Biography Catagories

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ሰዒድ መሀመድ ብርሃን

 

ትግራይ ክልል ሽሬ አውራጃ በ1954 ዓ/ም ሲወለዱ ለወላጆቻቸው ሁለተኛውና የመጨረሻው ልጅ ሆኑ፡፡ በግብርና የሚተዳደሩት እናትና አባት ሁለት ወንድ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከህይወት ጋር ትግል መግጠም ግዳቸው ነበር፡፡ አቶ ሰዒድ ያኔ የስልጣኔ ንፋስ ሽው ባላለበት ሽሬ ሲኖሩ መደበኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል የ45 ደቂቃ መንገድ በእግራቸው መጓዝ ግድ ይላቸው ነበር፡፡ የ14 ዓመት ታዳጊ ሳሉ በ1968 ዓ.ም አባታቸው ከሰሊጥ እርሻቸው 600 ብር ማግኘት ቻሉ፡፡

 

እኒህ ሰው ልጆቻቸው እንደርሳቸው ገበሬ ሆነው እንዲቀሩ ፈጽሞ አይፈልጉም ነበርና በዚህች ለፍተው ባገኟት ገንዘብ ለመጀመሪያ ልጃቸው የልብስ ስፌት ሱቅ ከፈቱለት፡፡ ሰዓድም ከወንድማቸው ጋር እዚያች ሱቅ የሚውሉበት ዕድል ተፈጠረ፡፡ያኔ ታዲያ ጥብቆ መቀምቀም፤ ገምባሌ መስፋት፤ ቁምጣ መስራት ጀመሩ፤ ከወንድማቸው ጋር፡፡

ይህ ወቅት ለሽሬ አውራጃ ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ አንዴ በህወሃት እጅ፤ አንዴ በደርግ እጅ፤ አንዴ በኢዲዩ እጅ ትወድቅ የነበረችው ሽሬ ተረጋግታ የነዋሪዎቿንም ህይወት ልታረጋጋ አልቻለችም፡፡ ለአምስት ዓመታት ብቻ ከሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ጋር ህይወትን ሲታገሱ የቆዩት አቶ ሰዒድ የወንድማቸውን ወደ መቀሌ መጓዝ ተከትለው 1973 ዓ/ም ሽሬን ለቀቁ፡ ያኔ በእጃቸው የነበረችው 200 ብር ብቻ ነበረች፡፡

 

መቀሌ እንዳሰቡት ስራ የሚያገኙበት ቦታ አልሆነም፡፡ ጥቂት ጊዜ ቆዩና ከመቀሌ 12 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ኩኻ ከተማ አቀኑ፡፡ እዚያ የተሻለ ዕድል አገኙ፡፡ የገቡት አቶ ሰዒድ ብላታ ኢብራሂም መሸሻ ከተባሉ ሰው ጋር ተገናኙ፡፡ “ስራ የለም እንጂ የልብስ ስፌት መኪና አለ“ አሏቸው ብላታ ለአቶ ሰዒድ፡፡ እስኪ ልሞክረው አሉና ከልብስ ስፌት ማሽኑ ኋላ ተቀመጡ፡፡ ቀስ በቀስ እያለ ስራው መምጣት ጀመረ፡፡ በአብዛኛው የወታደሮችን ዩኒፎርም በማጥበብና አንዳንድ ጥቃቅን ስራዎችን በመስራት 11 ወራት ያህል ኩኻ ከተማ ውስጥ አሳለፉ፡፡እኚህ ሰው ብርቱ ዓላማ ነበራቸውና በነዚህ ወራት ምግባቸውን ችለው ለባለስፌት መኪናውም የሚገባቸውን ከፍለው 3 ሺህ ብር ማጠራቀም ቻሉ፡፡ያቺን 3 ሺህ ብር ይዘውም የተሻለ ነገር ለመስራት ወደ መቀሌ ተመለሱ፡፡ የዛሬው የልብስ ስፌት ኢንዱስትሪያቸው መሰረት የተጣለውም በዚሁ ጊዜ ሆኑ 1974 ዓ/ም፡፡ ኒክ በሚል ስም የሚታወቅ እንግሊዝ ሰራሽ የልብስ ስፌት ማሽን ገዙ፡፡ ለዚህ ግዢ፤ 1 ሺህ ብር አውጥተዋል፡፡ ማሽናቸውን ይዘው ቤት መፈለግ ጀመሩ፡፡ ከብዙ ልፋት በኋላ አንድ የቀበሌ ቤት አገኙ፡፡ የዚህን ቤት ቁልፍ ከሰው ላይ በ2 ሺህ 500 ብር ሊገዙ ተዋዋሉ፡፡ አሁን ከልብስ መስፊያ በተጨማሪ ቤት ተገኘ፡፡

