Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ስኬት ምንድን ነው? የስኬት ቁልፍስ? በሳይኮሎጂስቶች እይታ

ስኬት ምንድን ነው? የስኬት ቁልፍስ? በሳይኮሎጂስቶች እይታ

 

 

 

ስኬታማ ሕይወት እንዴት ያለ ነው? ሰዎች “ለእኔ ስኬት ማለት ይኼ ነው ይኼ ነው” ብለው ሀሳባቸውን በሚገልፁበት ወቅት ስምም የሆነ አገላለፅ መስማት የተለመደ አይደለም፡፡ ለአንዱ እንደ ስኬት የሚታይ ነገር ለሌላው እዚህ ግባ የማይባል ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ቤተሰብ መስርቶ፣ ልጅ ወልዶ ወዘተ ማሳደግ ለአንድ አንድ ሰዎች ትልቅ የሕይወት ስኬት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ለሌሎች ዓለምን እየተዘዋወሩ ማየት የስኬት ሁሉ ስኬት ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛው ሕይወት ነው ስኬታማ ሕይወት ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ ወደዛ በስኬት አሸብርቋል ወደምንለው ሕይወት የሚወስደን ጎዳናስ የትኛው ነው የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ ጥያቄ ነው፤ የታሰበበት እና የተጠና ምላሽም ይፈልጋል፡፡

 

በስነ ልቡና ባለሙያዎች ዘንድ ከሞላ ጎደል የሚያግባባው አንዱ ሀሳብ “ስኬታማ ሕይወት ሚዛናዊ ሕይወት ነው” የሚል ነው፡፡ ሕይወት ብዙ ፈርጆች፣ ገፆች እና ጎኖች አሏት፡፡ ሁላችንም አነሰም በዛ እዚህ ምድር ላይ በምንኖርበት ወቀት የተለያየ ሚና እንጫወታለን፤ የተለያየ ኃላፊነት እንሸከማለን፡፡ ታዲያ እነዚህ የተለያዩ የሕይወት ግፆችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በሕይወት ወጣ ገባ መንገድ ላይ መኖር መቻል ስኬትም የስኬት ቁልፍም ነው፡፡ ዝነኛው ሳይኮሎጂስት ሲግመንድ ፍሮይድ “ስራ እና ፍቅር የሰው ልጅ ሕይወት የማዕዘን ራስ ናቸው (Love and work are the corner stone of our humans)” ይላል፡፡ በአጭሩ እነዚህን ሁለት የሕይወት ገፆች ፍሬያማ በሆነ መልኩ መኖር መቻል ስኬትም የስኬትም ቁልፍ ነው፡፡ አንድ ሰው በስራው እጅግ በጣም ውጤታማ ቢሆንና ለወዳጅ ዘመዶቹ ግን የረባ እንኳን ጊዜ መስጠት ባይችል ይህ ሰው ሕይወትን በሙላት እየኖራት እና እየተሳካለት ነው ማለት ይቸግራል፡፡ በዙሪያችን ከሚገኙ ሰዎች ጋር ፍቅር በፍቅር ሆነን ውጤታማ ስራ መስራት ካልቻልንም ያው ነው፡፡ ስኬት እነዚህን ሁለት የሕይወት ገፆች የሚጠይቁትን ጊዜ መስጠት መቻል፣ ሁለቱም የሚያሸክሙንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት፣ በሁለቱም በኩል አትራፊ መሆን መቻል ነው፡፡

 

