር ግን ዛፍን ለማሳደግ ከስሩ ቆርጠን ማጥፋት አይደለም። በእያንዳንዱ ሙዚቃ ላይ የሚቀርበው ውዝዋዜና አልባሳት ከነጌጣጌጡ ትክክለኛ የባህሉን ባለቤት የሚወክል መሆን አለበት። ይህን በተመለከተም የባህሉ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ ትክክለኛነቱን ሊያውቅ ይገበዋል። አዲሱ ትውልድም ቢሆን የጥበብ ሥራን ሲሰራ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍና ከገንዘብ ይልቅ ለሙያው ተቆርቋሪነትን ማሳየት ይኖርበታል። በሌላ መልኩ ደግሞ የአንድን ብሔረሰብ ባህልና ወጉን፣ አስተሳሰቡን፣ አጊያጌጡን ለማሳየት በምንፈልግበት ጊዜ ትክክለኛነቱን የጠበቀ እንዲሆን የኃላፊነት ስሜት መኖር እንዳለበት እንጂ ባህልና ወጉን ማንም እንደፈለገ አሻሽላለሁ ብሎ ቱባውን ባህል ማጥፋት እንደሌለበት ለማስገንዘብ እወዳለሁ» አርቲስ አልጋነሽ በሥራ ዘመኗ ለብዙዎች አርአያ የነበረች አሁንም የሆነች ጠንካራ የጥበብ ሰው ናት። በተለይም ባህል አክባሪነቷና ተቆርቋሪነቷ ለብዙዎች በአርአያነት የሚጠቀስ ምግባር ነው። በቀሪ ዘመኗ ረጅም ዕድሜና ጤና እንዲሰጣት እንመኛለን

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