Biography Catagories

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ቆንጂት ሥነ-ጊዮርጊስ ወልደማርያም

 

ቆንጂት ሥነ-ጊዮርጊስ ወልደማርያም

“ከወንድሜ ከቀሰምኳቸው የሕይወት ቁምነገሮች አንዱ፤ ለራስ ክብር መስጠት ሲሆን ይሄንንም ለማሳካት ታማኝና ሃቀኛመሆን እንደሚያስፈልግ ተምሬአለሁ፡፡

ላለፉት 50 ዓመታት አገሬን በዲፕሎማትነት ለማገልገል በመቻሌ በእጅጉ ክብር ይሰማኛል፡፡ በዲፕሎማት ዘመኔ ታሪካዊውን የአፍሪካ ዕድገት ሽግግርና አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላትን ቦታ በአማኝነት የማየት አንዳንዴም የመሳተፍና የመደገፍ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ እግዚአብሔር አገሬን የማገልገል ዕድሉን ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ ለራሴ ባደረግሁት ትግል ሴቶች በዚህ የሙያ ዘርፍ ተወስኖ የተቀመጠላቸውን የገደብ ጣራ ገፍቼዋለሁ፡፡ ዛሬ በእኔም የሙያ መስክ የተሰማሩ ወንዶችና ሴቶች በእኩል ደረጃ መፎካከር ችለዋል፡፡ ለዚህ ለውጥ የእኔ ትግል ያበረከተው አንዳች አስተዋጽኦ ካለ ደስተኛ ነኝ፡፡

