Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ዶ/ር እሌኒ፣ ወደር የለሿ ኢትዮጵያዊት…

 

ዶ/ር እሌኒ፣ ወደር የለሿ ኢትዮጵያዊት…የምንማሯቸው 10 የጥበብ ምስጢሯ!!

‹‹ሕልማችሁን አጥብቃችሁ ያዙ››

 

 

           

በ1848 እ.ኤ.አ 82 ገበሬዎች እና እህል ነጋዴዎች በመሰባሰብ፣ ቺካጐ ቦርድ ኦፍ ትሬድስ (Chicago board of trades) በሚል ያቋቋሙት የምርት ገበያ ድርጅት፣ በዓለም የመጀመሪያውና እስከ ዛሬም ትልቁና ጠንካራው ነው፡፡ ቺካጎ ቦርድ ኦፍ ትሬድስ፣ ከ167 ዓመታት በፊት ሳይቋቋም የአሜሪካ ገበሬዎችና የእርሻ ምርት ነጋዴዎች፣ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮችንና ኪሳራዎችን ለረዥም ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ ገበሬዎቹ በተለይም በመካከለኛውና ምዕራብ አሜሪካ ግዛቶች ለሚገኙ ገበሬዎች፣ ምርቶቻቸውን ወስደው ለመሸጥ በሚሺጋን ወንዝ ረጅም መንገድ አቋርጠው መሄድ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ይኸን ሁሉ መንገድ አልፈው ከታሰበለት ገበያ ሲደርሱ፣ ያመረቱት ምርት ዋጋ ቀንሶ ከጠበቃቸው አልያም ገዢ ሳያገኙ ከቀረም፣ በድጋሚ ያንን ሁሉ መንገድ ተመልሰው ምርታቸውን አጓጉዘው፣ በኪሳራ ወደ ቀያቸው መመለስ ይጠብቃቸዋል፡፡ አብዛኛውና አነስተኛ ገበሬ ያልተሸጠውን ምርት በድጋሚ ወደ ቀዬው የመመለሻ ካፒታል ስለማይኖረውና ለበለጠ ኪሳራም ስለሚዳርገው፣ እዛው ሚሺጋን ወንዝ ላይ ምርቱን ጥሎ ባዶ እጁን ይመለስ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ሥቃይ የተማረሩ 82 አሜሪካውያን ናቸው፣ ከ167 ዓመታት በፊት ምርት ገበያን በአሜሪካም ሆነ በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቋቋሙት፡፡

የመጀመሪያው የምርት ገበያ ከተመሠረተ ወደ ሁለት ምዕት ዓመት ቢጠጋም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ለሀገራችን ገበሬዎችና እህል ነጋዴዎች፣ አሜሪካኖች ድሮ የተቸገሩበትን ዓይነት የአምራችና የነጋዴ መራራቅ ችግር አጥልቶበት ኖሯል፡፡ ሆኖም ይህን ችግር አስተውላ፣ መፍትሔውም ጥሩ የሆነ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማመቻቸት ነው በማለት ተነስታ፣ ዓላማዋን ከግቡ ያደረሰችው ኢትዮጵያዊት ሴት ዶ/ር ዕሌኒ ዘውዴ ገ/መድኅን ትባላለች፡፡ የዛሬው የዝነኞች የስኬት ምሥጢር እንግዳ ስናደርጋትም ምርጥ ተሞክሮዋን ለማጋራት በሚል ነው፡፡

ዶ/ር ዕሌኒ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ኮርኔል ከሚባል የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪዋን ከሚሺጋን እስቴት ዩኒቨርስቲ፣ የዶክትሬት ዲግሪዋን ደግሞ ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ያገኘች ሲሆን፣ በዓለም ባንክ ውስጥ ዋና ኢኮኖሚስት በመሆን ለረጅም ጊዜ አገልግላለች፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በኢኮኖሚስትነትና የምርት ልውውጥ ኤክስፐርት በመሆን ሠርታለች፡፡ ከዛም በማስከተል በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲዎች ምርምር ተቋም (IFPRI) ለረዥም ጊዜ አገልግላለች፡፡

