Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

የሌሊሣን ሥራዎች ባህርይ ለመለየት ያደረግኩት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም

በነጻነት ቀለም የሚደጉስ ፀሐፊ

 

 

የሌሊሣን ሥራዎች ባህርይ ለመለየት ያደረግኩት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ሌሊሣ በዱር እንጂ ‹‹በዙ›› (በቤተ - አራዊት) የሚኖር ፀሐፊ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሐሳቦቹ ከቱሪስት ዓይን ቶሎ አይገቡም፡፡ እንዲህ መሆኑን የተረዳሁት ሳነበው ሳይሆን በሂስ ዓይን ስመለከተው ነው። በትንሽ ጥረት ተፈልቅቆ የሚወጣ አንድ ልዩ ባህርይ ከሥራዎቹ ማውጣት እንደምችል አስቤ የጀመርኩት ጥረት፤ ሌሊሣ አስስቸጋሪ የሆነ ፀሐፊ መሆኑን በማረጋገጥ ተጠናቀቀ፡፡ ስለዚህ፤ ለጊዜው የ‹‹ቤቱን›› መዋቅር ለመረዳትና ለማስረዳት መጣጣሩን በመተው፤ የቤቱን ጓዝ ወደ መዘርዘር ዝቅ አልኩ፡፡ ስለ ሥነ ጽሑፉ ማሰቡን ትቼ፤ ስለ ፀሐፊው ወደ ማውጠንጠን ወረድኩ፡፡ 

ሌሊሣ የሚያነሳቸው ሐሳቦች ኮስታራ ናቸው -እንዳበሻ አረቄ፡፡ በቅርጽም አጫጭር ናቸው - እንደ አረቄው መለኪያ፡፡ ስለዚህ ፉት እያልን ቁጭ የምናደርጋቸው እንጂ ጅው አድርገን የምንጠጣቸው አይደሉም፡፡ የሌሊሣን አንድ ዛንታ (ወግ ወይም ታሪክ) ፉት አድርጌ በከፈተልኝ የሐሳብ አጸድ ለሽርሽር እወጣለሁ፡፡ ንባቤ የሐሳብና የስሜት ሰደድ ያስነሳብኛል፡፡ ከሐሳብ ውቂያኖስ ጥሎ ማዕበል አስነስቶ ያንገላታኛል። በራሴው የሐሳብ ሁዳድ ያባዝነኛል፡፡ እርሱ ጠብመንጃ ሆኖ፤ እኔን ተተኳሽ ጥይት ያደርገኛል። መገረም ያበዛልኛል፡፡ አንዳንዴም አኩኩሉ ያጫውተኛል፡፡ በጨዋታ ዓይኔን አስሮ ‹‹ያዕቆብ›› እያሰኘ ያዳክረኛል፡፡

አንዳንዴ የተደበቀ የምስጢር ቀበቶ ያገኘሁ ይመስለኛል፡፡ አፈፍ አድርጌ፤ ‹‹ያዕቆብ›› እለዋለሁ። በቀኜ ቆሞ አጨብጭቦ ወደ ግራ ስልብ ይላል፡፡ ቀበቶውን ሾጥ አደርጋለሁ፡፡ ሲደክመኝ፤ በሆነ መንገድ ጨዋታ አፈርሳለሁ፡፡ ወይም ቀጣዩን የመገረም ወግ ሰረቅ አድርጌ ለማየት እሞክራለሁ። ከሌሊሣ ጋር እንዲህ እጫወታለሁ፡፡

