Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

አርቲስት መሪ እንጂ

አርቲስት መሪ እንጂ ገበያ ተከትሎ የሚሮጥ አይደለም ሙዚቀኛ ሔኖክ

 

Related image

 

‹‹790›› ሔኖክና መሐሪ ብራዘርስ ከወራት በፊት የለቀቁት አልበም ነው፡፡ ሔኖክ መሐሪና ወንድሞቹ ከሙዚቀኛ አባታቸው እንዲሁም ዳንሰኛና ኬሮግራፈር እናታቸው ተወልደው፣ በሙዚቃዊ ቤተሰብ ውስጥ አድገዋል፡፡ ሔኖክ መሐሪ የመጀመሪያ አልበሙ ‹‹እውነተኛ ፍቅር››ን ከለቀቀ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሔኖክና ወንድሞቹ እንደ ዘሪቱ ከበደና ኢዮብ መኰንን ያሉ ድምፃውያንን ከማጀብ፣ የራሳቸውን ሥራ እስከማስደመጥ ደርሰዋል፡፡ የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ በመሥራትም ይታወቃሉ፡፡ አዲሱ አልበም ከተለቀቀ በኋላ፣ ሔኖክ የኦል አፍሪካ ሚውዚክ አዋርድስ (አፍሪማ) ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በኰክ ስቱዲዮ ከናይጄሪያዊቷ ድምፃዊት ሲንትያ ሞርጋን ጋር ተጣምሮ አቀንቅኗል፡፡ ስለ አልበሙ፣ ስለ ሽልማቱና ሌሎችም ሙዚቃ ነክ ጉዳዮች ሔኖክ መሐሪን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራዋለች፡፡ 

 

ሪፖርተ፡-  በቅርቡ ‹‹እወድሻለሁ›› በተሰኘው ዘፈንህ የአፍሪማ ምርጥ አር ኤንድ ቢና ሶል አርቲስት ሆነህ ተሸልመሃል፡፡ ምን ተሰማህ? ውደድሩስ ምን ይመስል ነበር?

 

ሔኖክ፡- ያስደነግጣል፡፡ ደስ ይላልም፡፡ ያስደነገጠኝ ሽልማቱን ስላልጠበቅኩት ነው፡፡ በአሁን ወቅት በአገራችን ኢንተርኔት የለም፡፡ በውድድሩ 50 በመቶ የሕዝብና 50 በመቶ የዳኞች ድምፅ ያስፈልጋል፡፡ ከሕዝብ የሚፈለገውን ድምፅ እንደማናገኝ ነበር የገመትነው፡፡ ውድድሩም ከባድ ነበር፡፡ ከ15ቱ ተወዳዳሪዎች ሰባቱ ናይጄሪያውን ሁለቱ ደቡብ አፍሪካውያን ነበሩ፡፡ ስማችን ሲጠራ ማመን አልቻኩም ነበር፡፡

 

ሪፖርተር፡-  አልበማችሁ በተለቀቀ በጥቂት ወራት ሽልማቱን ማግኘታችሁን እንዴት ታየዋለህ?

 

ሔኖክ፡- በዛ ቅጽበት ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጥቷል፡፡ አልበማችን ከወጣ ስድስት ወራት ሆኖታል፡፡ አልበሙን የሠራነው ንግድ ተኮር አድርገን አይደለም፡፡ እንደ አርቲስት ማለት የፈለግኩትን ያልኩበት እንጂ የኢትዮጵያን ገበያ ያተኮረ አይደለም፡፡ ትልቁን ድርሻ የምሰጠው ማንነቴን ለሚገልጽ ሥራ ነው፡፡ አልበሙ ገበያ ላይ ትልቅ ፈተና እንደሚገጥመውና በአንዴ እንደማይጮህለት አውቃለሁ፡፡ ከተማ ውስጥ ካሉ ያልበሰሉ ውድድሮች ያገኘነው ሙያዊ ያልሆነ ምላሽም ተፅዕኖ አለው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው አፍሪካዊ ውድድር ዕውቅና ሰጥቶ ሲሸልም ያስደስታል፡፡ ከዚህ በሻገር የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወክዬ ስለሄድኩኝ ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል፡፡ ታሪክ መጻፍ እፈልግ ነበርና የመጀመርያውን እንደሞከርኩ ይሰማኛል፡፡

 

ሪፖርተር፡-  ንግድ ተኮር አልበም ያለመሥራትን ከባድ አማራጭ እንዴት ወሰድክ?

 

ሔኖክ፡- አልበሙ ንግድ ተኮር አይደለም ያልኩት ከአገሪቱ አንጻር ነው፡፡ ሌላ አገር ከቋንቋው በስተቀር አልበሙ ንግድ ተኮር ሊሆን ይችላል፡፡ ከበፊቱ አልበሜና የሙዚቃ ተሞክሮዬ ጨምሬያለሁ፡፡ በአልበሙ የብዙ ባለሙያዎች ጥረት እንዲጨመር አድርጌያለሁ፡፡ ካሉት ሁለት ምርጫዎች ማለትም፣ እራስን ከመሆንና ገበያውን ተከትሎ ሰውን አስደስቶ ራስን ከመተው መካከል ራሴን መሆንን መርጫለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኼ መንገድ ጊዜ ይፈጅ ይሆናል እንጂ ይሠራል፡፡ አድማጭ ይኼንን አይሰማም ብለን መደምደም አንችልም፡፡ የራሳችንን አድማጭ ማፍራት አለብን፡፡ 90 ሚሊዮን ሕዝብ ለማስደሰት መሞከር ጤናማ አይደለም፡፡ የሰማውና የመረጠው ሰው ይስማው ሌላው እየቆየም ሊሰማው ይችላል፡፡ አርቲስት መሪ እንጂ ገበያ ተከትሎ የሚሮጥ አይደለም፡፡

 

ሪፖርተር፡-  በመረጥከው መንገድ ሄደህ ለአልበሙ ያገኘኸው ምላሽ ምን ይመስላል?