ወደ ሀገሯ ተመልሳ እንድታገለግል ያደረጋት አጋጣሚ፣ በ2002 እ.ኤ.አ በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ነበር፡፡ ዶ/ር ዕሌኒ በእንደዚህ ዓይነቱ የችግር ዜና ስትረበሽ የመጀመሪያዋ ጊዜ አይደለም፡፡ በኮርኔል ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ስትማር 1984 እ.ኤ.አ ኢትየጵያ በ77ቱ ድርቅ ክፉኛ የተጐዳችበት ጊዜ ነበር፡፡ ታዲያ በአንድ ምሽት በዩኒቨርስቲው የመመገቢያ አዳራሽ ራት ለመመገብ ከአንዲት ኢትዮጵያዊት ጓደኛዋ ተማሪ ጋር ተቀምጣለች፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ሁሉም ተማሪዎቹ ምግብ በመወራወር ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡ በሁኔታው እጅግ የተበሳጨችው ዶ/ር ዕሌኒ ከተቀመጠችበት ተነስታ ወንበር ላይ በመቆም፣ ‹‹አቁሙ! እንዴት እንደዚህ ታደርጋላችሁ? ሀገሬ ሰው በረሃብ እያለቀ ነው…” ብላ በቁጣና በጩኸት ተናገረች፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ጓደኛዋ በመገረምና በድንጋጤ ፈዛ ዶ/ር ዕሌኒን ተመለከተች፡፡ ከምንም ያልቆጠሯት ተማሪዎቹ ግን ምግቡን ወደርሷ በመወርወር ጨዋታቸውን ቀጠሉ፡፡ በወቅቱ በኮርኔል ዩኒቨርስቲ ከነበሩት 17,000 ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ኢትዮጵያውያት ብቻ ነበሩ፡፡ በድርጊቱ በጣም ያዘነችው ዶ/ር ዕሌኒ፣ በነጋታው ወደ ዩኒቨርስቲው መጽሔት አዘጋጆች በመሄድ፣ ሁኔታዎችን አስረድታና አሳምናቸው በመጽሔቱ ላይ እንዴት ከአንድ የተማረ ኅብረተሰብ የማይጠበቅ ሥራ እንደሠሩ አጽፋለች፡፡

ዶ/ር ዕሌኒ ሁሌም ችግሮችን በተመለከተች ቁጥር ወደ መፍትሔ የምትሄድ፣ ጠንካራ የሥራና የቴክኒክ ሰው ነች፡፡ ለሥራዎቿም በርካታ ዕውቅናዎችንና ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በ2012 እ.ኤ.አ አፍሪካ ባንከር ኢኮን፣ በዚያው በ2012 በጂ.ኤይት (G8) ስብሰባ ላይ በአሜሪካ ካምፕ ዴቪድ በሚባለው የፕሬዝዳንቶች ማረፊያ ተገኝታ ባራክ ኦባማና ዴቪድ ካሜሮን በተገኙበት በእንግድነት ተሣትፋለች፡፡ አሁንም በ2012 ከመቶ አፍሪካዊ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዷ ሆና ተመርጣለች፡፡ በ2009 እና በ2010 እ.ኤ.አ፣ የዓመቱ ምርጥ ኢትዮጵያዊት ተብላ ተሰይማለች፡፡ በ2012 በኢትዮጵያ እህል ምርት ገበያ ድርጅት ባበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽዖ፣ ያራ የሚባለው የኖርዊጂያን ዓለም አቀፍ ሽልማትን ተቀብላለች፡፡

