የየም ብሄረሰብ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች

የየም ብሄረሰብ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች

 

 Image result for የደቡብ ብሄረሰብ

የየም ልዩ ወረዳ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ አስራሶስት ዞኖች በአንዱ ውስጥ ይገኛል። «የም» የሚለው ስያሜ የብሄረሰቡ መጠሪያ ሲሆን «የምሳ» ደግሞ የብሄረሰቡ መደበኛ ቋንቋ ነው።

ብሄረሰቡ ከአስራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ታዋቂና ጠንካራ መንግስት መስርቶ ይኖር እንደነበርም የጥናት መዛግብት ያስረዳሉ። ከነባር ጎሳዎች ሌላ ከየመንና ከጎንደር ፈልሰው የመጡ ህዝቦች በአካባቢው ተቀላቅለው ይኖሩ እንደነበርም ይጠቆማል።

አቀማመጥ

የወረዳው መሬት ኮረብታማና ወጣ ገባ ነው። ከጊቤ ወንዝ አንስቶ እስከ ቦር ተራራ ያለው አቀማመጥም ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ የሚሄድ በመሆኑ ለመኖሪያነት አመቺ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የአየር ንብረት ይዞታው ደጋና ወይናደጋ ሲሆን ምስራቃዊው ክፍልና የጊቤ ተፋሰስ ደግሞ በቆላነት ይመደባል።

ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ስፍራዎች

ብሄረሰቡ የራሱ የሆነ ባህል፤ ቋንቋ፤ ታሪክና ወግ አለው። በአካባቢው ታሪካዊ ቤተ መንግስት፣ የእምነት ስፍራዎች፣ እድሜ ጠገብ ደኖች፣ትክል ድንጋዮች፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ዋሻዎች በብዛት ይገኛሉ። በርካታ ትክል ድንጋዮች የሚገኙበት ስፍራ «ዞፍካር» ይባላል። ይህ ስፍራ የየም የመጨረሻ ንጉስ በነበረው «አባቦግቦ» ዘመን ቀብር ይፈፀምበት ነበር። አካባቢው በታሪካዊነቱና በአንጋፋነቱ ከሌሎች የተመረጠ በመሆኑም በፓርክ ክልልነት እንዲለይ ተደርጓል። «አንጋሪ» የተባለው ጥንታዊ ቤተ መንግስትም በጥቅጥቅ ደኖችና በአገር በቀል ዛፎች የተከበበ በመሆኑ በመስህብነት ያገለግላል።

ባህላዊ መገልገያ ቅርሶች

የብሄረሰቡ የቤት ውስጥ መገልገያዎች፣ የንጉሳውያን አልባሳት፣ ከዝሆን ጥርስ የተሰሩ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያዎችና የሸክላ ወጤቶች እድሜ ጠገብ ከመሆናቸውም በላይ የብሄረሰቡ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ናቸው።

ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች

በብሄረሰቡ በዋንኛ ምግብነት ከአስር የማያንሱ የእንሰት ውጤቶች ይዘጋጃሉ። በልዩ ማህበራዊ ግንኙነት ወቅት የሚዘጋጅ የቆጮ ድፎ «ኮባና» ይባላል። በገንፎና በቂጣ መልክ የሚዘጋጀው ቡላም «ኬዳኦ» የሚል መጠሪያ አለው። የቆጮ ገንፎ «ናቱ» ሲባል ከጎመንና ከቆጮ የሚዘጋጀው ፍርፍር ደግሞ «ዎቶ» ይሰኛል። «ፈጨ» የሚባለውም ለህፃናት ምግብነት የሚዘጋጅ ነው።

ከብሄረሰቡ ባህላዊ መጠጦች ዋናው «ቦርዴ ማኡሻ» ይባለል። የሚዘጋጀውም ከገብስ፣ ከዳጉሳ፣ ከቀይ ጤፍና ከብቅል ነው። የጥራት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ የሚዘጋጀው ሌላው ባህላዊ መጠጥ ደግሞ «ኪአ» የሚል መጠሪያ አለው። ይህ የመጠጥ አይነት ውሃ ሳይጨመርበት ድፍድፉ ብቻ ተጨምቆ የሚቀርብ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ ይነገርለታል። በልዩ ዝግጅት ወቅት የሚዘጋጀው ባህላዊ መጠጥም «ኡሻ» ይባላል።

 

መስቀልና የዘመን መለወጫ በዓል

በየም ብሄረሰብ በዘመን መለወጫነት የሚታወቀው በዓል መስቀል ሲሆን በብሄረ ሰቡም ዘንድ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ተወላጆቹ በዓሉን «ሄሄቦ» ሲሉ ይጠሩታል። ትርጓሜውም የዓመቱ የመጀመሪያ ወር እንደማለት ነው።

በዘመድ አዝማድ መካከል የቆየ ቅሬታና መቀያየም ቢኖር ከበዓሉ በፊት መስከረም አስራ አራት ቀን እርቅ እንዲወርድ ይደረጋል። ቂምና ጥላቻን ይዞ ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገር ነውር ነው።

ምንጭ፡-ethpress.gov.et