Biography Catagories

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ሰሎሜ ታደሰ ምህረቱ

 

ሰሎሜ ታደሰ ምህረቱ

የማህበረሰብ መብት ተሟጋች፣ ሥራ ፈጣሪ፣ አነቃቂ ዲስኩር  አቅረቢ፣ የሚዲያ ስራ አስፈፃሚ


ሰሎሜ ታደሰ ምህረቱለጊዘው ልንቸገር እንችላለን፡፡ 
ዋናው ነገር ግን በውስጣችን ያለውን እምነት እና የሚገጥሙንን መልካም እድሎች እንዴት እንደምንጠቀምባቸው ማወቅ ነው፡፡

አባቴ ህልምን መተለም አስተምሮኛል፡፡ ትላልቅ ነገሮችን መስራት እችላለሀሁ፣ የሚል እምነት እንዲያድርብኝ የሚያስችለኝን ልበ ሙሉነት ያስታጠቀኝ እሱ ነው፡፡ ይሄ ለእኔ ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ በእርግጥ ይሄን ታላቅ ስጦታ እንዴት መጠቀም እንደምችል ለማወቅ የተወሰነ ጊዜ ፈጅቶብኛል፡፡ ወጣት ሳለው ጥሩም ይሁን መጥፎ ሁሉን ነገር የመቃወምና የመፈታተን አመል ነበረብኝ፡፡ በዕድሜ ስበስል ግን ነገሩ ከሰዎች እንደሚያራርቀኝ እየተገነዘብኩ በመምጣቴ ባህሪዬን አስተካክልኩ፡፡ 29 ዓመት ገደማ እስኪሆነኝ ድረስ ከራሴ ማንነት ጋር ሰላም መፍጠር የቻልኩ አይመስለኝም፡፡ ይሄኔ ነው ስለራሴና ስለሕይወት ጉዞዬ መፈተሸ፣ የጀመርኩት፣ ለመሆኑ ምን ያህል አበረከትኩ፣ እንዴትስ ነው ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳደርኩት፣ እናከመነሻውስ የመኖሬ ፋይዳ ምንድነው፣ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ በንቃት ማሰብ ያዝኩ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አሁን ድረስ ለራሴ የማቀርባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በእርግጥም ማንነትን ለሰዎች ከማረጋገጥ ይልቅ ራሴን ሆኜ ለመኖር መቻል ሺ ጊዜ የተሸለ ነው፡፡

እናቴ አሰፋሽ ካሳሁን ብርቱና ለጋስ ሴት ናቸው፡፡ አምስት ልጆቿን ጨምሮ እኔ የበኩር ልጅ ነኝ) ከዘመድ አዝማዱ ጋር 16 የሚደርሰውን የቤተሰቡን አባላት ቀጥ አድርጋ ታስተዳድር ነበር፡፡ ቤት ያፈራውን ተካፍሎ መብላትን፣ ከሰዎች ጋር በደስታ መኖርንና ሕይወትን ቀለል አድርጎ መመልከትን የተማርኩት በለጋ እድሜዬ ነው፡፡ ከቤታችን ጠፍቶ የማያውቀውን ሳቅና ጨዋታ እያጣጣምኩ ነበር የልጅነት እድሜየን ያሳለፍኩት፡፡ እናቴ መምህርት ነበረች፡፡ በ13 ዓመቴ አባቴ ከሞተ በኋላ ያንን ሁሉ ቤተሰብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ደሞዟ ቀጥ አድርጋ አስተዳድራለች፡፡ ለጊዜም ልንቸገር እንችላለን፡፡ ዋናው ነገር ግን በውስጣችን ያለውን እምነት እና የሚገጥሙንን መልካም ዕድሎች እንዴት እንደምንጠቀምባቸው ማወቅ ነው፣ ይሄንንም የተማርኩት ከእናቴ ነበር፡፡

