Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ሀገር በቀል እውቀት

 

 

Ethiopian Traditional Knowledge

 

 

ሀገር በቀል እውቀት ማለት በውስን አካባቢዎች ላይ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ገፅታዎች ዙሪያ ላሉ ክፍተቶች መፍትሄ ይሆኑ ዘንድ ባህላዊ በሆነ መንገድ በአንድ ወይም በተወሰኑ ሰዎች የሚመነጭና የሚተገበር እውቀት ነው፡፡ በእንግሊዘኛዉ በዋናነት “Indigenous knowledge” የሚለው የሚገልፀው ሲሆን “Traditional knowledge“ ወይም “Local knowledge” የሚሉትም ሊተኩት ይችላሉ፡፡ የማህበረሰብ እውቀት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ የህይወት ገፅታዎች የሚዳሰሱበትና መፍትሄ የሚሰጥበት የተገለፀና ያልተገለፀ እውቀትና ልምድን ያጠቃለለ ነው፡፡ በብዙ ዘመናት ልምድ የዳበረና በባህል ውስጥ ሰርፆ ከትውልድ ትውልድ በታሪክ፣ በዘፈን፣ በአባባል፣ በእምነት እና በሌሎች መንገዶች በአካባቢው ቋንቋ የሚተላለፍ እውቀት ነው፡፡ እውቀቶቹ በተገኙበት ቦታ ምንጭ ለሆኑት ግለሰብና ቤተሰብ የተሰጠ ልዩ ጥበብ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን በአብዛኛው ግን በጊዜ ሂደት በአካባቢው ማህበረሰብ እየተለመደና እየሰፋ ሲመጣ የማህበረሰቡ የጋራ ንብረት ይሆናል፡፡ እንደ ሀገራችን ባሉ በተፈጥሮ ሀብት በበለፀጉ ሀገራት በተለይ በግብርና፣ በጤና እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች የሀገር በቀል እውቀቶች እና ቴክኖሎጂዎች ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም በትራንስፖርት ዘርፉ የሀገር በቀል እውቀቶች እና ቴክኖሎጂዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ በግብርናው ዘርፍ የእፅዋትና አዝርእት ተከላ፣ መረጣና አሰባሰብ ሂደት፣ በእንስሳት እርባታና አያያዝ ስርዓት እና ለመሳሰሉት ተግባራት መሠረት የሚሆን በግለሰብና በማህብረሰብ ውስጥየዳበሩብዙእውቀቶች አሉ፡፡

 

Ethiopian Coffee

 

በጤናው ዘርፍ አብዛኞቹ ዘመናዊ መድሃኒቶች፣ የመዋቢያ ወይም የኮስሞቲክስ ምርቶች እንዲሁም የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲሁም የውሃ ማጣራት ዘዴዎች መሠረታቸው የማህበረሰብ እውቀት ነው፡፡ ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ የባዮቴክኖሎጂ፣ ፋርማሲውቲካል እና የህክምና ኢንዱስትሪዎች ሀገር በቀል እወቀቶች ላይ ያላቸው ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሄዷል፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሀገር በቀል እውቀቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገትን በመምራት ረገድ ያላቸውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ነው፡፡ ሀገር በቀል እውቀቶች፤ ስነ-ምህዳር እንዴት እንደሚሰራና እንደሚደጋገፍ ለመረዳት በሰፊው ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን በተለይ ዘላቂ እድገትና ልማት ከማምጣት አንፃር በብዝሀ-ህይወትና ስነ- ምህዳር አጠባበቅና አጠቃቀም ላይ ብዙ እውቀቶችና ልምዶች ካብተዋል፡፡ እነዚህ እውቀቶች ለዘመናዊ ኢኮኖሚ እና ለምርምርና ስርፀት የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት በ2001 ባወጣው ሪፖርት ከባህላዊ መድሃኒት ብቻ በአመት አውስትራሊያ 1 ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር፣ ቻይና 2.3 ቢሊዮን ዶላር፣ ጃፓን 1.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ 543.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ማሌዢያ 2 ቢሊዮን የማልዢያ ገንዘብ/ብር፣ ፊሊፒን 10 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሲንጋፖር 13 ሚሊዮን የሲንጋፖር ገንዘብ/ብር እንደሚያገኙ አስታውቋል፡፡ በአህጉራችን አፍሪካ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የደቡብ አፍሪካው ሳን ጎሳ ‹ሁዲያ› የተባለውን ተክል የባለቤትነት መብት ለእንግሊዝ ኩባንያ በሀያ ሚሊዮን ዶላር የሸጠ ሲሆን ሀገሪቷ ከዚህ ባህላዊ መድሃኒት ሽያጭ በአመት ሀያ ዘጠኝ ቢሊዮን ራንድ ታገኛለች፡ ፡ በሌላ በኩል ዴቭልስ ክላው ከተባለው ተክል የሚገኘውና ህመምን ለመቀነስ የሚያስችለው ባህላዊ መድሃኒት ለናሚቢያ በአመት ሁለት ሚሊዮን ዶላር ያስገኝላታል፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ እና ከካሜሮን በ1994 ወደ ጀርመን የገባው ‹ፕሩኑስ አፍሪካና› (ጥቁር እንጨት) ከተባለው ተክል የሚመረተው የህክምና መድሃኒትና ምርቶች በአለም ደረጃ በአመት 220 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለአምራቾቹ ኩባንያዎች ያስገኛሉ፡፡

 

Ethiopia Traditional

 

