የላፓራስኮፒ (LAPAROSCOPY) የሕክምና ዘዴ

Laparoscopy in Ethiopia

“አሁን፣ የላፓራስኮፒ (LAPAROSCOPY) የሕክምና ዘዴ ላይ፣ ስልጠና እንዲሰጥ የተደረገው፣ ከግልና ከመንግስት የህክምና ተቋማት ለተመረጡ የማህጸን ሀኪሞች ነው። ለአገራችን አዲስ ነው። በዚህ የሕክምና ዘዴ የሰለጠነ ሰው የለም። በእርግጥ፣ በፍላጎት የሚሰሩ ሐኪሞች አሉ። ይሄ ግን ትክክል አይደለም። ምክንያቱም የምናስተናግደው የሰው ሕይወት ነውና ቢሳካ ባይሳካ በሚል ሙከራ ሊደረግበት የሚገባ ነገር አይደለም። በዚህም መሰረት በዚህ የላፓራስኮፒ የህክምና ስራ የተለየ ስልጠና ያስፈልገዋል። ስልጠናውም ሁልጊዜ ፍተሻን የሚፈልግ አይነት ነው። በላፓራስኮፒ የህክምና ቴክኒክ እኛ ከመጀመሪያው ደረጃ ላይ ነው ያለነው። ሐኪሞቹም ሆንን ታካሚዎቻችን አለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ አለም የሚጠቀመውን ቴክኒክ የሳይንስ እድገት እንድንጠቀም ለማድረግ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው። በዚህ እረገድ የማህጸን ሐኪሞች ማህበር ባደረገው ዝግጅት አሁን ለስልጠናው የተውጣጡት የማህጸን ሀኪሞች ከተለያዩ የህክምና ሙያ ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ነው። የላፓራስኮፒ ስልጠና አራት ደረጃ ያለው ነው። ከአሁን ቀደም ስልጠናውን የሰጠው ካርል ስቶርስ የተባለው ካምፓኒ ከጥቁር አንበሳ ማህጸን እና ጽንስ ዲፓርትመንት እንዲሁም ከቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ጋር በመነጋገር በኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ኢሶግ አስተባባሪነት በተለይም ለማህጸን ሐኪሞች ነው። ” ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የጽንስና ማህጸን ሐኪም እና መምህርት ከአምስት አመት በፊት ለላንቺና ላንተ አምድ ከሰጡት መልስ የተወሰደ። በዚህ የህክምና ዘዴ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያለውን ሁኔታ ምን ይመስላል ስንል ቀደም ሲል በስልጠናው የተሳተፉትን ዶ/ር ማህሌት ይገረሙን ለዚህ እትም አነጋግረናቸዋል። ዶ/ር ማህሌት የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል። “LAPAROSCOPY & HYSTEROSCOPY የተሰኘው የቀዶ ሕክምና በአለም ስራ ላይ የዋለው እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1940 ዓ/ም ጀምሮ ነው። ዛሬ በአለም ላይ ወደ 90 በመቶ የሚሆኑት ኦፕራሲዮኖች የሚሰሩት በዚህ ዘመናዊ ዘዴ በላፓራስኮፒ ሕክምና ነው።

 

በአገራችን ደግሞ ምናልባትም መሳሪያው ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም በሙያው ለመጀመሪያ ጊዜ ለባለሙያዎች ስልጠና ከተሰጠ ወደ ስድስት አመት ገደማ ይሆነዋል። የዚህ ሕክምና ባህርይ ሰውነት እንደቀድሞው የቀዶ ህክምና አሰራር ሙሉ በሙሉ ሳይከፈት በተወሰኑ ከ5-7 በሚደርሱ ቀዳዳዎች በቪድዮ ስክሪን ማለትም በተሌቪዥን መስኮት በመመልከት ሕመምን ለማስወገድ የሚቻልበት አሰራር ነው። ይህ የኦፕራሲዮን ዘዴ በጣም ትንንሽ በሆኑ ቀዳዳዎች አማካኝነት ስለሚሰራ ለታካሚው በውበትም ይሁን በሆስፒታል ቆይታ ወይንም የቀዶ ሕክምናው የሚፈጀው ጊዜ ምእጅጉ የተለየ ነው። አንዳንድ ጊዜ ታንሚዎች ቀዶ ሕክምናው ተሰርቶላቸው በሆስፒታል ሳያድሩ ወደቤታቸው የሚሄዱበት ሁኔታ አለ። ታካሚዎች በቶሎ ወደቤታቸው ሄዱ ማለት ደግሞ ጥቅሙ ለታካሚዎቹ ብቻ ሳይሆን ሆስፒታሎችም አልጋቸውን እንዲሁም ባለሙያዎቻቸውን ለሌላ ለከፋ ችግር እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው ይሆናል። ታካሚው ለኢንፌክሽን የመጋለጡን እድል በእጅጉ የሚቀንስ ሲሆን ሌሎች አንዳንድ ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ እንደ መቀስ ወይንም ጎዝ የመሳሰሉትን በተከፈተ ሰውነት ውስጥ የመርሳት እድሎችን ሁሉ የሚያስቀር አሰራር ነው። በሽተኞች ለአደገኛ ባክሪያዎች እንዳይጋለጡም ስለሚረዳ በአለም ላይ በአሁኑ ጊዜ ተመራጭ የህክምና ዘዴ ሆኖአል። ዶ/ር ማህሌት እንዳሉት በኢትዮያ የላፓራስኮፒ መሳሪያ ከገባ ወደ አስር አመት ገደማ ይሆነዋል። በወቅቱ አንድ ሙሉ በሙሉ የሰለጠነ ባለሙያ ስለነበር በእሱ ምክንያት ሕክምናው ይሰጥ ነበር። ነገር ግን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በላፓራስኮፒ የሚሰራውን ቀዶ ሕክምና ሙሉ በሙሉ ከጀመረ አራትና አምስት አመት ገደማ ይሆነዋል። ይህም በጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍል ብቻ ሳይሆን በሌላም የሰውነት ክፍሎች ለሚሰሩ ቀዶ ሕክምናዎች ነው። በአገር አቀፍ ደረጃም ስንመለከት ብዙ የህክምና ተማሪዎችን የሚያስመርቁ ዩኒቨርሲቲዎች በክኖ ሎጂው ለመስራት እየሞከሩ ያሉበትን ሁኔታ እንመለከታን።