አባቴ በእኔ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ መጀመሪያ በዕደማርያም ላቦራቶሪ ትምህርት ቤት ፣ ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምሯል፡፡ በኋላ ላይ ከጓደኞቹ ጋር ዓለም የሕዝብ ግንኙነት የተባለ ድርጅት አቋቋመ፡፡ አባቴ በአዕምሮ ብሩንነትም ሆነ በቁንጅና ማንም ጫፌ ላይ እንደማይደርስና የተፈጠርኩትም ታላላቅ ነገሮችን ለማከናወን እንደሆነ እየነገረኝ ነበር ያደግሁትና ራሴን ሰማይ አሳክዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ የትምህርት ውጤቴ ጥሩ ይሁን እንጂ በትምህርት ቤት ረባሽ መሆኔ አባቴን አያሳስበውም ነበር፡፡ እንደውም ለረባሽነቴ ሰበብ ይፈጠርልኝ ነበር፡፡ ሌላው ተማሪ ሙሉ ቀን የሚፈጅበትን ትምህርት፣ የኔ ልጅ በግማሽ ቀን ፉት ትለዋለች፡፡ ከዚያ ምን ታደርግ? ይሰለቻታል፣ ለዚህ ነው ረባሽ የሆነችው” እያለ እናቴን ለማሳመን ሲሞክር አስታውሳለሁ፣ እኔም ታዲያ ያንን አምኜ እቀበል ነበር፡፡ በወ.ወ.ክ.ማ የሚዘጋጀውን የተማሪዎች ክርክር እሱ በሊቀ-መንበርነት ሊመራ ሲሄድ እኔንም ይወስደኝና ክርክሩን እንድከታተል ያደርጋል፡፡ ዝግጅቱም ተጠናቆ ወደቤታችን ስንመለስ ደግሞ፣ በክርክሩ የተለያዩ ሀሳቦችን ይዘው የተሳተፉትን ሁለቱንም ወገኖች ተከራክሬ የምረታበትን ዘዴና ብልሃት ያስተምረኝ ነበር፡፡ አባቴ በልጅነቴ በውስጤ ያሳደረብኝ ልበ ሙሉነት አሁንም ድረስ አብሮኝ አለ፡፡

አባቴ በ42 ዓመቱ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ሲያልፍ፣ ሰማይ የተደፋብኝ መሰለኝ፡፡ መላ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት ጫንቃዋ ላይ የወደቀባት እናቴ የምታፈናፍን አልነበረችም፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ወጥቼ ሻይ ቡና እንድል እንኳን አትፈቅድልኝም ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብገባም አልተሳካልኝም፡፡ ከቤቴ ወጥቼ በዩኒቨርሲቲ መኖሪያ ቤት ስኖር የመጀመሪያዬ ስለነበር፣ አዲሱን ነፃነቴን ሳጣጥም ትምህርቱን ችላ አልኩትና በፈተና ወደቅሁ፡፡ እንደ አባቴ ሃሳብ ቢሆን ኖሮ ወደ አሜሪካ ሄኔ ነበር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን የምከታተለው፡፡ ይሄ እንደማይሳካ ሲገባኝ፣ ማስቸገር ጀመርኩ፡፡ ይሄኔ ለሩሲያ ነፃ የትምህርት ዕድል እንዳመለክት ቤተሰቤ ወሰነ፡፡ በወቅቱ ውሳኔውን ተቃውሜ ነበር፡፡ የሚሰማኝ አላገኘሁም እንጂ፡፡ የሆነው ሆኖ የትምህርት እድሉን አገኘሁና ወደ ሩሲያ ሚኒስክ ተጓዝኩ፡፡ እዚያ የገጠመኝ ነገር ጨርሶ ያልጠበቅሁት ነበር፡፡ ሕዝቡንና ባህሉን ወደድኩት ቋንቋውና ስነ-ጽሁፉም ማረከኝ፡፡ ከቤተሰቤ ጋር የምገናኘው በደብዳቤ ብቻ ነበር፡፡