ሚዛናዊ ስለመሆን ስንነጋገር ከእኛ ውጪ ያሉ የሕይወት ገፆችን ብቻ ሳይሆን እኛ ውስጥ የሚገኙ የማንነታችንን ክፍልፋዮች ሚዛንም ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው አንድ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ውስጡ በሚገኙት የተለያዩ የማንነት ክፍሎች ምክንያት ብዙ ሰውም ነው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ የተለያዩ የማንነ ክፍሎች የሚፈልጉትን እና የሚያስፈልጋቸውን ያህል ቦታ ከሰጠናቸው፣ ከሰማናቸው፣ ፍላጎታቸውን ካሟላንላቸው፣ አንዱ ከአንዱ ጋር በስምምነት እንዲኖር መፍቀድ ከቻልን ትልቅ ስኬትም የስኬት ቁልፍም ነው፡፡ በአንፃሩ አንዱን ወደፊት አድርገን አንዱን ወደ ኋላ ከተውን፤ አንዱ ዘወትር እንዳሻው እንዲሆን ፈቅደን አንዱ ላይ በር ከዘጋን፤ የአንዱን ጥሪ አድምጠን ሌላውን ጆሮ ዳባ ልበስ ካልን ውስጣችን (አእምሯችን፣ መንፈሳችን ወዘተ) እነዚህ የማንነታችን ክፍሎች የሚራኮቱበት የጦር አውድማ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ልዩ ልዩ ስነ ልቡናዊ ችግሮችም ይፀነሳሉ፤ ይወለዳሉም፡፡ ኤሪክ በርኔ የተባለ ሳይኮሎጂስት የሰው ልጅ ሰብዕና የሶስት ልዩ ልዩ ማንነቶች ጥምረት/ቅንጅት ውጤት ይላል፡፡ የመጀመሪያው “ወላጅ (Parent)” ነው ይላል፡፡ ይህ ክፍል ሁልጊዜ የሚመዝን፣ የሚቆጣጠር፣ እንከን የለሽ ለመሆን ጥረት የሚያደርገው ጥንቁቁ የሰብዕናችን ክፍል ነው፡፡ የዚህ የሰብዕና ክፍል መሰረት ራስ ወዳድነት፣ ደህንነት (security) እና ለሚደርገው ማናቸውም ነገር በቂ ምክንያት (justification) መስጠት መቻል ነው፡፡ ሌላኛው የሰብዕናችን ክፍል “አዋቂ (Adult)” ይባላል፡፡ ይህ የሰብዕና ክፍል ምክንያታዊ፣ አመዛዛኝ እና ነገሮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድ የሚያወቅ ይሆናሉ ወይስ አይሆኑም የሚለውን ጨምሮ መቀየስ መረዳት የሚችለው ነው፡፡ የሚያደርገውን ማናቸውንም ነገር የሚያደርግበት ምክንያት የውስጥ እርካታ፣ የመማር እና የማወቅ ፅኑ ፍላጎት ነው፡፡ ሶስተኛውና የመጨረሻው የሰብዕናችን ክፍል “ልጅ (Child)” የሚል ስያሜ አለው፡፡ ይህ ክፍል በአንፃሩ የፈጠራ አቅሙ የላቀ፤ ሰፊ ምናብ ያለው፤ ማደግ፣ መበልፀግ፣ መጫወት፣ ማጥፋት ወዘተ ነፍሱ የሆነ ነው፡፡ የሚፈልገውና የሚያደርገው ነገር መሰረቱ ደስታ፣ እርካታና ጥፋት ነው፡፡

 

እነዚህ ሶስት የሰብዕና ክፍሎች አንዳቸው ያለአንዳቸው እንዳሻቸው እንዲሆኑ ብንፈቅድላቸው በጎም በጎ ያልሆነም ውጤት ያስከትላሉ፡፡ አንዱ የሰብዕና ክፍል ብቻውን ፈላጭ ቆራጭ ሲሆን አሉታዊ ነገሮች ሕይወታችን ውስጥ ይበረክታሉ፤ ደስታ ይርቀናል፤ እረፍት ከአድማስ ባሻገር ያለ ሩቅ ሀገር ይሆንብናል፤ ስኬታማ እንደሆንን አይሰማንም፤ ስኬታማ ለመሆን የምናደርገው ትግልም በግጭት የታጀበ ይሆናል፡፡ የደስታ፣ እረፍት፣ ሰላም ወዘተ በጥቅሉ የስኬት ምንጭ እነዚህን ሶስት የሰብዕናችንን ክፍሎች አቻችሎ፣ አስማምቶ እና ሚዛን ጠብቆ ሕይወትን መምራት መቻል ነው፡፡ አንዱን ጥሎ ሌላውን ብቻ አንጠልጥሎ መኖር ተገቢም ገንቢም አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ጥልቅ ተፈጥሮአዊ ፍላጎቱ ማደግ፣ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እና እምቅ ችሎታውን አውጥቶ መጠቀም መቻል ነው፡፡ ይህንን ፍላጎቱን እያሟላ ለመኖር በእነዚህ ሶስት የሰብዕና ክፍሎች መካከል እርቅ፣ ስምምነት እና ሚዛናዊ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፡፡ ቅርብ ጊዜ አንድ ትልቅ ፓርቲ ላፍቶ ሞል የመታደም እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ዙሪያዬ ይገኙ የነበሩ ወጣቶች ጨዋታና ቡረቃ ሌላ ነው፡፡ ይዘፍናሉ፤ ይደንሳሉ፤ የራሳቸውን ግጥምና ዜማ እዛው ጭምር እየፈጠሩ ምን አለፋችሁ በቃ ራሳቸውንም በአካባቢያቸው የሚገኘውንም ታዳሚ ዘና ማድረግ ቻሉ፡፡ ምሽቱ እገፋ፣ ወደ ጉሮሮ የሚንቆረቆረው መጠጥ መጠኑ እየጨመረ ሲሄድ ግን ሁኔታዎች መልካቸውን ቀየሩ፡፡ ቅጥ ያጣ ዳንስና ልፊያ፤ የሌላውን መብት የሚጋፍ ድርጊት መፈፀም ተጀመረ፡፡ ያስደሰቱት ሰው ያዝንባቸው፣ ይታዘባቸው፣ ይናደድባቸው ገባ፡፡ ይህ እንግዲህ ሚዛንን መጠበቅ ያለመቻል ውጤት ነው፡፡