 

ሔኖክ፡- እንደፈራነው አይደለም፡፡ አዲስ የተለወጠ ትውልድ አለ፡፡ እኔ ከልጅ ሚካኤል አልበም ተምሬአለሁ፡፡ ሂፕ ሃፕ በአማርኛ ተሠርቶ እንደዚህ መወደዱ እንደ ፕሮዲውሰር ትልቅ ትምህርት ሰጥቶኛል፡፡ የእሱ ኮንሰርት ላይ ኪቦርድ ስጫወት ያየሁትን የሰባት ሺሕ ወጣት ገበያ ማንም አያውቀውም ነበር፡፡ በየትኛው ዕድሜ ክልል ያለውን አድማጭ ታሳቢ እንደምናደርግ ማወቅ አለብን፡፡ በአልበማችን እንደጠበቅነው ሳይሆን ደስ የሚሉ የድጋፍ፣ የፍቅርና የማረታታት ምላሾች መጥተዋል፡፡ በቁጥር ካየነው ግን ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ ይኼም ለወደፊት ይቀየራል፡፡ ካለኝ ልምድ ሙዚቃ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀስ እያለ ነው የሚሰማው፡፡

 

ሪፖርተር፡-  በአፍሪማ ከአንተ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች የታጩ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ነበሩ፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት በአህጉራዊ ውድድር የሚሳተፉ ሙዚቀኞች ቁጥር መጨመሩ ምን ያመላክታል?

 

ሔኖክ፡- ቁጥሩ ብዙ የሆነው ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም ነገር ከዜሮ እየጀመርን ነው፡፡ ፀደንያና ጆኒ ራጋ በእኛ ትውልድ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ፀደንያ የኮራና አፍሪማ ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡ ጆኒ ራጋ ቻናል ኦ ተሸልሟል፡፡ ይኼ ለኛ ብርቅ ነው፡፡ ነገር ግን ለውድድር ስንቀርብ አምስት ሳይሆን አምሳ መሆን አለብን፡፡ የዚህ ትውልድ አርቲስቶች ኃላፊነት አለብን፡፡ እኔም ጓደኞቼ እንዲወዳደሩ እየገፋፋሁ ነው፡፡ አብሮኝ የሔደው አንተነህ ሁለት ነጠላ ዜማ ለቆ ነው የተወዳደረው፣ በዚህም አድንቄዋለሁ፡፡ የግድ አልበም መጠበቅ ወይም ታዋቂ መሆን አያስፈልግም፡፡ አቅሙ አለን፡፡ አስተሳሰባችን ግን መቀየር አለበት፡፡ የተሸለምነው ዕድለኞች ስለሆንን ሳይሆን ስለሚገባን ነው፡፡ በራሳችን የመርካት ነገር ቀርቶ በውድድሮችና ፌስቲቫሎች በመሳተፍ ስላለንበት ደረጃ ለዓለም ማሳወቅ አለብን፡፡

 

ሪፖርተር፡-  በአህጉር አቀፍ ተሳትፎ ረገድ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች በኮክ ስቱዲዮ የነበራቸው ቆይታ ይጠቀሳል፡፡ አንተም ከተሳታፊዎቹ አንዱ ነበርክና ስለቆይታህ ብትነግረን?

 

ሔኖክ፡- በሙያዬ ትልቁ ቦታ መድረክ ማግኘት ነው፡፡ ከመድረክ ጀርባ ትክክለኛውን ሕይወት ስንኖረው ለማሳየት ኮክ ስቱዲዮ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ከሙዚቃው ጀርባ ያለንን ፍልስፍና ሕዝብ አያውቀውም፡፡ ኮክ ስቱዲዮ ይኼን ለማሳየት ዕድሉን ከፍቷል፡፡ የተለያየ ባህል ካላቸው ሙዚቀኞች ጋር ተገናኝተን እንዴት እንደሠራን የታየበት ነው፡፡ በተሞክሮው በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሌሎች ሙዚቀኞችም ዕድሉን እንዲያገኙ እመኛለሁ፡፡ የጥበብ የመጨረሻ ጥጉ ይሄ ነው፡፡ ብቃታችንን ዓለም ማወቅ አለበት፡፡ ስለምናደንቃቸው ሰዎች ሕይወት ብዙ እናውቃለን፡፡ እኛስ ለዓለም የምንሠጠው ምንድን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ወደ ኋላ የቀረነው ስለማንችል ሳይሆን ሁኔታዎች ስላልተመቻቹልን ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡-  በሙያዬ ትልቁ ነገር መድረክ ማግኘት ነው ብለሀል፡፡ ነገር ግን ሙዚቃ የሚቀርብባቸው መድረኮች ውስን እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ፌስቲቫሎች ቢጀመሩም ቀጣይነታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ ሙዚቀኞች ቋሚ መድረክ እንዲያገኙ ምን መደረግ አለበት?