ከ2008 እስከ 2012 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ያገለገለችው ዶ/ር ዕሌኒ ወደ ሀገሯ የተመለሰችው፣ ለ30 ዓመታት በትምህርትና በሥራ ውጭ ሀገር ከቆየች በኋላ ነው፡፡ ዶ/ር ዕሌኒ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ስትሆን በአሁኑ ወቅት በቋሚነት የምትኖረው በአዲስ አበባ ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጇ 17 ዓመቱ ሲሆን ያሬድ ይባላል፤ ሁለተኛው ልጇ የ14 ዓመት ሲሆን ስሙም ዜጋ ነው፡፡ ዶ/ር ዕሌኒ ልጆቿን በምትወደው ሀገሯ ብታሳድጋቸውም እርሷ ግን ይሄንን ዕድል በልጅነቷ አላገኘችም፡፡ አባቷ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በትልቅ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ይሠሩ ስለነበር፣ በርካታ ሀገራት በተዘዋወሩ ቁጥር መላው ቤተሰቡም ይዘዋወር ነበር፡፡

ገና በ4 ዓመቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ከአዲስ አበባ ወጥታ ወደ አሜሪካዊቷ በኒውዮርክ ሲቲ ሄደች፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ሲመጡ፣ በወቅቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት ስለነበር መላው ቤተሰቡ ወደ ሩዋንዳ በማስከተልም ወደ ቶጐ እና ማላዊ በመጨረሻም ወደ ኬኒያ ሄዱ፡፡ ዶ/ር ዕሌኒም የልጅነት ጊዜዋን በ6 ሀገራት መካከል አሳልፋለች ማለት ነው፡፡ በተዘዋወረችባቸው ሀገሮች ትምህርቷን በእንግሊዘኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋ ስትከታተል፣ ስዋሒሊ የሚባለውን የአፍሪካ ቋንቋም ተምራለች፡፡ አማርኛን በቤተሰቦቿ ዕርዳታ የተማረችው ዶ/ር ዕሌኒ አሁንም ድረስ አማርኛ መፃፍና ማንበብ በጣም ያስቸግራታል፡፡

ዶ/ር ዕሌኒ ስለቤተሰቦቿ ስትናገር፣ ‹‹በሕይወቴ ላለው መልካም ነገር ሁሉ መሠረት የሆኑት ቤተሰቦቼ፣ በእኔና በእህቴ ላይም ጥሩ የሆነ የሀገር ፍቅርንና ኩራትን በውስጣችን ቀርፀውብናል፡፡ ለረጅም ጊዜ ስለሀገሬ ሳስብና ሳሰላስል ያለኝ ብቸኛው መንገድ፣ ቤተሰቦቻችን የነገሩን የእናቶቻችን፣ የአባቶቻችን፣ የሀገራችን ታሪኮች እና ትውስታዎች፣ በአዕምሮዬ ውስጥ ተስለው የተቀመጡት ነው፡፡ እናቴ ብዙወርቅ ስለተወለደችበት ስለሐረር አውርታ አትጠግብም፤ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ስለቅድመ አያቴ እማሆይ ሳባ ይፋት ብዙ ትነግረኝ ነበር፡፡ እማሆይ ሳባ ከመንዝ መጥተው በሐረር ገጠራማ አካባቢ ይኖሩ ነበር፡፡ መነሻቸውም ከጐንደር ሲሆን ጣልያን ኢትዮጵያን ሲወር ከነበሩ ጥቂት ሴት ዐርበኞች መካከል አንዷ ነበሩ፡፡ ስድስት ልጆቻቸውን እና የእርሻ መሬታቸውን ከጣሊያን ለማዳን ሲሉ፣ የእርሳቸው ልጅ የሆኑት የእኔ አባት ፣ በዳኝነት ሥራ ላይ ተሰማርተው በሐረር ከተማ አገልግለዋል፡፡ በልጅነቴ ከእናቴ እናት ከአያቴ በለጥሻቸው ጋር ተቀምጬ ታሪክ ማዳመጥ እወድ ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እማሆይ በለጥሻቸው፣ በአሮምኛ ብዙ የድሮ ታሪኮችን ከእናቴ ጋር ታወራ ነበር፡፡ የቡና እርሻዋን እንዴት አድርጋ በፌዴሳና እና በድሬዳዋ ታስተዳድር እንደነበር እየሳቀች አውርታ አትጠግብም ነበር…፡፡