 

በእርግጥ የባለሙያዎች ስልጠና በአገር ውስጥ ስለማይሰጥ ባለሙያዎችን ወደውጭ በመላክ ስልጠናው እንደሚሰጥና ታካሚዎችን ለመርዳት በሁሉም በኩል ዝግጁ አንደሆነ ይታወቃል።” ብለዋል። ዶ/ር ማህሌት በማከልም “ይህ ሕክምና የሚያገለግለው በተለይም በማህጸን አካባቢ በቀዶ ጥገና ዘዴ መፍትሔ ለሚሹ ሕመሞች ወይንም ደግሞ ከኦፕራሲዮን በፊት ሊታወቁ የማይችሉ ሕመሞችን ለማወቅ ይጠቅማል። ስለዚህም ጥቅሙ ሁለት ነው። 1. እንደመመርመሪያ መሳሪያ መጠቀም ይቻላል። 2. እንደሕክምና መሳሪያ ያገለግላል። የማህጸን እጢዎች... ኢንፌክሽኖች... ሕመሞች... በወር አበባ መዛባት ምክንያት የሚፈጠር የማህጸን ጠባሳን ...ምክንያታቸው ምንድነው የሚለውን ለማወቅ እንዲሁም ለመውለድ ከመቸገር አንጻ ርም ያለውን ሁኔታ ለመረዳት የሚጠቅመው የላፓራስኮፒ ሕክምና ነው። በእርግጥ በዚህ የህክምና ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎች ሁሉም አይነት ሕመምተኞች ላይሆኑ ይችላሉ። ላፓራስኮፒ የራሱ የሆነ ስነምግባር ያለው የህክምና ዘዴ ነው። ለምሳሌም በጣም ወፍራም ለሆኑ ሴቶች...መሳሪያው ወደሆድ ውስጥ ለመግባት ስለሚቸገር እና በውስጥ ያለውንም ሁኔታ ለማየት የስብ ክምችት ስለሚያስቸግር ላፓራስኮፒ ጠቃሚ አይሆንም። ከዚህም በተጨማሪ ለምሳሌ በማህጸን የውስጥ መድማት ችግር ያለባቸው ሴቶች እይታን ስለሚከልል እንዲሁም በጣም ከባድ ጠባሳ በማህጸን ውስጥ ካለ አስቸጋሪ ስለሚሆን ላፓራስኮፒ መጠቀም አይቻልም። ነገር ግን አንድ ታካሚ በላፓራስኮፒ ሊሰራለት ከተጀመረ በሁዋላ የውስጥ ሁኔታው አስቸጋሪ ከሆነ ስራው ወዲያውኑ ወደ ሙሉ ቀዶ ሕክምና ሊዛወር እንደሚችል ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ አብራርተዋል። የአሜሪካን የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ጉባኤ በድረገጹ እንዳስነበበው በላፓራስኮፒ ሕክምና ውስብስብ ነገሮች አይፈጠሩም ቢባልም ግን ሙሉ በሙሉ የተወገዱ ናቸው ማለት አይቻልም። የመጀመሪያው የአካል መመረዝ ነው። የተለያዩ ባእድ አካላት ወደሰውነት ውስጥ ገብተው የሚሰራ ስራ በመሆኑ ምንም እንኩዋን እንደቀድሞው አሰራር ከበድ ያለ ስጋት ባይሆንም አካል መመረዝ ሊከሰት ይችላል። የመድማት ሁኔታዎችም አይከሰቱም ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እጢው በላፓራስኮፒ ከወጣ በሁዋላ ተመልሶ በእንቁላል ማምረቻ ውስጥ የሚፈጠርበት አጋጣሚም አለ። ቢሆንም ግን በጣም የተሻሻለና ቀደም ሲል ከነበረው ወይንም በአገራችን አሁንም የሚሰራበት ቀዶ ሕክምና ውስብስብ አጋጣሚዎች ጋር ምንም የማይገናኝ ጠቃሚ ዘዴ መሆኑን ባለሙያዎች ይመሰክራሉ። በአገራችን ብዙ ጊዜ እንደሚታየው በተለይም የተለየ ሕክምና ወይንም የመሳሪያ አገልግሎት በሚጠየቅበት ጊዜ የረዥም ጊዜ ወረፋ እንደሚጠየቅ አስታውሰን በላፓራስኮፒ ሕክምና ያለውን ሁኔታ ዶ/ር ማህሌት እንዲያብራሩ ስንጠይቃቸው የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል። “ይህንን ነገር ከብዙ አቅጣጫ መመልከት ያስፈልጋል። ለእኛ አሁንም ቢሆን ላፓራስኮፒ አዲስ ክኖሎጂ ነው። ስለዚህ መሳሪያው የሚገኘው በተወሰነ ቦታ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰለጠነ ሐኪም ብቻም ሳይሆን የሰለጠኑ ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያ ዎችም ያስፈልጋሉ። ምክንያቱም መሳሪያዎቹ በጣም ውድና በተለየ እንክብካቤ መያዝና ጽዳታቸው መጠበቅ ያለባቸው ናቸው።

