Biography Catagories

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

አርቲስት ዘላለም ኩራባቸው

 

Zelalem Kurabachew“እኛ ቤት ጨዋታ፤ ፍቅርና ደስታ ተዝቆ አያልቅም“ዘላለም ኩራባቸው ተወልዶ ያደገው በሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ የሃይስኩል ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሜጋ አድቨርታይዚንግ በ “ፍሪላንሰት “ ወደ ማስታወቂያ ስራ የገባው ዘላለም የሰዎችን ድምጽ አስመስሎ በማቅረብ በእጅጉ አድናቆት አትርፏል፡፡

ከአንድ እናት ከአንድ አባት …. አስራ አንድ ልጆች ነው የተወለደው፡፡ 11ኛውና የመጨረሻው ልጅ እኔ ነኝ፡፡ እኛ ቤት ውስጥ ጨዋታ፤ ፍቅር፤ ደስታና ተግባቢነት ተዝቆ አያልቅም፡፡ ከእንግዲህ ዓይነት ቤተሰብ መውጣቴ በህይወቴ ላይም ተጽዕኖ አለው፡፡ትምህርት ቤት ውስጥ ከብዙዎች ጋር ነበር የምግባባው፡፡ በኪነጥበብ እንቅስቃሴዎች ላይም ቁጥር አንድ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ ከ9 -12ኛ ክፍል በታርኩበት ተምህርት ቤትም የሚኒ ሚድያ አቅራቢና አዘጋጅ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡በጋራየሚሰሩ ስራዎች ላይ የጉልበቱን ሳይሆን የሞራል ማነቃቂያውን እኔ ነበር የምሰራው፡፡ በሀዋሳ ጥሩ የልጅነት ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡

መጀመሪያ በሬድዮ ነበር የቀረብኩት፡፡ ድሮ የኢቲቪ ህብረ ትርዒት ወይም 120 ፕሮግራም ካየሁ በኋላ የሰዎቹን ድምጽ አስመስዬ በመድገም አቀርብ ነበር፡፡ ሰኞ ተማሪዎቹ እኔን ነበር የሚጠብቁኝ፡፡ በዚያ ውስጥ ነው ያደግኩት፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ የአካባቢዬን ሰዎች ድምጽ በማስመሰል መስራት ቀጠልኩ፡፡ እያደገና እየሰፋ መጣና የሶስት ሰዎችን ድምጽ አስመስዬ በሬድዮ ቀረብኩ፡፡ከዚያ በኋላ ነው “አለቤ ሾው “ የቀረብኩት፡፡ ….. አለቤ በጣም …. በጣም የምወደው ባለሙያ ነበር፡፡ ሁላችንም አጥተነዋል፡፡ እኔ እድሜ ልኬን በአለቤ ስስቅ ነው የኖርኩት፡፡ እርሱ ያገኘኝ ቀን ደግሞ እየሳቀ ወደ እኔ ሲመጣ ገረመኝ፡፡እየሳቀ መጥቶ በቲቪ አቀረበኝና ይኸው ዛሬም ድረስ መነጋገሪያ ሊሆን ችሏል፡፡ለእናቴ የመጨረሻ ልጇ እኔ ነኝ፡፡ ልጅ ሆኜ አባቴ ስለሞተ ያለ አባት ው ያሳደገችኝ፡፡ ለዚህም ነው የተለየ ቅርበት የተጠርነው፡፡ እናታችን ብዙ ነገር ሆና ነው ሁላችንንም ያሳደገችን፡፡ እኔንና ቤተሰቦቼን ጨምሮ ልጆች እንድንሆን፤ ራሳችንን እንድንችል ያደረገችን፤ ቆንጆ ፍቅር የሰጠችን እናት አለችን፡፡ በዚያ ላይ በጨዋታ እናቴ ከእኔ ትበልጣለች እንጂ አታንስም፡፡ሙያውን እንደ እኔ አድርገው ወደ ሚዲያ አላወጡትም እንጂ የእኛ ቤት ሁሉም ልጆች ተጫዋቾችና ተግባቢዎች ናቸው፡፡ ወደ ሚዲያው የወጣሁት እኔ ብቻ ልሁን አንጂ ብዙዎቹ ተሰጥዖ አላቸው፡፡

