Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

‹ፊት ለፊት ብታይም ለስኬቴ ብዙዎች ከኋላዬ አሉ›

‹‹ፊት ለፊት ብታይም ለስኬቴ ብዙዎች ከኋላዬ አሉ››

 

 

ሲስተር ጥበበ ማኮ፣ የሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

ሕይወት ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ ድጋፍና ክብካቤ ድርጅት የተቋቋመው ከ17 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ድርጅቱ ሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት በሚል ስያሜ ከኤድስ በተጨማሪ የልማት ሥራዎችን አቀናጅቶ መሥራት እስከጀመረበት እ.ኤ.አ. 2012 ድረስ፣ ኤድስ ላይ ትኩረት አድርጐ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ድርጅቱን የመሠረቱት ሲስተር ጥበበ ማኮ፣ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በ1970ዎቹ በነርሲንግ ከተመረቁ በኋላ ትዳር ልጅ ሳይሉ በቅጥርና በበጐ ፈቃድ አገልግሎት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከሥራቸው ጋር በተያያዘም ከአምስት ያላነሱ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ የሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ሲስተር ጥበበ ማኮ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ኤችአይቪ ኤድስ ላይ መሥራት ሲጀምሩ ግንዛቤው ያልዳበረበት አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ እንዴት ወደ ሥራው ገቡ?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ ኤችአይቪ ኤድስ አገሪቷ ላይ ብዙ ወጣቶችን የገደለበት፣ እናት ልጆቿን የደበቀችበት ጊዜ ነበር፡፡ ሞትም ከፍተኛ ነበር፡፡ መጀመሪያ ድርጅቱ የተመሠረተው ዘነብወርቅ፣ አለርት አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ በአካባቢው ድህነት በስፋት የሚታይበት፣ የሥጋ ደዌ ህሙማን ያሉበት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱት እህቶቻችን በብዛት በሴተኛ አዳሪነት የሚሰማሩበት፣ አካባቢው ለከተማው ቆሻሻ መጣያ ቅርብ በመሆኑ፣ ወጣቶች ከቆሻሻው ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶችን መሸጥ የኑሮ መሠረት ማድረጋቸውና ወንጀል የሚሠራበት በመሆኑ፣ በአካባቢው ላይ የድህነቱ ጥልቀት የተወሳሰበ ነበር፡፡ ለህመሙ ትኩረት ባመኖሩ የታመሙ ይደበቃሉ፣ ቤተሰብ ይገለላል፣ ህሙማን ከቤት አይወጡም፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እሠራበት ከነበረው የኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት የጤና ክፍል ኃላፊነት ለቅቄ ወደ ሥራው ገባሁ፡፡ በተለይ በኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት እየሠራሁ አንዲት ከክልል መጥታ የሞተች እናትን የሚቀብራት ሰው ጠፍቶ ማየቴና ከጎኗ የነበረችው የስምንት ዓመት ሕፃን ሁኔታ፣ ቀጥታ ወደ ሥራው ለመግባት እንድወስን አድርጐኛል፡፡ ብዙ ገንዘብ ባንዴ ስላፈሰስን ብቻ ሳይሆን ሁላችንም በየምንችለው ስንተባበር ችግሩን እንቀርፋለን ብዬ የጀመርኩት ሥራ ውጤታማ ሆኗል፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ሥራውን የጀመሩበት ጊዜ ስለኤድስ ለመነጋገር ከባድ ወቅት ቢሆንም፣ እድሮችን ማሳተፍዎ፣ ለስኬትዎ አስተዋጽኦ ነበረው ይባላል፡፡ እንዴት ነበር ከእድሮች ጋር የምትሠሩት?