አባቴ ዘውዴም፣ በየሄድንበት ሀገር በሚሰጡን መኖሪያ ቤት ውስጥ ያሉትን የውሃ ታንከሮች፣ ‹‹የቡልጋ ምንጭ›› እያለ በአያቴ በአቶ ገ/መድኅን የትውልድ ቦታ ስም ይጠራቸው ነበር፡፡ አያቴ ገ/መድኅን ከሰሜን ሸዋ አካባቢ ሲሆን ወደ ወላይታ ሶዶ በመሄድ፣ ወ/ሮ አየለች አላይን አግብተው አባቴን ወልደዋል፡፡ የወላይታው ንጉሥ ጦና የአያቴ ወ/ሮ አየለች አጎት ነበሩ፡፡ በሰባት ዓመቴ አስታውሳለሁ፤ ወደ ሶዶ ሄጄ የአባቴን የትውልድ ቦታ ጎብኝቼና በርካታ ዘመዶቼን አግኝቼ ያሳለፍኩትን ጊዜ፣ አያቴም ገ/መድኅን የቡና እርሻ ቦታውን ያሳየኝ እና ስለ አባቴ የልጅነት ጊዜ ታሪኮች እየነገረኝ እኔ ግን በወቅቱ፣ በእንግሊዝኛ የሕፃናት ቀልዶችን ሳወራለት ምንም ሳይረዳኝ ፈገግ ብሎ ያየኝ የነበረውን አስተያየት መቼም አልረሳውም…›› ዶ/ር ዕሌኒ በዚህ መልኩ የምታስታውሰውን የልጅነት ጊዜዋንና በውስጧ ተስሎ የቀረውን የቤተሰቦቿን ታሪክ ‹‹ናዝሬት ዶት ኮም‹‹ በተባለ ድረ ገፅ ላይ ጽፋለች፡፡

ዶ/ር ዕሌኒ እ.ኤ.አ 2007፣ ቴድ ተብሎ በሚታወቀውና እጅግ በጣም ብዙ የዓለማችን ምርጥ ተመራማሪዎች፣ የሀገር መሪዎች፣ የፈጠራ ሰዎች፣ የሥነ ጥበብ ባለሞያዎች በጣም ያማረና አጭር፣ በከባድ ፍሬ ነገር የተሞላ የ20 ደቂቃ ብቻ ንግግር በሚያደርጉበት መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጋብዛ ቀርባ ነበር፡፡ በመድረኩ ላይም ስላሰበችው ሥራና ስላነሳሳት ጉዳይ ባማረ መልኩ አብራርታለች፡፡ በወቅቱም እንዲህ ብላለች፡- ‹‹ደስተኛነት ማለት የመምረጥ ነፃነት ማለት ነው፡፡ የት ልኑር፣ ምን ልሥራ፣ የት ልሥራ፣ ምን ላድርግ የሚሉትን በነፃነት መወሰን ነው፡፡ የሀገራችን ገበሬ ያመረተውን ይዞ ምርት በበዛበት ወቅት ይመጣል፤ በቅናሽ ዋጋም ይሸጣል፤ ከጥቂት ወራት በኋላም ተመልሶ ለመሸመት ወደ ገበያ ይወጣል፤ ምርት ባጠረበትና ዋጋ በናረበት ወቅት ቤተሰቡን የመመገብ ኃላፊነት ስላለበት ብዙም ሳያማርጥ ይኖራል፡፡ ብዙም ደስተኛ ሳይሆን ማለት ነው›› በማለት ያለውን ችግር በአጭር መንገድ ተናገረች፡፡ የመሠረተችውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ስትገልጽም፡- ‹‹1. ገበሬው እና ነጋዴው (ገበያተኛው) በአካል ተገኝተውም ሳይገናኙም 2. ጥራቱን ለማረጋገጥ ምርቱን ሳይመለከቱ 3. ረጅም መንገድ ምርቱ ተጓጉዞ 4. እስከ 18 ወራት በመጋዘን ተቀምጦ፣ 5. ገንዘባቸው ሽያጩ በተካሄደ 24 ሰዓት ውስጥ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ነው›› ብላ ገልፃለች፡፡