መሳሪያው በሚቀመጥበት የቀዶ ሕክምና ክፍል... መሳሪያው በትክክል እንዲያዝ የማጽጃ ሁኔታ መመቻቸት አለበት። ይህ ሁኔታ አሁን ሙሉ በሙሉ አለ ወይ ቢባል መልሱ የለም ነው። ምክንያቱም ይህን አገልግሎት ለማሟላት የሚቻለው ስልጠናው አገር ውስጥ ቢመቻች ነው። በውጭ አገር ስልጠና ይህን ሁሉ ነገር ማሟላት አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ ወረፋ ይኖራል ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ... አዎን ወረፋ ይኖራል የሚል ይሆናል። ምክንያቱም ስራው የሚሰራው በጥቂት ባለሙያዎች ስለሆነ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ጥቁር አንበሳን ጨምሮ በሌሎቹም ሆስፒታሎች የሚሰሩት ቀዶ ሕክምናዎች ከላፓራስኮፒ በአይነትም የተለዩ ናቸው። ለምሳሌም የካንሰር ሕመምን ብንመለከት በውጭ ሀገር ሕመሙ ገና ሲጀምር ስለሚታወቅ የሚሰራው በላፓራስኮፒ ነው። እኛ ሐገር ግን ለሕክምናው ካለው ቅርበት መሳሳት የተነሳ የካንሰር ህመሙ ገፍቶ ስለሚመጣ በላፓራስኮፒ የሚታከም አይሆንም። ይህ አይነቱ ሕመም በሙሉ ቀዶ ሕክምና የሚታከም ነው። ስለዚህ የበሽታው አይነት የደረሰበት ደረጃ፣ የመሳሪያው በየቦታው አለመኖር ፣የሰለጠነ ሰው ኃይል ባለመሟላቱ የተነሳ ላፓራስኮፒ መሰራት እያለባቸው በሙሉ ቀዶ ሕክምና የምንሰራቸው ስራዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ነገር ግን ባለፈው አራት አመት እንደተመለከትነው የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ነው የመጣው። ላፓራስኮፒ እይታው ብሩህ ነው” ብለዋል ዶ/ር ማህሌት። አንድ ታካሚ በላፓራስኮፒ ከተሰራለት በሁዋላ የመመረዝ ሁኔታ ቢያይ ወይንም በተፈጠሩት ቀዳዳዎች አካባቢ የመቅላት ሁኔታ ካለ ወይንም ከፍተኛ የሆነ ትኩሳትና ማሳከክ በቁስል አካባቢ ካለ፣ እብጠት ከታየ፣ ሕመም ካለው፣መቆጣጠር የማይቻል የራስ ምታት ካጋጠመ እንዲሁም በብልት አካባቢ መድማት ወይንም ሌላ ፈሳሽ የመታየት አዝማሚያ ካለ፣ ሳልና የተዛባ የአተነፋፈስ ስርአት ካጋጠመ ሐኪሞችን በፍጥነት ማማከር ወይንም ወደሕ ክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል። እነዚህ ከላይ የተጠቆሙት ነጥቦች በላፓራስኮፒ ለሚሰጥ ሕክምና ብቻም ሳይሆን በማንኛውም ቀዶ ሕክምና ጊዜ ቢታዩ ቸል ሊባል አይገባም። በአጠ ቃላይ ግን የላፓራስኮፒ ሕክምና ደረጃውን የጠበቀና አደጋንም የማያስከትል የህክምና ዘዴ ነው እንደ ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና መምህርት እማኝነት።

 

Source: አዲስ አድማስ ነሐሴ 21 ቀን 2008 ዓ.ም

 

  

Related Topics