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ ድንጋይ ሁሉ ተወርውሮብኛል፡፡ በስማችን ልትነግድ ነው ተብዬም ነበር፡፡ እኔ የተነሳሁት እድሮችን መሠረት አድርጌ ነው፡፡ እድር ሁሉን አቀፍ የሆነ የሕዝቡ ኢንሹራንስ ስለሆነ፣ ዘነብወርቅ የሚገኘው አቡነአረጋዊ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኙ እድሮች ነበር ሥራውን የጀመርኩት፡፡ የእድርን ግንዛቤ በመጨመር ከሞት ባለፈ አባላት ሲታመሙ እንዲረዳ ትልቅ ሥራ ሠርተናል፡፡ መንግሥትና ድርጅቶች ስለለፉ ብቻ ችግሩ ሊቀረፍ ስለማይችል ማኅበረሰቡ ችግሬ ነው ብሎ እንዲነሳ፣ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲያግዝ አድርገናል፡፡ በወቅቱ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገንዘብ ቢያፈሱም ስርጭቱ እየሰፋ እንጂ እየቀነሰ አልሄደምም ነበር፡፡ ስለሆነም ከመሠረቱ ገብተን በሃይማኖት ተቋማት፣ በእድሮችና በወጣቶች አካባቢ ሠርተናል፡፡ በእድሮችና ሃይማኖት ተቋማት ላይ ስንሠራ ከባድ ነበር፡፡ ዘነብወርቅ አካባቢ እድሮች ለቤተክርስቲያን ቅርብ ሆነው ስለሚሠሩ፣ አቡነአረጋዊ ቤተክርስቲያን እድሮችንና አባላትን አሰባስበን ለማሳመን የነበረውን ጫና አልረሳውም፡፡ ለ45 ደቂቃ ያህል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አያይዤ ኤድስን እንዴት እንደምንከላከል ንግግር አደረግሁ፡፡ ተሰብሳቢውም አጨበጨበ፣ ‹ጥሩ ነው ልጆቻችንን ይዘን መጥተን ግንዛቤ እንዲያገኙ እናደርጋለን› አሉ፡፡ በኋላ ዝግጅቱን ለመዝጋት አንድ ካህን ተነስተው ንግግር አደረጉ፡፡ ንግግራቸው አምስት ደቂቃ ያህል ቢሆንም፣ ከ45 ደቂቃ በላይ ያደረግሁትን ንግግር ዜሮ ያስገባ ነበር፡፡ ፈጣሪ ብዙ ተባዙ እንደሚል በመጥቀስ፣ ምንም እንኳን የኤድስ መከላከያ ከሆኑት አንዱን ኮንዶም ተጠቀሙ ያላልኩ ቢሆንም፣ ኤድስን መከላከል ሲባል ከኮንዶም ጋር አያይዘው በመረዳታቸው ያደረጉት ንግግር፣ ተሰብሳቢው እኔን እንዲቆጣ፣ ድንጋይ እንዲወረውር አድርጓል፡፡ በወቅቱ ተስፋ ቆርጬ ነበር፡፡ ሆኖም እዛው የሚገኙ አንድ መምህር ‹ገና ብዙ ችግር ይገጥምሻል፡፡ ተስፋ አትቁረጪ!› ባሉኝ መሠረት፣ ግንዛቤ ማስጨበጡን ገፋንበት፡፡ በቤተክህነት አካባቢ ትምህርት የሚሰጡ ምሁራን በመድረኩ ትምህርት እንዲሰጡ አደረግን፡፡ ቀስ በቀስ ሕዝቡን ያሸፈቱብኝ አባትም ሆነ ነዋሪውና እድሮች ተቀበሉን፡፡ የታመሙ ሰዎችን ማጽናናትም የካህናት ሥራ ሆነ፡፡ ሲሞቱ ያለምንም ክፍያ ጸሎተ ፍትሐትና ቀብር እንዲከናወንም ረዱን፡፡ ፈተና የነበረ ቢሆንም፣ ቀስ በቀስ የእምነት ተቋማትም ሆነ እድሮችና ማኅበረሰቡ ረድቶን በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ከ50 ሺሕ በላይ ሰዎችን መድረስ ችለናል፡፡ በየቀኑ በድርጅታችን ብቻ በቀን እስከ አሥር ሰው እንቀብር ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ተቀይሯል፡፡ 