ገበያ መኖር የአንድን ነጋዴ ምርታማነት ያሳድገዋል ብላ የምትከራከረው ዶ/ር እሌኒ የፈለገው ምርታማነትን የሚያሳድጉ ኢንቨስትመንቶችን ብናደርግ ለወጣው ወጭ የሚክስ ትርፍና ትርፉንም የሚፈጥር ገበያ እስከሌለ ድረስ የትም መድረስ አይቻልም ብላ ተከራከራለች፡፡ ዶ/ር እሌኒ ‹‹Transforming the Ethiopian Economy by Becoming a Global Commodity Market of Choice›› የሚለውን ትልቅ ራዕይ በመሠነቅ ነበር ‹‹ECX›› በመባል የሚጠራውን የግብይት ስርዓት የገነባችው፡፡ ለመሆኑ ኢሲኤክስ እንዴት ነበር ይህን ማሳካት የቻለው?

እንደ ዶክተር እሌኒ ገለፃም ኢሲኤክስ አራት ዋና ዋና ሚናዎችን መጫወት እንዲችል ተደርጎ ነው የተገነባው፡፡ የመጀመሪያው ነገር ምርት ገበያው የሚሸጡ ምርቶችን የጥራትና ብዛት ደረጃ ይወስናል፤ማረጋገጫ ይሠጣል፡፡ በአምራቹ ስምም በመጋዘኑ እንዲቀመጥ ያደርጋል፡፡ ይህ በተለይ የምርቱን ገዥዎችና ላኪዎች የጥራት ችግር ይፈታላቸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለአምራች ገበሬዎች ከገዥዎች በፍጥነት (በ24 ሰዓት ውስጥ) ክፍያቸው እጃቸው ላይ እንዲደርሰ የሚያስችል የገንዘብ ማስተላለፍ ሂደትን ይሠራል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ካሁን ቀደም አምራቾችና ሌሎች ሻጭ ነጋዴዎች ምርታቸውን ሸጠው ክፍያቸው ግን በፈለጉት ጊዜ ውስጥ አይከናወንም ነበር፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ገዥና ሻጭ ፊት ለፊት ተገናኝቶና ተደራድሮ የሚገበያይበትን መድረክ ይፈጥራል፡፡ በፊት ሻጭና ገዥ ፊት ለፊት የማይገናኙበት እንደውም በመሃከል የተለያዩ ደላሎች የነበሩበት ነበር፡፡ አሁን ይህን ነባር ቢሮክራሲያዊ አሠራር ይፈታል፡፡ በመጨረሻ ለአምራቾችና ሻጮች በወቅቱ የምርት ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ወቅታዊ መረጃዎች በየክልሉና መንደሩ በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እንዲሠራጩ በማድረግ ሻጮች በመረጃ ላይ የተንተራሠ ውሳኔ እንዲተገብሩ ያስችላል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የዶ/ር እሌኒን ራዕይ ማሳካት የሚችለው ልዩ ፈጠራ፡፡

በ2007 በድጋሚ ቴድ ተብሎ በሚታወቀው ፕሮግራም ላይ ተጋብዛ ባደረገችው ንግግር፣ ያሰበችውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ አድርጋ፣ ሥራውን ብቃት ወዳላቸው ባለሞያዎች አስተላልፋ አዲስ ሕልም ይዛ እንደቀረበች ተናግራለች፡፡ አዲሱ ዕቅዷ አንድ ቢሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ በምርት ገበያ ሂደት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሆነና ገበሬው ገና ከቤቱ ሲወጣ በእጁ ላይ ስላለው ምርት ጥራትና ወቅታዊ የገበያ ዋጋ በቂ ዕውቀት ኖሮት በአቅራቢያው እንዲሸጥ እና የጥሩ ትርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይሄንንም መረጃ እንዳደጉት ሀገራት የግድ በኮምፒዩተርና በኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን፣ በቀላሉ በሚያገኛቸው ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የየቀኑን የገበያ መረጃ ማድረስ ነው፡፡ ይህም ሬዲዮንን፣ ቴሌቭዥንን፣ የሞባይል ስልክና በአቅራቢያው በሚገኙ መጋዘን ቦርዶች ላይ በመረጃ መደገፍ ነው፡፡

