Biography Catagories

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ሳምሶን ታደሰ

 

ሳምሶን ታደሰ/ ቤቢ

 

ሳምሶን ታደሰቆንጆ፡- ከበዓላቶች ውስጥ ለየት ያለ ስሜት የሚፈጥርብህ የትኛው በዓል ነው?

ሳምሶን፡- ለእኔ እንቆጣጣሽና ፋሲካን ነው የበለጠ የምወደው፡፡ ደመቅ ብሎ ነው የሚታየው ከድሮም ጀምሮ ነው ደስ የሚያሰኝ ነገር ሁሉም በዓላቶች ያስደስቱኛል፡፡ በተለይ ከልጅነቴ ጀምሮ ብዙ ትዝታ ስላለኝ ሊሆን ይችላል እናም የእንቁጣጣሽና የፋሲካ በዓል በጣም ልዩ ስሜት ነው የሚሰጡኝ፡፡

ቆንጆ፡- በባዓላት ወቅት ከቤተሰቦችህ ወይም ከጓደኞችህ ጋር ስጦታ የመለዋወጥ ልምድ አለህ?

ሳምሶን፡- ብዙም ልምድ የለኝም ግን አሁን አሁን እየለመድኩት ሳልመጣ አልቀርም፡፡

ቆንጆ፡- በስምህ በመጨረሻ ቤቢ የሚል ቅጽል ስም አለ ይህ ስም ከልጅነት ተያያዥነት አለው?

ሳምሶን፡- አዎ ከተለወድኩ ጀምሮ እናቴ ነች ቤቢ ያለችኝ እናም የቤት ስሜ ቤቢ ሆነ የትምህርት ስሜ ግን ሳምሶን ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ግን ቤተሰብ ድረስ የምንቀራረብ ጓደኞቼ ቤቢ ነው የሚሉኝ ሥራም ቦታ ላይ ቤቢ ነው የምባለው እናም ይህ ስም በዛና ከዋናው ስም ተቀጽላ ሊሆን  ቻለ፡፡
ቆንጆ፡- በየትኛው ስምህ ስትጠራ ደስ ይልሃል?

ሳምሶን፡- ሁለተም ደስ ይለኛል ሁለቱም ያደኩበት ስሜ ስለሆነ እወደዋለሁ፡፡

ቆንጆ፡- ወደዚህ ሙያ ውስጥ እንዴት ልትገባ ቻልክ?

ሳምሶን፡- ወደዚህ ሙያ ውስጥ ልገባ የቻልኩት በቢኒያም ወርቁ አማካኝነት ነው፡፡ ቢንያም በጣም ጠንካራን ያለማንም ድጋፍ ሥራዎችን መስራት የሚችል ሰው ነው፡፡ እናም ወደዚህ ሙያ ውስጥ ልገባ የቻልኩት በእርሱ ነው፡፡

ቆንጆ፡- ባንተ በሰለሞን ቦጋለና በቢንያም ወርቁ መካከል ያላችሁ ግንኙነት ግለጽልኝ?

ሳምሶን፡- እኛ አሁን ከጓደኝነትም ዘሎ ወደ ወንድማማችነትና የቤተሰብ ስሜት ነው መሄላችን ያለው፡፡ በጣም ከፍተኛ ፍቅር ነው ነው ያለን በየቀኑም ባንገናኝ እንኳን ስንገናኝ ካቆምንበት ነው የምንጀምረው በአሁን ጊዜ በጣም በጣም ቤተሰብ ነን፡፡

ቆንጆ፡- የመጀመሪያ ሥራህ ቲያትር ነው ወይስ የፊልም?

ሳምሶን፡-የመጀመሪያ ሥራዬ የመድረክ ነው አጋጣሚ ሆኖ በጀመርኩ በአጭር ጊዜ ብዙ ሕዝብ ባለበት ነው የመጀመሪያ ሥራዬን ያቀረብኩት፡፡ በጣም ደስ የሚልና ልዩ ትዝታ ነበረው ፊልሙም ግን ብዙ ርቀት የለውም፡፡ ከማይዘነጋው ውለታ ካምፓስ፣ የሚል ፊልም አለ እነዚህም ፊልሞች ሙያውን የጀመርኩ አከባቢው ነው የሰራኋቸው ሥራዎች ናቸው፡፡

ቆንጆ፡- እንደ ጀማሪነት የተለየ የፈጠረብህ ስሜት አለ?