በአጭር ጊዜ
ውስጥ ሌላ ሰው ሆንኩ፤ በፍጥነትም በአእምሮ በሰልኩ፡፡ ከአራት ዓመትሰ በኋላ ግን ያላሰብኩት ችግር ተፈጠረ፡፡ እዚያው የተቋቋመ የኢትዮጵያ ወጣቶ ማህበር፣ ፀረ-አብዮተኛ ብሎ ወነጀለኝ፡፡ እግሬ አውጪን ብዬ ከሩሲያ በማምለጥ በፖላንድ በኩል ጀርመን ገባሁ፡፡ ሩሲያና ኢትዮጵያ በወዳጅነት የከነፉበት ወቅት ስለነበር፣ መዘዙ ለቤተሰቦቼም እንዳይተርፍ ሰግቼ ደብዳቤ መፃፃፉንም ተውኩት፡፡ ጀርመን ውስጥ የጠበቀኝ የስደት ኑሮ የከፋ ነበር በማትፈልገኝ አገር ውስጥ ወይ አልኖርኩ ወይ አልሞትኩ በሚያሰኝ እንጥልጥል ሕይወት ውስጥ ሞራል የሚያላሽቅ አስጨናቂ ጊዜ አሳለፍኩ፡፡ ጥሎ አይጥልም እንዲሉ፣ ደጋግ ሰዎች አላጣሁም፡፡ ያንን ክፉ ጊዜ ያሳለፍኩት በእነሱ እርዳታ ነበር፡፡ የማታ ማታም በአሜሪካ ጥገኝነት አገኘሁ፡፡ አሜሪካ ሄጄም ቢሆን ደጋግ ሰዎች ላይ ነበር የወደቅሁት፡፡ በእነሱ ድጋፍ፣ በማውንት ሆልዮክ ኮሌጅ ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘሁ፡፡ በኮሌጁም ትምህርቴን ተከታትዬ በ27 ዓመቴ በአለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪዬን አገኘሁና የአባቴን ምኞት ለማሳካት በቃሁ፡፡

ከዚያም ወደ ቦስተን ሄጄ ሥራ ጀመርኩኝ፡፡ ታናናሾቼንና እናቴን ወደ አሜሪካ አምጥቻቸው ስለነበር እነሱን ለመርዳት በሁለት ቦታዎች መስራት ነበረብኝ ከሰኞ እስከ አርብ በስደተኞች ማዕከል ስሰራ ቅዳሜና እሁድን ደግሞ በቦስተን ሎገን አውሮፕላን ማረፊያ የስጦታ መደብር አስተዳድር ነበር፡፡ በኋላ ላይ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ሄጄ የአባቴ ወዳጅ አቶ ፀሐይ ተፈራ በሚመሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ልማት  ምክር ቤት ውስጥ መስራት ጀመርኩ፡፡ በ1983 ኣ.ም የደርግ ወታደራዊ መንግስት ከስልጣን ሲገረሰስ፣ አለቃዬ በአቶ ፀሐይ አማካኝነት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በአምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ፕሬስ አማካሪነት ተቀጠርኩ፡፡ በኤምባሲው ስቀጠር ስለፕሬስ አማካሪነት የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ጥልቅ የሥራ ስሜት የነበራቸው የሥራ ባልደረቦቼ ምስጋና ይግባቸውና፣ በእነሱ ድጋፍ ሥራ ላይ ሆኜ ሙያውን ተማርኩት፡፡ ከአዲሱ መንግስት ጋር ፖለቲካዊ ግንኙነት ባይኖረኝም፣ ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ የመቆም ዕድል እንዲያገኝ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ በኢምባሲው ለስድስት ዓመት ካገለገልኩት በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ የመስራት ፍላጎቴም ተሳካ፡፡ በቢቢሲ ሞዴል ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ እንድሰራ እንደ አዲስ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በኃላፊነት እንድመራ ተሾምኩ፡፡ የሰራተኞቹን ቅጥር አሳንሼ ባስብም 1500 ሠራተኞች እንደነበሩት ተረዳሁ፣ በዚያ ላይ ፖለቲካ ምን ያህል የሥራ ድባቡን እንደሚጫነው በቅጡ አልመዘንኩትምና እንደ ቀላል ነበር የቆጠርኩት፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ አዳዲስ ፕሮግራሞችን የመጀመር ጉጉቴ በተጨሰማሪ ቲቪ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሬግራም በኢቴቪ ከመጀመራችን በተጨማሪ ቲቪ አፍሪካ የተሰኘ ፊልሞችን የሚያሰራጭ ሁለተኛ ቻናል ከፍተናል፡፡ በኔ በኩል፣ ሕብረተሰቡ ኢቴቪን ወዶትና ተማርኮበት እንዲመለከተው እንጂ አማራጭ የቴሌቪዥን ሥርጭት ሳላጣ ብቻ እንዲያየው አልፈልግም ነበር፡፡ ጋዜጠኞቹ አዳዳዲሶቹን ፕሬግራሞች ማራኪ ለማድረግ፣ እጥፍ ድርብ ትጋት አሳይተዋል፡፡ ትጋታቸውም ታዲያ መና አልቀረም፡፡ ሕብረሰቡ ፕሮግራሞቹን ወደዳቸው፡፡ በድርጅቱ የአራት አመታት ቆይታዬ፣ ግሩም የባለሙያዎች ቡድን ድጋፍ አልተለየኝም፡፡

