ባልሰራበትም መማር በራሱ ትልቅ ነገር ነው ብላለች

ቤቲ ጂ. ‹‹የማይቻል የለም›› ትላለች

 

 

  ቤቲ ጂ. ‹‹የማይቻል የለም›› ትላለች

 

 * ምርጥ ኢትዮጵያዊ ዘፋኞች የምትላቸውን ትዘረዝራለች

                       *ባልሰራበትም መማር በራሱ ትልቅ ነገር ነው ብላለች

                        *በሙዚቃ ህይወት ፈታኙ የሥራ ዲሲፕሊን ነው

    አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ቤቲ ጂ፤ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በሊሴ ገ/ማሪያም ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ከታናሽ እህቷ ጋር ለትምህርት ወደ ፈረንሳይ ብታቀናም በትምህርቷ ብዙ ሳትገፋ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡ ለምን? ሆኖም በአገሯ ላይ ተምራ ሁለት ድግሪዎችን አግኝታለች፡፡ ከታዳጊነቷ ጀምሮ ግን ላለፉት 12 ዓመታት ከሙዚቃ አልተለየችም፡፡ ቤቲ ጂ. እንዴት ወደ ሙዚቃው ህይወት ገባች? “ማነው ፍፁም?” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሟ ምላሽ ምን ይመስላል? በሚሉትና በአዲስ ዓመት ዋዜማ ከአብዱ ኪያር ጋር በጊዮን ሆቴል ስለምታቀርበው የሙዚቃ ኮንሰርት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር አውግታለች፡፡

 

    ዋና ስምሽ ብሩክታዊት ጌታሁን ቢሆንም የምትጠቀሚው ግን ቤቲ ጂ. የሚለውን ነው፡፡ የተለየ ምክንያት አለሽ?

የሙዚቃ ፍቅሩ በውስጤ ካደረብኝ ጊዜ ጀምሮ መጫወት የምፈልገው በዓለም አቀፍ መድረክ ነበር፡፡ እናም ብሩክታዊት የሚለውን ስም የውጭ ዜጎች ሲጠሩት ስለሚከብዳቸው ያበላሹታል የሚል ስጋት አደረብኝ። ስለዚህ እናቴ ባወጣችልኝ ስም ‹‹ቤቲ›› እንዲሉኝና ጌታሁን በሚለው የአባቴ ስም የመጀመሪያ ፊደል ‹‹ጂ›› ቀለል ብሏቸው እንዲጠሩኝ በማሰብ ነው ቤቲ ጂ.ን የመረጥኩት፡፡

እንዴት ወደ እንግሊዝኛ ዘፈኖች ልታደይ ቻልሽ ?

የተማርኩት ሊሴ ገ/ማሪያም እንደመሆኑ ሙዚቃ የጀመርኩት እዚያው ት/ቤት ውስጥ በተዘጋጀ ካርኒቫል ላይ ነው፡፡ ገና የ16 ዓመት ልጅ እያለሁ ማለት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 12 ዓመታት በዘፈኑ ነው የቀጠልኩት፡፡ ከት/ቤቱ ካርኒቫል በኋላ ሀይስኩል መድረክ ላይ ሰራሁኝ፡፡ ከዚያም ኢምፔሪያል ሆቴል “Rising Hiphop Squad” ከተባሉ ቡድኖች ጋር ስሰራ ከዲጄ ፋትሱ ጋር ተዋወቅን፡፡ ከዚያም ዘሪቱ ከበደ ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር የምትሰራውን የክለብ ስራ ስታቆም፣ እኔ እሷን ተክቼ እንድሰራ አደረገኝ፡፡ ይሄ እንግዲህ የዛሬ 12 ዓመት አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ እንዴት ወደ እንግሊዝኛ ዘፈን ልታደይ ቻልሽ ላልሺኝ፣ የተማርኩበት ትምህርት ቤት ሊሴ ገ/ማሪያም የፈረንሳይኛ ቋንቋም ተፅዕኖ አሳድሮብኛል፡፡ እህቴ ደግሞ ካቴድራል ትማር ስለነበር ብዙ እንግሊዝኛ ዘፈኖችና ፊልሞችን እናይ ነበር፡፡ በነዚህ ተፅዕኖዎች እንግሊዝኛ መዝፈን ቀጠልኩ ማለት ነው፡፡ እነ ማይክል ጃክሰንን እያየሁ ስላደግሁ፣እንደነሱ የመሆን ህልም ነበረኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ወደ እንግሊዝኛው አደላ የነበረው፡፡

በአብዛኛው ፊቸሪንግ በመግባትና አጅበሽ በመዝፈን ነበር የምትታወቂው፡፡ ለብቻሽ የወጣሽበት የመጀመሪያ ነጠላ ዜማሽ “ካንተ አይበልጥም” የሚለው ይመስለኛል…?