ዘመናዊ ምርምሩን በመምራትና በመደገፍ ለእነዚህ መድሃኒቶችና ምርቶች መገኛ መሰረት የሆኑት በየሃገራቱ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶች ናቸው፡፡ ከማህበረሰቡ አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ ለዘመናዊ ኢንዱስትሪ ያላቸው ሚና ጉልህ በመሆኑ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው ፍላጎት የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃን ጨምሮ የተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮችን ማስነሳት ከጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ ሀገራችን የረጅም አመታት ታሪክ ባለቤት፣ የልዩ ልዩ ስነ-ምህዳር እና የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሀገር ስትሆን ይህም የተለያዩ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽሀብቶች፣ባህሎችእናተያያዥሀገርበቀልእውቀቶችናቴክኖሎጂዎች ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ጤፍ፣ ቡና፣ እንሰት እና ሌሎች አዝርእትን የማላመድ እንዲሁም ከነዚህና ሌሎች ተክሎች ምግብና መጠጥ የማዘጋጀት ሂደት በሌሎች ሀገራት ያልተለመደና በሌሎች ዘንድ የማይታወቅ የማህበረሰባችን የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ በአለም ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለረጅም አመታት የእርሻ ስራቸውን በእጅ በሚሰሩ መሳሪያዎች በሚጠቀሙበት ጊዜ የእኛ ማህበረሰብ የፈጠራ ክህሎት የታከለበትን ባህላዊውን የአስተራረስ ዘዴ ማለትም በበሬ (ወይም በሌሎች የጋማ ከብቶች) ጠምዶ የእርሻ ስራውን ያከናውን ነበር፡፡ በተመሳሳይ የኮንሶና አካባቢው ህብረተሰብ ትሩፋት የሆነው የእርከን ስራ ችግር ፈቺ እና ውጤታማ የሆነየሀገር በቀል የአፈርና የውሀ ጥበቃ ዘዴ ነው፡፡ እነዚህ ተግባራት የማህበረሰባችንን የፈጠራ ችሎታ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዘመናዊ ህክምና ባልተስፋፋባቸው ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሆነ ዘመናዊ ህክምና እየተስፋፋበት በመጣበት በአሁኑ ሰዓት የማህበረሰባችን ባህላዊ ህክምና እና መድሃኒቶችን የመጠቀም ዝንባሌው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ባህላዊ ህክምና እና መድሃኒቶችበአቅራቢያ ስለሚገኙ፣ የገንዘብ አቅምን የማይፈትኑ እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታመንባቸውና በተግባርም ፈዋሾች መሆናቸው ነው፡፡

 

 ከዚህ ጋር ተያይዞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የህክምና ተክሎችን በቤት ውስጥ የአትክልት ቦታ የመትከል ዝንባሌ አለው፡፡ የእንዶድ ቅጠል ለቢላሃርዝያ በሽታ መዳሃኒት መሆኑ በዶ/ር አክልሉ ለማ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከመተዋወቁ በፊት ብዙ የማህበረሰባችን ክፍል ባህላዊ በሆነ መንገድ ሲጠቀምበት መቆየቱ ሀገር በቀል እውቀቶች ለሳይንሳዊ ስራዎች መሠረት ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ በተጨማሪ ዘመናዊ የእንስሳት ህክምና ተደራሽ ባልሆነበት ዘመን አብዛኛው የአገሪቱ የከብት ባለቤት ባህላዊ ሀኪሞችና ቀማሚዎች ከሚሰጡትአገልግሎትተጠቃሚሲሆን ቆይቷል፤ አሁንምየሚጠቀምበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ከዘመናዊው የህክምና እና የመድሃኒት እውቀቶች በተጨማሪ ሀገር በቀልና ባህላዊ እውቀቶችን የያዙ ብዙ መቶ አመታትን ያስቆጠሩ መፃህፍት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በስነ- ህንፃ ዘርፍ በተለይ ከአክሱም ዘመነ-መንግስት ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የታዩት የተለያዩ ሀውልቶች፣ ውቅር አብያተ- ክርስትያናት፣ ቤተ-መንግስቶች፣ የግንብ ስራዎች እንዲሁም ሌሎች ስነ- ህንፃ ስራዎች በማህብረሰቡ ውስጥ ታምቆ የነበረውን የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችሎታ አመላካች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሀገር በቀል እውቀቶቹና ቴክኖሎጂዎች ባለቤቶችና አዋቂዎች እውቀቱን መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታት፤ ለንግድ አላማ ለሚውሉ የሀገር በቀል እውቀትና ምርቶች ከለላ መስጠት፤ እንዲሁም የሀገር በቀል እውቀቶችን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሀገር በቀል እውቀት ባለቤቶችና አዋቂዎች እና በተመራማሪዎች መካከል የጋራ ጥቅም የሚያስገኝ ትስስር እንዲፈጠር ማድረግና ትስስሩን መደገፍ አለባቸው፡፡ ስለሆነም ሀገር በቀል እውቀቶችን/ቴክኖሎጂዎችን ለመጠበቅና ለመጠቀም ይቻል ዘንድ ለእውቀቶቹና ቴክኖሎጂዎቹ ከለላ ለመስጠት፣ ለመመዝገብና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል እንዲሁም የእውቀቱ ባለቤቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ መቅረፅ፤ የእውቀቱ ባለቤቶች መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸውን እንዲያውቁ የግንዛቤ ማዳበሪያ ስራዎችን መስራት፤ ማህበረሰቡ የፈጠራ ክህሎቱን ለልማት ለማዋል ያስችለው ዘንድ ድጋፍ ማድረግ፤ እንዲሁም የእውቀቱና የቴክኖሎጂው ባለቤት በሆኑት ግለሰቦችና ማህበረሰቦች መካከል የልምድ ልውውጥ እና የንግድ ትስስር እንዲኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡

 

ምንጭ፡  ሳይንስ ቴክ ቅጽ 2፣ 2007