ሳምሶን፡- አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለሕዝብ እንደሚቀርብ ተነግሮናል ከዛም በኋላ እኔ በጊዜ ነበር የተገኘሁት የምጫወተው ገፀባህሪ የጀነራል ነበር አዳራሽሳሽፅ ደግሞ በእለቱ ከ700-800 የሚጠጋ ተመልካች ነበረ፡፡ እናም ሜካፕ ተደርጎልን ትያትሩ ተጀመረ፡፡ የተመልካቹን ስሜትና ጉምጉምታ ማየት ሲመጣ በጣም ፈራሁኝ እግዚአብሔር ለዚህ ነገር መርጦኛል ማለት ነው ብለህ እንድታሰስብ ያደርግሃል፡፡ የሆነ ሰዓት ላይ በጣም ተጮኸ ሰለሞን ቦጋለ ፊት አውራሪ ሆኖ ነበር የሚሰራው የእኔ ገፀባህሪ እሱን የሚያስገድድት ነበር፡፡ ልመታው የምዝትበት ቦታ አለ እዛ ጋር ስደርስ በጣም ጮኹ ሳቅ… ያ ለእኔ ልዩ ስሜት አስደንጋጭ ነበር፡፡

ቆንጆ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመልካች ጋር ፊት ለፊት ስትገናኝ ፍርሃት አልፈጠረብህም?

ሳምሶን፡- ያስፈራል፡፡ ይህ ነገር ግን ሁልጊዜ ነው ያለው፡፡ የሚገርም ነገር 6 ወር ሙሉ የሠራኸው ትያትር ወደ መድረክ ልትገባ ስትል ሁሌም ልብህ ይፈራል፡፡ አብዛኞቹ ተዋናዮች ብትጠይቃቸው ይህ ነገር አለ፡፡ የሚገርም ነገር 6 ወር ሙሉ የሰራኸው ትያትር ወደ መድረክ ልትገባ ስትል ሁሌም ልብህ ይፈራል፡፡ አብዛኞቹ ተዋናዮች ብትጠይቃቸው ይህ ነገር አለ፡፡ ልብህ ይረበሻል በተለይ የትርዕይቱ መክፈቻ ይህ ነገር አንተ ከሆንክ በጣም ያስጨንቃል፡፡ አመትም ሁለት አመትም የሰራኸው ሥራ ቢሆን ያስጨንቃል ግን ያኛው ትንሽ የተለየ ስሜት ነበረው፡፡ በተለይ የሌሎች ሰዎች ፍርሃት የጋባብኝ ነበር፡፡ እናም መድረክ ላይ ስትገባ ሁሌም ነው የሚያስፈራው፡፡

ቆንጆ፡- እስካሁን ድረስ ምን ያህል ትያትሮችና ፊልሞችን ሰርተሃል፡፡

ሳምሶን፡- እርግጠኛ አይደለሁም ከዚህ በፊት የሰራኌቸው ሥራዎችን ልቆጥር ሞክሬያለሁ እንዲሁ ደግሞ ልናገር ካልኩ ከ16 በላይ የሆኑ ትያትሮችንና ፊልሞችንም ከዚያ በላይ ሰርቻለሁ፡፡

ቆንጆ፡- ከሰራኋቸው ሥራዎች ልዩ ስሜት የፈጠረብህ የትኛው ሥራ ነው?