ልክ ነው፡፡ በጣም የታወቅሁት ናቲ ማን በፊውቸሪንግ ባጀበኝ “ከአንተ አይበልጥም” የተሰኘ ነጠላ ዜማዬ ነው፡፡

እስቲ በመድረክ ላይ ከእነማን ጋር እንደሰራሽ አስታውሺን…?

ከናቲ ማን ጋር ለረጅም አመታት አብረን ሰርተናል፡፡ ነፍሱን ይማረውና ከኢዮብ መኮንን ጋር ነጠላ ዜማ በጋራ ባናወጣም፣ ብዙ መድረኮችን አብረን ተጫውተናል፡፡ የረጅም ጊዜ ትውውቅ  ነበረን፡፡ ከዘሪቱ ጋርም ሰርቻለሁ፡፡ ከሄኖክ አበበ ጋር እንዲሁ አብረን ሰርተናል። ከብዙዎቹ ድምፃውያን ጋር አብሬ ሰርቻለሁ ማለት እችላለሁ፡፡

በርካታ የምሽት ክበቦች ውስጥ በመስራት ራስሽን በሙዚቃ እንዳሳደግሽ ይነገራል፡፡ የት የት ሰርተሻል?

መጀመሪያ የሰራሁበት ክለብ ‹‹ሀርለም ጃዝ›› ይባላል፤ ቦሌ ጫፍ ላይ ነበር የሚገኘው፤ አሁን ሳይዘጋ አይቀርም፡፡ እኔ በምሰራበት ጊዜ ሳፋሪ ነበር የሚባለው፡፡ ባለቤቶቹ አርመንና የኢትዮጵያ ክልሶች ነበሩ። እዚያ ለአንድ ዓመት ያህል አገልግያለሁ፡፡ ከዚያም ‹‹ፓንዳ ክለብ›› ለአንድ ዓመት፣ አምባሳደር ሲኒማ ስር በሚገኘው ‹‹ኢሉዢን›› ብዙ ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ‹‹ፍሪ ዞን›› የተባለ ክብ ውስጥም ተጫውቻለሁ፡፡ አሁን የማላስታውሳቸው ብዙ ክለቦችም ሰርቻለሁ፡፡

ሙሉ በሙሉ የእንግሊዝኛ ዘፈኖች አልበም እየሰራሽ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለሱ አውጊኝ?

እውነት ነው፤ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ መጫወት የምፈልገው በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ነው፡፡ አለም አቀፍ አርቲስት ለመሆን የሚያበቃኝ ሙሉ በሙሉ እንግሊዝኛ የሆነ አልበም ከግማሽ በላይ ሰርቼያለሁ፡፡ ወደ ስምንት ዘፈኖች ገደማ አልቀዋል፤አሁን ተጨማሪ  ዘፈኖችን እየሰራሁ ነው፡፡

ከእነማን ጋር ነው አልበሙን እየሰራሽ ያለሺው?

በቅርቡ ያወጣሁትን ‹‹ማነው ፍፁም›› የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሜን ከሰሩልኝ ድርጅቶች ጋር ነው የምሰራው፡፡ አፍሪካ አሜሪካዊያን ሲሆኑ ‹‹One vision production ›› እና ‹‹Exposure Entertainment›› የሚባሉ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያ አልበሜንም ጥሩ አደርገው ነው የሰሩት፡፡ ይህም አልበም ሲያልቅ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

‹‹ፍፁም ማነው›› የተሰኘው አልበምሽ በጣም ተወዷል፡፡ ከእንግሊዝኛ ሙዚቃ ወደ አማርኛ መግባቱ አልከበደሽም?

