Quick Links

 

 

 

 

አዲሷ አለም አቀፍ የቡና ቢዝነስ ተፅዕኖ ፈጣሪ

 

 

ዓለም አቀፍ የቡና ቢዝነስ

አገልግሎት ከጨረሱ የመኪና ጎማዎች እንዲሁም ከተለያዩ ግብዓቶች ልዩ ልዩ ጫማዎችን በማምረት፣ በአጭር ጊዜም በዓለም ገበያ ውስጥ ታዋቂነትን በማትረፍ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን የተጎናጸፈችው ቤተልሔም ጥላሁን፣ የኢትዮጵያን ልዩ ቡናዎች ለዓለም በማስተዋወቅ ዳግመኛ ተፅዕኖ ለመፍጠር ተነስታለች፡፡

 

ለአካባቢ ጥበቃ የሚያደርጉት አስተዋጽኦና ትርጉም ተቀባይነትን ያስገኘላቸው፣ ‹‹ሶልሬብልስ›› በሚባል የንግድ ምልክት በዓለም ላይ ታዋቂነትን ያተረፉ የጫማ ምርቶችን ስታቀርብ የቆየችው የሶልሬብልስ ኩባንያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁን፣ በአሁኑ ወቅት በቡና ንግድ መስክ የጫማዎቿን ያህል ስኬታማ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀቷን ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያን የቡና ባህል የሚያንፀባርቁ የቡና መሸጫ መደብሮችን በተለያዩ ከተሞች ለመክፈት እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ ለሪፖርተር የገለጸችው ቤተልሔም፣ ከሁለት ወራት በኋላ ሁለት የቡና መሸጫ መደብሮችን በአሜሪካ ከተሞች ለመክፈት ማቀዷን አስታውቃለች፡፡  በአሁኑ ወቅት የቡና ብራንዶችን የሚወክሉ የዲዛይንና የማስተዋወቂያ ሥራዎች ዝግጅት ላይ መጠመዷን የገለጸችው ቤተልሔም፣ ‹‹በኢትዮጵውያን ባለሙያዎች በእጅ የተቆላ›› የሚል መልዕክት የሚኖረው ‹‹ጋርደን ኦፍ ኮፊ›› ወይም በግርድፉ ‹‹የቡና ገነት›› የተባለ ብራንድ ይዛ ወደ ዓለም ገበያ እንደምትወጣ ይጠበቃል፡፡

በማኅበራዊ ድረ ገጿ ‹‹ሲዳሞ ሌጀንደሪ›› የተሰኘና የሲዳማ አካባቢን የሚወክል ቡና፣ ‹‹ሐረር ሬጋል›› የተሰኘው ደግሞ የሐረርን ቡና፣ ‹‹ጂማ ሉክስ›› የተሰኘ የጂማን ቡና እንዲሁም ‹‹ይርጋጨፌ ማጂክ›› የተሰኘ የይርጋጨፌ ቡናን የሚወክል የልዩ ቡናዎች ብራንድ ይፋ አድርጋለች፡፡ እነዚህ ቡናዎች በልዩ ቡና (ስፔሻሊቲ) አብቃይነትና አምራችነት ከሚታወቁ የአገሪቱ አካባቢዎች በብዛት ታዋቂዎቹ ሲሆኑ፣ በተለይ የይርጋጨፌ፣ የሲዳማና የሐረር ቡናዎች በዓለም የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ የተገኘባቸው የኢትዮጵያ ቡናዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በእጅ የተሠሩ፣ ካገለገሉ የመኪና ጎማዎችና ከተለያዩ ቁሳቁሶች በመጠቀም በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ፣ ልዩ ጫማዎችን የሚያመርተው ሶልሬብልስ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም 12 ያህል የመሸጫ መደብሮችን ያስተዳድራል፡፡ እንደ ቤተልሔም ማብራሪያም እሥራኤል የሶልሬብልስ ምርቶች መዳረሻ አገር ለማድረግ ዝግጀቶች ተጠናቀዋል፡፡ አዲስ መደብር በእሥራኤል ከተማ፣ በቴል አቪቭ እንደሚከፈት ይጠበቃል፡፡