ድርጅቱን በመራሁባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት ከ1990 እስከ 1992 ዓ.ም)፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዙሪያ የመንግስት ቃል አቀባይ በመሆን አገልግያለሁ፡፡ ጦርነቱ የፈነዳው ከአሜሪካ ከመጣሁ ር በኋላ ነበር፡፡ አገሪቱ በጦርነት ላይ በነበረችበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት የተሸለ አስተዋጽኦ በማበርከትበት ዘርፍ የድርሻዬን የመወጣት ኃላፊነት አለብኝ የሚል እምነት ስለነበረኝ፣ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ ቀንና ሌሊት ሳልል በየዕለቱ እስከ አራት ጊዜ በተደጋጋሚ ስለጦርነቱ ሁኔታ መግለጫ አእሰጥ ነበር፡፡

ከኢዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስወጣ፣ ምንም የመስራት ዕቅድ አልነበረኝም፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር፣ መዓዛ አሸናፊ መንግስቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅትን ለመመስረት እንዳግዛት የጠየቀችን፡፡ የድርጅቱ ዓላማ የሴቶችን ድምጽ በማጉላት መብታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ድርጅቱን ለማቋቋምና መነሻ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ፣ ከዚያም ድርጅቱን የምትመራ ዋና ዳይሬክተር ለመቅጠር አመት ያህል ፈጅቶብኛል፡፡ በመቀጠል የሰራሁት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የሥነ-ፆታና ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ከዚያም ከኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ጋር ዩኒሴፍ በቀረፀው ፕሬጀክት ላይ በትብብር ሰርቻለሁ፡፡ ልጃገረዶች በትምህርት ቤት የሚጋፈጡትን ችግር ወደ አደባባይ የሚያወጡበት፣ የልጃገረዶች መድረክ የማቋቋም ዓላማ ያነገበው ይሄ ፕሮጀክት፣ በጣም የማረከኝ ሥራ ነበር ማለት  እችላለሁ፡፡ በ1994 ዓ.ም የተከሰተውን ረሃብ ለመቋቋም፣ አንድ ብር አንድ ወገን” የተሰኘውን የገንዘብ ማሳሰቢያ ዘመቻ ከጓደኞቼ ጋር የመራሁትም በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ በበጎ ፈቃደኞች የተጠነሰሰው ይሄው ዘመቻ፣ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለው በሕዝቡ የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ ነበር፡፡ ያልተሳተፈበት ዜጋ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሕፃናትን፣ የንግድ ሰዎችን፣ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ዝነኞችንና የዩኒቨርሲቲ ምሁራኖችን እንዲሁም የወታደሩን ክፍል ሳይቀር ባሳተፈው ፕሮጀክት፣ 14 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡ በወቅቱ ለወገኑ ለመድረስ የድጋፍ እጁን የዘረጋው የሰው ብዛት ሲታይ፣ ሁለመናን በስሜ የሚያጥለቀልቅ ኃይል ነበረው፡፡