እርግጥ ከባድ ነው፡፡ ሰው እስከ ዛሬ በእንግሊዝኛ ዘፈን ለምዶሽ ወደ አማርኛ ስትመጪ ብዙ ነገሮች ሊከብዱ ይችላሉ፡፡ ብዙ ጥንቃቄም አድርጌያለሁ፡፡ ጥንቃቄ አድርጌያለሁ ስልሽ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዘፈን ሳበረክት፣ ህዝቡ ከሚወደው መራቅ የለብኝም፣ እኔም የምወደውን ማጣት የለብኝም በሚል፣ መሀከሉን ቦታ ለማግኘት በጣም ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ከባድ ቢሆንም በጣም ተሳክቷል፡፡ የሥራውን መሳካት የምለካው በሚደርሱኝ አስተያየቶች ነው፤በጣም ተቀባይነት አግኝቷል በደንብ ተደምጧል፡፡ ወጥቶ ለህዝብ ጆሮ እስከሚደርስ ጭንቀትና ፍርሀት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አላሳፈረኝም። አሁን እየሰራሁት ላለው አዲስ አልበም፣ ብርታትና ጉልበትን ሰጥቶኛል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

በተለይ የከሚሴ ምት ያለው “ና”  የተሰኘው ዘፈንሽ በጣም ተወዷል፡፡ ግጥምና ዜማውን ማን ነው የሰራው? የቪዲዮ ክሊፑንስ?

“ና” የተሰኘው ዘፈን የእኔን ማንነት፣ ኢትዮጵያዊነቴን የሚወክል ነው ተብሎ የተሰራ ነው፡፡ በጣም ተወዷል፡፡ የአልበሙን ግጥምና ዜማ አብዛኛውን ናቲ ማን ነው የሰራው፡፡ እኔ የሶስትና አራት ዘፈኖችን ግጥምና ዜማ ሰርቻለሁ፡፡ ቅንብሩንና የፕሮዳክሽኑን ስራ እንደነገርኩሽ ‹‹One Vision Production›› እና ‹‹Exposure Entertainment›› የተባሉት ድርጅቶች ናቸው የሰሩት፡፡

የሙዚቃ ቪዲዮውን የቀረፅነው ባህርዳር ሄደን ነው፡፡ ምቱ የከሚሴ ብቻ አይደለም፤ የሰቆጣ አለው፤ የጎንደርና የጎጃምም አለበት፡፡ በአጠቃላይ የአማራውን የሙዚቃ ስልት አንድ ላይ አድርጌ የተጫወትኩበት ነው፡፡

በሙዚቃ ህይወት  ፈታኝ የሚባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው ትያለሽ?

በሙዚቃ አለም ውስጥ ዋናውና ፈታኙ ነገር ራስን ገዝቶ መስራት ነው፡፡ ምን ማለት ነው? ስራው አለቃ ስለማይኖረው አንቺ የራስሽ አለቃ ሆነሽ፣ ቀን ቆርጠሽ ፕሮግራም ይዘሽ፣ በዚህ ጊዜ አልበሜን ለአድማጭ ማብቃት አለብኝ፤ ጠዋት ተነስቼ ግጥምና ዜማ መፃፍ አለብኝ… የሚለውን ወስነሽ መስራት ከባድ ነው፡፡ ስራው በሰዓት ያልተገደበ፣ አለቃ የሌለው እንደመሆኑ ትንሽ ያሰንፋል፡፡ ልክ ቢሮ በሰዓት ገብተሽ… ሰርተሽ፣ በሰአት የምትወጭበት አይደለም፡፡ ስለዚህ ስራውን አለቃ አድርገሽ ራስሽን ገዝተሽ፣ መስራት ፈተና ነው፡፡ መዘናጋትና ስንፍና  ስለሚኖር ማለቴ ነው፡፡ ሌላው ክለብ ውስጥ በሳምንት አምስትና ስድስት ቀን የምትሰሪ ከሆነ፣ እየሰራሽ እንደሆነ ስለሚሰማሽና ብር ስለምታገኚ፣ ወደ ሌላው ደረጃ ራስሽን ለማሸጋገር ትዘናጊያለሽ፡፡ አልበም በማውጣት ወደተሻለ ደረጃ ለማደግ መጣርን ትረሺዋለሽ፡፡ ይህም አንዱ ፈተና ነው፡፡ ሌላውና የሁሉም አርቲስት ችግር የሆነው ደግሞ የቅጂ መብት አለመከበር ነው፡፡ አንዴ አልበም ከወጣ በኋላ እረፍት የለም፡፡ ተሰረቀ አልተሰረቀ የሚል ሀሳብ አለ፣ የፕሮሞሽን ጉዳይ አለ፣ ስፖንሰር የሚፈልገው ራሱ አርቲስቱ ነው፤ይሄ ሁሉ የዘርፉ ፈተና ነው፡፡