 

ሔኖክ፡- ይኼንን የቤት ሥራ ሙዚቀኛው መውሰድ አለበት፡፡ የፌስቲቫል ባለቤቶች  ሙዚቀኛች ሆነው ከዛ ሙዚቃን የሚያከብሩ ባለሀብቶችን ማካተት ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ባንድ የራሱን ፌስቲቫል ማዘጋጀት ይችላል፡፡ ይኼ ግን ትልቅ እገዛ ያስፈልገዋል፡፡ ሁሌ ነጋዴ መጥቶ እንዲያዘጋጅ የምንጠብቅ ከሆነ ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ ብናስተካክላቸው ከምሽት ክለብ ጀምሮ ብዙ መድረኮች አሉ፡፡ የመንግሥትና የተለያዩ አካላት ኃላፊነት እንዳለ ሆኖ ሙዚቀኛው መድረኩን ካልፈጠረ ማንም አይፈጥርም፡፡ እንደ ኮክ ስቱዲዮ ዓይነት ድርጅት ለብዙዎች ትምህርት ይሰጣል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመጠጥ ድርጅቶች አንድ ዓይነት አካሄድ አላቸው፡፡ እነሱ ግን ታሪካዊ ውለታ ውለውልን፣ ከብዙ ነገር የተገለልን ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች እየሠራን ያለውን ለአፍሪካ ሙዚቀኞች እንድናሳይ አድርገዋል፡፡ አቅም አፍስሰው ይኼን ማድረጋቸው ከኋላ ያሉት ሰዎች ለሙዚቃ ያላቸውን ቦታና የአስተሳሰብ ምጥቀት ያሳያል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ሌሎች ድርጅቶችም ራሳቸው ተጠቃሚ ሆነው ጥበቡንም መጥቀም ይችላሉ፡፡

 

ሪፖርተር፡-  ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአህጉሪቱ ዕውቅናን ያላገኘው ለምንድን ነው?

 

ሔኖክ፡- ጥፋተኝነቱን መውሰድ ያለበት ሙዚቀኛው ነው፡፡ አንድ የሚያስቀኝ ነገር ‹‹እናንተ አልጀመራችሁትም›› የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ ዕይታ ጥበብ ወቅታዊ ነው፡፡ ሁልጊዜ ስለሞዛርት እያወራን አንኖርም፡፡ ኦስትርያ ውስጥ ሞዛርት እንደ ታሪክ ቢኖርም አዳዲስ ሞዛርቶችም ተፈጥረዋል፡፡ አርቲስቱ እንቅልፍ ላይ ስለሆነ መንቃት አለበት፡፡ ዝም ብለን ዳንስና እስክስታ ብቻ እንደሆንን ተደርጎ የተሣለብን ሥዕል አለ፡፡ ሙዚቃ ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡ ፍልስፍናና ሥነ ልቦናዊ ሕክምና አለውና ማኅበረሰብን ይገነባል፡፡ ሙዚቀኞች በትንሽ ሕልም ደስተኛ ነን? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የሆነ ጊዜ ከሆነ ሬከርድ ሌብል ጋር መሥራት ሞክረው ከሆነ ፕሮጀክት በኋላ ያቆሙ ትልልቅ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ሁሌ ይጠቀሳሉ፡፡ ቀዳሚዎቹ ቀጥለውበት ቢሳዩን ኖሮ ይኼኛው ትውልድ ይከተል ነበር፡፡ እውቅናቸውን ማሳጣት አልፈልግም፤ አልችልምም፡፡ ነገር ግን በነሱ ስም ሁል ጊዜ እንቀጠቀጣለን፡፡ እኔም ታሪክ እየሠራሁ ስለሆነ ቦታ እፈልጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ውጣ ውረድ ከሌሎቹ አፍሪካውያን ወይም አውሮፓውያን ሙዚቀኞች ጋር አይገናኝም፡፡ እኛ ብዙ ኋላ ቀር የሆኑ አሠራሮችን አልፈን ስኬታማ ለመሆን እንጣጣራለን፡፡ እኔ ራሴን በዓለም ገበያ ውስጥ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ የግድ በኢትዮ ጃዝ ብቻ ሳይሆን በምወደው ኮንቴሞፖራሪ ሙዚቃ ስኬታማ እየሆንኩ ነው፡፡ እኔ ያደግኩት ከተማ ስለሆነ መናገር የምችለው የበላሁትንና የጠጣሁትን ነው፡፡ ስለ ኦሪጅናሊቲ ሲነሳ መናገር የምችለው የማውቀውን ነው፡፡ የከተማ ልጅ ነኝ፣ ኢትዮጵያዊም ማንነት አለኝ፡፡ የአርቲስት ኦሪጅናልነት ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች የአፍሪካ አርቲስቶች የደረሱበት ቦታ ለመድረስ አርቲስቱ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት፡፡

 

ሪፐርተር፡- ባለፈው ሳምንት ‹‹ሚውዚክ ኢን አፍሪካ›› ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር፡፡ አፍሪካ ውስጥ በሙዚቃው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን የማገናኘት ዓላማ አንግበው ወደኢትዮጵያ እንደመምጣታቸው ለኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል?

