የአሜሪካው ጆን ዲር ትራክተሮች በኢትዮጵያ ሊገጣጥሙ ነው

 

የአሜሪካው ጆን ዲር ትራክተሮች በኢትዮጵያ ሊገጣጥሙ ነው

 

 

በዓለም በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች አምራችነቱ የሚታወቀው የአሜሪካው ጆን ዲር ኩባንያ የሚያመርታቸው ትራክተሮች በኢትዮጵያ ተገጣጥመው ለገበያ ሊቀርቡ ነው፡፡ በእርሻ ማሽነሪዎች ምርት ከ180 ዓመታት በላይ የዘለቀው ጆን ዲር፣ ትራክተሮችና ሌሎች የእርሻ መሣሪያዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ይገጣጥምበታል የተባለው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተገባደደ በመሆኑ ከሁለት ወራት በኋላ ሥራ ይጀምራል ተብሏል፡፡

 

በኢትዮጵያ የጆን ዲር ወኪል የሆነው ገደብ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ቅዳሜ መስከረም 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው የደንበኞች ዓመታዊ በዓል ወቅት እንዳደረገው፣ የጆን ዲር ትራክተሮች የሚገጣጠሙበት ፋብሪካ በገደብ ኢንጂሪንግና በእንግሊዙ ሎንአግሮ ኩባንያ ጥምረት የተቋቋመ ነው፡፡

 

በሆለታ ከተማ ሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ፋብሪካ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ወጪ ይጠይቃል፡፡ የመገጣጠሚያ ፋብሪካው ሁለት የማምረቻ መስመሮችን በመዘርጋት እያንዳንዳቸው አሥር ትራክተሮችን በቀን የመገጣጠም አቅም እንዳላቸው የጆን ዲር ወኪልና የገደብ ኢንጂነሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቾምቤ ሥዩም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 

የጆን ዲር ምርቶች ከሌሎች ተመሳሳይ ምርቶች ይልቅ ለየት የሚያደርጋቸው መለኪያዎች እንዷቸው የሚገልጹት የገደብ ኢንጂነሪንግ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ በዋጋቸውም ቢሆን ከሌሎች ተመሳሳይ ምርቶች ይልቅ ከፍ ያለ ዋጋ ይጠየቅባቸዋል ተብሏል፡፡

 

የጆንዲር ትራክተሮች በኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጠማቸው ግን ትራክተሮቹ ከውጭ መጥተው ለሽያጭ ይቀበርቡበት ከነበረው ዋጋ እንደሚቀንስ ይጠበቃል፡፡ በተለይ የጆን ዲር ትራክተሮችን ለመግዛት ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረውን ክፍተት ለማስቀረት ያስችላል ተብሏል፡፡

 

‹‹ስለ ጆን ዲር ምርቶች እናውራ ከተባለ ከ30 ዓመታት በፊት ተገዝተው ሥራ ላይ ያሉ የጆን ዲር ምርቶች አሁንም ድረስ እየሠሩ ይገኛሉ፤›› በማለት ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡ ምርቱ ሁለት ትውልድ ሊሻገር ይችላል ያሉት የገደብ ኢንጂነሪንግ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ጥላሁን አበበ፣ ከዚህ አንፃር ለትራክተሮቹ የሚጠየቀው ዋጋ ውድ ሊባል እንደማይችል በመግለጽ ይከራከራሉ፡፡

 

በደንበኞች ቀን አከባበር ላይ ስለጆን ዲር ምርቶች በደንበኞች በኩል ባላቸው ተፈላጊነት መሠረት እንደልብ በቶሎ አለመቅረባቸው ተነስቶ ነበር፡፡ በርካታ ደንበኞች የጂን ዲር ምርቶች ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና በተባለው ጊዜ እንደማይቀርቡላቸው ሲያማርሩ መቆየታቸውን በማስታወስ ከደንበኞች ጋር የነበረን ግንኙነት የሻከረ እንዲሆን የተገደድንበት ጊዜ ነበር ሲሉም አቶ ቾምቤ ይገልጻሉ፡፡

 

የገደብ ኢንጂነሪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቾምቤ አስተያየት ትክክል እንደሆነ በዕለቱ ባሰሙት ንግግር ላይ ተንፀባርቋል፡፡ ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ጠንካራ ጎናችን የነበረው ጥራት ያለው መሣሪያ ማቅረብና ጥሩ አገልግሎት መስጠት ነበር፤›› ያሉት አቶ ቾምቤ፣ ‹‹ደካማ ጎናችን ደግሞ በኩባንያችንም ሆነ ከኩባንያችን ውጭ በሆኑ ምክንያቶች መሣሪያዎችን በቶሎ ማቅረብ አለመቻሉ ነው፤›› በማለት እስካሁን ለነበረው ችግር ደንበኞችን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

 