ሳምሶን፡- እንግዲህ ብዙ አመትና ብዙ ሥራ ነው የሰራሁት፡፡ አሁን ላይ ግን ወደ ኋላ ያን ሁሉ አመት ተጉዘህ ለመናገር ይከብዳል፡፡ አሁን ላይ ግን ትዝ የሚለኝና ልዩ ስሜት የሚፈጥርብኝ የቬነሱ ነጋዴ ላይ የዊሊያም ሼክሰፒር ሽያሌክን ስጫወት ነበር የተለየ ስሜት የሚፈጠረብኝ ነበር፡፡ በተለይ ክላሲክ ሥራዎች፡፡ እሱም ልዩ ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ በተረፈ ግን ሁሉም ትያትሮች የራሳቸው ስሜት አላቸው አስናም አንዱን ጠርተህ ሌላውን ማጉደል ይከብዳል፡፡

ቆንጆ፡- ከትያትር ወይም ከፉልም ሥራ የትኛው ያስደስትሃል?

ሳምሶን፡-ትርያትር ተሰርቶ አልቆ እዛው ከሕዝብ ጋር ነው የምትገናጨው፡፡ እዛው ጋር ነው የሕዝብንም ፊድ ባክና ምላሹንም የምታየው፡፡ የመድረክ ሲሆን ደስታ ይፈጥርብሃል ለእኔ ብቻ አይመስለኝም ለሌሎች ተዋናዮች ይመስለኛል የመድረክ ሥራ ይበልጣል፡፡ ፊልም የተቆራረጡ የዳይሬክተሩ እጅ ነው፡፡ የተቆጣጠረ ነገር ሰርተህ ተገጣጥሞ የድምጽ እፌክት ተሰርቶለት ከሕዝብ ጋር ሲመረቅ አንተም ከሕዝብ ጋር ነው የምታየው የዚያን ቀን ነው ያንተ ደስታ እስከዛች ቀን ደረስ የሕዝቡን ስሜት አታውቀውም፡፡ የትያትር ግን ቀጥታ የሚታይ ነው እናም ትያትር ደስ ይላል፡፡

ቆንጆ፡- የትኛውስ ይከብዳል?

ሳምሶን፡- ሁለቱም ይከብዳል፡፡ ቀላል የምትለው ነገር የለም፡፡ ካራክተር መጫወት ብዙ አመት ለፍቶ ያተዋጣለት ይኖራል፡፡ በእርግጥ ከእግዚአብሔር የሚሰጠው ስጦታ ነው፡፡ ከፉልም የበለጠ የትያትር ሥራ ከበድ ይላል ፊልም ላይ ልትሳሳት ትችላለህ፡፡ ትያትር ላይ ግን ፐርፌክሽን ይጠበቅብሃል፡፡ ፊልም ላይ ብትሳሳት ችግር የለውም ጊዜህንና የሰውን ጉልበት የምታባክነው እንጂ ካሜራው ቆሞ እንደገና አስተካክለህ ትቀጥላለህ፡፡ ትያትር ላይ ግን ይ የለም፡፡ ያለምንም ስህተት ጎበዝ ሆነህ መውጣት መቻል አለብህ፡፡

ቆንጆ፡-በአንድ ሳምንት ውስጥ አምስት ያህል ትያትሮችን መጫወት አይከብድም?

ሳምሶን፡- እግዚአብሔር ይመስገን እንደ ልብህ ወዲ ወዲህ ማለት ባትችልም እንደነዚህ የሚጠበቁብህ መስዋዕቶች ይኖራሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ ጤነኛ መሆን አለብህ ሲኖር ክፍለ ሀገር መሄድ አትችልም እንደነዚህ እንደነዚህ የሚጠበቁብህ መስዋዕቶች ይኖራሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ ጤነኛ መሆን አለብህ ጤናን ደግሞ ያው እግዚአብሔር ነው የሚጠብቀው፡፡ ጉንፋን እንኳን ቢያምህ ስንት ፕለይ ላይ ችግር እንደሚፈጥር ስታስበው ረጅም ጊዜ በጤናና በሰላም መስራት ይህ ከእግዚአብሔር ነው ከማንም አይደለም፡፡ ራስንም ማዘጋጀት ይፈልጋል፡፡

ቆንጆ፡- ከሌላ ስራዎችህ ጋር አይጋጭብህም?

