Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ሰዎችን እንዲታመሙ የሚያደርጋቸው ምንድነው? ለምን እንታመማለን

==ሰዎችን እንዲታመሙ የሚያደርጋቸው ምንድነው? ለምን እንታመማለን?==

 

 

የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ በሽታዎች ሲለከፍ፣ ሲታመምና ያለጊዜው ሲሞት ኖሯል፤ ታሪክ የመዘገባቸውን የቅርብ መቶ ዓመታት ሁኔታ እንኳን ስንመለከት በሽታዎች በሰው ልጅ ላይ የሚያደርሱትን የተፅእኖ መንገድ በመቀያየር የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ ዛሬ በየሕክምና ማዕከሉ እንደቀልድ የሚነገረን “ታፎይድ ነው” የሚባለው በሽታ እንኳን መድኃኒቱ ባልተገኘለት የቅርብ ዘመን የሚልዮኖችን ሕይወት ቀጥፎአል፡፡

በአንፃራዊነት ሲታይ ባሁን ዘመን የጤና ሁኔታ ከሌሎች ጊዜያት የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ይችላል፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ሰው ከሁኔታዎች ጋር የመለማመድ ችሎታው በመጨመሩ፣ የተለያዩ ክትባቶች መፈጠራቸው፣ አንዳንድ በሽታዎችን(Infections) የመቋቋም አቅሙ ማደግ እንዲሁም የሕክምና ዕውቀት አድጎ መስፋፋት መቻሉ እንደሆነ ይታመናል፡፡

አሁን በምንገኝበት ዘመን አንዳንድ በሽታዎች ጊዜያዊና ለክፉ የማይሰጡ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በሰውነት የውስጥ አካላት አሰራር ላይ ጣልቃ የሚገቡና ስርዓቱን የሚለውጡ ወይም የሚያዛቡ በመሆናቸው በጣም አደገኛ ናቸው፡፡ በርግጥ ሰዎች በበሽታ የሚያዙበት መንገድ በጣም የተለያየና የተወሳሰበ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ለባክቴሪያና ለቫይረስ በመጋለጥ፣ የተበከለ ምግብና መጠጥ በመጠቀም፣ በጥገኛ ተዋሲያን አማካኝነት፣ በምግብ እጥረት፣ በዘር በሚተላለፉ በሽታዎች፣ ጤነኛ ባልሆነ የአኗኗር ዘይቤ የሚከሰት፣ ለአንዳንድ ጠንቀኛ ኬሚካሎች መጋለጥና ሌሎች ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

==በሽታዎችና መንስኤዎቻቸው==

በሽታዎች እንደአጠቃላይ ተላላፊና የማይተላለፉ ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ፤ መንስኤዎቻቸውን ለማወቅ ግን አብዛኛውን ጊዜ ሲቸግረን ይታያል፤ አንድ በሽታ በአንድ የሆነ ምክንያት አሊያም በብዙ ምክንያቶች ድምር ውጤት ሊከሰት ይችላል፤ በመሆኑም መንስኤዎችን ለማግኘት አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ ጥልቅ ምርመራዎችን ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

አንድ ሰው ከላይ የተጠቀሱትን የጤንነት መስፈርቶች ሙሉ ለሙሉ ማሟላት ይከብደዋል፤ ምክንያቱም በአካላዊ ጤንነት ላይ ብቻ እንኳን ብንመለከት ጤናን ሊያሳጡ የሚችሉ ገጠመኞች በጣም ብዙ በመሆናቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ጤንነት ከብዙ ነገሮች ጋር በሰንሰለታማ ግንኙነት የተሳሰረ በመሆኑ ያንዱ መጓደል ለሌላ ምክንያት እየሆነ የሚወሳሰብ ነገር ነው፡፡ እንደአጠቃላይ አካላዊ ጤና ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ምክንያቶች ሊስተጓጎል ይችላል፡-

1. በተፈጥሮ የሚከሰት የአካል ወይም የይዘት መዛባት፣

2. በዘር የሚወረስ ለተወሰኑ በሽታዎች ተጠቂነት (ለምሳሌ፡- የደም አለመርጋት ችግሮች)፣

3. ከወሊድ ችግሮች ጋር በተያያዘ (ለምሳሌ፡- የነርቭ ጉዳት)፣

4. በጥቃቅን ህዋሳት አማካኝነት፣

a. በቫይረሶች፡- (ለምሳሌ፡ ኩፍኝ፣ ጉድፍ፣ ጆሮ ደግፍ፣ ጉንፋን፣ የህፃናት ተቅማጥ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ)፣