 

ሪፖርተር፡‑ ድርጅቱ በቤት ለቤት እንክብካቤም ይታወቅ ነበር፡፡ ብዙዎቹም በጐ ፈቃደኞች ሴቶች ነበሩ፡፡ ስለሥራው ቢገልጹልን?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ የቤት ለቤት እንክብካቤ ዋና ዓላማው የሆስፒታሎችን ጫና ለመቀነስ ነው፡፡ እንዳሁኑ ሆስፒታል ባለመስፋፋቱ፣ ያሉት ሆስፒታሎች በሌሎች ህሙማን የተጨናነቁ ነበሩ፡፡ የኤድስ ህሙማን የሚሞቱ ስለሆኑ ብዙም ትኩረት አይሰጣቸውም፡፡ ብዙዎቹም ደሃ በመሆናቸው፣ ለተጓዳኝ በሽታዎች እንኳን መክፈል አይችሉም ነበር፡፡ የቤት ለቤት እንክብካቤ በማድረግ መገለልና መድሎውን ቀንሰናል፣ ጐረቤት አሳትፈናል፣ ታማሚው ሆስፒታል ቢተኛ የአካባቢው ሰው ልጆችን ያግዛል፡፡ ይህ ሁሉ በእድር አማካይነት ከአካባቢው በሚመለመሉ በጐ ፈቃደኞች የተሠራ ነው፡፡ እድሮች ከሞት ባሻገርም በቁም መረዳዳት እንዲጀምሩ የዘረጋነው አሠራር ዛሬ ላይ እድሮች በተለያዩ ልማቶች እንዲሳተፉም መሠረት ጥሏል፡፡ በወቅቱ በእኛ ድርጅት ብቻ የ27 እድሮች ኅብረት እንዲመሠረት አድርገናል፡፡ በአዲስ አበባ በአሥር ክፍላተ ከተሞች 109 ወረዳ ውስጥ እንሠራም ነበር፡፡ ከ800 በጐ ፈቃደኞች 95 በመቶው ሴቶች ሲሆኑ፣ በየክፍላተ ከተሞቹ እድሮችም ከጐናችን ነበሩ፡፡ ኅብረተሰቡ እያገዘን የሞቱትን በክብር እየሸኘን በኋላ መድኃኒቱ መጣ፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ መድኃኒቱን መቀበልም ከባድ ነበርና እንዴት ተወጣችሁት?  