እነዚህን ፈተናዎች አንቺ እንዴት ተወጣሻቸው? ተሞክሮሽን ንገሪን…

አንዳንዴ ሪስክ ወስደሽ የምትወስኚባቸው ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ እኔ በስፖንሰር በኩል እግዚአብሔር ይመስገን፤ቢጂአይ ኢትዮጵያ ነው አልበሜን ያሳተመልኝ። በጣም ተባብረውኛል፡፡ እኔም መጀመሪያ ወደ እነሱ ነው የሄድኩት፤ ተቀብለው አሳትመውልኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ቢጂአይ ኢትዮጵያን አመሰግናለሁ፡፡ እኔ እድለኛ ሆኜ ነው እንጂ ስፖንሰር ፍለጋ ብዙ ልንከራተት እችል ነበር፡፡ እኛ አገር ይህን የሚሰራ ኤጀንት ስለሌለ፣ ራስሽ ነሽ ስፖንሰር ፍለጋ የምትሄጂው፡፡ በፕሮሞተርነት ደረጃ የሚንቀሳቀሱት ይህን ሁሉ ኃላፊነት ሊሸከሙልሽ አይችሉም፡፡ በውጭው ዓለም ይህን የሚሰሩ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ብቻ ብዙ ነገር ቀላል ቢመስልም ከባድ ነው፤ ነገር ግን የማይቻል የለም እላለሁ፡፡

የአንቺ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ማን ነው?

የኔ የመጀመሪያው ምርጥ ዘፋኝ፣ በጣም የማደንቀው፣ ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ በደንብ ካደግኩና ከበሰልኩ በኋላ አልበሞቹን እየገዛሁ ማዳመጥ ስጀምር የድምፅ አወጣጡ፣ አገላለፁ ሁሉ… እያስደነቀኝ መጣ። በዘፈኑ ሲያዝን አብረሽ ታዝኛለሽ፣ ሲተክዝም ሲደስትም እንደዚያው አብረሽ ትጓዣለሽ፡፡ ጥላሁንን በጣም ነው የምወደው፡፡ ጋሽ ማህሙድ አህመድንም በጣም እወደዋለሁ፤ የቴዲ አፍሮ የግጥም አፃፃፍ በጣም ያስደንቀኛል፤ የዜማ አካሄዱ ይማርከኛል፡፡ ዘሪቱንም በጣም እወዳታለሁ፤ጎበዝ ድምፃዊት ናት፤ብዙ ጊዜም አብሬያት ስለሰራሁ ችሎታዋን በቅርበት አውቀዋለሁ። እነዚህ የማደንቃቸው ሰዎች የተለየ ተሰጥኦ ስላላቸው ከነሱ ብዙ ትምህርት እወስዳለሁ፡፡ አዲስ ከመጡት ልጅ ሚካኤል በጣም አሪፍ ዘፋኝ ነው፡፡ ናቲ ማን ያው ይታወቃል… እንደማደንቀው። ከጋሽ ማህሙድ ጋር አሜሪካ ሲልቨር ስፕሪንግ ውስጥ አንድ ፌስቲቫል ላይ አንድ ላይ ባንዘፍንም፣ እሱም እኔም እዛው መድረክ ላይ ተጫውተናል፡፡ የድምፅ ጉልበት፣ የመድረክ አያያዝና የድምፅ አወጣጥን ---- ከጋሽ ማህሙድ ብዙ መማር አለብን፡፡ በተመሳሳይ መድረክ በመዝፈኔ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፡፡

አልበም ከወጣ በኋላ ኮንሰርት ማቅረብ ተለምዷል። አንቺ አልበሙን አስመርቀሽ፣ ኮንሰርቱን ዝም ያልሽው ለምንድነው ነው?