 

ከ3 ሺህ ብሩ እጃቸው ላይ የቀረው 2000 ብር ብቻ ስለነበር 250 ብር ከየት ያምጡ? ሲፈሩ ሲቸሩ አንዲት ሱቅ የነበራቸው የሩቅ ዘመዳቸውን ብድር ጠየቁ፡፡ አልከለከሏቸውም፡፡ አቶ ሰዒድ የቤት ባለቤት ሆኑ፡፡ የልብስ ስፌት ስራን ያለምንም ካፒታል በ 250 ብር እዳ ጀመሩ፡፡

 

የ19 ዓመቱ ሰዒድ መቀሌል የእድላቸው፤ በር መክፈቻ ነበር ያደረጓት፡፡ ወትሮም ተቀጠሮ ከመስራት የራሳቸው የሆነ ነገር ባለቤት መሆን ይመኙ ነበርና ብዙም የቤት ኪራይ ሳይኖርባቸው በአንዲት ማሽናቸው በአብዛኛው የወታደሮችን አለፍ ሲልም የአካባቢውን ነዋሪ ልብስ እየጠቀሙ ገቢ ማግኘት ጀመሩ፡፡ ሳይነሰለቹ ሰሩ፡፡ መቀሌ መጀመሪያ ሲረግጧት “ስራ የለም ብላ ብታባርራቸውም ገንዘብ ይዘው መጥተው ልስራብሽ ሲሏት ግን አላሳፈረቻቸውም፡፡ ጥሪት መቋጠር ጀመሩ፡፡ ትህትናቸውንና ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ብዙዎችን ወደ እነኚህ ልብስ ሰፊ ይስባቸው ጀመር፡፡ የልብስ ስፌት ቤታቸውን ከአንድ ወደ ሁለት አሳደጉ፡፡

 ናሽናል ልብስ ስፌትና አሁንም ድረስ አጎታቸው ስያሜውን ወስደው የሚሰሩበት መርካቶ ልብስ ስፌት ቤት የወጣቱ ሰዒድ መንትያ ሱቆች ሆነ፡፡ ቀስ በቀስም አንዲት የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ መለስተኛ ቡቲክ ከፈቱ፡፡ ያኔ ተፈላጊ የነበሩትን እንደ ጅንስና ሌሎች አልባሳትን መሸጥም ጀመሩ፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የጥረታቸውን ፍሬ ማየት ቻሉ፡፡ ቀንና ሌሊት ሳይሰለቹ ሰሩ፡፡ አዲስ አበባ ድረስ የዘለቀ የንግድ ግንኙነት መፍጠር ቻሉ፡፡

አልፎ አልፎ ብትን ጨርቅ ከመርካቶ ነጋዴዎች ላይ ያስገዙና በጥበባቸው ልብስ ሰፍተው ይሸጡም ጀመር፡፡ የሚያሳድጋቸው ጥረታቸው ብቻ ሳይሆን በጥረታቸው የሚያገኟትን ጥቂት ገንዘብም ቆጥቦ ማሰቀመጥ መሆኑን የወጣት ልባቸው መገንዘብ አላዳገተውም፡፡ በመቀሌ ባንክ ውስጥ 130 ሺህ ብር ማጠራቀም ቻሉ፡፡ 200 ብር ይዘው ከትውልድ ቀያቸው የወጡት ሰው፤ የ250 ብር ዕዳ ይዘው የመቀሌን ህይወት አሃዱ ያሉት ግለሰብ፤ በያኔው ጥሪ ከፍተኛ የተባለውን ብር አጠራቀሙ፡፡ አሁን ምኞታቸውም ከፍ አለ፡፡ የጭነት መኪና ከነተሳቢው መግዛት ተመኙ፡፡