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ ተጽእኖ ነበር፡፡ ስሙ ዕድሜ ማራዘሚያ ስለነበር፣ ቤተክርስቲያን አካባቢ መድኃኒት የሚጠቀሙ፣ መድኃኒቱን የጣሉበት ጊዜ ነበር፡፡ እዚህ ላይ በጐ ፈቃደኞችና እድሮች ሠርተው፣ ውይይቶች ተደርገው ፀረ ኤችአይቪ ተባለ፡፡ ቤተክርስቲያንም ተቀብላን፣ በየፀበል ሥፍራው እያስተማርን ለውጥ አምጥተናል፡፡ ለዚህ የቀድሞ ፓትሪያርክ ያደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ ትልቁን ሥራ ታች ሠርተናል፡፡ ሆስፒታሎችን አግዘናል፡፡ መድኃኒቱን በተለይ መግዛት ለማይችሉ በቅድሚያ በነፃ ሰጥተናል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርም ከእኛ ጋር ሠርቷል፣ ረድቶናል፡፡ እያደር ህሙማኑ በሽታውን የመከላከል አቅማቸው ዳብሮ፣ የመተላለፍ ስርጭቱም ቀነሰ፡፡ በኤድስ ምክንያትም የሚሞት ሰው የለም፡፡ ተጓዳኝ በሽታዎችን በመከላከል፣ ከአልኮልና ከሌሎች ሱሶች በመጠበቅ፣ ፆታዊ ግንኙነቶችን በመገደብ፣ በሽታው አለብኝ ብሎ በመቀበልና ሥርዓተ ምግብን በማስተካከል መኖር ይቻላል፡፡ ይህን አቀናጅተን ኤድስ ላይ በሠራነው ሥራም ለውጥ አምጥተናል ብለን እናምናለን፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት በሚል ስያሜ እየሠራችሁ ነው፡፡ በዚህኛው ፕሮጀክት ምን ተካቷል?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ የኤድስ ስርጭት፣ የታመመ ሰውና ሞት ሲቀንስ፣ አቅጣጫችንን ወደ ልማት አድርገን፣ በአራት ፕሮግራሞች ላይ እየሠራን ነው፡፡ ኤድስ ላይ የምንሠራው ቢኖርም፣ እንደ በፊቱ ለብቻው ትኩረት አንሰጠውም፡፡ ፕሮግራሙንና ሽፋናችንን አስፍተን በአምስት ዓመት መርሐ ግብራችን አካተን የኅብረተሰቡ ልማት ላይ እየሠራን ነው፡፡ አገሪቷ ያላትን የልማት ዕቅድ በሚደርስ መልኩ ዕቅድ አውጥተናል፡፡ አንዱ የሕፃናትና የወጣቶች ልማት ሲሆን፣ ይህ ፕሮግራም ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ችግሮች መቅረፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ፣ ትምህርት፣ መጠለያ፣ የምክር አገልግሎትና የሕግ ከለላ በመስጠት ዙሪያ ሕፃናት ላይ እንሠራለን፡፡ ልጆች ባሉበት ቦታ ሳይፈናቀሉ ማኅበረሰብ አቀፍ የሆነ የጤና ክብካቤ እናደርጋለን፡፡ ልጆች ወላጆቻቸው እንኳን ቢሞቱ፣ ዘመዶቻቸው ጋር ሆነው ማንነታቸው እንደተጠበቀ፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን አውቀው እንዲኖሩ እናደርጋለን፡፡ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ብዙ ሕፃናት አሉ፡፡ እነዚህ ሕፃናት ሆዳቸው ባዶ መሆን የለበትም፡፡ ስለሆነም የምግብ ፕሮግራምም አለን፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ በዚህ ፕሮግራም ሥር ምን ያህል ተረጂዎች አላችሁ?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ አዲስ አበባ በሁሉም ክፍላተ ከተሞችና ሰሜን ሸዋ ውስጥ አሁን ላይ 15 ሺሕ ያህል ሕፃናትና ታዳጊዎች እንረዳለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በስፖንሰርሺፕ የምናግዛቸው አሉን፡፡ ውጭ ያሉ በወር ለአንድ ልጅ 20 ዶላር፣ አገር ውስጥ ያሉ 400 ብር እየደገፉን፣ ገንዘቡንም ለሚያሳድጉ ቤተሰቦች በየወሩ ቀጥታ እየሰጠን የምናግዝበት አሠራር አለ፡፡ ከ15 ሺዎቹ 600 ያህሉ በስፖንሰር የሚረዱ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና ክብካቤ እንሠራለን፡፡ ኤድስ እዚህ ውስጥ ተካቶ ይሠራል፡፡ በዚህ ፕሮግራም የግልና አካባቢ ንጽህናን ጨምሮ ጤና ነክ ነገሮች ይከናወናሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የቤተሰብን ኢኮኖሚ ማጠናከር ነው፡፡ በዚህ ሥር ቁጠባን ጨምሮ መሠረታዊ የንግድ ክህሎት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ኢንተርፕረነርሺፕ ላይም እናሠለጥናለን፡፡ በዚህ በተለይ ለሴቶች ትኩረት እንሰጣለን፡፡ የብድርና ቁጠባ ማኅበር በማቋቋም ያለወለድ እየወሰዱ ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም መቆጠብ ግድ ነው፡፡ የዚህ ዓላማ በጣም የተቸገሩትን ከተረጂነትና ጥገኝነት ማላቀቅ ነው፡፡ ሌላው ባላቸው ቦታ ላይ የጓሮ አትክልት እንዲያበቅሉ ነው፡፡ ሰሜን ሸዋ ላይ ምርጥ ዘር እንሰጣለን፡፡ በተሰጣቸው ዘር አምርተው ለሌሎች እንዲያዳርሱ እናደርጋለን፡፡ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አትክልት እንዲያበቅሉና እንዲመገቡ፣ ብሎም እንዲሸጡ እያስቻልን ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ኤድስ ላይ መዘናጋት አለ ይባላል፡፡ በእናንተ በኩል መልሶ እንዳያገረሽ ምን እያደረጋችሁ ነው?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ እንደ ድሮው በጅምላ ሳይሆን ማነው ለበሽታው ተጋላጭ የሆነው የሚለውን ለይተን ሴተኛ አዳሪዎች ላይ እየሠራን ነው፡፡ ደብረ ብርሃን፣ መሀል ሜዳ፣ ፍቼ፣ ገብረጉራቻ፣ጎሃ ጽዮን ሱሉልታና ሰንዳፋ እንዲሁም በአዲስ አበባ ቂርቆስና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ ፒኤስአይ እየረዳን እንሠራለን፡፡ ሴተኛ አዳሪዎቹ እንዲመረመሩ ተደርጐ፣ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ወደ ሕክምና እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ 15 በመቶ የሚሆኑ ሴተኛ አዳሪዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው፣ ብዙ ቦታዎች ላይ ግን በጣም ትንሽ ነው፡፡