በመሰናክሎች የተሞላውን የሙያ ዘርፍ በድል ተወጥቼ ለስኬት የበቃሁት ለምንም ነገር አይበገሬ ስለሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ታላቅ ወንድሜ በልጅነቴ በውስጠ ያስረፀብኝ የነፃነትና በራስ የመቆም መንፈስ ለስኬቱ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ያደግሁት እናቴ ያለአባወራ ባስተዳደረችው ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ ደስተኛ ልም ነበርኩ፡፡ ከአንድ ወንድምና ሁለት እኩዮቼ ከነበሩ ሀለት የዘመድ(ወንድ) ልጆች ጋር ነው የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት፡፡ እናቴ ታቀብጠኝ ነበር፡፡ ውሎዬም ከወንዶች ጋር ነበር እናም ወንዳወንድ ሆኜ ዛፍ ላይ እየወጣሁ ብስክሌት እየነዳሁ ፈረስ እየጋለብኩና ጠጠር እየተጫወትኩ ነበር ያደግሁት፡፡ እናቴ ትኩረቴን ወደ ወጥ ቤት የቤት አያያዝ ልትስበው ብትሞክርም በፌ አላልኳትም፡፡ ፓርቲ መውጣትና መደነስ ነፍሴ ነበር፡፡ እናቴይሄን የምትፈቅድልኝ ግን በጥብቅ ቁጥጥርና የሰዓት ገደብ ነበር፡፡ እሷ ቤት በሌለች ጊዜ ታላቅ ወንድሜ ሙሉጌታ የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ይረከባል፡፡ እሱ ግን ከቁጥጥር ይልቅ ነፃነቴን ከኃላፊነት ሰጋር ያሸክመኝ ነበር፡፡ በፈለግሁት ሰዓት ሄጄ ራሴ የሰዓት ገደብ አስቀምጬ ወደ ቤት እንድመለስና ሁሉን ነገር በራሴ እንድወስን ይፈቅድልኝ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ የጣለብኝን እምነት እንዳከበርና በኃላፊነት ስሜት እንድንቀሳቀስ አደረገኝ፡፡ ወንድሜ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንዳስብ፣ ነገሮችን በራሴ እንድወስንና በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዳልሆንም አስተምሮኛል፡፡ ከወንድሜ ከቀሰምኳቸው የሕይወት ቁም ነገሮች አንዱ ለራስ ክብር መስጠት ሲሆን ይሄንንም ለማሳካት ታማኝና ሀቀኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ተምሬአለሁ፡፡ ወንድሜን ለዚህ ውለታው አመሰግነዋለሁ፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እስከማጠናቅቅ ድረስ በምን ሙያ ላይ መሰማራት እንደምሻ አላውቅም ነበር፡፡ ከታላቅ እህቴ ጋር ወደ እንግሊዝ ከተጓዝኩ በኋላ እሷ በነርስነትና በአዋላጅነት ስትመረቅ፤ እኔ በትምህርት ሰርተፊኬት ወሰድኩ፡፡ ከዚያም በለንደን የጽህፈት ት/ቤት ገብቼ በጣም ፈጣን የአጽርኦተ-ጽሁፍ(ሾርት ሃንድ) ፀሐፊና ታይፒስት ሆንኩኝ፡፡ አንድ ቀን ግን ብቻዬን  ተቀምጬ እድሜ ልኬን እሺ ጌታዬ የለም ጊታዬ እያልኩ ልኖር ነው፡፡ ስል እራሴን ጠየቅሁ፡፡ ያ ደግሞ የእኔ ባህርይ እንዳልሆነ አውቀው ስለነበር አንድ በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ያጠና የነበረ የቤተሰብ ወዳጅን ፈለግ ተከትዬ ይሄንን ትምህርት ማጥናት ያዝኩ፡፡ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኮርሶችን እየወሰድኩ ሳለ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ላይ የተፃፉት በርካታ መጻሕፍትን ያነበብኩ ሲሆን በድርጅቱ  ልዕለ ሀሳቦችም በእጅጉ ተደነቅሁ፡፡ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ የተቋቋመ አንድ ድርጅት፤ እንዴት እንደሚሰራና በዓለም ሕዝቦች የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ እንደሚወሰን እያሰብኩ እገረም ነበር፡፡ እናም የድርጅቱን አሰራር የማየት ፍላጎት አደረብኝ፡፡ ከዚያም አንድ በኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ የሚሰራ ተስፋዬ መካሻ የሚባል ወዳጅ፣ በኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ውጥ ሥራ እንዳለክት በመምከር፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ልዑክ ውስጥ የማገልገል ተስፋ እንዳለኝ አረጋገጠልኝ፡፡ እኔም ምክሩን ተቀብዬ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከቻዬን ላክሁኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በተመለስኩ ጊዜ ግን በትምህርት ሚኒስቴር ከውጭ ተምረው ተመለሱ ኢትዮጵያውያንን ሥራ እንዲመድብ የተቀመጠው ኃላፊ ለሴቶች የሚሆን ቦታ አይደለም” አለኝ፡፡ እኔ ግን ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ በተለመደው አይበርገርነቴ ገፋሁበት፡፡ ቀን በቀን ሰውዬው ቢሮ ደጃፍ ላይ እየተቀመጥኩ ሳስቸግረው፣ ሳይወድ በግዱ መደበኝ፡፡  እንደ እድል ሆኖ መጀመሪያ የተመደብኩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ሥራውን እንደጀመርኩ ለወንድ ባልደረቦቼ ጽሁፎችን መተየብ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የመጀመሪያ አለቃዬ አስፋው ለገሰ “ዲፕሎማት የመሆን ፍላጎት ካለሽ መተየብ አልችልም ማለት አለብሽ ሲል ይሄ ነው የማልወጣው ችግር ውስጥ እንደሚከተኝ አስጠነቀቀኝ፡፡ እናም ለቀጣዮቹ 30 ዓመታት የትየባ ማሽን የሚባል ፈጽሞ አልነካሁም፡፡ በዚህ የተነሳ ፈጣን የአጽርኦተ ጽሁፍ  ችሎታዬን ማጣቴ ይቆጨኛል፡፡ የእርሱን ምክር ባልከተል ደግሞ ፀሃፊ ሆኜ እቀር ነበር፡፡