ሳምሶን፡- አይጋጭም እንዴት መሰለህ መንፈሱ እራሱ ይለያያል፡፡ ሕንደኬ ላይ ያቢ ሶፊያን ላይ ስጫወት ከብዙ ዓመት በፊት ያለ ሴቲንግ ነው አለባበሱ ይለያያል አብረህ የምትሰራቸው ሰዎች ይለያዩ ሜካፑ ራሱ ይለያያል፡፡ ሜዳልያ ትዳር ሲታጠን ፎርፌ ሩብ ጉዳይ ላይ ስትመጣ የምታገኛቸው ተዋንያኖች አልባበሱ ዕድሜውን ገፀባህሪውን ይለያያል እናም የመጋጨት ብዙ ነገር የለውም፡፡

ቆንጆ፡- እንደውም አንድ ወቅት ላይ በአንድ እሁድ ሁለት ትያትሮችን ትሰራ ነበር? እስቲ ስለእሱ ትንሽ በለን?

ሳምሶን አዎ… ሩብ ጉዳይ ሀገር ፍቅር ትያትር ሕንደኬ ደግሞ ብሔራዊ እጫወት ነበር በጣም የሚገርምህ ነገር በመሀል አጭር ሰዓት ነው ያለችው ሕንደኬ በጣም ብዙ ሜካፕ አለው ሙሉ በሙሉ ፀጉሬን ነጭ ሆኖ ነው የምሰራው፡፡ ሩብ ጉዳይ ላይ ለው ገፀባህሪ ደግሞ የወጣት ካራክተር ነው፡፡ እንደወጣሁ እያደረቅሁ በሩጫ ወደ ሀገር ፍቅር እንመጣለን፡፡ እዚህ ደግሞ እጅግ በጣም አድካሚ ነበር፡፡ እንደዛም በምሰራበት ሰዓት ላይ ሰኞ ሙሉ ቀን ከቤት ሳልወጣ ነበር የምውለው፡፡ ግን በጣም ደስ የሚል ነበር፡፡

ቆንጆ፡-  በፊት የትያትር የተመልካች ይህ ነው የሚባል አልነበረም አሁን ግን ተመልካቹ ራሱ ወደ ትያትር እያደላ ይገኛል፡፡ ይህንን እንዴት ታየዋል?

ሳምሶን፡- ለሁሉም ጊዜ አለው አይደል የሚባለው ግን ደግሞ አሁን ያሉት ስንት ትያትር ቤቶች ናቸው የአዲስ አበባ የሕዝብ ቁጥርስ ምን ያህል ነው? ያሉት ትያትር ቤቶች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከሶስት አይበልጡም፡፡ እናም ይህ ካለው የሕዝብ አኳያ በቂ አይደለም፡፡ ጥሩ ነገር፡፡ ከሰራህለትና ካዘጋጀህለት ሕዝቡ ይመጣል፡፡ አሁን አይተኸው ከሆነ ፊልም ቤቶችን ተመልካች አላቸው፡፡ ግን ደግሞ ትያትር ቤቶች በኋይለስላሴ ጊዜ የተሰሩ ናቸው፡፡ ያኔ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ስንት ነበር? ዛሬ ላይስ ስንት ነው ያለው በጣም ብዙ እጥፍ ነው ያደረገው፡፡ እናም በነዚህ ትንሽ ትያትር ቤቶች አሁን ያለው ተመልካች በዝቷል፡፡ ማለት አትችልም እንደውም አዳራሹ በጣም ሞልቶ ነው መመለስ ያለበት፡፡

ቆንጆ፡- የጥበብ ሙያ ለነፍስም ሆነ ለስጋ አስፈላጊ የሆነ ሙያ ነው ይባላል ላንተስ?

ሳምሶን፡- እውነት ነው!! በተለይ ከሥጋን በሌላ በምግብም ሆነ በሌላ ነገሮች ሊሞላ ይችላል ወደ ሙዚቃ አርቱ፣ ትያትሩ ስትመጣ ነፍስህን የሚያስደስቱ ናቸው የግድ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ናቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ቆንጆ፡- ምን አይነት ገፀ-ባህሪ መጫወት ያስደስትሃል?