ከየትኛውም ዓለም አፍሪካ ትልቅ የእህል አምራች መሆን እየቻለች፣ ተረጂ ሆና በችግር የምትኖር አህጉር ናት፡፡ የአፍሪካ 7% ብቻ የሚሆነው መሬት በመስኖ እየለማ ሲሆን፣ በኢስያ ግን 40 ከመቶ በላይ የሚሆነው የእርሻ መሬት በመስኖ ይለማል፡፡ በኢሲያ 6 እጥፍ ከአፍሪካ በላይ መንገዶች ሲገኙ፣ በደቡብ አሜሪካም 8 እጥፍ ከአፍሪካ በላይ የእርሻ ትራክተሮች ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ‹‹ለውጥ እያመጣን ነው!›› ትላለች ዶ/ር ዕሌኒ፡፡ ገበያዎች በራሳቸው እንደማይከሰቱ አፍሪካ እየተረዳች ነው የምትለው ዶ/ር ዕሌኒ፣ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እንደቀረፀችው ዓይነት የምርት ገበያ ድርጅት፣ በአራት የአፍሪካ ሀገሮች ከጊዜውና ከየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚሄድ መልኩ ቀርፃ እየሠራች ትገኛለች፡፡ በምዕራብ አፍሪካ ለጋና እና ካሜሮን፣ በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ በኬንያ እና ታንዛኒያ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡

‹‹መልካም ገበያ መመሥረት ማለት፣ ምርትን በጥሩ ዋጋ መሸጥ ማለት ብቻ አይደለም፤ በጥሩ መሠረተ ልማቶች ላይ መዋለ ነዋያችንን ማፍሰስ ማለት ነው፡፡ ያ ከሆነ ገበያው በብዙ የፈጠራ ሐሳቦች የተሞላ መልካም ምርትና ትርፍ የሞላበት ይሆናል፡፡›› ትላለች ዶ/ር ዕሌኒ፡፡

በቅርቡ በሰይፉ ሾው ላይ ቀርባ በሰጠችው ቃለመጠይቅ፣ በስተመጨረሻ የምታስተላልፊው መልዕክት ካለ ተብላ ተጠይቃ ነበር፤ መልሷም ‹‹ሕልማችሁን ምንጊዜም ቢሆን አጥብቃችሁ ያዙ! እኔ ገና በ15 ዓመቴ ኬንያ አዳሪ ትምህርት ቤት እያለሁ፣ አድጌ ኢኮኖሚክስ ተምሬ፣ ዶክትሬቴን ይዤ፣ የአፍሪካን ችግር እቀርፋለሁ ብዬ ሕልሜን ጽፌ ነበር፡፡ ያን ህልም ነው እንግዲህ ዛሬ በመኖር ላይ የምገኘው›› ብላለች፡፡

 

የስኬቷ ምሥጢሮች

1. የፈጠራ ችሎታ፡- ዶ/ር ዕሌኒ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ስትመሠረት በአሜሪካ ወይም ከሌሎች ያደጉ ሀገሮች ያለውን የድርጅት አሠራር ቀጥታ አምጥታ ሳይሆን፣ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚሆነውን አሠራር በመቅረጽ ስኬታማ ለመሆን በቅታለች፡፡ በአሁኑ ሰዓትም “ELENY LLC” በሚባል ድርጅቷ፣ በተለያዩ ሀገራት እየሠራች ያለችው ብዙ የፈጠራ ችሎታዋን ተጠቅማ ነው፡፡

2. በለውጥ ማመን፡- ነገሮች እንደሚቀየሩ ማመን፤ ወደ 200 ዓመታት የቆየው የአሜሪካዎቹ የምርት ገበያ ድርጅት፣ እጅግ የተደራጀ ጠንካራና ግንባር ቀደም ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት የቻይና የምርት ገበያ ድርጅት እየበለጠው ይገኛል፡፡ የህንድ የምርት ገበያ ይከተለዋል፡፡ የአፍሪካም ቢሆን ከጥቂት ዓመታት ቀዳሚ እንደሚሆን፣ ነገሮችም ጠንክረን ከሠራን እንደሚቀየሩ እርግጥ ነው፡፡

