ጫት በማህበራዊ ቀውስና በኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መካከል እያከራከረ ነው

 

የጫት ነገር

 

Image result for የጫት ጉዳት

 

ጫት በማህበራዊ ቀውስና በኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መካከል እያከራከረ ነው

ጫት በኢትየጵያ ያለው የገበያ ድርሻም ሆነ ማህበራዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው። በወጪ ንግድ ያለው የገቢ መጠን፤ እንደዚሁም ምርቱ ካለው ሰፊ የገበያ ዝውውር አኳያ ለኢኮኖሚው ያለው ድጋፍ በቀላሉ የሚታይ አይደለም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በዚያው መጠን ምርቱ በዜጎችን ላይ በብዙ መልኩ ጉዳትን በማድረስ እየፈጠረ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖም በዝርዝር መታየት አለበት የሚሉ ወገኖችም በሌላ አቅጣጫ ድምፃችን ይሰማ ማለት ጀምረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጫትን በተመለከተ እየተደረጉ ያሉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች አሉ። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ጫት በህብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት መሰረት በማድረግ አሁን ያለው የምርቱና የገበያ እንቅስቃሴው ቁጥጥር እንዲደረግበት የሚሹ ናቸው። አንዳንዶች ከዚህ ባለፈ ምርቱ እገዳ ተጥሎበት በሂደት ከገበያ መውጣት አለበት የሚሉም ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጫትና ሺሻ ንግድና አጠቃቀም ላይ በቀጣይ የሚያተኩር ህግን ለማውጣት በፍትህ ሚኒስቴር አማካኝነት ረቂቅ ህግ የተዘጋጀ ሲሆን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በዚሁ ዙሪያ የራሱን እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወጣትና ልማት በኢትዮጵያ በሚል ርእስ በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ አዘጋጅነት አንድ ውይይት በግዮን ሆቴል ተካሄዶ ነበር። ውይይቱ ጫት በሀገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሰፊው የተዳሰሱበት ነበር። በእለቱ “ወጣትና ጫት” በኢትዮጵያ በሚል ርእስ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዶክተር ግርማ ነጋሽ አቅርበዋል። ባለሙያው ጫት እያደረሰ ካለው ማህበራዊ ቀውስ ጀምሮ ለሀገሪቱ እያስገኘ ካለው የውጪ ምንዛሪ ገቢ ድረስ ሰፋ ያለ ዳሰሳን አድርገዋል። በኢኮኖሚ ጥቅሙና በማህበራዊ ጉዳቱ መካከል ያለውን አነጋጋሪ ጉዳይም ለመዳሰስ ሞክረዋል። ጫት ከማሳ ዝግጅት ፣እስከ ተጠቃሚው እጅ እስከሚደርስ ድረስ ያለውን ፈጣንና የተቀላጠፈ እንቅስቃሴንም በመዳሰስ በኢትዮጵያ በሌሎች የምርት የገበያ ተስስሮች ላይም ይህ አሰራር በጥሩ ማሳያነት ሊታይ የሚችል መሆኑንም ባለሙያው አመልክተዋል።

 

ሕግና ጫት

 

     ጫትን በተመለከተ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በኢትዮጵያ ገደብን የሚጥል ህግ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ እስከዛሬም የወጣበት ሁኔታ የለም። ሆኖም በአንድ መልኩ መንግስት ከምርቱ ግብይቱ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ለማግኘት በዚያው መጠንም በምርቱ ላይ ግብርን ከፍ በማድረግ ተጠቃሚውን እንዳይደፋፈር ለመከላከል ኤክሳይዝ ታክስ የተጣለበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ ቀደም በአዋጅ 309/1987 በጫት ላይ ግብር ተጥሎ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ በ1995 ዓ.ም ቢራን፣ ወይን ጠጅን፣ ውስኪን ሲጋራን በመሳሰሉ ምርቶችና ሌሎች የቅንጦት እቃዎች ላይ ታክስ ሲጣል ጫት ግን በዚህ አዋጅ የተጠቀሰበት ሁኔታ አልነበረም። ሆኖም ቀደም ሲል ጫትን በተመለከተ 1987 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ 309 በመሻር በ2004 የጫት ኤክሳይዝ ታክስ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። የአዋጁ አላማ እንደሚገልፀው አዋጁ እንዲወጣ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት፤ የሀገር ውስጥ የጫት ፍጆታ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመሄዱ ይህንኑ ሁኔታ ለመለወጥ ነው። በዚህ አዋጅ መሠረት በአገር ውስጥ ተመርቶ በመነሻው ክልል ጥቅም ላይ የሚውልና ወደ ሌላ ክልል የሚጓጓዝ ጫት፤ በኪሎ ግራም አምስት ብር ታክስ እንዲጣልበት ይደነግጋል። ኤክሳይዝ ታክስ ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክሶች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን በዋነኝነት የሚጣለው በተለያዩ ሁኔታዎች በቀጥታ በማይከለከሉ፤ ነገር ግን በማይበረታቱ የምርት አይነቶች ነው። ከሚጣለው ግብር ጋር በተያያዘ ምርቶቹ ወይም አገልግሎቶቹ ዋጋቸው ከፍ እንዲል በማድረግ የተጠቃሚውን ቁጥር ዝቅ ለማድረግ የሚጣል የታክስ አይነት በመሆኑ በአሜሪካ በተለይ በቁማር አገልግሎት ላይ ከፍ ያለ የአክሳይዝ ታክስ የተጣለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