ከሶስት ዓመታት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ቋሚ ኢትዮጵያ ልዑከ ሁለተኛ ፀሃፊ በመሆን ወደ ነውዮርክ የመሄድ ዕድል አገኘሁ፡፡ ግን አሁንም ፈተናዎች ተከትለውኝ መጓዛቸው አልቀረም፡፡ መመደብ ያለብኝ በዋና የዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ነው ወይስ በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ በሚል ከአዲሱ አለቃዬ ጋር ተጋጨን፡፡ በመጨረሻም ግን በቆንስላው እርዳታ ጦርነቱን አሸንፌ ቀድሞውኑ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተመደብኩበት የተባበሩት መንግስታት የፀረ-ቅኝት ግዛት ኮሚቴ ውስጥ መስራት ጀመርኩ፡፡ ከአምስት ዓመታት የሥራ ቆይታ በኋላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሰራር ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ ብዙ ይወራል እንጂ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ተፈፃሚነት ወይም ውጤታማነት ለመገምገም እምብዛም ዕድል የለም ወደሚል ድምዳሜም ደረስኩ፡፡ እናም ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡

ቀጣዮቹን 10 ዓመታት አገሬ ላይ የተቀመጥኩ ሲሆን መሃል ላይ የንጉሱ መንግስት በወታደራዊው አገዛዝ ስልጣኑን ተነጠቀ፡፡ እኔም ንብረታቸው በደርግ የተወረሰባቸውን እናቴንና ቤተሰቤን በቁርጠኝነት መደገፍ ጀመርኩ፡፡ በዚህ ጊዜ በዋናነት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አጋር  ያልሆኑ አገራትን በሚመለከተው ክፍል ውስጥ ስሰራ ቆየሁ፡፡ የደርግ አገዛዝ ጠንካራ አፈና በቀነሰበት 1970ዎቹ፣ በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ቋሚ የኢትዮጵያ ልኡከ ምክትል ቋሚ ተወካይ ሆኜ ተመደብኩ፡፡ በዚህ ኃላፊነት ለ10 ዓመት ከሰራሁ በኋላ፣ በ1980ዎቹ በአምባሳደርነት ደረጃ የተሸምኩ ሲሆን በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ቋሚ የኢትዮጵያ ተወካይና የኦስትሪያ አምባሳደር ሆንኩኝ፡፡ ይሄ ሹመት የመጣው ከ28 ዓመታት የዲፕሎማሲ አገልግሎት በኋላ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በተከታታይ ስምን የአምባሳደርነት ሹመቶችን ያገኘሁ ሲሆን በአጠቃላይ በሰባት አገራት ሶስት ጊዜ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኋላ የአፍሪካ ሕብረት የተባለው) ቋሚ ተወካይ ሆኜ ተመድቢያለሁ፡፡ በሙያ ዘመኔ በራሴም ሆነ ለአገሬ ባበረከትኩት አገልግሎት ኩራት ይሰማኛል፡፡ ያለምኩትን ሁሉ አሳክቻለሁ ብሔ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ስኬት ምስጢሩ ለሥራ ያለኝ ከፍተኛ ፍቅር ነው፡፡ ስራዬ ለእኔ ሕይወቴና ቦጋለ ውስጣዊ ፍቅር የምተጋለት ሁሉ ነገሬ ነው፡፡