ከዚህ በኋላም በመላው አፍሪካ የአመራር ሰጪነት ፕሮግራም ከሚቀርፁ አምስት ሴቶች አንዷ አንድሆን ከብሪቲሽ  ካውንስል ሀሳብ ቀረበልኝ፡፡ ይህንኑ በመቀበል ፕሮግራም በመቅረጽ ብቻ ሳይሆን፣ ተግባራዊ የሚያደደርጉ ሰዎችን በማሰልጠን ለአራት ዓመታት ሰራሁ፣ ከእውቀታችን ከተሞክሯችን ጋር አብሮም እያደገ የመጣ መመሪያም አወጣን፡፡ ይሄ አጋጣሚ በአንድ በኩል አፍሪካን በቅጡ እንዳውቃት ዕድል የፈጠረልኝ ሲሆን፣ በሌላ በኩልም ደግሞ ፕሮግራማችን ለማቀድና ለመቅረት የሚያስችል ልበሙሉነትን እንዳዳብር አስችሎኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች እርስ በእርሳቸው ሲሳካልሽ እርስ በርስ እንዲደጋገፉና አንቺ ሲሳካልሽ እኔም ይሳካልኛል፤ አንቺ ስትደምቂ እኔም እደምቃለሁ” የሚል ባህል እንዲኖራቸው እመኛለሁ፡፡

ኢመርጅ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር የተባለ የራሴን አማካሪ ድርጅት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የመሰረትኩት ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ የልጃገረዶችን አቅም የሚያጎለብት “የኛ” የተሰኘ ድንቅ ፕሮጀክት ላይ መስራት ጀምረናል፡፡ ኢመርጅን እንደገና በአዲስ መልኩ የማቋቋም ዕድሉ ቢሰጠኝ፣ የምክር አገልግሎት ተቋም ከማድረግ ይልቅ፣ በአመራር፣ በሥነ-ፆታና በተግባቦት ዙሪያ ድንቅ ውይይቶች የሚያብቡበት፣ እንዲሁመ ለትግበራ የሚመቹ አዳዲስ ሀሳቦች የሚፈልቁበት የልህቀት ማዕከል ነበር የማድርገው፡፡ በአዲስ አበባ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሃውልት ለማሳነጽና የራሴን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመጀመር አልማለሁ፡፡ የሴቶች ኮሌጅ የመክፈት ህልምም አለኝ፡፡

ለሥራ የሚገፋፋኝ ኃይል የሚመነጨው፣ እዚህ ምድር ላይ ያለሁት ለዓላማ ነው” ከሚለው እምነቴ ነው፡፡ ይህ እምነቴ “የሚረበቅብኝ ያህል አልሰራሁም የሚል ሀሳብ ሽው ሲልብኝ፣ አንዳንዴ የመረበሽና ያለመረጋጋት ስሜት ይፈጥርብኛል፡፡ ይሄም  ሆኖ ግን ሥሰራ እቅሜን ሁሌ አንጠፍጥፌ እንደምሰራ ስለማውቅ በምሰራው ሥራ እኮራለሁ፡፡ ሁሌም ለራሴ ታማኝ ነኝና በምሰራው ስራ ላይም እምነት አለኝ፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሰዎች ሁሉ ያሻቸውን ሕልም መተለም የሚችሉባት አገር እንድትሆን እመኛለሁ፡፡ አሜሪካ ታላቅሰ አገር ለመሆን የበቃችው፣ ሰዎች ያሻቸውን ማለም የሚችሉባት አገር ስለሆነች ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ብቃትና አቅም እንዲሁም የማለም ችሎታ የሚለመልሙባትና የሚከበሩባት አገር እንድትሆን እሻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች እርስ በርስ እንዲደጋገፉና “አንቺ ሲሳካልሽ እኔም ይሳካልኛል፣ አንቲ ስትደምቂ እኔም እደምቃለሁ” የሚል ባህል እንዲኖራቸው እመኛለሁ፡፡

ለልጃገረዶች በራሳችሁ ላይ እምነት ይኑራችሁ፣ ራሳችሁንም አድንቁ፤ የምትሹትን ነገርም እንደሚገባችሁ እመኑ እላለሁ፡፡ መሆን የምትሹትን ሁሉ መሆን ትችላላችሁ፡፡ ለሌሎች ሰዎች ወሬም እምብዛም አትጨነቁ፤ ይልቁንም ከራሳችሁ ጋር ለምታደርጉት ውይይት ትኩረት ስጡ፡፡ ጥላችሁም የምትሄዱት የእግራችሁ አሻራ ለሌሎች በር የሚከፍትና ጥርት ብሎና ደምቆ የሚታይ መሆኑም እርግጠኞች ሁኑ፡፡