 

 ምናልባትም ቀድመዋቸው የወጡት ታላቅ ወንድማቸው ሹፌር ሆነው መስራታቸውም ይሆናል ይህን አዲስ ቢዝነስ ያሳሰባቸው፡፡ ለማንኛውም ከባንክ በመበደር እና የዕቁብ ብር በመጨማመር የተመኙትን ባለተሳቢ የጭነት መኪና ገዙ፡፡ በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳሉ የከባድ መኪና ባለቤት የሆኑት እኚህ ሰው ያኔ ሁሉንም አስገረሙ፡፡ይህ ስኬት ግን በዚሁ ፍጥነት መቀጠል አልቻለም፡፡አዲሱ የስራ መስክ የአቶ ሰዒድን የባንክ ብር ጠቅልሎ የያዘ ብቻ ሳይሆን በባንክ ዕዳም የሚንቀሳቀስ ነበር፡፡ሰውየው ከዚህ መኪና ጠቀም ያለ ትርፍ ይጠብቃሉ፡፡ ነገሩ ግን እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ መኪናው ብዙ ሳያገለግል ተገለበጠ፡፡ የአቶ ሰዒድ የስኬት ጉዞም ከመኪናው መገልበጥ ጋር አብሮ ቀጥ አለ፡፡ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ ከ 1974 እስከ 1981 ዓ/ም ለሰባት ዓመታት ያህል የለፉበት ጥሪት ሁሉ ገደል ገባ፡፡ መኪናው ለ8 ወራት ያህል ጋራዥ ውስጥ ለእድሳት በቆመበት ጊዜ ዕዳውን ለመክፈል ያላቸውን ሁሉ መሸጥ ግድ ሆነባቸው፡፡

ልብስ ስፌት ቤቶቻቸውን ሁሉ ዘጋጉ፡፡ ሱቃቸውንም እንዲሁ፡፡ የመኪናውን እዳ የቀደመውን የገቢ ምንጫቸው የሆነውም ስራ በመሸጥ ከፋፈሉ፡፡ እንደርሳቸው አባባል  “ሱቅ እና መኪና እርስ በእርሱ ተብላላ”፡፡ ለሰባት ዓመት በስኬት የቆዩባትን መቀሌን ሲለቁ፤ በእጃቸው የቀረበው 21 ሺህ ብር እና አራት የልብስ ስፌት መኪና ነበር፡፡ ያ ዘመን የደርግ ሰራዊት ከመቀሌ የለቀቀበት ወቅት አካባቢ በመሆኑ ከተማዋ ላይ የኑሮአቸው መሰረት የነበሩት የመንግስት ሰራተኞች ወደየመጡበት የተመለሱበት ጊዜ ነበር፡፡ የመቀሌ እንቅስቃሱ ተዳከመ፡፡ መብራት ጠፋ፡፡ ህይወት ትግል ሆነ፡፡ አቶ ሰዒድም ከኪሳራቸው ጋር ተዳምሮ መቀሌ ላይ ዳግም የሚያንሰራሩ አልመስልህ አላቸው፡፡ ወደ አዲስ አበባ አቀኑ፡፤

 

መርካቶ ተቀበለቻቸው፡፡ ያኔ የ27 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ በዚህ እፍኝ በማይሞላ ዘመናቸው ስኬትንም ኪሳራንም አይተዋልና ህይወትን ለመታገል አላፈገፈጉም፡፡ አዲስ አበባ ለአቶ ሰዒድ አዲስ አካባቢ፤ አዲስ ሰፈር ናት፡፡ በእጃቸው ያለውን 21 ሺህ ብር ይዘው ለአራቱ የስፌት መኪኖቻቸው ቤት ፈለጉ፡፡ በ8ሺህ ብር መርካቶ አስፋው ወሰን ሆቴል አካባቢ የአንድ ሱቅ ቁልፍ መግዛት ቻሉ፡፡ ቤቱ ጠባብ ስለነበረ ከኋላ ጥቂት ገፋ አድርገው የነበተችው ቦታ ከቤቱ ጋር አቀላቅለው ሰሯት፡፡በዚህች ቤት ቀን ቀን የሚሰፉትን ልብስ ሲተኩስበት ማታ ማታ ደግሞ አንዲት ታጣፊ አልጋ ከጥጥ ፍራሽ ጋር በ80 ብር ገዝተው ያድሩበት ጀመር፡፡ መስሪያ ቤታቸውም፤ ሱቃቸውም፤ ማደሪያቸውም እዚያው ሆኖ እየሰሩ ለአንድ ዓመት ያህል መጸዳጃ  እና መታጠቢያ በሌላት በዚያች ቤት ኖሩ፡፡