 

ሔኖክ፡- ከተለያየ አፍሪካ አገር በሥራው ያሉ ትልልቅ ባለሙያዎች መጥተዋል፡፡ ከሶኒና ውሜክስ የመጡም ሰዎች ነበሩ፡፡ ከተነሱ ነገሮች መካከል ኦሪጅናል የመሆን ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ እኔ እንደ አርቲስት የመጀመሪያው ግባችን ራሳችንን ማስደሰት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ከአውሮፓ ከወጡ ፕሮዲውሰሮች ጋር መሥራት ጀምረን እነሱ እንደሚፈልጉት ሊቀርጹን በመሞከራቸው ሳንስማማ ትተነዋል፡፡ ሔኖክ መሐሪና መሐሪ ብራዘርስን የአዝማሪ ሙዚቃ ተጫወቱ ሲሉ መገናኘት አልቻልንም፡፡ ይህንን ዓይነት ሙዚቃ በቅርጽና በፍላጎትም ከእኛ ጋር ስለማይሄድ እውነተኛ መሆን ነበረብን፡፡ የግድ ተቀጥቅጠን ተጠርበን መግባት ብንችልም፣ የራስን ነገር ገድሎ ሌላ ሰውን ማስደሰት ይሆናል፡፡ ሁለቱን ግን ማቀራረብ ይቻላል፡፡ ከኮንፈረንሱ ያገኘሁት ነገር ሁለቱንም አካል ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መሔድ እንደሚቻል ነው፡፡ ማንነታችንን ሳንለቅ ገበያ ውስጥ ለመግባት መሞከር ማለት ነው፡፡ ያመንበትንና የምንወደውን ነገር መሥራት ትልቁ አዋጪ ነገር እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ አፍሪማ የተሸለምኩት ራሴን አስደስቼና የምወደውን ሙዚቃ ሠርቼ ነው፡፡ አንድ የሴኔጋል አርቲስት ‹‹እነሱ የሚፈልጉን እኛ በአገራችን ስኬታማ ስንሆን ነው፤›› ሲል ነበር የገለጸው፡፡ እነሱ ስላሉ ሁሉም ነገር ትክክል ነው ማለት ስላልሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የአሜሪካን ሙዚቃ ድጋሚ ብንጫወት ኪሳራ ነው፡፡ በአማርኛ መዝፈን በራሱ ይገልጸናል፡፡ ቋንቋችንን እንድንጠቀምም እንበረታታለን፡፡ ከኮንፍረንሱ በኋላ ሙዚቃችንን አቅርበን ከብዙ ባለሙዎች ጋር ተሞክሮ ተለዋውጠናል፡፡ ባለሙያ የሚመለምሉት በዚህ መንገድ ስለሆነም በዚህ ዓመት ብዙ ፌስቲቫሎች እንደምንካፈል ተስፋ አለኝ፡፡

 

ሪፖርተር፡-  በቅርቡ አዲስ የሙዚቃ መገበያያ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ የኮፒራይት ጥሰትን በመከላከልና ባለሙያዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ሥርዓቱ ለሙዚቀኛው ምን ያመጣል ብለህ ታስባለህ?

 

ሔኖክ፡- ‹‹ሚውዚክ ኢን አፍሪካ›› ሲምፖዚየም ላይ ከሌጎስ የመጣው የሶኒ ኤጀንት የመጀመርያ ጥያቄው ኢትዮጵያ ውስጥ ከቴሌኮም ጋር የምትሠሩበት የሙዚቃ አሻሻጥ አለ ወይ? ነበር፡፡ ዓለም ላይ በኮፒራይት ጥሰት የተጎዳችው ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም፡፡ የእኛ ግን የባሰ ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ እንደኛ ባሉ የተጎዱና አማራጭ ያጡ አገሮች መተግበር ያለበት ነው፡፡ እኔ የመጀመርያው አልበሜ ስንት እንደተሸጠ አላውቅም፡፡ የአሁኑን ራሴ ስላሳተምኩት መረጃው አለኝ፡፡ ሙዚቃው አይሸጥም በሚባልበት ኢንዱስትሪ ሰዎች እንዴት የሙሉ ጊዜ ሻጭ ይሆናሉ ብለን ስንጠይቅ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቀኞች እየተዘረፉ እንደሚኖሩ ያሳያል፡፡ ሻጮቹ ትልልቅ ሀብት ያካበቱት በሙዚቃ ሽያጭ ነው፡፡ ለሌብነት እንዲመቻቸው ምንም ዓይነት መረጃ ሊሰጡን አይፈልጉም፡፡ በቴክኖሎጂ ታግዞ ሙዚቃን በስልክ መሸጥ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ እኛ 47,000 ሙዚቃ መሸጥ አቅቶናል፡፡ አሁን ግን 47 ሚሊዮን ሰብስክራይበር አለ እየተባለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 47,000 መሸጥ ፕላቲንየንም እንደመሸጥ ይቆጠራል፡፡ የምናጣው ነገር ስለሌለ መሞከር አለብን፡፡ ተመራጭ ሐሳብ ስለሆነ እስከ ዳር መድረስ እንዳለበትም አምናለሁ፡፡

 

ሪፖርተር፡-  ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ግብይቱ ምን መሰናክሎች ሊገጥሙት ይችላሉ?