 የማስታወቂያ ድርጅቴ “ዘኩራ አድቨርታይዚንግ “ ይባላል፡፤ ዘላለም ማስታወቂያ ድርጅት ማለት ነው፡፡ ከማስታወቂያዎቹ በተጨማሪ ጥናታዊና ዘጋቢ ፊልሞችን ይሰራል፡፡ በርካታ ክሊፖችና በቅርቡ ለዕይታ የሚበቁ ፊልሞችም በእኔ ስቱዲዮ ተሰርተዋል፡፡ በተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወረ የመዝናኛ ዝግጅቶችን እንዲሁም የታላላቅ ኩባንያዎችን ፕሮፋይልም ጭምር ይሰራል፡፡ የሀዋሳን 50ኛ ዓመት በተመለከተ እዚያ ጊዜያዊ ቢሮ ከፍተን ነበር፤ አሁን ግን ፕሮጀክቶችን ወስጄ እየሰራሁ ነው፡፡ ዋናው ቢሮአችን ባምቢስ ግሪክ ት/ቤት ፊት ለፊት አፔክስ ህንጻ 1ኛ ፎቅ ነው፡፡በጣም የሚያስደስተኝና የምወደው ሙዚቃን ነው፡፡ ዓለም ዓቀፍ ሙዚቃዎችን እሰማለሁ፡፡ጭንቀት አልወድም፡፡ ከሰዎች ጋር ተግባብቶ በማዳመጥም በመናገርም አሪፍ ጊዜ ማሳለፍም ያስደስተኛል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየትም እርካታን ይሰጠኛል፡፡ በተለያዩ አመለካከትና ነጻ አስተሳሰብ ይመቸኛል፡፡ብዙዎቹ ጓደኞቼ የኮሜዲ ተሰጥዖ እንዳለኝ ያውቃሉ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየፈጠርን የምናቀርባቸው ቀልዶች አሉ፡፡ በኮሜዲው ዘርፍ አንድ ቀን ደረጃውን የጠበቀ ስራ ይዤ እንደምቀርብ ፈጽሞ አልጠራጠርም፡፡ መስራትም እችላለሁ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ስንጨዋወት በእኔ ደስተኞች ናቸው፡፡ ማንኛውንም ከወቅቱ ጋ የሚሄዱ ጨዋታዎች እንጫወታለን፡፡ እኔም ተሰጥዖው አለኝ ብዬ አምናለሁና ወደፊት በፕሮፌሽናልነት መምጣቴ አይቀርም፡፡በሀገራችን ብዙ ኮሜዲያኖች አሉ፡፡ ለምሳሌ መኮንን ላዕከን እኔ በጣም እወደዋለሁ፡፡ ክበበው ገዳ ደግሞ በጣም አሪፍ ኮሜዲያን ነው፡፡ ተስፋዬ ካሳ አንደኛና ምትክ አልባ ኮሜዲያን ነበር፡፡ እናም በግልም በጋራም የምንሰራቸው ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

በዋነኝነት ማስታወቂያ ነው የምሰራው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በሚዲያዎች ላይ እየተጋበዝኩ ድምጽ ማስመሰልን እሰራለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ድምጻቸውን አስመስዬ በመናገሬ ቅር ይላቸዋል፡፡ አንዳንዴ በወዳጄ በሳምሶን ማሞ ድምጽ ነው እያስመሰልኩ የማቀርበው፡፡ ይህን ደግሞ ራሱ ነው፤ የፈቀደልኝ፡፡ ሀዋሳ የእኔ ብቻ አይደለችም፡፡ የማንም ከተማ ናት፡፡ ዛሬ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ፤ ብሎ መኩራራት የቀረ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ሀዋሳ የኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ዋና ከተማ ናት ማለት እደፍራለሁ፡፡ ከየትም ቦታ የመጣ ሰው በነጻነት የሚንቀሳቀስበትና የሚተነፍስባት፤ አንዴ ከጎበኟት ደጋግመው የሚመላለሱባት የሁሉም ከተማ ናት፡፡ በመተሳሰብና በመፈቃቀር የሚኖርበት ቦታ ናት፡፡ አስተዳደጌ ሃዋሳ አንደመሆኑ መግልጽነት፤ በመዋደድ፤ በመተሳሰብ የሚኖርባት የአንድነት ከተማ መሆኗን መመስከር እችላለሁ፡፡ የፍቅር ከተማ ናት፡፡