ሌሊሣን ተገን አድርጌ፤ መጫወቻና መዘበቻ የምታደርገኝን ህይወት፤ ለአፍታ ዘበት አደርጋታለሁ፡፡ ደግሞም ከክፋቷ አዘናጋታለሁ። እየሳቅኩ እላፋታለሁ፡፡ ያሸከመችኝን ሸክም በዛንታ አዘናግቼ አወርደዋለሁ፡፡ ለአፍታ ያህል፤ ህጻን ልጅ ሆኜ በነጻነት እከብራለሁ፡፡ ሌሊሣ፤ እያሰላሰሉ፣ እየመረመሩ የሚያነቡት ጸሐፊ ነው፡፡ አረፍ እየተባለ መነበብ በሚገባው በዚህ መጽሐፍ፤ ፍሬ አልባ ከንቱ ዐ.ነገሮችን አታገኙም። በእያንዳንዱ ዐ. ነገር የሐሳብ ‹‹ፎቶሲንተሲስ›› ሲካሄዱ ታያላችሁ፡፡ በየሐረጉ የተንዠረገገ ድንግል ዘይቤ ትመለከታላችሁ፡፡

ሲተርክ በማነጻጸር፣ በማወዳደር፣ በማጣቀስ፣ በማፍረስ፣ በመገንባትና እንደገና በመገንባት ነው፡፡ የትረካ ጉዞው እንደ ውሃ መንገድ በገርነት የሚፈስስ ነው፡፡ ሌሊሣ የሰራውን ነገር ሳያመነታ ያፈርሳል፡፡ ደግሞ ያፈረሰውን እንደገና ይሰራል። በቀዳሚው አንቀጽ የገነባውን ሐሳብ፤ በቀጣዩ አንቀጽ ያፈርሳል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ መነኩሴ መቁጠሪያ በአንድ የነገር ክር ሰክቶ ጨዋታ ያደራል፡፡ የሌሊሣ ዛንታ፤ ልጇን አደን ከምታስተምር ሴት አንበሳ ሁኔታ ተመሳስሎ ይታየኛል፡፡ በዛንታው እያጫወተ ከህይወት ዱር ያስገባኛል፡፡ በሌሊሣ የምትዘከር ህይወት በምስጢሯ ግርማ ታስፈራራለች፡፡ በጥበቧ ታስገርመናለች፡፡ የህይወት እንቆቅልሽ ከሚገኝበት ዋሻ አግብታ የምስጢር ጅራት ታስጨብጣለች፡፡ የአራስ ነብር ጅራት ነው፡፡ ወትሮም ‹‹የነበር ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም›› ይባላል፡፡ የአራስ ነብር ጅራት የሆነ አንድ ሐሳብ አስይዞ፤ በዱር በገደሉ እየጎተተ ከሚያደክም የህይወት ምስጢር ጋር ያታግለኛል፡፡ የተያዘ የተጨበጠ የመሰለ ነገርን እንደ ገና ያደክመኛል፡፡ 

ሌሊሣ ከሰረገላ ተቀምጦ በፍስሐ ከመቀማጠል ይልቅ፤ በአደገኛ ገደል የህይወት ዛፍን እያዘመመ ጢሎሽ መጫወትን ይመርጣል፡፡ በልማድ ፈረስ ከሚጎተት ምቹ የሰርክ ሰረገላ መቀመጥ አይወድም፡፡ ሌሊሣ የተጦለ (ግርዱ ከፍሬው የተለየ) የህይወት ህብስት አይፈልግም፡፡ ቶሎ ይሰለቸዋል፡፡ አዕምሮውን ማጦያ ወይም ጭራንፎ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ እርሱ ግርድ እና መለየት፤ ደግሞ መልሶ ማቀላቀል ሥራ ፈትነት መስሎ አያታየውም፡፡  ቆቅን ሰድዶ ማሳደድ፤ ቆብን ቀድዶ መስፋት፤ እውነትን መመርመሪያ ብልሃት፤ ኪነትን ማደኛ ወጥመድ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። ከመሰልቸት ያወጡታል፡፡ የጊዜ ሸክም ማራገፊያ ወደብ ሆነው ያገለግሉታል፡፡