 

ሔኖክ፡- ከ47 ሚሊዮን ሰብስክራይበር ስንቱ አንድሮይድና አይፎን ይጠቀማል? ወይስ ቴክኖሎጂያቸው ደከም ባሉ ስልኮችም ማግኘት ይቻላል? የሚለው ጥያቄዬ ነው፡፡ ከመንግሥትስ ምን ያህል ድጋፍ ይሰጠናል? ከዚህ በፊት በቴሌኮሙዩኒኬሽን ከተጎዱ አንዱ ነኝ፤ ለሰብሳቢዎች (አግሪጌተር) ሰጥተው በግልጽ ብርሃን አጭበርብረውናል፡፡ ይኼ ከቀጠለ ያስፈራል፡፡ ጨረታ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዴት በእኔ ሙዚቃ ሰዎች ይጫረታሉ? እኔ መሸጥ የምፈልገው እንደዚህ ነው የምለው መሰማት አለበት፡፡ የተሻለ የቢዝነስ ፕሮፖዛል ለቴሌ የሰጠውን ሁሉ ከተቀበሉ ኃላፊነት አይሰማቸውም ማለት ነው፡፡ ይኼ እንደሚስተካከል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን በመጣው መንገድ በሥነ ሥርዓት ከተሄደበት እኛም እንጠቀማለን፤ አገሪቷም ታክስ ታገኛለች፡፡ ሙዚቃ ዝም ብሎ የሚሸጥ ዕቃ አይደለም፡፡ ከሙዚቃ ጀርባ ሰው አለ፡፡ የሚተርፈው ገንዘብ ብቻ መታሰብ የለበትም፡፡ መንግሥት መሥሪያ ቤቱን ያለ ተቀናቃኝ ስለያዘው በትክክል ቢያስኬደው ሁላችንም ደስተኛ እንሆናለን፡፡

 

ሪፖርተር፡- የ‹‹790›› አልበም ዝግጅት ምን ይመስል ነበር?

 

ሔኖክ፡- የመጀመርያው አልበም ሲሠራ የምሽት ክለብ ሄጄ አላውቅም፡፡ ቤቴ ጨርሼው ከተለቀቀ በኋላ ነው ብዙ ባንዶች ገብቼ የሠራሁት፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ ስህተቶቼን ለይቼ አውቄያለሁ፡፡ ቀድሞ ቦታ የምሠጣቸው ቁም ነገሮች ዛሬም ያው ቢሆኑም፣ አድጌያለሁ፡፡ ቀድሞ ያልበሰለ አካሄድ ነበረኝ፡፡ ፕሮዳክሽኑም ጥራት ይጎድለው ነበር፡፡ ያንን ማንነቴን ባከብረውም መብሰል ነበረብኝ፡፡ የአሁኑ አልበም ወደ አምስት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ብዙውን ነገር የሠራሁት እኔ ነኝ፤ ባለሙያዎችን ለማሳተፍም ሞክሬያለሁ፡፡ እንደ ዘሪቱ፣ ቤቲና ኤልያስ ያሉ ሙዚቀኞች አልበሜ ጫፍ እስኪደርስ አብረውኝ ነበሩ፡፡ ኤልያስ ይኼን አድርግ፣ ይኼ ዜማ ላንተ ይሆናል እያለ አቅጣጫ አመላክቶኛል፡፡ አንዳንዴ ንግድ ተኮር አልበም ሠርቼ ልክበር እንዴ? ብሎ ግራ መጋባትም አለ፡፡ ነገር ግን ለራስህ ታማኝ ሁን ብለው ያበረታቱኝ ነበሩ፡፡ ብዙ ዜማዎች ገዝቼ ስላልተስማሙኝ ጥያለሁ፡፡ ዘሪቱ ሦስት ሙዚቃ ጽፋልኝ ተቀብያለሁ፡፡ ባንዴ ሙዚቃውን ላይቭ ተጫውቶ አልበሙን ሙሉ በሙሉ ፕሮዲውስ አድርጌያለሁ፡፡ ከባንዱ ውጪ ቫዮሊንና ፐርከሽን የሚጫወቱም ጋብዘናል፡፡ ኪሩቤል ተስፋዬ የሙዚቃ ኢንጂነሪንጉን ሠርቶልናል፡፡ በስተመጨረሻ ጥሩ ውጤት ያለውና የምንደሰትበት ሥራ ሠርተናል፡፡

 

ሪፖርተር፡-  መሐሪ ብራዘርስ ለዓመታት እንደ ባንድ ዘልቃችኋል፡፡ ብዙ ባንዶች ደግሞ ጀምረው ሲያቋርጡ ይታያል፡፡ ችግሩ ከምን የመነጨ ነው?