 

መቀሌ እያሉ ያውቋቸው የነበሩ የሚሊተሪ ተራ ብትን ጨርቅ ሻጮች ጨርቅ እየሰጧቸው፤ እሳቸውም የቻሉትን ያህል እየሰፉ በዚያች ቤት ውስጥ ዳግም ማንሰራራት ጀመሩ፡፡ አራቱ የስፌት መኪኖቻቸው ላይ ሰው ቀጥረው እየሰሩ ቆዩ፡፡ ይህ ህይወት ግን ከ3 ዓመታት በላይ አልዘለቀም፡፡ አቶ ሰዒድ 1984 ላይ ሁሉም ነገር አስጠላቸው፡፡ ጠብ ከማይል ኑሮ ጋር መታገል ሰለቻቸው፡፡ የስራ ዘርፋቸውን ሊቀይሩ ፈለጉ፡፡ ያጠራቀሙትን ጥቂት ገንዘብ ያዙና ሰፊዎቹን አሰናብተው ቤታቸውን ዘጉ፡፡

 

መሰማራት የፈለጉት በኤሌክትሪክ ዕቃዎች መሸጥ ስራ ላይ ነበር፡፡ ከአንድ ሰው ላይ ሱቁን ተከራዩ፡፡ የኤሌክትሪክ ዕቃ ሻጭ ሆኑ፡፡ለ5 ወራት ያህል ሰራውን አዩት፡፡ ከባድ ነው፡፡ በዚህ ላይ እሳቸው ይህን ዘርፍ ቀድመው አያውቁትም፡፡ ስራ ብዙም ሳይቆይ ቀዘቀዘባቸው፡፡ ከዚህ በላይ መቀጠል ስላልቻሉ ተዉት፡፡ ወደ ቀድሞ ስራቸው ተመለሱ፡፡

 

አቶ ሰዒድ የልብስ ስፌት ስራቸውን በሰፊው ለመያዝና ለማሳደግ ያቀዱት ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ ሲጀምሩት፤ በመሃል ዘንግተው የሌላ ስራ መቋቋሚያ ሲያደርጉት የቆዩበት የልብስ ስፌት ሊለቃቸው አልቻለም፡፡ ራሳቸውን አሳመኑ፡፡ ማደግ ካለባቸው በዚህ ቀዳሚ ስራቸው ነው ማደግ የሚችሉት፡፡ እናም 1990 ዓ/ም የልብስ ስፌቱን በፋብሪካ ደረጃ በማሳደግ ከመርካቶ ወጥተው ዘሪሁን ህንጻ ላይ ቢሮ ተከራዩ፡፡ ትንሹን ስራ ወደ ትልቅ ደረጃ በማዛወር ለመንቀሳቀስ አለመ፡፡

 

የአምባሳደር ልብስ ስፌት ፋብሪካ ጥንስስ የተጀመረውም ይኼኔ ነበር፡፡ ግን ፋብሪካ ለማቋቋምና በዚህ ደረጃ ቢዝነሱን ለመጀመር የሚያስችል ዕውቀት በሀገር ውስጥ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ያላቸው አማራጭ በድፍረት ውጪ ሀገር በመሄድ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎችን መጎብኘት ነበር፡፡ አንድ ባለሙያ ያዙና በተከታታይ ወደ ቻይናና ደቡብ ኮሪያ አመሩ፡፡ አሁን ቢያንስ ይህን ስራ “ይቻላል “ ለማለት የሚያስችል ድፍረት አገኙ፡፡ ገቡበት፡፡

 

 