3. በተስፋ የተመላ አመለካከት፡- ዶ/ር ዕሌኒ የምትሠራባቸው ቦታዎች በብዙዎች ሲታዩና ታሪካቸውም ሲቃኝ ብዙም ስኬታማ የሚሆኑ አይመስሉም፡፡ ነገር ግን ተስፋ በሞላበት አመለካከቷ እየተነሣች ጠንክራ በመሥራት ነገሮችን ከስኬት ደረጃ አድርሳቸዋለች፡፡ ብዙ የሚገድቡን የሚመስሉ አልያም የሚጎሉን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሙሉ አቅምና ሐሳባችንን በችግራችን ላይ ሳይሆን በመፍትሔዎች ላይ በማድረግ ስኬታማ መሆን እንችላለን፡፡ በራስ ሙሉ በሙሉ መተማመን፣ የራስን ታሪክ ከየት ተነስቼ የት ደረስኩ የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አይተናል፡፡

4. ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ፡- አስተሳሰባችን በአሁኑ ሰዓት በአንድ ከተማ ወይም ሀገር ላይ ታምቆ የሚቀር መሆን የለበትም፡፡ ዓለምአቀፍና ከጊዜው ጋር የሚራመድ መሆን አለበት፡፡ የምናልማቸውንም ነገሮች ትልቅ ልናደርጋቸው ይገባል፡፡ ዶ/ር ዕሌኒ ድንበር የለሽ ነች፡፡

5. ጠንክሮ ምሥራት፡- ሰው ጠንክሮ ከሠራ የልፋቱን ዋጋ እንደሚያገኝ ግልጽ ነው፡፡ በሥራው ውስጥም ጠንክሮ በዕውቀት እና በዘዴዎች የተሞላ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

6. ማዕከላዊ ክፍሉ ላይ አጥቃ፡- ሁሌም ችግሮችን ስንፈታ ምልክቶችን ብቻ የምናክም ከሆነ የትም አንደርስም፡፡ እሌኒ ይህን መሠል ችግር አፈታት ‹‹vicious cycle›› ትለዋለች፡፡ መልሶ ችግሩ ከተነሳበት የሚጥል፤ ወንዝ የማያሻግር መፍትሄ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ የችግሩ ዋና አከርካሪ መመታት አለበት፡፡ ይህ እንግዲህ ‹‹Centre of gravity›› የሚባለው ነው፡፡ የችግሮችን አከርካሪ በመለየት እሡ ላይ በትሩን ማሳረፍ፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ መሠረቱ ግብርና ነው፡፡ የአከርካሪው መሠረት ደግሞ ገበሬው ነው፡፡ የገበሬውም ምርታማነት የሚወሠነው በገበያ ነው፡፡ ትልቁ ችግርም ማምረት ሳይሆን ገበያ መፍጠሩ እንደሆነ የገባት፡፡ ለዚያም ነው ለዶ/ር እሌኒ ‹‹Market maker›› (ገበያ ፈጣሪዋ) የሚል ቅጥል ስም የተሠጣት፡፡

7. ሠፊና ትልቅ ራዕይ ሠንቅ፡- ሠፊና ትልቅ ስራ እንድንሠራ ያስችለናል፡፡ ራዕዩ ሁሉ ራዕይ አይደለም፡፡ እንደ ዶ/ር እሌኒ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ከድህነት ሊያወጣ የሚችል ሠፊ ራዕይ፡፡ የሚተገበር፤ የሚለካ ራዕይ ምን ያህል ሃይል እንዳለው እናያለን፡፡ ሩቅ ማሰብ ወደበለጠ ስኬት እንጂ አብዛኞች እንደሚፈሩት ወደ ውድቅት አይመራም፡፡ ‹‹ዓላማን በፍቅር መውደድ እና ለዓላማ አለመደራደር!›› የስኬት መሠረት ነው ብላ ታምናለች፡፡ ከዶ/ር ዕሌኒ ሕይወት የምናየው በራዕይ የታገዘ የእኔነት ስሜቷ፣ ከሀገሯ አልፎ ለአህጉሯ እንድትፈለግ አስገድዷታል፡፡