 

ሔኖክ፡- መሐሪ ብራዘርስ ስንመሠርት ሁላችንም ሌሎች ባንዶች ውስጥ ሠርተናል፡፡ ሙዚቃ የስሜት ሥራ ስለሆነ ተኮራርፎ መሥራት ከባድ ነው፡፡ ስሜቱ መድረክ ላይ ይታያል የሠራሁባቸውን እንደ ኤክስፕረስ፣ አፍሮ ሳውንድ፣ ዛየንስና የመሳሰሉት ባንዶች ልምድ እንዳካብት አድርገውኛል፡፡ ባንድ ሲኮን ሁሉም ኃላፊነትና ባለቤትነት ሊሰማው ይገባል፡፡ በቢዝነስ ጎኑ የባንድ ባለቤቶች ብዙ ገንዘብ እያገኙ ተቀጣሪው ትንሽ ስለሚያገኝ የተሻለ ጥቅም ሲገኝ ባንዱ ይፈርሳል፡፡ ስለባንዱ ቀጣይ አቅጣጫ እርስ በርስ መነጋገርና ተስፈኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እኛ መቼ እንደምናሳካው ባናውቅም ከልጅነታችን ጀምሮ ባንድ የመመሥረት ህልም ነበረን፡፡ ዕቃ ከማሟላት ጀምሮ ስማችንን እስከመትከል ድረስ መዘጋጀት ነበረብን፡፡ የተሻለ ልምድና ስም እስከምናገኝ በተለያየ ባንድ ውስጥ እያገለገልን ቆየን፡፡ ዘሪቱ ለረዥም ጊዜ ህልማችንን የምታውቅ ቤተሰብ ስለሆነች ለምን አሁን አትመሠርቱም አለች፡፡ በወቅቱ የሷ አልበም ጥሩ ጉልበት ሰጥቶናል፡፡ እሷ እኛን ይዛ መድረክ ላይ ለመውጣት ፈቃደኛ ስለነበረች ሁላችንም ከያለንበት ተሠባስበን ሠራን፡፡ ከባዱ ፈተና የአገራችን የጉምሩክ ቀረጥ ሕግ ነው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ ይዞ ለመግባት የሚዘገንን ቀረጥ ይጠየቃል፡፡ ይህ ከዘመኑ ጋር በእቃና በችሎታም ለመወዳደር ፈተኝ  ያደርገዋል፡፡ ዕቃ እየተከራየን በመሥራት ለብዙ ዓመታት ታሽተናል፡፡ ሌላው ችግር የሙያ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቁት ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለአንድ ዘመናዊ ባንድ ስምንት ተወዛዋዥ ያስፈልጋል ይባላል፡፡ እኛ አምስት ሙዚቀኞች ገና በእግራችን ቆመን ለመሥራት እየታገልን የግድ ስምንት ሰዎች መቅጠር ሊያስፈልገን ነው፡፡ መንግሥት በግል ተቋም ጫና የሚጥልበት ሕግ ነው፡፡ እኔ ሙዚቃ አጥንቼ በግድ ተወዛዋዥ ማስተዳደር አለብኝ ማለት ነው፡፡ ሕጉን ሥራዬ ነው ብሎ የሚያስተካክል ተቆርቋሪ የለም፡፡ ታክስ መክፈል ግዴታችን ስለሆነ ደስ እያለን እንከፍላለን፡፡ ነገር ግን ውስኪ በነፃ እየገባ ኪቦርድና ጊታር እንደ ወንጀል ሆኖ እጥፍ እንከፍላለን፡፡ ሁሉም ፈተናችን ያለው በመንግሥት እጅ ነው፡፡ ብዙዎችን ያለንበት የደረስነው በግል ጥረታችን በመሆኑም መበረታታት አለብን፡፡

 

ሪፖርተር፡- ይህ ችግር በተደጋጋሚ ሲነሳ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሁኔታውን ለማስተካከል ሙዚቀኛው የሚገባውን ያህል ርቀት ሔዷል? የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ኃላፊነት ማስተማር ቢሆንም በጉዳዩ ዙሪያ ምን አድርጓል ብለው የሚጠይቁም አሉ፡፡

 

ሔኖክ፡- ሙዚቀኛው ነገሩን መግፋት እንዳለበት እስማማለሁ፡፡ ሕጋዊ ሁን ስባል ሕጋዊ ሆኛለሁ፡፡ ነገር ግን በዘርፉ ስንት ሕጋዊ ባለሙያዎች አሉ? የሚለውን መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ሕጋዊ በመሆኔ ስጎዳ ሌሎች ሕገ ወጥ በመሆን ይጠቀማሉ፡፡ የእኔ ሥራ ሙዚቃ መጫወት እንጂ ይኼን ማስተካከል አይደለም፡፡ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትም ፈርዶበት ሁሌ ይቀጠቀጣል፡፡ አንድ የክላሲካል ሙዚቃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ አቅም ካለው ቢደግፍ መልካም ቢሆንም ግዴታው አይደለም፡፡ እኛና አባቶቻችንም የተማርንበት ስለሆነ ተቋሙ ብቻውን መቀጥቀጥ የለበትም፡፡ እንኳን ሌላ ነገር ውስጥ ሊገባ ራሱን ማስተዳደርስ ችሏል? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለን ሙዚቀኞች ሙሉ በሙሉ የሚጠበቅብንን ያደረግን አይመስለኝም፡፡ ጥበብ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም የማይጨነቅለትና ከምንም ነገር በታች የሆነ ነው፡፡ ሕዝቡ ሳይሆን በአስተዳደር ደረጃ የጥበብን ኃይል የተረዱት አይመስለኝም፡፡ ሚዲያዎቻችን ሜንስትሪምና አንደርግራውንድን አይለዩም፡፡ ማንን እንደሚያደንቁ ማንን ፕሮፌሰር እንደሚሉ አይታወቅም፡፡ አንድ ሐያሲ የሙዚቃ ተመራማሪ ተብሎ ይመጣል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ ሳይጫወትና ሳይዘፍን የሙዚቃ ፈላስፋ ተብሎ ሚዲያ ላይ ሲወጣ ሕዝቡም ይወናበዳል፡፡ ጥበብ ላይ የሚሠራው ሳይሆን የሚያወራው ይከበራል፡፡ የሙዚቃ ኤክስፐርት የሚባል ነገር ዓለም ላይ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ባህልና ቱሪዝም ውስጥ ፈቃድ የሚሰጡን ሰዎች ሙዚቃ የሚሠሩ አይደሉም፡፡ ማን ማንን እንደሚመራ አለመታወቁ እንደ አገር ያሳፍራል፡፡ ሥርዓት የሚባል ነገር የለም፡፡ ባለሙያዎች በቦታቸው ቢቀመጡ ሕጉም ይስተካከላል፡፡ ለምሳሌ ስለ ሮያሊቲ ክፍያ ሲነሳ ዲጄዎች ለዘፋኝ ይክፈሉ ሲባል፣ በምን መንገድ የሚለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ መጀመርያ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ኤፍኤሞች ከፍለው ማሳየት አለባቸው፡፡ ሥርዓት መጀመር ያለበት ከላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኮፒራይት ማኅበር አባል ስትሆን ሁሉም ይስተካከላል፡፡ አሁን ግን መንግሥት ማስተካከል ያልቻለውን እንዴት ባለመያው ይችላል?