ስኬት የተቀዳጀሁት በቀላሉ አልነበረም፡፡ የሚገባኝን ዕድገት ለማግኘት በእጅጉ ከተፋለምኩና ከሥራው ውጭ ያሉትን ነገሮች ሁሉ መስዋዕት ካደረግሁት በኋላ ነበር፡፡ በአስተዳደርም አከባቢ ሴት ልጅ ማግባትና ልጆች መውለድ ከዚያም ሥራዋን መልቀቅ አለባት የሚል ሥር የሰደደ እምነት ስለነበር፣ በተደጋጋሚ ብዙ እድገቶችን ተዘልያለሁ፡፡ ግን ገደቡ የት ድረስ እንደሆነ ለመፈተን ወስኜ ነበርና በዝምታ አላለፍኩም፡፡ በዚህ እህል አስጨራሽ ትግል ውስጥ እኔው እራሴ ቀድሜ እንዳልሰበር ቆርጬ የተነሳሁት፡፡ መጀመሪያ ከቁም ነገር እንዲቆጥሩኝና ከዚያም እድገት እንዳገኝ ሳላሰልስ ከወንድ ባልደረቦቼ የላቀ እለፋ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ የሥራዬ ዓመታት፣ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ውስጥ እጅግ ኃይለኛ አለቃ ከሚባለው ከአቶ ተስፋዬ መካሻ ጋር ለሰባት ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ አቶ ተስፋዬ የሙያ አባቴ ነበር፡፡ ከእሱ የቀሰምኩት ትልቁ ትምህርት እጅግ ጠንቃቃነትን ሲሆን ለዚህ ሁሉም ባለውለታዬ ነው፡፡ ከእልህ አስጨራሽ የሙከራና የልምምድ ጊዜ በኋላ አለቃዬ እምነቱን የጣለብኝ ሲሆን ከእኔ በላይ የተሾሙት ቆንስላዎችን ሥራ እንዳርምና እንዳሻሽል ሁሉ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ በመጠየቄ ኩራት ቢሰማኝም ያለውን እውነታ ን ሁሌም ከማስታወስ ቦዝኜ አላውቅም፡፡ በችሎታዬ እምነት ቢኖረኝም ቅሉ ዕድገት ለማግኘት ግን  ብዙ መታገል ነበረብኝ፡፡ ምን ጊዜም እድገት ያለአግባብ ስታለፍ ቅሬታዬን ከመግለጽና ኢፍትሐዊ አሰራርን ከማጋለጥ ተዘናግቼ አላውቅም፡፡ አለቆቼ ሴት እንደመሆኔ  እድገት አትጠብቅም ብለው እንዳያስቡ፣ ፈጽሞ በዝምታ አላልፍም ነበር፡፡ በቤተሰቦቼ ተጽእኖ እድገት ባገኝ በራስ የመተማመን ስሜቴን አጣለሁ ብዬ እሰጋ ስለነበር፣ ዕድገትን በተመለከተ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉትን ቤተሰቦቼን እንኳን ጣልቃ አላስገባኋቸውም ነበር፡፡ በመጨረሻም የስዊዘርላንድና የአስትሪያን ስኬታማ ጉብኝት ያሰናዳሁላቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጄኔቫ ያሉትን የቅርብ አለቃዬን ተቃውሞ ችላ በማለት አምባሳደር ሆኜ እንድሾም አደረጉኝ፡፡ የጀኔቫው አለቃዬ የአምባሳደርነት ሹመቴን የተቃወመው የፓርቲ አባል አልሆንም በማለቴ ነው፡፡

በሹመት  ወደ ላይ እያደግሁ ስሄድ፣ የዚያኑ ያህል በትጋት መስራት ነበረብኝ፡፡ የአቅሜን ያህል ምርጥ ሥራ መስራት እፈልግ ነበር፡፡ እናም በጣም ከፍ አድርጌ እያለምኩ ሕልሞቼን ለማሳካት ችያለሁ፡፡ ሁል ጊዜ ሩጫዬ ከጊዜ ጋር ነበር፡፡ ለዚህም ነው ዘወትር ሰነዶችን እያያዝኩ ወደ መኝታዬ እሄድ የነበረው፡፡ በተለይ የአፍሪካን ዲፓርትመንት ስመራና የአፍሪካ ሕብረት ተሸላሚ ሆኜ ስሰራ፣ የለምንም ፋታ በየአገሩ የምጓዝዝባቸው ወቅቶች ነበሩ፡፡ ከትዳር ጋር ትወውቅ የለኝም፡፡ በእርግጥ የሆነ ጊዜ ላይ እናቴን ለማስደሰት ስል ለማግባት አስቤ ነበር፡፡ ከቤተሰቤና ከሥራዬ ቅድሚያ የምሰጠው ለሥራዬ እንደሆነና በዚህም ቤተሰቤ እንደሚጎዳ ስገነዘብ ግን የማግባት ሀሳቡን እርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡ ለሥራዬ ብዙ መስዋዕትነት ከፍያለሁ፡፡ ግን እነዚያን መስዋዕቶች በመክፈሌና ሥራዬ ላይ ብቻ ለማተኮር በመቻሌ ነው ዛሬ ድረስ በምወደው ሥራዬ ስኬታማ የሆንኩት፡፡