8. የቴክኖሎጂ ሽግግርን ተግብር፡- ለስኬት ትልቅ ቦታ አለው፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር፡፡ ነገሮች እንዴት በተሻለ መልኩ እንደሚሠሩ ከሌሎች ልምድ በመውሰድ ጥበቡን ለራስ አዙሮ መጠቀም የስኬታማዎች ቁልፍ ስልት ነው፡፡ የቺካጎው የምርት ገበያ ተሞክሮ ለዶ/ር እሌኒ እንደመነሻ ተወስዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዶ/ር እሌኒ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለምታካሂዳቸው የምርት ገበያ ማዕከላት ግንባታዎች ደግሞ ውጤታማው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ትልቅ ሚናን ተጫውቷል፡፡ ይህ ነው የቴክኖሎጂ ሽግግር ጥበብ፡፡

9. በምርጥ ት/ቤት እለፍ፤ ምርጥ ልምድህንም ተጠቀም፡- ጥራት ያለውን ትምህርት ዘልቆ መማር ብዙ በሮችን ይከፍታል፡፡ ብዙ ዓለማቀፍ ዕድሎችንም እንድንሣተፍ ይረዳናል፡፡ በሕይወታችንም የሚታይ ለውጥ ያመጣል፡፡ በዓለም ላይ በስመ ጥር ተግባራዊ ትምህርት ተቋምነቱ የላቀ ቦታ የሚሠጠውና በየዓመቱ ጥቂቶችን ብቻ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈለ የሚያስተምረው ሳታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ተቋማት የገነቡ ምሩቃኖችን ያፈራ ነው፡፡ ዶ/ር እሌኒም በዚህ ስመ ጥር ተቋም ያለፈች መሆኗም ለዛሬው ውጤታማነቷ ሚና ተጫውቷል ብለን እናስባለንና ወላጆች ለልጆቻችው ምርጥ ትምህርት በሚቀስሙባቸው ቦታዎች በኩል እንዲያልፉ ማድረግን ከእሷ እንማራለን፡፡ ዶ/ር ዕሌኒ ከትምህርቷም ባሻገር 20 ዓመታትን በሥራ ላይና 10 ዓመታትን በአጠቃላይ 30 ዓመታት፣ ያካበተችውን ልምድ ይዛ ነው ለውጥ የሚያመጣ ሥራ ሀገሯ ላይ ለመሥራት የበቃችው፡፡

10. ገበያ የምርታማነት መሠረት መሆኑን ተረዳ፡- ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ መፈጠር ትልቁ አስተሳሠብ ያለው ምርታማነት ከኋላ ሳይሆን ከፊት የሚመጣ ውጤት መሆኑን ነው፡፡ በአንድ ወቅት ገበሬው ብዙ በቆሎ አመረተ የምትለው ዶ/ር እሌኒ የገበያ ዋጋ ግን በእጅጉ ወረደ፤ በኩንታልም እስከ 25 ብር ተሸጠ፡፡ ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ዓመት የበቆሎ ምርት ዝቅተኛ ሆነ በማለት ገበያ ከሌለ ምን ያህል የገበሬው ምርታማነት እንደሚቀንስ ታስረዳለች፡፡ የገበሬውን ምርታማነት የሚጨምረው የማዳበሪያና ማሸነሪዎች ባለቤትነት ብቻ ሳይሆን በዋናነት ሠፊ ገበያ መኖር ነው ትላለች፡፡ ይህ እንግዲህ ለብዙ ነጋዴዎችም አብይ ትምህርት ሊቀስሙበት የሚገባ ፍልስፍና ይመስላል፡፡ መልካም ስኬት እየተመኘሁ እኔም በዚሁ አበቃሁ፤ ሠላም!                                                                                                                                    

  ምንጭ፡- ከስኬት ሚስጥሮች መጽኀፍ የተወሰደ