የአምባሳደር ልብስ ስፌት አዲስ ዘመን እነሆ ባተ፡፡ አቶ ሰዒድ የረር አባባቢ የጃክሮስ መኖሪያ ቤቶች በሚገኝበት ስፍራ በሊዝ 1500 ካ.ሜ ቦታ ወሰዱና የመጀመሪያውን ፋብሪካቸውን ገነቡ፡፡ ከዚያም ከጃፓን ሀገር ብዙ የልብስ ስፌት ማሽኖችን ገዝተው ወደ ሀገር ውስጥ አስገቡ፡፡እነዚህ ማሽኖች በቀን ከ 50-150 ሙሉ ልብሶችን አምርተው ማውጣት የሚያስችሉ ነበሩ፡፡ ከዚያም 80 ሰራተኞች ቀጠሩና ስራ ጀመሩ፡፡ የልብስ ስፌት ባለሙያዎችን በሀገራችን ውስጥ እንደፈለጉ ማግኘት አለመቻላቸው፤ በተፈለገው መንገድ ጥሬ እቃ እና የሰው ሃይል አቅርቦት አለመኖሩና እያንዳንዱን ነገር ከወጪ የሚያስገቡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስራውን መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ አድርጎባቸው ነበር፡፡ቀስ በቀስ ግን እያስፋፉትና ምርቶታቸውንም በየጊዜው እያስተዋወቁ ገበያው ውስጥ መግባት ጀመሩ፡፡ የአምባሳደር ልብስ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲታወቅ የሚያስችላቸውን መሰረት በመጣላቸውም የግዢ ፍላጎት መጨመር ጀመረ፡፡ገበያው በራሱ ጊዜ እየፈጠረ የመጣው ዕድል አቶ ሰዒድ ፋብሪካቸውን እንዲያስፋፉት ምክንያት ሆናቸው፡፡ በ1995 ዓ/ም እዚያው የቀድሞው ፋብሪካ በመገንባት የአሁኑን አምባሳደር ጋርመንት ኤንድ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያን እውን አደረጉት፡፡

 

 በአሁኑ ወቅት በመላው ሃገሪቱ 50 የሚደርሱ የሽያጭ ሱቆችን በመክፈት ሁሉንም ህብረተሰብ ያማከለ ምርት የሚያከፋፍለው አምባሳደር ልብስ ስፌት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ የታወቀ እና የተወደደ ስም አለው ለማለት ያስደፍራል፡፡አምባሳደር ጋርመንት አሁን ከ 650 በላይ ሰራተኞች ያሉት ግዙፍ የልብስ ስፌት ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ፋብሪካው ወደሚገኝበት ስፍራ አምርተን እንዳየነው ከሆነም በርግጥም ይህ ኢንዱስትሪ ከዚያች አንዲት የልብስ መስፊያ ማሽን ተነስቶ የተፈጠረ ነው ቢባል ለማመን ይከብዳል፡፡በሰፊው የፋብሪካው ቅጥር ጊዜ ውስጥ ኮሽ የማይለው ድምጽ በዚህ ግዙፍ ተቋም ውስጥ ምን እንደሚሰራ ለመገመት አያስችልም፡፡

 

በመኖሪያ ቤት ውብ ዲዛይን የተሰራውና ከፊት ሲመለከቱት የማምረቻ ኢንዱስትሪ የማይመስለው ፋብሪካ ወደውስጥ ሲዘልቅ ለተመልካች ዓይን የሚጋብዘው ነገር አያጣም፡፡ ሰርተፍኬቶች፡፡ አምባሳደር ልብስ ስፌት እስካሁን ባለው የስራ ዘመኑ ያገኛቸውን 55 የሚደርሱ ሰርተፍኬቶች በፋብሪካው የፊት ለፊት በር ገባ ብሎ በሚገኘው ግድግዳ ላይ ውብ በሆነ መልኩ ደርድሯቸዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ የንግድና ዘርፍ ማህበራት እስከ ኡጋንዳ ማኑፋክቸርስ አሶሴሽን እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የአፍሪካ ህብረት ድረስ ለዚህ ድርጅት የተሰጡ የምስጋና፤ የተሳትፎ እና የላቀ አድናቆት ሰርተፍኬቶች ግድግዳውን ሞልተውት ሲታይ ድርጅቱ በሌሎች ዘንድ ያለውን ተቀባይነትና መልካም ስም በቀላሉ መገመት አያዳግትም፡፡

