Quick Links

 

 

 

 

ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የክብር አምባሳደር ሆኖ ተሰየመ:

 

Photo Source: Ezega.com

ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በቀድሞዋ የኖርዌይ ማራቶን ሯጭ በተመሠረተውና ‹‹አክቲቭ ኤጌኒስት ካንሰር›› በተባለው ፋውንዴሽን የፀረ ካንሰር እንቅስቃሴ የክብር አምባሳደር ሆኖ ተሰየመ:: የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላይላ ኮሃሪ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ ወቅት፣ ኃይሌ የክብር አምባሳደር መሆኑ ካተረፈው ዕውቅናና ትልቅ ተቀባይነት አኳያ በፀረ ካንሰር ዘመቻ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አክለው እንደተናገሩት፣ ‹‹እንደ ኃይሌ ያሉ ታላቅ ሰዎችን ማግኘታችን በጣም ጠቃሚ ነው:: እኔ በፖለቲካው መስክ እንዲሁም ስለመንግሥታችን ሥራዎች ተፅዕኖ መፍጠር እችል ይሆናል::

 

ኃይሌ ግን ወጣቶች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችልበት የተለየ ኃይል አለው:: ለኢትዮጵያና ለሥራ አጋሮቹ ብቻም ሳይሆን ለነገ የዓለም ተረካቢዎች ሁሉ ምሳሌ የሚሆን ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው፤›› በማለት ስለ አትሌቱ ተናግረዋል:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ በተመረጠ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በዓለም ተዋቂ ከሆኑ ኩባንያዎች ጋር አብሮ ከሚሠራው አክቲቭ ኤጌኒስት ካንሰር ከተባለው ተቋም ጋር በመሥራት ላይ የሚገኘው ኃይሌ፣ በኢትዮጵያ የካንሰር ሥርጭትን ለመቀነስ በሚደረጉ ክንውኖች ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር ስለሚሰጡት ጠቀሜታ እንደሚሠራ ለሪፖርተር ተናግሯል:: ምንም እንኳ ከሩጫ ስፖርት ራሱን ቢያገልም ዛሬም ድረስ ልምምድ እንደሚሠራ የገለጸው ኃይሌ፣ የአዲዳስ ኩባንያ ወኪል በመሆን በአክቲቭ ኤጌኒስት ካንሰር ፋውንዴሽን ሥራ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲሠራ መቆየቱንም ጠቁሟል:: ፋውንዴሽኑ በቀድሞዋ የኖርዌይ የማራቶን ሯጭ ጌሬት ዋይዝና አጋሮቿ የተመሠረተው እ.ኤ.አ. በ2007 ነበር::

 

በማራቶን ስፖርት ስሟ በልዩነት የሚጠቀሰው ጌሬት ዋይዝ በተለይ በኒውዮርክ ማራቶን ለዘጠኝ ጊዜ በማሸነፍ ብቸኛዋ አትሌት በመሆን ስትታወስ እንደምትኖር የታሪክ ማኅደሯ ይናገራል:: ኃይሌም ስለአትሌቷ የተለየ ብቃት ደጋግሞ አውስቷል:: በዓለም ብቸኛ የዚህ ማራቶን ደጋግሞ አሸናፊ መሆኗን አውስቷል:: ይሁንና የካንሰር ታማሚ መሆኗ ለፋውንዴሽኑ ምሥረታ ምክንያት መሆኑ ሲጠቀስ፣ አትሌቷም በዚሁ በሽታ እ.ኤ.አ. በ2011 ለሕልፈት መብቃቷን ሻለቃ ኃይሌ አስታውሷል:: እንዲህ ያሉትንና ሌሎችም በሽታዎችን ለመከላከል የኖርዌይ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎችን በየዓመቱ ወደ ኖርዌይ እየወሰደ የሚያሠለጥንበት፣ ከኖርዌይም ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ የሚማማሩበት ትምህርታዊ የልምድ ልውውጥ መድረክ ሲካሄድ መቆየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ላይላ ኮሃሪ አስታውሰዋል:: በትምህርትና በጤና መስኮች ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ፣ ኬኤፍ ኖርዌይ የተባለው መንግሥታዊ የኖርዌይ ኤጀንሲ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ12 አገሮች ቅድሚያ በመስጠት የሕክምናና የሌሎች መስኮች ባለሙያዎች ሥልጠና እንደሚሰጥ አስታውቋል::

 

ከመጪው ዓመት ጀምሮም ለኢትዮጵያ የነርቭ ሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጥ ሥልጠናን ጨምሮ ሌሎችም ድጋፎች እንደሚሰጡ ታውቋል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ስለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ሲገልጹ፣ ‹‹እንዲህ ባለው ወቅት በሰብዓዊ መብቶችና በፖለቲካ መስክ የተሻለ ብስለት በማሳየት ምሳሌነትን የምታሳይ አገር እንደምትሆን አስባለሁ፤›› ካሉ በኋላ፣ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑ የሕክምና ባለሙያዎች ተዘዋውረው ለመሥራት እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል:: በኢትዮጵያ የተወለዱ የኖርዌይ ዜጎችም በሙያቸው ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እየሠሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል::

Source: Ethiopian Reporter, ቅፅ 22 ቁጥር 1732 ,  እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2009