 

መዝናናት እና መደሰት አስፈላጊና እጅግ ጠቃሚ ነገሮች ነው፡፡ ሁሉም ሰው ማንነት ውስጥ መቦረቅ የሚፈልግ “ልጅ” ማንነት አለ፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ማንነት ሙሉ ለሙሉ ወንበሩን ያለ ኃይ ባይ ሲቆጣጠር ከሚለማው ይልቅ የሚጠፋው ያመዝናል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት ታዲያ ሀይ ባዩ፣ ከልካዩ፣ ተቆጪው፣ ቆንጣጩ “ወላጅ” ማንነታችን አብሮን ሊኖር ይገባል፡፡ “ይበቃል፤ እንዴ! ተው አንጂ፣ ሰው እኮ እየረበሽክ ነው፣ ኋላ ችግር ውስጥ እንዳትገባ! ነግሬሀለሁ!” ወዘተ ሊል ይገባል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አመዛዛኙና አዋቂው ማንነታችንም እንዲሁ ምንጊዜም አብሮን ሊሆን ይገባል፡፡ “እየመሸ ነው ብንሄድ ሳይሻል አይቀርም፤ የጀመርካትን ጨርስና ጓደኞችህን ተሰናበት፤ ስትጨፍር ሌላውን ላለመርገጥ ተጠንቀቅ፤ መጠጡንም ቢሆን ከዚህ በላይ አትውሰድ፣ ረሳኸው እንዴ ነገ እኮ ስራ ገቢ ነህ ባለፈው ዓመት እንዲህ ስትጠጣና ስትጨፍር አድረህ የሆንከው ጉድ ትዝ ይልሀል” ወዘተ እያለ አዛዡን እና አማፂውን ማንነታችንን የሚያግባባ፤ ምክንያታዊ እርምጃ እንድንወስድ የሚያግዘን አዋቂ ማንነታችንን ያለ ልዩነት ሊጠነክር ይገባል፡፡ ሶስቱም የማንነት ክፍሎች ድምፅ ኖሯቸው እንደ ዴሞክራሲያዊ ስርዐት “check and balance” እየተደራረጉ ሲኖር ስኬታማ መሆን ይችላል፤ ተፈጥሮአዊ እምቅ ችሎታን አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስችል እድል ይፈጠራል፡፡ አንዱ አንዱን ወርሶ ዙሪያ ገባውን ሲያጥር፤ አንዱ ብቻውን አድራጊ ፈጣሪ ሲሆን ግን ውጤቱ ጥፋት፣ ደስታ አልባ መሆን፣ ለመግባባት መቸገር ወዘተ ነው፡፡ ስለዚህ እንደየሁኔታው ሶስቱንም የሰብዕና ክፍሎች ቦታ ሰጥቶ፣ አግባብቶና አቻችሎ፣ ሚዛን ጠብቆ፤ ጨዋታና ጭፈራ አስፈላጊ የሆነበት ቦታ ተጫውቶና ጨፍሮ፣ ቁም ነገር የሚቀድምበት ቦታም እንዲሁ ቁም ነገረኛ ሆኖ፣ ለነገና ከነገ ወዲያም አስቦ፣ ተጠቦ እና ተጠንቅቆ እንደ ወላጅ፣ አዋቂና ልጅ መኖር ስኬትም ነው የስኬትም ቁልፍ ነው፡፡

ቸር እንሰንብት!

ምንጭ፡-. /psycet