ሳምሶን ፈታኝ የሆነና በጣም የሚያታግል የውስጥህን ስሜት ሊያወጣ የሚችል ቅርጽ ያለው በደንብ የተገነባ ገፀ- ባህሪ መጫወት ደስ ይለኛል፡፡

ቆንጆ፡- ይህንን ገፀባህሪ ባልተጫወትኩኝ ያልከው አለ?

ሳምሶን፡- አይመስለኝም…. የለም

ቆንጆ፡- አሁን እየተሰሩ የሚገኙ ፊልሞች ላይ ብዙ አትታይም? ወይስ ሰርተሃቸው ያልወጡ አሉ?

ሳምሶን፡-አዎ ሰርቼ ያልወጡ ፊልሞች አሉ አሁን በቅርብ ጊዜ ከሁለት ወር ወይም ከሶስት ወር በኋላ ገበያ ላይ ይውላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ አንድ ወቅት ላይ ተከታትሎ ይወጣል፡፡አንድ ወቅት ላይ ደግሞ ሌላ ሥራ ላይ ስትሆን ጠፍ ልትል ትችላለህ፡፡

ቆንጆ፡- አርቲስት ባትሆን ኖሮ ምን ሆናለሁ ብለህ ታስባለህ?

ሳምሶን፡- ባይን የሚባል ነገር የለም፡፡ የሆነው ነው የሚሆነው፡፡ የሆነው ባይሆን ኖሮ አይሆንም ነበር፡፡

እሱን ማወቅ አይቻልም፡፡ አንድ ሾፌር ሹፌር ባትሆን ምን ትሆን ነበር ብትለው ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ ሕይወት በየትኛው መንገድ ልትወስድህ እንደምትችል አታውቃትም፡፡ ምን አልባት ነጋዴ ሹፌርጻደር ሀኪም መሆን እችላለሁ፡፡ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቀውም፡፡

ቆንጆ፡- ለዚህ ሙያ ነው የተፈጠርኩት ብለህ ታስባለህ?

ሳምሶን፡- እግዚአብሔር ይመስገን አዎ፡፡

ቆንጆ፡- ወደፊት በሙያህ ለወገንህ ምን የተለየ ነገር ለመስራት አስበሃል?

ሳምሶን፡- እንግዲህ ብዙ እናትና አባት የሌላቸው ሕፃናቶች አሉ፡፡ አረጋዊያንና የሰው እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ከፈቀደልኝና ከተሳካልኝ እንደዚህ አይነቶችን ሰዎች ማገዝና መርዳት አስባለሁ፡፡

ቆንጆ፡- እስኪ አሁን ደግሞ ስለቤተሰቦችህ አጫውተኝ?

ሳምሶን፡- ሰባት ነን… ሶስት ሴቶችና አራት ወንዶች ነን እቤት ውስጥ ያለነው፡፡ እናቴ ቱቱ ታደሰ ትባላለች ይሄ ነው የሚመስለው፡፡

ቆንጆ፡- ለቤተሰቦችህ ስንተኛ ልጅ ነህ?

ሳምሶን፡- እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡

ቆንጆ፡- ቤተሰቦችህ ስላለህበት ኪነ-ጥበብ ሙያ ምን ይላሉ?

ሳምሶን፡- ሁሉም ደስተኞች ናቸው በነገራችን ላይ አያቴ ነው ያሳደገኝ፡፡ እሱ በሕይወት ኖሮ ይህን ነገር ቢያየው በጣም በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በጣምም የሚቆጨኝ ይሄ ነገር ነው፡፡ በሕይወት ኖሮ ቢያየኝ በጣም ደጋፊ ይሆነኝ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ ሊቃወመኝ እንደሚችል አውቃለሁ በኋላ ላይ ደግሞ ደጋፊዬ እንደሚሆን አምን ነበር፡፡

ቆንጆ፡- የራስህን ፊልም ወይም ትያትር ለመስራት አላሰብክም?