b. በባክቴሪያዎች (ለምሳሌ፡- የሳምባ ምች፣ ተስቦ፣ የደም ተቅማጥ፣ የሳምባ ነቀርሳ፣ ስጋ ደዌ፣ ቂጥኝ)፣

c. በጥገኞች ወይም ፓራሳይቶች (ለምሳሌ፡- ወባ፣ ዝሆኔ፣ ኮሶ፣ ወስፋት እና ሌሎች ጥገኛ የአንጀት ትላትሎች)፣

d. በፈንገስ (ለምሳሌ፡- ጭርት፣ ቋቁቻና መሰል የቆዳ በሽታዎች)፣

5. በምግብ ወይም አስፈላጊ የምግብ ንጥረ ነገሮች ጉድለት (ለምሳሌ፡- የደም ማነስ፣ ክዋሾርኮር)፣

6. በአካል ላይ በሚደርስ ቀጥተኛ አደጋ (ለምሳሌ፡- ቃጠሎ፣ የመኪና አደጋ፣ ድብደባ)፣

7. በኬሚካሎች መመረዝ(መርዛማ እፅዋት በመመገብ፣ መድኃኒቶችን ከታዘዘው በላይ በመውሰድ)፣

8. የሆርሞኖች ምርት መዛባት (ለምሳሌ፡ እንቅርት፣ የስኳር በሸታ)፣

9. ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የሕዋስ መባዛት (ቲዩሞር ወይም ካንሰር) እና

10. የማይታወቅ መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡

የተለያዩ በሽታዎችን ለመረዳት፣ ለመከላከል ወይም ለማከም በሚታሰብበት ጊዜ የመንስኤ ምክንያቶችን አንጥሮ መለየት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡

==ተላላፊ በሽታዎች==

ተላላፊ በሽታዎች ከሕመምተኞች ወደ ጤነኞች ሊተላለፉ የሚችሉ ሲሆን የማይተላለፉ በሽታዎች ደግሞ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው የማይተላለፉና የበሽታዎቹም መንስኤ ለየት ያለ ነው፡፡ ስለዚህ የትኞቹ በሽታዎች ተላላፊ እንዲሁም የትኞቹ የማይተላለፉ እንደሆኑ ለይቶ ማወቅ ሁኔታውን ለመቆጣጠር አስፈላጊ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ እና በሌሎችም ታዳጊ ሃገሮች ውስጥ አብዛኛውን ህብረተሰብ የሚያጠቁት በሽታዎች በጥቃቅን ህዋሳት አማካኝነት የሚተላለፉ ሲሆኑ ሌላው ደግሞ በምግብ እጥረት ምክንያት የሚመጣ ነው፡፡ በተለይም ወባ፣ የሳምባ ነቀርሳ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ እንዲሁም የህጻናት ተቅማጥና የሳምባ ምች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፤ እነዚህ በሽታዎች በየአመት የብዙ ሰዎችን ህይወት ይቀጥፋሉ፡፡

በህዋሳት አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎች እንደ ህዋሳቱ ዓይነት የተለያየ የመተላለፊያ መንገድ ያላቸው ሲሆን ባጠቃላይ ግን እነኝህ መተላለፊያ መንገዶች እንደሚከተለው ሊመደቡ ይችላሉ፡፡

1. በምግብ የሚተላለፉ፡- (ለምሳሌ፡- ኮሶ፣ የምግብ መመረዝ፣ ተስቦ፣ የህፃናት ተቅማጥ)

2. ውሃ ወለድ የሆኑ (ለምሳሌ፡- አተት/ኮሌራ፣ ተስቦ )

3. ከሰገራ ጋር በሚኖር ንክኪ ማለትም በእጅ፣ በዝንቦች ወይም ከመጠጥና ምግብ ጋር በሚኖር ንክኪ የሚተላለፉ (ለምሳሌ፡- ወስፋት፣ አሜባ፣ የህፃናት ተቅማጥ)

4. በነፍሳት አማካኝነት የሚተላለፉ ማለትም የተለያዩ ትንኞች፣ መዥገር፣ ቅማል የሚተላለፉ (ለምሳሌ፡- ወባ፣ ቢጫ ወባ)

5. በቀጥተኛ ንክኪ የሚተላለፉ (ለምሳሌ፡- የቁስል ማመርቀዝ፣ የዐይን ማዝ፣ የተለያዩ የቆዳ በሽታዎች፣ የእብድ ውሻ በሽታ)

6. በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ (ለምሳሌ፡- ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች፣ ቂጥኝ)

7. ከደምና ከሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ጋር በሚደረግ ንክኪ የሚተላለፉ (ለምሳሌ፡- ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የተለያዩ ዓይነት የጉበት ልክፍቶች)

8. በትንፋሽ ወይም በአየር የሚተላለፉ (ለምሳሌ፡- ማጅራት ገትር፣ ኩፍኝ፣ ጉድፍ፣ ጉንፋን፣ የሳምባ ነቀርሳ) መጥቀስ ይችላል፡፡