 

ሪፖርተር፡- በሙዚቃዊ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ ምን ይመስላል?

 

ሔኖክ፡- የተለየ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አብሮ አደጎቻችን ሙዚቀኛ ሊሆኑ ሲሉ እንኳን ቁጣ ይደርስባቸው ነበር፡፡ በእኛ ቤተሰብ ግን ስለሙዚቃና ዳንስ እየተወራ ነው ያደግነው፡፡ አባታችን ትምህርት ላይ ጠንካራ ቢሆንም ሁሉንም እኩል እንድናስኬድ ይፈልጋል፡፡ ሙዚቃ እንድንተው አይፈልግም፡፡ ተሰብስበን እንድንጫወት ይፈልግ ነበር፡፡ የሚገርመው ሙዚቀኛ እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ለትምህርት ትልቅ ቦታ እሰጥ ነበር፡፡ እያደግን ስንመጣ ግን ሙዚቃ በደማችን ስለገባ ምንም ዓይነት ሙያ ቢኖረኝ ሙዚቃን እንደማልተው ተረዳሁ፡፡ ያሬድ ከገባን በኋላ በቤተክርስቲያንም ሙዚቃና ድራማ እንሠራ ነበር፡፡ እያልን እያልን እዚህ ደረስን፡፡

 

ሪፖርተር፡- የማትረሳው የልጅነት ትዝታህ ምንድን ነው?

 

ሔኖክ፡- ከሰፈር ልጆች ጋር በተቀደደ ሳፋ፣ ጎማና እንጨት ጊታርና ከበሮ ሠርተን ትርዒት እናሳይ ነበር፡፡ ተመልካቾች የሚከፍሉት የከረሜላ ወረቀት ነበር፡፡ ያልከፈሉ እንዳያዩት ትርኢቱን በካርቶን እንሸፍነው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ እናቴ የላከችኝን ረስቼ እዘፍናለሁ፡፡ በትርዒቱ መካከል ከኋላዬ መጥታ ኮረኮመችኝ፡፡ ከዛ አቋርጬ የተላክሁትን ገዛሁና ወደ መዝፈኑ ተመለስኩ፡፡

 

ሪፖርተር፡- የአልበማችሁ መጠሪያ የቀድሞ የቤት ቁጥራችሁ ነው፡፡ ትኖሩበት የነበረው ቤት ምን ይወክላል ብለህ ታስባለህ?

 

ሔኖክ፡- የገለፅኩት ዓይነት ብዙ ታሪኮች የተፈጠሩት እዛ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ወላጆቻችን ጠዋት ስለነበራቸው ልምምድ ሲያወሩ እንሰማለን፡፡ የመጨረሻ አልበሜን ሠርቼ መጠሪያ ስፈልግ ነበር፡፡ ዘፋኝ ነው መባል ብቻ  ሳይሆን በአልበሙ ምን መልዕክት አስተላልፏል መባል እፈልጋለሁ፡፡ ወንድማማቾቹ ከየት ነው የተነሳነው? ብዬ ሳሰብ ሙዚቃን ያስተዋወቁን ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ የት? ሲባል ደግሞ ተወልደን ያደግንበት ቤት ቁጥር መጣልኝ፡፡ ቁጥሩ ይገልፀናል፡፡ ትምህርት ቤት ስንገባ ስማችንን እስከ አያታችን አጥንተን እንሄድና ስልክና የቤት ቁጥር አድራሻ እንናገራለን፡፡ ሐሳቡን ለወንድሞቼ ስነግራቸው ወደዱትና አልበሙ ‹‹790›› ተባለ፡፡ ስድስት በሙዚቃ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችን ይገልጻቸዋል፡፡

 

ሪፖርተር፡- ሔኖክና መሐሪ ብራዘርስ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዴት ታየዋለህ? ምን አምጥተናል ብለህስ ታምናለህ?