 

ከ50 ሺሕ በላይ ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ድጋፍ ብናደርግም፣ ሁልጊዜ ግን ድጋፍ እየሰጠን አንቀጥልም፡፡ ራሳቸውን በኢኮኖሚ እያጠናከርን ከድጋፍ እንዲወጡ እናደርጋለን፡፡ በዚህም ከልጅነት ጀምሮ ይዘናቸው ዩኒቨርሲቲ የገቡ፣ ተመርቀው ሥራ የያዙ አሉን፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ በሠራችሁት ሥራ የመጣውን ለውጥ እንዴት ይገመግሙታል?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ ሥራው ፈተና አለው፡፡ ሆኖም ትልቅ ለውጥ አይተናል፡፡ ሞትና የታማሚዎች ቁጥር ቀንሷል፡፡ ትልቁ ነገር ሕይወት ማዳን ነው፡፡ እሱን አድርገናል፡፡ ሕፃናቱ እየተማሩ ነው፡፡ በዘነበወርቅ አካባቢ ሁለት ላይብረሪ ሠርተናል፡፡ የአካባቢው ልጆች እየተጠቀሙበት፣ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያም እያለፉ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ሥራውን ሲጀምሩ መነሻዎት ምን ነበር?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ ሥራውን የጀመርኩት በራሴ አቅም ነው፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ያለኝን ሀብት ተጠቅሜ ነው የጀመርኩት፡፡ ትዳር የለኝም፣ ልጅ የለኝም፡፡ ጤና ባለሙያም የሆንኩት እንደ አባት የምናየው ወንድሜ ታሞ በማየቴ ነው፡፡ ገንዘብ ባይኖረኝ በእውቀቴ ወንድሜን እንከባከባለሁ ከሚለው በጐ ዓላማ ተነስቼ ሕዝባችንን ለመርዳት በቅቻለሁ፡፡ የበጐ ሥራ ከውስጤ ያለ ነው፡፡ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በ1970ዎቹ በነርስነት ከተመረቅሁ በኋላ፣ አሰብና የተለያዩ ቦታዎች ሠርቻለሁ፡፡ በሙያው የገባሁት ዩኒፎርሙ አምሮኝ፣ ብር ለማግኘት ሳይሆን፣ ሌሎችን ለመረዳት ነው፡፡ በኋላ ኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት ገብቼ ወላይታ ላይ የነበረውን የድርቅ ተጐጂ ለመታደግ ሠርቻለሁ፡፡ የፕሮጀክት ኃላፊም ነበርኩ፡፡ የራሴን ድርጅት ከ17 ዓመታት በፊት ከመመሥረቴ በፊት ሰሜን ሸዋ፣ ተጉለት፣ ጅማና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሠርቻለሁ፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች አግኝተዋል፡፡ ቢጠቅሱልን?

 

ሲስተር ጥበበ፡‑ የአፍሪካ ሊደርሺፕ ፕራይዝ ማለትም በአፍሪካ የአመራር ብቃት ላሳዩ መሪዎች የሚሰጥ ሽልማት ሲሆን፣ ኔልሰን ማንዴላ ዩዌሪ ሙሴቬኒና ሌሎችም ተሸልመውታል፡፡ እ.ኤ.አ. 2001 ላይ ከታችኛው ኅብረተሰብ ክፍል ገብተው ችግሮችን ከሥር ለመቅረፍ የሚሠሩም በመካተታቸው ከምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ ሆኜ ሎሬት ሲስተር ጥበበ ማኮ የሚል የአፍሪካ ሊደርሺፕ ፕራይዝ ተሸልሜያለሁ፡፡ አብሮ 50 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር የተሰጠኝ ሲሆን፣ ይህንንም ለድርጅቴ ሰጥቻለሁ፡፡ በወቅቱ የኒውዮርክ ትራንስፖርትን የቻሉን ሼህ መሐመድ አላሙዲን ስለነበሩ፣ ለሱ የተሰጠኝን 5 ሺሕ ዶላር ጨምሬ፣ ለድርጅቱ ቢሮ ገዛንበት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 ቤስት ፐርፎርማንስ ፎር ሆም ቤዝድ ኬር በሚል፣ ከሴንተር ኦፍ ኢንተርናሽናል ለርኒንግ ማዕከል ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 ባንኮክ ታይላንድ የዓለም የኤድስ ኮንፍረንስ ሲደረግ፣ እድሮችን አሳትፌ የሠራሁበት መንገድ አዲስና የራሴ ፈጠራ ስለነበር፣ አክሰስ አዋርድ የሚባል ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ በዓለም ከ100 አገሮች ህንድ አንደኛ ስትሆን ከኢትዮጵያ በኛ ድርጅት ሁለተኛ ሆነን ተሸልመናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 ወርልድ ኦፍ ችልድረን፣ ሕፃናት ላይ በሠራነው ሥራ የ20 ሺሕ የአሜሪካ ዶላርና ሜዳልያ ሸልሞኛል፡፡ ኤድስን በመከላሉ ረገድ ድርጅታችን ላመጣው ለውጥ ከሲያትል ፕሪቬንት አዋርድ አግኝቻለሁ፡፡ አሜሪካ ካሉ ዳያስፖራዎች እንዲሁም ከአገር ውስጥም ተሸልሜያለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ስናገር እኔ ፊት ለፊት ብታይም ላስመዘገብኩት ስኬት ብዙ ሰዎች ከኋላዬ አሉ፡፡ ለዚህም ነው ከሽልማቱ አንድ ብር ለራሴ ሳልጠቀም ለድርጀቱ ያዋልኩት፡፡                 

ምንጭ፡- ሪፖርተር ቅፅ 22 ቁጥር 17 13