 

ወደፋብሪካው ዋነኛ ማምረቻ አዳራሽ ሲገባም ከ300 ሰራተኞች በላይ በአንድ ጊዜ በምርት ስራ ላይ የሚሳተፉባቸው ለቁጥር የሚያታክቱ የልብስ ስፌትና ሌሎችም ማሽኖች አየአይነታቸው ተደርድረው ይታያሉ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ጨርቅ ለክቶ በመቁረጥ አንስቶ እስከመጨረሻው የሱሪና የኮት ምርት ማውጣት ድረስ በየደረጃው የሚካሄደውን የምርት ስራ የሚያከናውኑ ሰዎች ያሉ ሲሆን፤ በሱሪና በኮት የምርት መስመር /line/ የሚያልፉት ምርቶች በመጨረሻ ላይ ጥንድ ሆነው ሙሉ ልብስ የሚሆንበት አሰራርም ለተመልካች የሚደንቅ አካሄድን የሚከተል ነው፡፡ በዚህ መልክ ታዲያ ይህ ፋብሪካ በየእለቱ ብዛት ያላቸው የሙሉ ልብስ ዓይነቶችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል፡፡

 

ፋሪካው “Made in Ethiopia“ ምርቶችን የሚያቀርብ እንደመሆኑ ከሌሎች ሃገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሙሉ ልብሶችን በዋጋና በጥራት ተወዳድሮ ተመራጭ ለመሆን ከፍ ያለ ጥረት እንደሚያደርግ የፋብሪካው ሃላፊዎች ይናገራሉ፡፡በተለይ ለደንበኞች ፍላጎት ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ ልብሶችን ዲዛይን በማድረግና አምርቶ በማውጣት በኩል አጥጋቢ ስራዎች ተከናውነዋል ብለውናል፡፡ ከዚሁ ፋብሪካ ውስጥ ሳንወጣ 45 ሰራተኞች በአንዴ ልብስ ሊሰፉበት የሚችሉበት MTM   የተባለ በትዕዛዝ የሚሰሩ ልብሶች የሚፈበረኩበትን መካከለኛ መጠን ያለው ፋብሪካም ቃኝተናል፡፡ በርግጥ ይህ ፋብሪካ ጋርመንት የሚለውን ስያሜ የሚያሟላ አወቃቀር ያለው ስለመሆኑም ብዙ ማለት አያሻንም፡፡

አቶ ሰዒድ እንደሚናገሩት በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰው የፋብሪካውን ምርት የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት አለ፡፡ ፋብሪካው ይህ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት አልቻለም፡፡ ወደፊት ምርቱን በስፋትና በጥራት የማቅረብ ዓላማም አለው፡፡ “ኢትዮጵያ 13 ወር ፀሐይ ያለባት ሀገር እንደመሆኗ በየትኛውም የአየር ፀባይዋ ሙሉ ልብስ ሊለበስባት ይችላል“ ይላሉ አቶ ሰዒድ፡፡ እንደ ፈረንጆቹ በሙቀት ጊዜ በካናቴራና በቁምጣ፤ በበረዶ ጊዜ በካፖርትና ካፍያ የሚኖርባት ሃገር አይደለችም፡፡ ከዚህ አኳያ ለሙሉ ልብስ ሰፊ ገበያና ፍላጎት ያለባት ሀገር ናት ብለዋል፡፡

 