ዛሬ ነገሮች በእጅጉ ተለዋውጠዋል፡፡ ለብሩህ ሴቶች በተከፈተላቸው በርካታ የእድል በሮች በእጅጉ ደስተኛ ነኝ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሴቶች በሥራቸው እውቅና ያገኙ ዘንድ ከወንድ ባልደረቦቻቸው የላቀ መስራትና ላሰማቸውም በእጅጉ መጠንቀቅ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህ ነው በማሰለጥናቸውና ሙያዊ ድጋፍ በምሰጣቸው ሴቶች ላይ ጠንከር የምልባቸው፡፡

በሚቀጥለው ዓመት ጡረታ ለመውጣት እየተዘጋጀው ሲሆን ልክ ወንድሜ ለእኔ እንዳደረገው ሁ ለመሉ ጊዜዬንን ከአስር ዓመቱ ወንድ ልጄ ጋር በማሳለፍ በራሱ የሚተማመን ነፃ ሰው እንዲሆን ያለ መኮትኮትና ለማስተማር እፈልጋለሁ፡፡ ቤት ውስጥ ያለ ሥራ መቀመጥ ስለማልችል አንድ የምሰራው ነገር እፈላልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ፋታ የሚሰጥና ከልጄ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ የማይሻማብኝ መሆን አለበት፡፡

የኢትዮጵያ መጪ ዘመን ብሩህ፣ እንደሚሆን ይታየኛል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን በያዘችው የዕድገት ጎዳና መገስገሷን ከቀጠለች በቅርቡ ታላቅ አገርም እንደምትሆን አምናለሁ፡፡ በቅርቡ የወንዶችና የሴቶች እኩልነት እንደሚረጋገጥ፣ ለገጠር ልጃገረዶች ማንበብና መፃፍ ባህል እንደሚሆን ረሃብና የሕፃናት የምግብ እጥረት እንደሚወገድ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እነዚህ ልንታገልላቸው የሚገቡ ግቦች ናቸው፡፡

ለዛሬ ወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች የምለግሳቸው ምክር፣ መጀመሪያ ራሳቸውን ማስተማር ከዚያም በመረጡት ሥራ ተግተው መስራት እንዳለባቸው ነው፡፡ ሕይወት የዋዛ አለመሆኑን መረዳት ይገባን ዋል፡፡ በመንገዳቸው ላይ መሰናክሎችን መጋፈጣቸው አይቀርም፡፡ እነዚህን መሰናክሎች እንዴት እንደሚያስወግዱና ህልማቸውን የማሳካት ጉዟቸው እንደሚቀጥሉ ማወቅ አለባቸው፡፡ የሚሰሩትን ነገር መውደዳቸው፣ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የሚሰሩትን ሲወዱ የበለጠ ደስተኛና ስኬታማ ይሆናሉና፡፡

ውሳኔዎችን በጥድፊያ መወሰን ተገቢ አለመሆኑ ተረድቻለሁ በእርጋታ ለማሰብ ጊዜ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ ለውሳኔ ከመጣደፋችሁ በፊት ጉዳዩን ለምታምኗቸውና ለምታከብራቸው ሰዎች አማክሯቸው፡፡ የተለያዩ አማራጮችን አዎንታዊ  አሉታዊ ጎኖች ፈትሹ፡፡ ከዚህ በፊት መሞክራችንና ስኬት ወይም ውድቀት ማምጣታቸውንም ገምግሙ፡፡ ከማንም የሰማችሁትን ጉዳይ ከቅርብ ጓደኛችሁም ቢሆን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይኖርባቸኋል፡፡ መረጃዎችን ሳታረጋግጡ ማናቸውንም ትላልቅ ውሳኔዎች አትወስኑ እነዚህ ነገሮች ሕይወትን በእጅጉ ያቀሉታልና፡፡

“ለዚህ ስኬት ምስጢሩ ለሥራዬ ያለኝ ከፍተና ፍቅር ነው፡፡ ሥራዬ ለእኔ ሕይወቴን በጋለ ውስጣዊ ፍቅር የምተጋለት ሁሉ ነገሬም ነው፡፡”

 

ቆንጂት በ1966 ዓ.ም በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ -መሃል ከተቀመጡት ወ/ሮ ዮዲት እምሩ ጎን፣ ከዳር በስተግራ የሚታዩት ሲሆን ዶ/ር ዘውዴ ገብረስላሴ በስተቀኝ ከዳር ይታያሉ (ፎቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት)