ጤነኛ ልብ እንዲኖረን የሚያደርጉ ልማዶች

 

ጤነኛ ልብ እንዲኖረን የሚያደርጉ ልማዶች

ጤነኛ ልብ እንዲኖረን የሚያደርጉ ልማዶች

 

  በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የልብ ድካም ህመም ለብዙ ሴቶች ሞት ምክንያት እየሆነ መጥቷል።

በጣም አስደንጋጩ እውነታ ደግሞ ከአራት ሴቶች አንዷ የልብ ህመም ተጠቂ እንደሆነች ጥናቱ ያሳያል።

እንዲያውም የልብ ህመም ከጡት ካንሰር ህመም በሶስት እጥፍ የከፋ አደጋ እንደሚያደርስ ጥናቶች ይጠቁማሉ። 

በአንዳንድ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች የተነሳ የልብ ህመም በወንዶች ላይ ብቻ የሚከሰት ይመስለናል።

ለዚህም ነው ብዙ ሴቶች እውነታውን ለመቀበል የሚከብዳቸው።

ነገር ግን ይህን ህመም መቆጣጠርና የከፋም አደጋ እንዳያደርስ ማድረግ ይቻላል።

ጤነኛ ልብ እንዲኖረን ከሚያደርጉን ልማዶች መካከልም የተወሰኑትን እንመልከት።

1. በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ

በሁሉም የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሴቶች በየቀኑ ከ30 እስከ 60 ደቂቃዎችን በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ ቢያውሉ በልብ ህመም የመጠቃታቸው ዕድል በ46 በመቶ ይቀንሳል።

ብዙዎቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለማድረግ ወደ ጅምናዚዬም መሄድን እንደግዴታ ይቆጥሩታል።

ነገር ግን አካላዊ እንቅስቃሴን ስራችንን እያከናወንን ማካሄድ እንችላለን።

ለአብነትም ከአሳንሰር ይልቅ ደረጃዎችን መጠቀም፣ የእግር ጉዞና ሶምሶማ ሩጫ ሴቶች በህመሙ የመጠቃት እድላቸውን በ45 በመቶ ይቀንሰዋል።

2. ጤናማ ሥነ ልቦና

ይህም በቀላል የሚታይ አይደለም። ከ55 ዓመት በታች የሆኑና በቀላሉ ለድብርት የሚጋለጡ ሴቶች በልብ ህመም የመጠቃታቸው እድል በእጥፍ ይጨምራል።

በድብርት ስሜት የተጠቃችሁ ከመሰላችሁም ሃኪሞችን ማማከሩ አይከፋም።

ምልክቶቹም የሃዘን፣ የተስፋ ማጣት እና ራስን የማጥፋት ስሜት፣ እንቅልፍ ማጣትና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሊሆኑ ይችላሉ።

3. ሲጋራ ማጨስ ማቆም

ሲጋራ ማጨስ ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ይታወቃል። 

ለሳምባ ነቀርሳ ብቻ ሳይሆን ማጨስ ለልብ ህመምና በድንገትም ለመቆም ይዳርጋል።

አጫሾች ከማያጨሱ ሰዎች በአራት እጥፍ የበለጠ በልብ ህመም የመጠቃት ዕድል አላቸው። 

በተጨማሪም አጫሽ ሴቶች ከአጫሽ ወንዶች በ25 በመቶ የበለጠ የመጋለጥ እድል አላቸው።

4. ጤነኛ የሆነ ግንኙነትን ማዳበር

በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ጤናማ ግንኙነትን በማዳበር በልብ ህመም የመጠቃት እድላችንን መቀነስ እንደሚቻል የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ተመራማሪዎች እንደሚያምኑት መግባባትና መደጋገፍ ድብርትን የሚስከትለውን ዕጢ እንዳያመነጭ ያግደዋል።

ይህም ደግሞ ልባችን በህመም እንዳይጠቃ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

5. መልካም አሳቢ መሆን 

መጥፎ ነገሮችን በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም፤ በበጎ ጎናቸው በመቀበል ድብርትንና በልብ ህመም መጠቃትን መቀነስ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይመክራሉ።

6. የተመጣጠነ ምግብ መመገብ

በቀን ውስጥ የምንመገባቸውን ትኩስ ምግቦች በመጨመር፤ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ የስብ ይዘት የሌለባቸውን ፕሮቲኖችን ለምሳሌ እንደ አሳ የመሳሰሉትን በመመገብ የልብ ህመምን መቀነስ ይቻላል።

7. ወሲብ መፈፀም 

በሳምንት ሁለት ጊዜ ወሲብ መፈጸም የደም ግፊትንና ድብርትን ለመቀነስ ይረዳል።

ይህም ደግሞ በቀላሉ በልብ ህመም እንዳንጠቃ ያደርገናል።

ብዙዎቻችን ወሲብን ለደስታ ብቻ ነው የምንፈጽመው፤ አሁን ግን ለጤንነትም ጭምር ወሲብ መፈፀም እየተመከረ ነው፤ ለምን ስሜታችን ከፍ እያለ ሲመጣ በሰውነታችን ውስጥ ያሉትና የተሻለ የደም ዝውውር እንዲኖረን የሚያስችሉን ዕጢዎች የተሻለ እንዲያመነጩ ያደርጋቸዋልና።

8. በቂ የሆነ እንቅልፍ ማግኘት

በቂ ያልሆነና ያልተስተካከለ እንቅልፍ በሰውታችን ላይ በጎ ያልሆነ ተፅእኖ ያሳድራል፤ በተለይም ደግሞ ልባችን ላይ። 

በአንድ ጥናት እንደተረጋገጠው የእንቅልፍ እጦት ለልብ ህመም ይዳርጋል።

እንዲሁም ያልተስተካከለ እንቅልፍም የደም ግፊትን በመጨመር ለልብ ህመም ይዳርጋል።

 

ምንጭ፦ www.healthylifetricks.com/

 

 

  

Related Topics