ልዩ የሰንደል ጫማዎችን፣ የወንዶችና ሴቶች ሽፍን ጫማዎችን፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ቀበቶዎችንና በቅርቡም የቆዳ ውጤቶች የሆኑ አልባሳትን ወደ ማምረቱ የገባችው ቤተልሔም፣ በተለይ ጫማዎቿ በዓለም ገበያ ከ80 ዶላር ጀምሮ እንደሚሸጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሜሪካ ከሦስት ዓመት በኋላ አሁን ያላትንና በካሊፎርኒያ ግዛት፣ ቢቨርሊ ሒልስ የሚገኘውን የሽያጭ መደብር ጨምሮ ወደ 50 የሚደርሱ ሱቆች እንደሚከፈቱ ከሶልሬብልስ ኩባንያ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህም በሻገር ከስድስት ዓመታት በኋላ በመላው ዓለም የሚንቀሳቀሱት የሶልሬብልስ ሱቆች ብዛት 500 እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

ከ12 ዓመት በፊት የተመሠረተው ሶልሬብልስ፣ በዓለም የፌር ትሬድ ተቋም ዕውቅና የተሰጠው የመጀመሪያው ኩባንያ መሆኑም ይታወቃል፡፡ በዚህም በአፍሪካ በፍጥነት እያደገና በዓለም እየተስፋፋ የሚገኝ ብራንድ ለመሆን የበቃው ሶልሬብልስ ኩባንያ፣ የአሜሪካውን ጨምሮ በባርሴሎና፣ በቪዬና፣ በዙሪክ፣ በአቴንስ፣ በቶኪዮ፣ በሲንጋፖር፣ በታይዋን፣ በቶሮንቶና በሌሎችም የዓለም ከተሞች የከፈታቸው የሽያጭ ሱቆች፣ ኩባንያው እግረ መንገዱን በአካባቢ ጥበቃ መስክ ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ የሚገኝ ተቋም መሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነትን እንዲያተርፍ ካስቻሉት መካከል የሚጠቀስለት ስኬታማ ተግባሩ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በ20 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል ዘመናዊ ፋብሪካ በመትከል ላይ የምትገኘው ቤተልሔም፣ ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር በአሁኑ ወቅት በቀን የሚመረተው 200 ጥንድ ጫማ ወደ 2500 ጥንድ ጫማ ከፍ እንደሚያደርገው ስትገልጽ ትታወሳለች፡፡ ቤተልሔም በአጭር ጊዜ ውስጥ ባስመዘገበቻቸው ስኬታማ የንግድና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የተነሳ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለመቀዳጀት በቅታለች፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የፎርብስ መጽሔት ከ20 ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣት ሴቶች መካከል አንዷ ለመሆን የበቃችበት ጊዜ ይታወሳል፡፡ ከዚያም ወዲህ ከአሥር ዋና ዋና ተፅዕኖ ፈጣሪና ስኬታማ አፍሪካዊ ሴቶች ተርታ ተመድባለች፡፡

‹‹የአፍሪካ ስቲቭ ጆብስ›› የሚሏትም አልታጡም፡፡ ዓምና ካገኘቻቸው ሽልማቶች መካከል ‹‹የአፍሪካ ሴቶች ሽልማት›› አንዱ ሲሆን፣ ቻምናም ከ100 ፈጣሪ ሰዎች መካከል ማለትም እንደ ማርክ ዙከርበርክ (የፌስቡክ መሥራች)፣ እነ ቢል ጌትስ (የማይክሮሶፍት የጋራ መሥራች) ተርታ ስሟ ሊሰፍር በቅታለች፡፡ ከዚህም በሻገር የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን ተመርጣ እየሠራች እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ ዘነበወርቅ አካባቢ የመሠረተችው፣ የጫማ ማምረቻ በበርካታ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች በየጊዜው እየተጎበኘ ይገኛል፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ከጎብኚዎቿ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡


ምንጭ፡ ሪፖረተር፣ 03 Aug, 2016