 

ሔኖክ፡- ከእኛ በፊትና በኋላም ብዙ ባንዶች አሉ፡፡ እኛ የቀየርነው ታሪክ እንዳለ ግን አምናለሁ፡፡ እኛ ወንድማማቾች ከመሆናችን ባሻገር ቤተክርስቲያን አብረውን ያደጉ የመንፈስ ወንድሞቻችንም አሉ፡፡ መድረክ ላይ ሰባት ድሬድሎክ ሙዚቀኞች እየዘለልን ሙዚቃ በመጫወት ያመጣነው ኃይል አለ፡፡ እየዘለለ የሚደንስ ባንድ ባልነበረባት ጊዜ ትኩስ ኃይል አምጥተናል፡፡ ከዛ በኋላ ብዙ እኛን የሚመስሉ ሙዚቀኞች መጥተዋል፡፡ ለረዥም ጊዜ መቆየታችም መገለጫችን ነው፡፡ ፈተና ስላልገጠመን ሳይሆን ትልቅ ህልም ስላለን ባንዱ ሳይዋዥቅ ቀጥሏል፡፡

 

ሪፖርተር፡-  እንደ ሙዚቀኛ ለሥራዎችህ ምን ያነሳሳሃል?

 

ሔኖክ፡- ከሕይወት በላይ የሚያነሳሳኝ የለም፡፡ ባለቤትና ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ ሙዚቀኛ ጓደኞቼም ያነሳሱኛል፡፡ ሕይወትን በጥበብ መግለጽ የሚያረካ ነገር ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡-  በሙዚቃህ ምን ማስተላለፍ ትፈልጋለህ?

 

ሔኖክ፡- ሙዚቃ ለእኔ ትልቅ መሣሪያ ነች፡፡ የማምነውን እውነትና ፍልስፍናዬን የማስተላልፍባት ነች፡፡ ጥበብ በአጠቃላይ የተሠራው እግዚአብሔርና ሰውን እንዲያከብር ነው፡፡ የሰው ልጅ ከአምላኩ ጋር ሰላም ካለው ከጎረቤቱ ጋር ሰላም ይኖረዋል፡፡ ከራስ ጋር እርቅ ካለ ዓለምን የምናይበት መነፅር ይቀየራል፡፡ ብዙ ዓለምን የሚረብሽ ነገር አለ፡፡ ዘፈኔ ይኼንን ረብሻ ካልተናገረ ትርጉም የለውም፣ ኃላፊነት ስለሚሰማኝ የሰውን ልጅ የማያከብሩና ርካሽ መልዕክት ያላቸው ዘፈኖች ውስጥ የለሁበትም፡፡ የፍቅር ዘፈንም ሲሆን ሰውን የሚያከብር እንጂ ሴትን እንደ አሻንጉሊት የሚያይ ዘፈን አይመቸኝም፡፡ መልዕክቶቼ ሰው ሰው የሚሉ ሆነው ሰውን የሚገነቡ፣ የሚያዝናኑ እንዲሁም አገርን ለማሞገስም ይሁን ሐዘንን ለመግለጽ ሰውን ባከበረ መልኩ የተቀረጹ ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡

 

ሪፖርተር፡-  በሙዚቃ ሕይወትህ የገጠመህ ትልቁ ፈተና ምንድን ነው?

 

ሔኖክ፡- ትልቁን ፈተና አሁንም አላለፍነውም፡፡ ኢትዮጵያን ለማስጠራት ሙዚቀኛ ባልሆንም፣ ኢትዮጵያ በእኔ ምክንያት ስትጠራ ግን ደስ ይለኛል፡፡ ነገሮች ተመቻችተውልኝ የበለጠ ብሠራ እመኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሳታሚ፣ ሬከርድ ሌብል፣ ፕሮዲውሰርና ወደ ሙዚቃ የሚያይ ባለሀብት ስለሌለ ያለነው ራሳችን ለራሳችን ነው፡፡ የምንወደው ሙያ ባይሆን ብዙዎቻችን ከዚህ ሥራ እንወጣለን፡፡ እኛ ስኬታማ ተብለን እንደዚህ ከታገልን ከታች የሚመጡት ልጆች እንዴት ሙዚቀኛ እንዲሆኑ ማበረታታት እንችላለን? በኋላ ቀር መንገድ መጥተን በኋላ ቀር መንገድ እንሄዳለን፡፡ የ90 ሚሊዮን ሕዝብ ገበያ እያለ ከዜሮ በታች መኖራችን ያሳዝናል፡፡ እንደምናልፈው ግን አምናለሁ፡፡

 

ሪፖርተር፡- በቅርብ ርቀት የያዛችሁት ዕቅድ ምንድነው?

 

ሔኖክ፡- ከአልበም ሪሊዝና ፌስቲቫል ውጪ አልበሙ ወደ ኮንሰርት አልተቀየረም፡፡ አልበሙን ከሰው ጋር በደንብ ለማጣጣም ፕሮጀክቶች ቀርፀናል፡፡አሁን ያለው ሁኔታ ወደ ኋላ ጎትቶን ነው እንጂ ነገሮች ጥሩ ሲሆኑ ወደ ኮንሰርት እንገባለን፡፡

 

 

ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