ቫሪኮስ ቬይንስ የምንለው የሕምም ዓይነት በማንኛውም የሰውነት ክፍላችን

 

ቫሪኮስ ቬይንስ (Varicose veins)

Image Credit to: gazeta.pl

ቫሪኮስ ቬይንስ የምንለው የሕምም ዓይነት በማንኛውም የሰውነት ክፍላችን ቬይኖች (የደም መልስ) ቱቦዎች ሊከሰት የሚችል ቢሆንም በአብዛኛው የሚያጠቃውና የተለመደው በእግር ላይ የሚከሰተው ነው፡፡

ይህም የሚሆነው ብዙ መቆምና በሰውነታችን ቬይንስ (የደም መልስ) ቱቦዎች ላይ ግፊት ስለሚፈጥር ነው፡፡

► ለቫሪኮስ ቬይንስ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች

✔ ዕድሜ ፡- ዕድሜ መጨመር ለህመሙ ያጋልጣል

✔ ፆታ፡- በሴቶች ላይ በአብዛኛው ይከሰታል ይህም የሚሆነው በሰውነታቸው ላይ ከሚከሰቱ ሆርሞን ለውጦች እና በእርግዝና ጊዜ ነው፡፡

✔ በዘር፡- ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ አንድ የቤተሰብ አባል ተጠቂ ከሆነ ለሌላው የቤተሰብ አባል የመያዝ ዕድሉን ይጨምራል፡፡

✔ ከልክ ያለፈ ውፍረት፡- የሰውነት ክብደት መጨመር በቬኖች የደም መመለስ ሥራ ላይ ጫናን ይፈጥራል፡፡

✔ ለብዙ ሰዓታት መቆም ወይንም መቀመጥ፡- ደም ከእግራችን ወደ ልብ የሚመላለስበትን ሁኔታ በማዛባት ለብዙ ሰዓታት መቆምም ሆነ መቀመጥ ለቫሪኮስ ቬን ሕመም ተጋላጭ ያደርገል፡፡

► የቫሪኮስ ቬይንስ ህመም ምልክቶች

በሽታው ብዙ ጊዜ ከፍተኛ ህመም ያለው ምልክት ባያሳይም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ

✔ ጥቁር ወይንጠጅ ወይንም ሰማያዊ ቀለም ያለው የደምስር እብጠት በእግራችን ላይ መኖር

✔ ጠመዝማዛ የሆኑና የአበጡ የደም ስሮች በእግሮ ላይ መታየት

✔ እግሮን የመክበድና ህመም ስሜት መሰማት

✔ በታችኛው የእግር ክፍሎ የማቃጠል፣ የመጨምደድና የመርገብገብ ስሜት መሰማት

✔ ለረጅም ሰዓታት ሲቆሙም ሆነ ሲቀመጡ የሚብስ የህመም ስሜት

✔ የማሳከክ ስሜት

► የቫሪኮስ ቬይንስ የመከላከያ መንገዶች

ሙሉ በሙሉ በሽታውን የምንቆጣጠርበት መንገድ ባይኖርም የደም ዝውውሮን ወይም የጡንቻ ጥንካሬን መጨመር ለበሽታው ያለውን ተጋላጭነት መቀነስ ይችላሉ።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ማድረግ በሽታንውን ለመከላከል ይረዱናል።

✔ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ

✔ ክብደቶን መቆጣጠር

✔ ጨው የበዛበት ምግብን መቀነስ

✔ ከፍታ ያለው ጫማ አለማዘውተር

✔ በእረፍት ወቅት ወይም ሲተኙ እግሮን በትራስ ከፍ ማድረግ

✔ አቋቋምዎንና አቀማመጥዎን መለዋወጥ

ቫሪኮስ ቬይንስ ከፍተኛ ጉዳትን በአብዛኛው ባያስከትልም ከታች የሚጠቀሱትን ችግሮች ግን አልፎ አልፎም ቢሆን ሊያስከትል ይችላል፡፡

✔ ቁስለት፡- እጅግ በጣም የሕመም ስሜት ያለው የእግር ቁስለት ከአበጠው የደም ስር አጠገብ በሚገኝ ቆዳ ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡

✔ በቆዳ ላይ የቀለም ለውጥ ከተከሰተ ወደ ሐኪም በመሄድ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

✔ የደም መርጋት፡- አንዳንድ ጊዜ ከውስጥ የሚገኙ የደም መልስ ቱቦዎች ሊያብጡ ይችላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ የተጎዳው እግር ዕብጠትን ያሳያል፡፡

✔ ድንገተኛ የሆነ ዕግር ማበጥ ከተከሰተ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና መሄድ ተገቢ ነው፡፡

ምንጭ፡-(በዶክተር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈር)

 

 

  

Related Topics