በቅርቡ ሶስት ሰዎች የተለያዩ የፊልም ስክሪብቶችን አምጥተውልኝ ነበር፡፡ እኔም ተደብቆ ያለ ችሎታ ካለኝ አውጥቼ የምሰራበት ጥሩ የሚባል ስክሪብት ካገኘሁ ወደፊልም ለመግባት ሃሳቡ አለኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየታየ ያለው የፊልም እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳየው እድገት መልካም የሚባል ነው፡፡ የፊልሞችን ርዕስ መዘርዘር ባያስፈልግም በርካታዎችን ተመልክቻለሁ፡፡ ፊልሞቻችን እያሳዩት ያለው ለውጥ እየተሻሻለ ቢሆንም አሁንም የተሻለ ቴክኒክና የተሻለ ታሪክ ይዘው መምጣት ከቻሉ ደግሞ እድገቱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ የካሜራና ሌሎች ዘመናዊነትን መከተልንም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ታሪካቸው ወደሀገራዊ ጎዳዮች ሊያተኩር ይገባል፡፡ በአንዳንዶቹ እንደታየው የሚሰሩት ፊልሞች ከነጮቹ ባይኮረጁና ድንግል የሆነ የራሳችንን ታሪክ ይዘው ቢነሱ የተሻለ ነገር ይታያል፡፡

ቀድሞ ባልተለመደ ሁኔታ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም የተለያየ ሲዝንና ክፍል ያላቸው ድራማዎችን በማቅረቡ ከቀጠለ በፊልሙ ላይ ተጨማሪ መነቃቃት ይፈጥራል፡፡መቼም ስም ለመጥቀስ አልገደድም፡፡ አንድ የገረመኝ ነገር ግን አለ፡፡ ብዙ ሰዎች ድምጻቸውን በሌላ ሰው አንደበት ሲሰሙ እንደሚደነግጡ ያስረዱኝ ሰዎች አሉ፡፡ ነፍሱን ይማረውና የጋዜጠኛ ደምሰው መርዕድን ድምጽ አስመስዬ በቲቪ ሳቀርብ ደምሰውም ደስ ብሎት አቅፎ አደነቀኝ፡፡ በጣም ከባዱ ድምጽ የእርሱን ማስመሰል ነበር፡፡ ከደምሰው ጋር ተዋውቀን ጥቂት እንደቆየን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ደምሰውን ለመቅበር እየሄድን ሳለ ከለቀስተኞቹ መሃል አንዷ ሴትዮ ጮክ ብለው “ደስ ይበልህ! ደፋኸው አይደል?“ አሉኝ፡፡ ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ ደግሞ ሌላ ድምጹን የማስመስለው የሬዲዮ ፋና ጋዜጠኛ መታፈሪያ አበበ እሱም በሞት ተለየ፡፡ ከዚያ ካስመሰልኳቸው ውስጥ ግዛው ዳኜ እርሱም ሞተ፡፡ አንድ ቀን ሽመልስ በቀለ እና ሰራዊት ፍቅሬ ቁጭ ብለው “…..ይሄ ልጅ የሚያስመስላቸው ሰዎች እየሞቱ ነው፤ የእኛን አይችለውም አይደል? …… እረ የእኛን ባልቻለው “ ሲባባሉ ሰማኋቸው፡፡አንዳንዱ ሰው ደግሞ የእርሱን ኮት ልታስወልቀው …… በእርሱ ድምጽ ልትነግድ የመጣህ አድርጎ ስለሚያስበው ያስፈራራሃል፤ የሚደብረው ሰውም አለ፡፡ እኔ ደግሞ የሚደብራቸውን ሰዎች ድምጽ አልልላቸውም፡፡የእውነት ለመናገር ሃይሌንም ደራርቱንም አደንቃቸዋለሁ፡፡ ለሃይሌ ገ/ስላሴ የሀዋሳ ሪዞርት ሆቴሌን ዶክመንተሪ ፊልም ሰርቼለታለሁ፡፡ እነርሱ ነጻ ናቸው፡፡ ድምጽ ማስመሰል የተለመደበት ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ የመግባትና የመውጣት ልምድ ስላላቸው የሚረዱት ይመስለኛል፡፡ አንዴ ግን ደራርቱ ሬዲዮ ፋና ላይ ቀርባ ሙዚቃ ስትመርጥ “ዘፈኑን በድምጽሽ ሞክሪው እስቲ“ ይሏታል፡፡ እሷም “በኋላ የዘላለም መቀለጃ ልታደርጉኝ ነው“ ብላ አለፈቻቸው፡፡