ስለገበያ ጥናታቸው ሲገልጹ፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን አሁን ከውጪ የሚመጣውንም ቢሆን ከሀገር ውስጥ ምርት ጋር በማነጻጸር ጥራትን የመለየትና የመምረጥ ነገር በተገልጋዮች ዘንድ እየተለመደ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ “ደንበኞች የትኛው ጥራት ያለው፤ የትኛው በርካሽ ማቴሪያል የተሰራ እንደሆነ ለማወቅ ብዙም የማይቸገሩበት ዘመን ላይ ነን“ ነው ያሉት፡፡“Made in Italy”አቶ ሰዒድ እንደሚናገሩት የድርጅቶቻቸው ልብሶች “Made in Ethiopia መባላቸው ያልተዋጠላቸው አንዳንድ ሰዎች ገበያ አይኖርህም በማለት Made in Italy የሚል ምልክት እንዲለጥፉበት “መክረዋቸው” ነበር፡፡ ድርጅቱ ጣፎ አካባቢ ከካራ ጉብታ ስር በወሰደው ሰፊ መሬት ላይ 80 እጅግ ዘመናዊ ቪላ ቤቶችና ባለ ሶስት ፎቅና 1200 አባወራ ማስፈር የሚችሉ 40 አፓርታማዎች ለመገንባት እቅድ ይዞ ሽያጭ ጀምሯል፡፡ያ ወቅት ለእኔ ፈታኙ ጊዜ ነው፡፡ የምርቴን ጥራት እያወቅኩት ለምንድነው በሃገሬም ስም የማልጠቀመው? ለምንስ “Made in Ethiopia በማለቴ ገበያ አጣለሁ? ብዬ እነርሱን ለማሳመን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በመጨረሻም ተሳክቶልኛል ብለዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ምርትን ሰው አምኖበት ገንዘቡን አውጥቶ ሲገዛና ሲጠቀምበት ማየት ደግሞ ከምንም በላይ የሚያረካቸው ነገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ሰዒድ ከሰራተኞች ጋር ተግባብቶና ያገኙትን እኩል ተካፍሎ መስራት በሰራተኞች ዘንድ “የኔነት “ ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል በተግባር ያረጋገጡ ሰው መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የትኛውም የፋብሪካው ሰራተኛ ለአምባሳደር ምርቶች ጥራት ተቆርቋሪ ነው ይላሉ፡፡

 

አምባሳደር የሚያመርታቸውን ልብሶች ወደ አፍሪካ ሀገራት በመላክ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘትና የኢትዮጵያን ምርት በአለም አቀፍ መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ እቅድ አለው፡፡  በዚህም በቅርቡ ቻይና ሻንጋይ ላይ በተካሄደው የንግድ ትርዒት ላይ ተገኝቶ፤ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለማምረት የሚያስችሉ ዘመናዊ ማሽኖችን ለመግዛት ራዕይ በቅርቡ ዕውን ለማድረግም ዕቅድ ይዟል፡፡ ያኔም በሌሎች ሃገራት ዜጎች ዘንድ “አታውልቀው ያምርብሃል“ የሚያስብል ኢትዮጵያዊ ልብስን የማስተዋወቅ ስራ እውን ይሆናል የሚል እምነት አለን፡፡

 

አቶ ሰዒድ መሃመድ ብርሃን በአምባሳደር ልብስ ስፌት የደረሱበትን ስኬትም በቅርቡ በተሰማሩበት የሆቴልና የሪል ስቴት ዘርፍ ለመድገም በሩጫ ላይ ናቸው፡፡ የዛሬ 2 ዓመት ገደማ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረውና ከሚሊኒየም አዳራሽ ፊት ለፊት የሚገኘው አምባሳደር ሆቴል አፓርትመንት የበኩር ውጤታቸው ነው፡፡ ቁልጭ ባለና ለአይን ቀለል በሚል ዲዛይን የተሰራው ባለሁለት ክንፍ ሆቴል አፓርትመንት በአሁኑ ወቅት በከተማው ካሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ጋር የሚስተካል አገልግሎ የሚሰጥ ሲሆን፤ በተለይም የራሳቸው ማብሰያ ኪችንና ሳሎን ያላቸው 52 ሱዊት ክፍሎት /አፓርታማዎች/ ከሌሎች ሆቴሎች የተለየ ያደርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፊቱን በአብዛኛው ወደ ሆቴል አገልግሎት ብቻ ያዞረው ይህ ሆቴል አፓርትመንት የማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደለት ነው፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቀውን ባለ 7 ፎቅ ሆቴል የሚያካትተው አምባሳደር ሆቴል በአጠቃላይ 150 ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ የራሱ መዋኛ፤ የጂምናዝየምና ሌሎች አገልግሎቶች ይኖሩታል፡፡ አምባሳደር ሆቴል ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ባለ 4 ኮከብ ደረጃ ያለው ሆቴል እንደሚሆን አቶ ሰዒድ ተናግረዋል፡፡ “የሆቴል ዘርፉ በጣም ስኬታማ ነው፡፡ ልናስፋፋውና በስፋት ልንሰራበትም የፈለግነው ለዚሁ ነው“ ብለውናል፡፡