ምርቶቹን በቶሎ ማቅረብ ያልተቻለባቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ከውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከኩባንያው አቅም ጋር የተያያዙት ይገኙባቸዋል፡፡ ይሁንና ከዚህ በኋላ  እንዲህ ያለው ክፍተት እንዳይፈጠር ትራክተሮቹ እዚሁ እንዲገጣጠሙ ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በደንበኞች የሚፈለጉ ትራክተሮች አገር ውስጥ መግባታቸውንና ከሁለት ወራት በኋላም መገጣጠሚያ ፋብሪካው ሥራ ስለሚጀምር የጆን ዲር ምርት ያለ ችግር ገበያ ላይ የሚቀርብበት ጊዜ እንደሚሆን የገደብ ኩባንያ ኃላፊዎች ለደንበኞቻቸው ገልጸዋል፡፡

 

እንደ ቀደሙ ጊዜ እነዚህን ምርቶች ለመግዛት ብዙ ጊዜ መጠበቅን ለማስቀረት የፋብሪካው ሥራ መጀመር እየተጠበቀ ሲሆን፣ ከሁለት ወራት በኋላ ሥራ ይጀምራል የተባለው ፋብሪካም ሦስት ምዕራፎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡ በመጀመርያው ምዕራፍ በፋብሪካው የሚገጣጠሙት ትራክተሮች ከመጀመሪያውም በተወሰነ ደረጃ (ሴሚ ኖክዳውን) ተገጣጥመው የሚመጡ ሲሆን፣ ቀሪ የመገጣጠም ሥራ በአገር ውስጥ የሚከናወንበት ምዕራፍ ይሆናል፡፡

 

ሁለተኛው የፋብሪካው ግንባታ ምዕራፍ የትራክተሮቹ አካላት ሙሉ ለሙሉ የሚገጣጠሙት በአገር ውስጥ እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡ በሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከትራክተሮቹ አካላት ውስጥ የተወሰኑት በአገር ውስጥ የሚመረቱ ግብዓቶች የሚታከሉበት ይሆናል፡፡ እንደ መወጣጫና መውረጃ ያሉ የትራክተሮቹ አካላትን በጆን ዲር ስታንዳርድ መሠረት አምርቶ ለመገጣጠም ሥራ እንደሚውል ተብራርቷል፡፡

 

ፋብሪካው በመጀመርያው የምርት ዘመኑ የሚገጣጥማቸው ከ45 እስከ 175 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን ትራክተሮች ነው፡፡ የፋብሪካው መከፈት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከውጭ በቀጥታ ሲገባ ሊሸጥበት ከሚችለው ዋጋ በታች እንዲሸጡ ማስቻሉ ብቻም ሳይሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን ለማስፋፋትና ለመጠቀም ለተያዘው ዕቅድ መሳካትም አስተዋጽኦ እንዳለውም የገደብ ኢንጂነሪንግ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

 

በተለይ የሜካናይዜሽን እርሻን ለማስፋፋት በመንግሥት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ፋብሪካው መክፈቱ ምርቱን ያለችግር በቅርበት ለማግኘት ያስችላል ተብሏል፡፡ በመንግሥት ዕቅድ መሠረት በአሥር ዓመት ውስጥ ለእርሻ የሚውሉ ትራክተሮች ቁጥር 120 ሺሕ እንደሚደርሱ ሲጠበቅ፣ ይህንን ግብ ለማሳካት እንደ ጆን ዲር ያሉ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች መስፋፋታቸው ግድ እንደሚል፣ በዚህም የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካው ሥራ መጀመርም አገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

 

ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ያላት የትራክተር አጠቃቀም እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የአገሪቱ የእርሻ ሥራ የሚከናወነው በበሬ የሚታረስ ዘዴ ነው፡፡ የአገሪቱ የግብርና መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እንዳሉ የሚገመቱት ትራክተሮች ቁጥር ከ12,500 የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ በበኩሉ አገልግሎት ላይ ያሉት ትራክተሮች 14 ሺሕ እንደሚጠጉ ይጠቅሳል፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት ኢትዮጵያ በ100 ካሬ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ሁለት ትራክተሮች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡባት አገር ሆናለች፡፡ አገሪቷ ካላት የቆዳ ስፋት አንፃር ሲታይ ይህ የትራክተር መጠን እጅግ አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች 100 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ያላቸው ትራክተር ከ25 በላይ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

በመንግሥት የተያዘው ዕቅድ ግን በአሥር ዓመት ውስጥ 100 ካሬ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ 25 ትራክተሮች እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት በበሬ የሚታረሰውን አገሪቱን የእርሻ መሬት በ50 በመቶ ለመቀነስ የታቀደ በመሆኑ፣ የትራክተር መገጣጠሚያዎችና ማምረቻዎች መስፋፋት እንዳለባቸው ያመላክታል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግም እንደ ጆን ዲር ያሉት ኩባንያዎች እየተስፋፉ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡

 