ሳምሶን፡- ሀሳብ አለኝ አንድ ሥራ ስጨርስ ሌላ ሥራ ይተካል ካራክተሮች ያጓጉኋል፡፡ ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ እያልኩ ነው እስካሁን የቆየሁት፡፡ ወደ ፊት ግን በፈጣሪ ፈቃድ እንደምሰራ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ቆንጆ፡- ጥሩ የሚባል ድምጽ አለህ፡፡ ለምን የድምጽ ማስታወቂያ ሥራዎችን አትሰራም? ወይስ ማስታወቂያ መስራት ስለማትፈልግ ነው?

ሳምሶን፡- ስለማፈልግ አይደለም .. እንዳልኩህ ለሁሉም ጊዜ አለው አሁን እኔ በዚህ ዕድሜ ላይ አክቲንጉን በደንብ መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ እናም ወደፊት ብዙ ማስታወቂያዎች ላይ ድምፄ እንደሚሰማ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ቆንጆ፡- በሕይወትህ የእኔ ነው የምትለው ጀግና ማነው?

ሳምሶን፡- አሁን ስንት ሺዎች ጀግኖች ባላት ሀገር ጀግናን መምረጥ ይከብዳል፡፡ ለእኔ ግን ቢኒያም ወርቁ ጀግና ነው፡፡

ቆንጆ፡- ከአርት ውጪ በልጅነትህ የምትወደው የሙያ ዘርፍ ነበር?

ሳምሶን፡- በጣም የሚገርምህ በልጅነቴ ግቢ ውስጥ ስጨፍርና ስዘፍን ነበር የምውለው በተለይ ሮክ ዘፈኖችን በቴሌቪዥን ላይ ላይ በጣም እመሰጥ ነበር፡፡ አለባበሳቸውና ዳንሳቸው በጣም ይመስጠኝ ነበር፡፡

ቆንጆ፡- ከሥራ ባልደረቦችህ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ያህል ድረስ ነው?

ሳምሶን፡- የሥራው ባህሪ እራሱ ነው የምትሆነው፡፡ አትለያይም ሌላ ስትሰራ ሌላ ቤተሰብ ትመሰርታለህ፡፡ እናም ብዙ ቤተሰብ እየኖረህ ነው የምትሄደው፡፡ ከሁሉም ጋር ያለኝ ግንኙነት የእህትና የወንድም ነው፡፡

ቆንጆ፡- በትርፍ ጊዜ ምን ያዝናናሃል?

ሳምሶን፡- ፊልም ማየት መጽሐፍ ማንበብ ሙዚቃ መስማት ከጓደኞቼ ጋር መሰባሰብ ያዝናናኛል፡፡

ቆንጆ፡- ብዙ ሴቶች ያስቸግሩሃል ይባላል እውነት ነው?

ሳምሶን፡- አይ.. አይ ውሸት ነው አያስቸግሩኝም፡፡

ቆንጆ፡- ኩራተኛ ነው ይባላል ይህስ እውነት ነው?

ሳምሶን፡- ….. ሳቅ አረ አይደለም፡፡ ምን አልባት የፊቴ ቅጽ አቀማመጥ ይሆን? አይገባኝም እንዳልኩህ አያቴ ነው ያሳደገኝ ብዙ እሱን የሚመስል ነገሮች አሉኝ ግንባሬ ኮስተር ይላል መሰለኝ ከድምፄም ጎርናናነት ይሁን አላውቅም ግን በፍጹም ኩራተኛ አይደለሁም፡፡

ቆንጆ፡- ለሴት ልጅ ያለህ አመለካከት ምን ይመስላል?

ሳምሶን፡- ሴት ልጆች ለወንዶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ለእያንዳንዱ የተሳካለት ወንድ አንድ ጠንካራ ሴት ከጀርባው አለች ይባላል፡፡ እናም ብዙ ነገር እኛን የማንችላቸው ነገሮች እነሱ የሚችሏቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለሕይወታችን ደጋፊዎች ናቸው፡፡

ቆንጆ፡- ማፍቀር ያስደስትሃል ወይስ መፈቀር?