 

አምባሳደር ሪል ስቴት የአምባሳደር ድርጅቶች ሶስተኛው ቅርንጫፍ ነው፡፡ አቶ ሰዒድ እንደነገሩን ከሆነ ድርጅቱ ጣፎ አካባቢ ከካራ ገብታ ስር በወሰደው ሰፊ መሬት ላይ 80 እጅግ ዘመናዊ ቪላ ቤቶችና ባለ ሶስት ፎቅና 1200 አባወራ ማስፈር የሚችሉ 40 አፓርታማዎች ለመገንባት እቅድ ይዞ ሽያጭ ጀምሯል፡፡ ለዚሁ ስራ እንዲረዳውም የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽኖችና ተሽከርካሪዎችን ከውጪ ለመግዛትና ለማስገባት እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 19 ቀን 2002 ዓ/ም ቦሌ ከሰይ ኬክ ቤት ገባ ብሎ በሚገኘው ቦታ ላይ የገነባቸው እያንዳንዳቸው ባለ 5 ፎቅ የሆኑ መንታ አፓርታማዎችን ያስመርቃል፡፡እነዚህ እያንዳንዳቸው 6+1 የሆኑ የግለሰብ መኖሪያቤቶችን በውስጣቸው የሚያካትቱ አፓርታማዎች የአምባሳደር ዘመናዊ ውጤቶች ናቸው ተብሏል፡፡ በቅርቡም የካርታ ርክክብ ከቤቱ ገዢዎች ጋር እንደሚፈጸም አቶ ሰዒድ ገልጸዋል፡፡200 ብር ይዘው ከትውልድ ቀያቸው የወጡት አቶ ሰዒድ መሃመድ ብርሃን ዛሬ የግዙፍ ድርጅቶች ባለቤትና ስማቸው የተጠራ ስራ ፈጣሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ለዚህ ስኬታቸው የባለቤታቸው የወ/ሮ መዲና መሃመድ ብርሃን/የአባታቸው ስም ሞክሼ ነው/ ከፍተኛ ድጋፍ እና እገዛ እንዳልተለያቸው ነግረውናል፡፡

 

የ7 ልጆች አባት የሆኑት አቶ ሰዒድ በትርፍ ጊዜያቸው እስፖርት ከማዘውተራቸው እና ስራ ከመውደዳቸው የተነሳ ይመስላል፤ ገና በ30ቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው ብሎ እድሜያቸውን የሚገምት ቢኖር አይፈረድበትም፡፡ አመጋገባቸውና አካላዊ ቁመናቸውን በጥንቃቄ ይዘው የሚጓዙ ስለመሆናቸው መስካሪ አያሻም እና፡፡አንድ ሰው ገንዘብ የለኝም ብሎ ከተቀመጠ፤ እሱ ያለውን ስጦታ ንቆታል ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው ያለ አንድ ተስጥኦ አይወለድም፡፡ “ያንን ካዳበረው በርሱ ገንዘብን ፈጥሮ ስኬት ላይ መድረስ ይቻላል”፡፡ ብለዋል አቶ ሰዒድ በውስጣቸው ያለውን የ “ይቻላል “ መርህ ሲያስረዱ፡፡ በአሁኑ ወቅት በተወለዱበት ሽሬ ከተማ አንድ ት/ቤት በመገንባት ላይ መሆናቸውንና በተለያዩ ማህበራዊና የበጎ ተግባር አንቅስቃሴዎች ላይ እየተሳተፉ መሆኑንም ገልጸውልናል፡፡ ኢትዮጵያን ሊቀይሯት የሚችሉትና ድህነቷን የሚያጠፉ የራሷ ልጆች የሆኑ ስራ ፈጣሪዎች ናቸው የሚል ጥብቅ እምነት ያላቸው አቶ ሰዒድ “ስራ ፈጣሪዎች በሀገሪቱ መብዛት አለባቸው“ ብለዋል፡፡