እንደ ጆን ዲር ያሉ ትላልቅ ኩባንያዎች በቀጥታ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በገደብ ኢንጂነሪንግና በተጣማሪው ኩባንያ የተጀመረው ሥራ ለሌሎችም መንገድ ሊከፍት ይችላል ተብሏል፡፡ ጆን ዲር አፍሪካ ውስጥ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ የለውም፡፡ በኢትዮጵያ የሚከፈተው መገጣጠሚያ ፋብሪካ በገደብ ኢንጂነሪንግ ፍላጎት የሚገነባ እንጂ ጆን ዲር ኢንቨስት ያደረገበት እንዳልሆነም ታውቋል፡፡ ሆኖም ትራክተሮቹ በኢትዮጵያ እንዲገጣጠሙ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ይህ ጅምር ጆን ዲር አፍሪካ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ሊያነሳሳው እንደሚችል አቶ ቾምቤ ያምናሉ፡፡

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከፈተው መገጣጠሚያ ፋብሪካ የጆን ዲር ኢንቨስትመንት ከታከለበት ለአፍሪካ ገበያ የሚቀርበው ምርት ከኢትዮጵያ እንዲሰራጭ የሚያስችል ይሆናል ተብሏል፡፡ ጆን ዲር ከአሜሪካ ውጭ ለመላው ዓለም የሚያቀርባቸውን ምርቶቹን የሚያመርተው በጀርመን፣ በሜክሲኮ፣ በቻይና፣ በብራዚልና በህንድ ነው፡፡

 

እነዚህ አገሮች ከ45 እስከ 225 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን ትራክተሮች የሚያመርቱ አገሮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ምርቶች ውጭ ያሉት የጆን ዲር ምርቶች በተለይ ትላልቆቹ በአሜሪካ ማምረቻዎች የሚመረቱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቾምቤ፣ በሒደት ሌሎች የጆን ዲር ትራክተሮች በሚገነባው ፋብሪካ ውስጥ እንዲገጣጠሙ ለማድረግ ዕቅድ አላቸው፡፡ የመጠቀም ውጥኑን ለማስፋት መንግሥት ለእርሻ መሣሪያዎች የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንዲሰጥ ማድረጉ መልካም እንደሆነ የሚጠቀሱት አቶ ቾምቤ፣ ሌሎች ማረሻዎችም ተመሳሳይ ድጋፍ ይሻሉ ብለዋል፡፡ ከቀረጥ ነፃ ምርቶችን ለመገበያየት ገበሬዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መጠየቅ የለባቸውም ብለዋል፡፡

 

ገደብ ኢንጂነሪንግ ከመገጣጠሚያ ፋብሪካ ግንባታው ባሻገር፣ በዚህ ዓመት ለገበያ የሚያቀርባቸውን ምርቶቹንም አስተዋውቋል፡፡ በተለይ ከአገሪቱ የግብርና ፀባይ ጋር ለተያያዙ ምርቶች ትኩረት በመስጠት ከጆን ዲር ጋር በመነጋገር እንዲመረቱ የሚያደርጋቸው ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡

 

ከዚህ ቀደም ጤፍን ለመውቃት የሚያስችል መሣሪያ ማስተዋወቁ ይታወሳል፡፡ በዘንድሮው የደንበኞች ቀንም ወደ ገበያ ይዟቸው እንደሚገባ ካስተዋወቃቸው የጆን ዲር ምርቶች መካከል ጤፍን በመስመር መዝራት የሚያስችለው ይገኝበታል፡፡ ይህ መሣሪያ በዋናነት ጤፍን በመስመር ለመዝራት የሚያስችል ቢሆንም ስንዴ፣ ገብስና ሌሎች አዝርዕትን በመስመር ለመዝራት የሚያስችል በመሆኑም፣ አገልግሎቱም አቅርቦቱም ተፈላጊ እንደሚሆን ይጠበቃል ተብሏል፡፡

 

‹‹ጤፍ ዓለም አቀፍ ምርት እየሆነ ነው፤›› የሚሉት አቶ ጥላሁን፣ ጤፍን የበለጠ  ምርታማ ለማድረግ ዘመናዊ መንገድ መጠቀም ግድ ሆኗል ብለዋል፡፡ በተለይ ጤፍን መካናይዝድ ለማድረግ በመንግሥት እየተሠራ ያለውን ሥራ ለማገዝ እንዲህ ያሉ መሣሪያዎችን መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ፣ የጤፍ የምርት ሒደትን በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድግ ከሚያስችሉ መሣሪያዎች መካከል አንዱ የሆነው ጤፍን በመስመር መዝራት የሚያስችለው መሣሪያ ለገበያ አቅርቧል፡፡ ይህ መሣሪያ ዘርን ከመቆጠብ በላይ አስቸጋሪና አድካሚ የሆነውን የጤፍ የዝግጅት ሒደትን ያስቀራል ተብሎለታል፡፡

 

ገደብ ኢንጂነሪንግ የጆን ዲር ምርቶችን ማከፋፈል ከጀመረ 11 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በጆን ዲር የሠለጠኑ አሥር ባለሙያዎችን የያዘ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትራክተር መገጣጠም ሥራ ላይ የተሠማሩ ሁለት ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

 ምንጭ፡- ሪፖርተር ቅፅ 22 ቁጥር 17 13