ውበትን ማየት የሚችለው በነጻነት ዓይን ብቻ ነው፡፡ ሌሊሣ እስረኛ አድርጎ የያዘው በመሰለው ነገር ላይ ሁሉ ያምጻል፡፡ ሥራዎቹ ሁሉ የተወለዱት ‹‹ከአመጽ›› ማህጸን ነው፡፡ ሐሳቦቹ ሰልፍ አይወዱም፡፡ ነጻነትን ከነፍሱ አብልጦ የሚወዳት ይመስላል፡፡ መጣጥፎቹ ሁሉ ጥልቅ እና ጥብቅ በሆነ የስሜት ዜማ ነጻነትን የሚወድሱ ‹‹ራፕሶዲ›› (Rhapsody) ናቸው፡፡ የሌሊሣ ዛንታዎች አጫጭር የነጻነት ‹‹ራፕሶዲዎች›› ወይም ተራኪ ግጥሞች ናቸው፡፡ ሆኖም ራሷ ነጻነት በመደጋገም ወህኒ መስላ ከታየችው ከእርሷም ሊጣላ ይችላል። እንደ ሌሊሣ በነጻነት የታመመ አንድ ማውቀው ሰው ዞርባ ብቻ ነው፡፡ ዞርባ በ‹‹ሳንቱሪው››፤ ሌሊሣ በብዕሩ ስለ ነጻነት ይዘምራሉ፡፡ እርሱም በ‹‹የሰከረ እውነት›› ዞርባን ዘክሮታል፡፡

የሌሊሣ ሥራዎችን ሁሉ፤ ልጥ ሆኖ ሊያስራቸው የሚችል አንድ ነገር ነጻነት ይመስለኛል፡፡ በሰማይ የምትበር ወፍ ከኋላዋ የጉዞ መስመሯን የሚያመለክት ፈለግ እንደማይኖራት፤ ሌሊሣም የሐሳብ ፈለጉን የሚጠቁም ዱካ አይተውም፡፡ አንድ እርምጃ ተራምዶ፤ ዞር ብሎ ዱካውን ያጠፋል -ሆነ ብሎ፡፡ ስለዚህ እንደ ሰማይ ወፍ ዱካ የለውም፡፡ ተጓዥነቱ እንጂ መጓዣ መስመሩ እና መዳረሻ ነጥቡ አይታወቅም። ጓደኛዬ አመጸኛ ነው። አጥር እያፈረሰ መሄድ ይወዳል፡፡ የሥነ ጽሑፍ ሰብእናው ከዚህ በታች ከምታነቡት የጠብመንጃ አንጋቹ መንገደኛ ባህርይ ጋር ይመሳሰላል፡፡

ባለጠብመንጃው

ሁለት ሰዎች ተረተሩን ይዘው እየተጓዙ ነው። ከወዴት እንደሚመጣና ወዴትም እንደሚሄድ የማያስታውቅ የሐሳብና የስሜት ነፋስ የሚያመጣላቸውን ወሬ እየጠረቁ ይጓዛሉ። በአፀደ ህሊናቸው ውር ውር የሚሉ ቢራቢሮ ሐሳቦችን እያሳደዱ፤ ቦዘኔ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሱ ይጥላሉ። በዚህ መሐል፤ ከኮረብታው ሥር ተንጣሎ ከሚታየው ሣር የለበሰ መስክ ሦስት ፈረሰኞች ሜዳ ሲያቋርጡ ተመለከቱ፡፡ ከሁለቱ መንገደኞች አንደኛው ቆም አለ፡፡ ጠብመንጃ ያነገተው ይህ መንገደኛ፤ ፈረሰኞቹን ያውቃቸው ኖሯል፡፡ እናም በእጁ ወደ ፈረሰኞቹ እያመለከተ፤