==ምርመራ==

ስለአንድ በሽታ ለማወቅ በሽተኛው ከሚገልፃቸው ምልክቶች በተጨማሪ የአካልና የቤተሙከራ(Lab) ምርመራ በተጨማሪ ይደረጋል፤ አንድ በሽታ በተላላፊ ህዋሳት የተከሰተ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት የሚለውን ለመለየት ማስረጃዎች ያስፈልጋሉ፤ ለምሳሌ አንድ ጠንቀኛ ህዋስ ወደ ሰውነታችን ገብቶ ከሆነ፣ ሰውነታችን ጠንቀኛውን ህዋስ ለመከላከል የሚያዘጋጀው የተለየ ፀረ ጠንቀኛ-ህዋስ በበሽተኛው ሰውነት ውስጥ መኖሩን የሚመለከት ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት በሽታውን ለመለየት የሚደረጉ ምርመራዎች ደም ወይንም ሌላ ከሰውነት የመነጨ ፈሳሽ ማለትም ሽንት፣ አክታ፣ ሰገራ፣ መግል፣ የሳምባ ልባስ ፈሳሽና ወዘተ… የሚፈትሹ ይሆናሉ፡፡

በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት የሚመጡ የተለዩ ምልክቶችን የሚሰጡ ጉልህ የሆኑ የአካላት የቅርፅ ለውጦችን በማየትም በሽታው ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚቻልበት ሁኔታም አለ፤ እነኚህን ለውጦች ለማየት በመሳሪያ የታገዘ ቀጥተኛ የሆነ የውስጥ አካል እይታ(ኤንዶስኮፒ)፣ በድምፅ-መሰል ሞገዶች የታገዘ የአልትራሳውንድ ምርመራ፣ ኤክስ ሬይ ወይም ራጅ፣ ሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ እና ሌሎችም የውስጥ አካላትን ጠልቆ ለማየት የሚያስችሉ ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሰውነት ውስጥ የተጠቃውን አካል ክፍል በትንሹ ቆንጥሮ በመውሰድ የሚደረግ የረቂቅ ማይክሮስኮፕ ምርመራ ውጤትም ስለበሽታው ዓይነት ፍንጭ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

==በሽታን መከላከል==

በሽታን ቀድሞ በመከላከል መንገድ የሚደረግ ዝግጅት አብዛኛውን ጊዜ አዋጭ መንገድ ነው፤ በተለይ ተላላፊ በሽታዎችን መሰረታዊ የሆኑ መርሆዎችን በመከተል ከበሽታው መያዝ መትረፍ ይችላል፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ደግሞ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል ሁኔታው እንዳይከሰት ርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል፤ ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች ቀድሞ መከላከል ላይ መሰረት ያደረጉ ርምጃዎችን በመከተል ሁኔታዎቹን ማስቀረት ይቻላል፡፡ እነኝህ ርምጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. ከአስተማማኝ ምንጭ ያልተገኘን የመጠጥ ውኃ ሁልጊዜ ካፈሉ በኋላ አቀዝቅዞና አጣርቶ መጠጣት፣

2. በጥሬነታቸው የሚበሉ ምግቦችን በሚገባ አጥቦ መመገብ፣

3. ምግቦችን በደንብ አብስሎ መመገብ፤ ያልተመረመረ ጥሬ ስጋ ኣለመብላት፣

4. አንዴ የበሰለን ምግብ ህዋሳት እንዳይራቡበት አቀዝቅዞ ማስቀመጥና ለመብላት ሲያስፈልግ በሚገባ ማሞቅ፣

5. የተመጣጠነ የምግብ አወሳሰድ ስልትን መጠቀም፣

6. ማንኛውንም አይነት ፍሳሽ ማለትም የህፃናት ሰገራን ጨምሮ በአግባቡ ማስወገድ፣

7. ከመፀዳዳት በኋላ ሁልጊዜ እጅን በደንብ በሳሙና መታጠብ፣

8. የግል ንፅህናን መጠበቅ፤ ገላን፣ ጸጉርን እንዲሁም ጥርስን በየጊዜው መታጠብ፣

9. በትዳር አንድ ለአንድ መወሰን፣

10. ከትዳር ውጪ በሚደረግ ወሲብ ወቅት በጭንብል መጠቀም፣

11. ደረቅ ቆሻሻን ማቃጠል ወይንም መቅበር፣

12. ዝንቦችን ማስወገድ፣

13. በተቻለ መጠን የትንኞች መራቢያ የሆነ የውኃ ጥርቅም ማጥፋት፣

14. በትንኞች ላለመነከስ በተለይ ማታ ተጠቂ በሆኑ አካባቢዎች በመከላከያ አጎበር ተከልሎ መተኛት፣

15. መኖሪያ ቤት እና ሌሎች ክፍሎች በቂ የንጹህ አየር ዝውውር እንዲኖራቸው ማድረግ፣

16. በሽታ ሳይጀምር የመከላከያ ክትባት ያላቸውን በወቅቱ መውሰድ ናቸው፡፡

 

ምንጭ፦ሰርቫይቫል 101/Survival 101