በአደገኛ ነገሮች ብንመረዝ ምን እናድርግ?

በአደገኛ ነገሮች ብንመረዝ ምን እናድርግ?

 

 

 

 

መርዝ ወደ ሰውነት ውስጥ ሲገባ ወይም ቆዳ ላይ ሲያርፍ፣ ወደ ደም ስሮች ሰርጎ በመግባትና ሕዋሳትን በመመረዝ የጤና መታወክ ወይም የሞት አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ማንኛውም ሰው በመብላት ወይም በመጠጣት፣ በማሽተት፣ በንክኪ፣ በመወጋት ወይም በመነደፍ ለመመረዝ አደጋ ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ለመመረዝ አደጋ የሚሰጠው የሕክምና እርዳታ የመርዙን በሰውነት ውስጥ መሰራጨት ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ እንዲሁም የትንፋሽ መቋረጥ ለደረሰበት ግለሰብ የሰው ሰራሽ አተነፋፈስ እርዳታ ለመስጠት ነው፡፡

 

 

 

በርካታ ሕፃናት መርዛማ ነገሮችን የመብላትና የመጠጣት አደጋ ያጋጥማቸዋል፤ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በሞት ይለያሉ፤ ይህ ሁኔታ እንዳያጋጥም በተለይ ለልጆች የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 

==ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው የታወቁ የመርዝ አይነቶች==

 

• የአይጥ መርዝ፣

• ዲዲቲና ተመሳሳይ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች፣

• ማንኛውም ዓይነት መድኃኒት(ከመጠን በላይ ሲወሰድ)፣

• አዮዲን፣

• የተለያዩ አሲዶች ወይም አልካላይን፣

• በረኪና፣

• የተበላሸ መጠጥ፣

• የእንጨት ዘይት ወይም አልኮል፣

• የመርዛማ እፅዋት ቅጠሎች ወይም ፍሬዎች፣

• የጉሎ ፍሬዎች፣

• ናፍጣ፣ ጋዝ፣ ቤንዚንና ሌሎችንም መጨመር ይቻላል፡፡

 

==የመጀመሪ ሕክምና እርዳታ==

 

አንድ ሰው መርዝ መጠጣቱ ወይም መብላቱ ከታወቀ የሚከተሉት እርምጃዎች በፍጥነት መወሰድ አለባቸው፡፡

 

• የመርዙ ዓይነት ጠንካራ አሲድና አልካላይን፣ ናፍጣ፣ ቤንዚን ከሆነ ወይም ግለሰቡ ራሱን ከሳተ ቢያስመልሰው ሌላ የመታፈን ሁኔታ እንዳይገጥመው በጎኑ ማስተኛት አለብን፤ በፍጥነትም ወደ ሕክምና መወሰድ አለበት፡፡ ራሱን የሚያውቅ ከሆነ መርዙን ለማዳከም ወይም እንዲወገድ ለማድረግ ወተት ማጠጣት፤ ወደ ሕክምና ማዕከልም በፍጥነት መውሰድ አለብን፡፡

• በኦርጋኖፎስፌት ማለትም የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች፣ የነርቭ ጋዞች፣ የትላትል መድኃኒቶችና እንዱስትሪያል ኬሚካሎች የተመረዘን ሰው ልብሱን አውልቆ ሰውነቱን ማጥብ ያስፈልጋል፤ ከዚያም አትሮፒን(Atropine) 2 ሚሊ. ግራም(ለአዋቂ) ወይም ለአንድ ኪ.ግ ክብደት ከ0.1-0.05 ሚሊ. ግራም(ለልጆች) በደም ስር ወይም በታፋ የዐይኑ ብሌን እስኪሰፋ ሳንባው ንፁሕ እስኪሆን ድረስ ከ15-60 ባለው ደቂቃ ውስጥ መስጠት ይገባል፡፡ ከዛም በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ መደረግ አለበት፡፡

• መርዙ የሌሎች ንጥረነገሮች ከሆነና ግለሰቡም ራሱን የሚያውቅ ከሆነ ጣትን ጉሮሮ ውስጥ በመክተት እንዲያስታውክ ማድረግ አለብን፡፡ በፍጥነት ወደ ሕምናም መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

 

==መርዛማ ኬሚካሎች==

 

አንድ ሰው በኬሚካል ነክ መርዞች ተመርዞ ከሆነ፣ በማስመለስ ለማስወጣት መሞከር ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል ሌሎች አማራጮችን መጠቀም አለብን፤ ነገር ግን የተመረዘው መርዛማ ዕፅዋቶችን በመመገብ ከሆነ እንዲያስመልስ በማድረግ የጉዳት መጠንን መቀነስ እንችላለን፡፡

 

መርዛማ ነገሮችን በሰውነት ውስጥ ለማርከስ ወይም ለመምጠጥ ከሻይ(ታኒክ አሲድ ስላለው) እና ከከሰል ማዘጋጀት እንችላለን፤ አላማው መርዛማ ንጥረገሮች እንዲመጠጡ እና ከከሰሉ ጋር አብረው እንዲወጡ ለማድረግ ነው፡፡ በኬሚካሎች አማካኝነት የሚደርስ መመረዝ በውጪው የሰውነት ክፍላችን ላይ ከሆነ፣ ውኃ በብዛት በማፍሰስ ልናፀዳው እችላለን፤ ነገር ግን ቁስለት ከፈጠረ ልክ የእሳት ቁስለትን በምናክምበት መንገድ መንከባከብ አለብን፡፡

 

ማስጠንቀቂያ! አብዛኛውን ጊዜ በሰርቫይቫል ሁኔታዎችም ይሁን በሰላማዊ ጊዜያት አንዳንድ ኬሚካሎችን ወይም መርዞችን ለሌላ ዓላማ በተዘጋጁ ጠርሙሶች ሰዎች ሊይዙ ይችላሉ፤ ለምሳሌ በኮካ ጠርሙስ ሌላ መርዛማ ነገሮች ተጨምረው ሊገኙ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ሰዎችን ሊያሳስት ይችላል፤ ስለዚህ እንድን ነገር ከመጠቀማችን በፊት በዕቃው ላይ በጽሑፍ የተመለከተው በውስጡ ያለውም በትክክል ቁሱ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ የተራበ እና የተጠማ ሰው፣ በተለይ ሕፃናት ለእንዲህ ዓይነቱ ስሕተት የበለጠ የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ጋዝ ወይም ቤንዚን በውኃ መያዣ እቃዎች ልንይዝ እንችላለን፤ ሰዎችን ያሳስታል፤ አለበለዚያ በእቃው ላይ ምን እንደያዘ ማስታወሻ ማስፈር አለብን፡፡

 

ማስጠንቀቂያ! በኬሚካሎች አማካኝነት የሚደርስን መመረዝ ለማምከን አብዛናውን ጊዜ ውኃ የምንጠቀም ቢሆንም፣ በዕውቀት ላይ ተመስርተን መሆን አለበት፤ ምክንያቱም አንዳንድ ኬሚካሎች ውኃ ሲነካቸው የባሰ ነውጠኛ ይሆናሉ፤ የበለጠ ጉዳትም ያደርሳሉ፡፡

ምንጭ፦/tmsurvival

 

  

Related Topics