አንድን ቁጥር ሳትጠራ 100 ላይ አትደርስም፡፡ ወደ ማስታወቂያ ስራ ከመሻገሬ በፊት የድምጽ ማስመሰል ተሰጥዖዬ ታዋቂ አደረገኝ ማለት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች “ዘላለም ኩራባቸው “ ስትላቸው “ይሄ ድምጽ የሚያስመስለው“ የሚሉት ታዋቂነቴ በምን እንደመጣ ጠቋሚ ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ኩባንያው የሚፈልገው ነጥብ አለ፤ “ዘላለም ይህንን ነጥብ አጉላልኝ” ይላል፡፡ መነሻ ያስፈልገኛል፡፡ ለምሳሌ ድርጅቱ ምርት መሸጥ ነው የሚፈልገው? ወይስ አዲስ ምርት እያመጣ መሆኑን ቀድሞ ማስታወቅ ነው የፈለገው? ….. የሚለው መነሻዬ ይሆንልኝና ቀጣይ የማስታወቂያ ስራው የእኔ ይሆናል፡፡ዕድገቱም የማስታወቂያ አስነጋሪዎችን ቁጥር ጨምሮታል፡፡ ምርታቸውንና ድርጅታቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አምነው የመጡ ደንበኞችን ቁጥር አበራክቷል፡፡ በማስታወቂያው ሂደት ግን ገና ሊሰሩ የሚገባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ብዙ ነገር ይቀረዋል፡፡አንዳንዴ ማስታወቂያ ተናጋሪው ጎልቶ የሚታይበት ማስታወቂያ ይቀርባል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በሂደት የሚወገዱ ናቸው፡፡ አንድ ማስታወቂያ ዒላማው ምንድነው? መልዕክቱ ምንድነው? እንዴትና ለማን ይቀርባል? የሚለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምንግዜም ማስታወቂያው እንደታየ ምርቱ ሊታወስ መቻል አለበት፡፡ አንዳንድ ማስታወቂያዎች ላይ የሰዎቹን ንግግር ታስታውሱና ያስተዋወቁት ምርት ምን እንደሆነ ላይታወስ ይችላል፡፡ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮችን ማሻሻል ይገባናል፡፡

ብዙ ባይሆንም ዋጋ በጣም አውርደው ለመስራት ማስታወቂያ አስነጋሪዎችን የሚጨቀጭቁ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ገበያውን መርተህ መዝለቅ የሚቻለው ዋጋ በማሳነስ ሳይሆን ጥሩ ይዘት ያለው ፕሮጀክት በመስራት ብቻ ነው፡፡

ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩትን የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝቻለሁ፡፡ ጎንደር የሚገኘውን የንጉስ ፋሲልና የበርካታ ነገስታትን ቤተመንግስትም ተመልክቻለሁ፡፡ በደቡብ ክልል የሚገኙ አብዛኞቹን የቱሪስት መስህቦች ተዟዙሬ አይቻለሁ፡፡ የአባይን ወንዝና የጢስ አባይ ፏፏቴን ተመልክቻለሁ፡፡ በዚህ በኩል እንኳ ሰነፍ አይደለሁም፡፡እነዚህን ቦታዎች ስመለከት የተለያዩ ስሜቶች ነው ያደረብኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጢስ አባይን ስመለከት በጣም አፈርኩ፡፡ እስከዛሬ የት ነበርኩ አልኩ፡፡ ላሊበላ ገብቼ ግን ዝም ነው ያልኩት፡፡ ዝም ….. ዝም ….. ዝም፡፡ በኋላ ኢትዮጵያዊነቴ እየተሞላ መጣ መሰለኝ፡፡

ወጣት የነብር ጣት ብዬ ነው የምጀምረው፡፡ አስተዋይ፤ ብልህ፤ የተማረና አንባቢ መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሀገርንና ወገንን በመልካምነት መጠበቅ፤ መተሳሰብ፤ መቻቻል፤ መደማመጥ ተገቢ ነው፡፡ የዛሬው ወጣት ሆይ ነገ የትም መድረስ ይቻላል፡፡