ሳምሶን፡- ማፍቀር ነው እንጂ!!! ማፍቀር ያስደስተኛል፡፡

ቆንጆ፡- ፍቅርን እንዴት ትገልፀዋለህ?

ሳምሶን፡- ለእኔ ፍቅር ማለት ሁሉንም ሰው ማፍቀር ነው፡፡ ሁሉንም ስታፈቅር እግዚአብሔር ያፈቅርሃል፡፡ እናም እርስ በእርስ መፈቀር ነው የሚያድንህና የሚያዋጣህ፡፡

ቆንጆ፡- እውነተኛ አፍቃሪ ነኝ ትላለህ?

ሳምሶን፡- አዎ.. እውነተኛ አፍቃሪ ነኝ፡፡

ቆንጆ፡- ከሴት ልጅ ውበት ምን ይማርክሃል?

ሳምሶን፡- ከባድ ጥያቄ ነው! ከሴት ልጅ ውበት ስትል አሁን ሞዴሎች በሁለት ከፍለውታል ውስጣዊና ውጫዊ ብለው ከሁሉም ግን ልብ ነው የሚማርከው፡፡ ላንተ የምትሰጥህ ነገር ይህ ነው ብለህ ምንም የምታውቀው ነገር አይደለም ፍቅር ምን መሰለህ የምትናገረው ሳይሆን የምታደረገው ነገር ነው፡፡ ትንታኔ ልትሰጥበት አትችልም፡፡

ቆንጆ፡- ዝምተኛ ወይስ ተጫዋች ሴት ትመችሃለች?

ሳምሶን፡- ተጫዋች ሴት ትመቸኛች፡፡

ቆንጆ፡- ከሴት ልጅስ የምትወድላት ባህሪስ?

ሳምሶን፡- ታማኝነቷን

ቆንጆ፡- ፍፁም የሆነች እህቴ ናት የምትላት የሴት ጓደኛ አለችህ?

ሳምሶን፡- የሁሉም ሴት ጓደኞቼ እህቶቼ ናቸው፡፡

ቆንጆ፡- ያንተን አርያ ለመከተል የሚፈልጉ ወጣቶች ምን ማስተላለፍ ትፈልጋለህ?

ሳምሶን፡- ይህንን ሙያ ለመከተል ለሚፈልጉ ሰዎች ሙያው የሚፈልገው ነገር ጽናት ነው፡፡ በጣም ተግቶ መስራት ነው፡፡ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች አሉ ብዙ ሞራልን የሚነኩ ነገሮች ያጋጥማሉ፡፡ ያሉትም መድረኮች ውስን ናቸው፡፡ መድረክ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ነድረኩንም ካገኘህ በኋላ ልታጣው ትችላለህ፡፡ ብዙ ብዙ የተወሳሰቡ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ወጣቶች ይህንን ነው መታገልና አሸንፎ ማለፍ ያለባቸው ሌላው ነገር ደግሞ መፋቀርና መዋደድ ነው፡፡ ታላላቅን ማክበር እግዚአብሄርን ማክበር በአጠቃላይ ሰውን ማክበር ይገባል፡፡ አርቲስት ስትሆን ንፁህ መሆን አለብህ፡፡ ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር መኖር አለብህ፡፡ ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር መኖር አለብህ፡፡ ውስጥ ክፋት ሳይሆን ንጽህና ያስፈልጋል፡፡

ቆንጆ፡- በመጨረሻም ማመስገን የምትፈልጋቸው ሰዎች ካሉ?

ሳምሶን የምወዳቸው ወገኖቼን ከቤተሰብ ጀምሮ የኢትዮጵያን ህዝብና ጓደኞቼን እንኳን አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

ቆንጆ፡- ለነበረን ቆይታ በቆንጆ መጽሄት አንባቢያን ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ሳምሶን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