‹‹ያ ነጭ ፈረስ የሚጋልበው ሰው ይታይሃል?›› አለ ለጓደኛው፡፡

‹‹የቱ? ሁሉም ነጭ ፈረስ እኮ ነው የሚጋልቡት›› ሲል መለሰ፡፡

‹‹አይ፤ ይኸ ባርኔጣ ያደረገው››

‹‹እንዴ?! ሦስቱም ባርኔጣ አድርገዋል እኮ››

‹‹ምነው፤ ኩፍ ጫማ ያደረገው ሰውዬ አይታይህም?››

‹‹ምን ይላል ይኸ ሰው፡፡ ሁሉም ኩፍ ጫማ እኮ ነው ያደረጉት!››

ነገሩ እንዲህ ቀጠለ፡፡ ባለጠብመንጃው ከሦስቱ አንደኛውን ለማመላከት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ተቸገረ፡፡ እናም እርምጃውን ገታ አድርጎ ቆም አለ፡፡ ከትከሻው ያነገተውን ጠብመንጃ አወረደ፡፡ የጠብመንጃውን አፈ ሙዝ ወደ ሦስቱ ጋላቢዎች አቅጣጫ አለመ፡፡ አልሞ - አነጣጥሮ ተኮሰና ከሦስቱ ፈረስ ጋላቢዎች አንደኛውን መትቶ ከፈረሱ ጣለው፡፡ ‹‹ይህን ነው የምልህ፡፡ እንዴት ያለ ሰው መሰለህ፤ የልብ ወዳጄ ነው›› ብሎ ጠብመንጃውን መልሶ ከትከሻው ጣል አደረገና ጉዞውን ቀጠለ፡፡

ሌሊሣ ለልማድ አይራራም፡፡ የታየውን እውነት ለመግለጽ ይተኩሳል፡፡ ጠብመንጃውን አንግቶ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ እንደ ኦቴሎ፤ ‹‹ስለ ወደድኩሽ ገደልኩሽ፤ ስለ ገደልኩሽ ሞትኩልሽ›› እያለ ይጓዛል፡፡

‹‹መለኮታዊ ሐዘን ነው፤ እንደ እግዜር ፍቅር አኳኋኑ፤

የሚወደውን ገድሎ ነው፤ የሚወስደው ወደ ጎኑ›› ያሰኛል፡፡

ሌሊሣ ‹‹የሰከረ እውነታ›› (2009)፣ ‹‹የነፋስ ህልም እና ሌሎች የምናብ ታሪኮች›› (2002) እና ‹‹መሬት አየር ሰማይ›› (2006) በተባሉ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ ከአንባቢ ጋር የተዋወቀ ፀሐፊ ነው፡፡ ሌሊሣ በሥነ ጽሑፍ መንገድ ለመሮጥ ሲንደረደር ጀምሮ አውቀዋለሁ፡፡ በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛም ይጽፋል፡፡ በዝርውና በግጥም መናገር የሚችል ፀሐፊ ነው፡፡ የሐሳብ ጎረቤቴ ነው፡፡ በሁሉም ሥራዎቹ ውስጡን ሲበረብር ይታያል፡፡ ሌሊሣ የተለየ መልክ ያለው ፀሐፊ ነው፡፡ ማሰብ ይችላል፡፡ እንደ ጣዝማ ሰርሳሪ የማሰብ ችሎታ ያለው ጸሐፊ ነው፡፡ የምናብ ካህን ነው፡፡ ሐሳቡን ለመግለጽ ሲል ልማድ ያጸናውን እውነት ይሽራል፡፡

አሮጌውን ገድሎ አዲሱ ነፍስ ዘርቶ እንዲነሳ የማድረግ ብቃት ያለው ጸሐፊ ነው፡፡ ‹‹ከፈለግህ ውሰደው፤ ካልፈለግህ ጣለው›› በሚል ስሜት ለመናገር የሚችል ደፋር ጸሐፊ ነው፡፡ ሌሊሣ እያንዳንዱን ጽሑፍ ጽፎ ሲጨርስ፤ ሊነግርን የሚችለውን ነገር ሁሉ ተናግሮ የጨረሰ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ዕድሜ ለነጻነት፤ ተመልሶ ባትሪውን ሙሉ አድርጎ ይመጣል፡፡ ሌሊሣ በነጻነት ቀለም የሚደጉስ ፀሐፊ ነው፡፡

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