Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

እባብ ለቁጥራቸው መቀነስ አስተዋፅኦ አድርጓል

ብርቅዬው ብሔረሰብ

 

Image result for ጂንካ

 

61 ብቻ ሲቀሩ፤ 12ቱ ብቻ ቋንቋውን ይናገራሉ

እባብ ለቁጥራቸው መቀነስ አስተዋፅኦ አድርጓል

 

      የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል የ56 ብሔሮች መገኛ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል 16 ያህሉ ዋና መናገሻቸውን ጂንካ ከተማን አድርገው በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ዞኑ በ8 ወረዳዎች እና 1 የከተማ አስተዳደር የተከፈለ ሲሆን ከነዚህ ወረዳዎች “ቀይ አፈር” የተባለች አነስተኛ ከተማን መናገሻቸው አድርገው የሚናሩት የበና፤ ፀማይ እና ብራይሌ ብሔሮች ወረዳ የሆነችው የበና ፀማይ ወረዳ አንዷ ነች፡፡

በወረዳው የበና እና ፀማይ ብሔሮች ከፍተኛውን ቁጥር የያዙ ሲሆን ብራይሌዎች በአንፃሩ በመጥፋት ስጋት ላይ ያሉ ብሔሮች ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰአት 61 የብራይሌ ብሔር አባላት ብቻ ሲኖሩ አንጐታ የተባለውን ቋንቋቸውን መናገር የሚችሉት 12 ያህል ብቻ ናቸው፡፡

የብሔረሰቡ አባላት በወረዳው በእንጨቴ ቀበሌ በልዩ ስሙ ገኤ ወንዝ፣ ድሮ ነው በሚባል መንደር ተሰባስበው የሚኖሩ ሲሆን፤ አንድም የብሔረሰቡ አባል ከተጠቀሰው መንደር ውጪ በየትኛውም ስፍራ አይገኝም፡፡

ብሔረሰቡ የተመሠረተበት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ድርቅና ረሃብ በመከሰቱ በምግብ ፍለጋ ስምሪት ሲሆን፤ ከሰባት ከማያንሱ ብሄረሰቦች ተሰባስበው የተመሠረተ ነው፡፡ እነዚህም ኮንሶ፣ ገዋዳ፣ ማሌ፣ ቦና፣ ጋቦ፣ ቦረና እና ኤርቦሬ ናቸው፡፡ ለብሔረሰቡ ቁጥር ማነስ ዋነኛ ምክንያቶች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በአካባቢው የትምህርትና የጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመገንባታቸው፣ በበረሃማው የአየር ንብረት ምክንያት በሚፈጠሩ መርዛማ እባቦች ተነድፎ መሞት እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ በወባ ወረርሽኝ እና በሌሎች የጤና እክሎች መጠቃት ይገኙባቸዋል እንደ ወረዳው የባህልና ቱሪዝም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ፡፡

በመጥፋት ላይ ያለው ይህ ብሔረሰብ 3 ባህላዊ የአስተዳደር እርከኖች አሉት፡፡ የበላይ ሆኖ የሚያስተዳድረውና 5 አባላት ያሉት “ባልኮ” ሲሰኝ፣ በተመሳሳይ 5 አባላትን ያቀፈውና የምክትል አስተዳዳሪነት ስልጣን ያለው አካል ደግሞ “ሙርጃል አፍ” ይሰኛል፡፡ “ሙርጃል አፍ” ዋነኛ ሃላፊነቱ በብሔረሰቡ መካከል ችግሮች ሲፈጠሩ ይፈታል፣ ስብሰባዎች ሲኖሩ ባህላዊ መጠጥ (ጨቃ) እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ ያስተላልፋል። ሶስተኛው የአስተዳደር እርከን እንደቀደሙት ሁሉ 5 አባላትን ያቀፈ ሲሆን “ጉርማልኮ” ይሰኛል፡፡ የዚህ ደረጃ ባለስልጣን መሆኑን ለመለየት “ዘንግ” ይይዛል፡፡ ዘንጉን የያዙት የሚሰበሰቡበት ሜዳ ላይ ሴቶች ድርሽ ማለት አይፈቀድላቸውም፡፡ የሜዳው ስም ናቦ ይባላል፡፡

ብራይሌዎች ሶስት የጋብቻ አይነቶች አሏቸው፡፡ የመጀመያው “ኢፋም” የተሰኘ ሲሆን በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈፀም ነው፡፡ “አይሳት ሻዳል ቤት” የተሰኘው ጋብቻ ደግሞ የውርስ ጋብቻ ነው፡፡

“እዴ ባዶጂካ ኢስማ” ደግሞ በተጋቢ ወላጆች ስምምነት የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡ ወንዱ ለአቅመ አዳም በሚደርስበት ወቅት በሴቷ ጥሎሽ የሚሰጠው አሣ፣ ማርና ጋቢ ነው፡፡ በብሔረሰቡ የወንድም ሆነ የሴት ግርዛት ነውር ነው፡፡

በብራይሌዎች ዘንድ በለቅሶ ወይም ሃዘን ወቅት ለልጅና ለአዋቂ የሚከወነው ስርአት የተለያየ ነው፡፡ አዋቂ ሲሞት አረቄ ተገዝቶ፣ ባህላዊ መጠጥ (ጨቃ) እየተጠጣ ይጨፈራል፣ መሣሪያ ይተኮሳል፣ የሟች ደግ ስራ በዘፈን ይወደሳል፡፡

ይህ ስርአት እየተከወነ አንድ ቀን ይታደርና ቀጥሎ ባለው ቀን ግብአተ መሬቱ ይፈፀማል፡፡ ወጣት ወይም ልጅ ከሞተ ደግሞ እጅግ ይታዘናል፡፡ አምርረው ያለቅሳሉ። የቡና ገለባ (ሸፈሮ ይባላል) አፍልተው ይጠጣሉ፣ ሃዘናቸውን ለመግለጽም አምባር፣ ጨሌና ሌሎችንም ጌጣጌጦቻቸውን ያወልቃሉ፤ ፀጉራቸውንም ይላጫሉ፡፡

ብራይሌዎች በስፋት ለምግብነት የሚጠቀሙት አሣ ነው፡፡ በአካባቢው ከሚገኘው የወይጦ ወንዝ አሣ በማውጣት፣ የአሣውን ስጋ እንደ ቋንጣ በመዘልዘል ይመገቡታል፡፡ ሙዝ፣ በርበሬና ሽንኩርት ይተክላሉ፡፡ በባህላዊ ቀፎ ንብ በማርባት በሚያገኙት የማር ምርትም ይታወቃሉ፡፡

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