እንዳልሺው አልበሙን በክለብ H20 አስመርቄያለሁ። ነገር ግን ኮንሰርቱን በተለያዩ ምክንያቶች ዘግየት ያደረግኩት ይመስለኛል፡፡ በአዲስ አመት ዋዜማ ከአብዱ ኪያር ጋር በመሆን ከአድናቂዎቼ ጋር ፊት ለፊት እገናኛለሁ፡፡ ለዋዜማ ኮንሰርት በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡

ከኮንሰርቱ ምን ትጠብቂያለሽ? ከአብዱ ኪያር ጋር ስትሰሪ የመጀመሪያሽ እንደመሆኑ ጥምረታችሁ የተዋጣለት ይሆናል ብለሽ ታስቢያለሽ?

ከኮንሰርቱ የምጠብቀው ጥሩ ስራ ሰርቼ ታዳሚውን ማስደሰት ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ አስደስታቸዋለሁ። እኔን በአዲሱ አልበሜ እንዳስደሰቱኝ ሁሉ፣ እነሱን ለማስደሰት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግሁ ነው። ከአብዱ ጋር በደንብ እንጣመራለን፡፡ ለምን? እኔ ከብዙዎቹ ጋር የመስራት ልምድ አለኝ፤ እሱም ጎበዝ አርቲስት ነው፡፡ ጥሩ ስራ ከመስራት የሚያግደን ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እኔ ራሴን ችዬ ከመስራቴ በፊት በፊቸሪንግ ከሰዎች ጋር በመስራት ነው ወደ እውቅናው የመጣሁት፡፡ ከናቲ፣ ከጆኒ ራጋ፣ ከሄኖክ አበበና ከሌሎቸም ጋር ፊቸሪንግ ሰርቻለሁ፤ በትብብር መስራትም እወዳለሁ፡፡ ወደፊትም እንዲህ አይነት የአብሮነት ስራዎችን እቀጥላለሁ፡፡

ለኮንሰርቱ ምን ያህል ከፍያ ጠየቅሽ?

ብዙም አልጠየኩም፡፡ እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለናፈቀኝ፣ ዋናው ትኩረቴ ከህዝቡ ጋር መገናኘት ነው፡፡ ቁጥሩን ባልገልፅም ብዙ አልጠየኩም፡፡ ጥሩ ስራ ከሰራሽ ገንዘቡ በኋላ በራሱ ጊዜ ይመጣል፡፡

ትዳር…መስርተሻል? ልጆችስ … እንዴት ነው?

ትዳር አልመሰረትኩም፡፡ ልጆችም አልወለድኩም። ጓደኛ አለኝ፤ ገና በሂደት ላይ ነኝ፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ሁሉም ይሆናል፡፡ አሁን በሙሉ ልቤ ስራ ላይ ነው ያለሁት፡፡

በትምህርት በኩል ሁለት ዲግሪ እንዳለሽ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?

እውነት ነው፡፡ በቢዝነስ ማኔጅመንትና በኦፊስ ማኔጅመንት ከኮሜርስ ሁለት ዲግሪዎችን አግኝቻለሁ። ግን አልሰራሁባቸውም፡፡ የተማርኩትም እናቴ ካልተማርሽ አትዘፍኚም ብላ ስላስገደደችኝ ነው፡፡ ለነገሩ መማር አይከፋም፤አንድ ቀን ከሙዚቃ ብወጣ በተማርኩበት ዘርፍ መስራት እችላለሁ፡፡ ባልሰራበትም መማር በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ 

መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልሽ ----

እኔም ለሁሉም መልካም አዲስ ዓመት እመኛለሁ። ለህዝቡ፡- በአዲስ አመት ዋዜማ በጊዮን ሆቴል ከአብዱ ኪያር እና ከመሀሪ ብራዘርስ ባንድ ጋር ላስደስታችሁ እየተዘጋጀሁ በመሆኑ እዛው እንገናኝ፤ ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን-----የሚል መልዕክት አለኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡

 

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ

 

  

Related Topics