ጫትና የአውሮፓ ገበያ

 

     ረዘም ላሉ ዓመታት ጫት በአውሮፓ ከፍተኛ ገበያ ነበረው። ጫትን በአውሮፓ የሚጠቀሙት በአውሮፓ ያሉ የየሀገሩ ተወላጆች ሳይሆኑ ከመካከለኛው ምስራቅና ከምስራቅ አፍሪካ በመሄድ ኑሯቸውን በአውሮፓ ያደረጉ አረቦችና አፍሪካውያን ናቸው። ከአረቦች የመናውያን በዋነኝነት ሲጠቀሱ ከምስራቅ አፍሪካ ደግሞ ሶማሌያውያን፣ ኢትዮጵያን እንደዚሁም ኬኒያውያን ይጠቀሳሉ። በጫት ላይ እገዳ ከመጣሉ በፊት በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የራሳቸውን ሰፊ ጥናት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በመጨረሻ ምርቱ ጥርስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፣ ሱሰኛ ያደርጋል፣ በሂደት ለአእምሮ   ህመምተኝነትም ያጋልጣል፣ እንደዚሁም ለማህበረሰባዊ ቀውስ ይዳርጋል በሚል የመጀመሪያውን የእገዳ እርምጃ የወሰዱት የሰሜን አውሮፓ ሀገራት ናቸው።

 

     ሆኖም በእንግሊዝ የጫት ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ የመካከለኛው ምስራቅና የምስራቅ አፍሪካ ሰዎች ስለነበሩና በሀገሪቱም የጫት ግብይት ረዥም ጊዜን ያስቆጠረ በመሆኑ እንደሌሎች ሀገራት በአንድ ጊዜ እገዳን መጣሉ ከባድ ነበር። እንደ ዘጋርዲያን ዘገባ ጫት በእንግሊዝ ከመታገዱ በፊት ከ60 ዓመት ላላነሰ ጊዜ በሀገሪቱ ገበያ ውስጥ ቆይቷል። ሌሎቹ የአውሮፓ ሀገራት በምርቱ ላይ እገዳን ቢጥሉም እንግሊዝ እገዳን አለመጣሏ ግን ሀገሪቱን በዋና ማዕከልነት በመጠቀም ምርቱ አውሮፓ ምድር ከገባ በኋላ በህገወጥ መንገድ ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የሚሰራጭበት ሁኔታ ነበር። ጫትን ከዩናይትድ ኪንግደም ማስወጣት ከመላ አውሮፓ ማስወጣት መሆኑን የተረዱ በርካታ ፀረ ጫት አቋምን የያዙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ቡድኖች በእንግሊዝ ህግ አውጪዎች ላይ የተደራጀ ጫናን ሲፈጥሩ፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ እነዚህን አካላት በመቃወም ጫትን የሚመለከት ረቂቅ ህግ እንኳን እንዳይኖር ከፍተኛ የማግባባት ስራን ሲሰሩ የነበሩት በዋነኝነት በዚያው በእንግሊዝ ይኖሩ የነበሩት የሶማሌ ማህበረሰብ አባላት ነበሩ።

 

     ጉዳዩ በጥብቅ ከማከራከሩ የተነሳ እስከ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት ድረስም አምርቶ ነበር። ጉዳዩን በኢኮኖሚ ትንታኔ በመመልከትም በተለይ ኑሯቸውን ጫት ላይ ያደረጉ የኬኒያ ገበሬዎችንም በምሳሌነት በማሳየት እገዳው የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖም ቀላል እንዳልሆነ ለማሳየት የተሞከረበት ሁኔታ ቢኖርም የጫት ደጋፊ ወገኖች ያካሂዱት የነበረው ዘመቻ ስኬትን ባለማግኘቱ ጫት ከሰኔ ወር 2014 ጀምሮ በዩናይትድ ኪንግደም እንዲታገድ መደረጉን የቢቢሲ የድረገፅ ዘገባ ያመለክታል።

 

በፎረም ፎር ሶሻል ሰተዲስ መድረክ ላይ ጫት በህብረሰቡ ላይ እያደረሰ ካለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ የጤንነት ጉዳት አኳያ እግዳ ሊደረግበት ይገባል ያሉ ተሳታፊዎችም ነበሩ። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ጫት በኢትዮጵያ ረዥም እድሜን ያሰቆጠረና ከሱስ ጀምሮ እስከ ሰንሰለታዊ የንግድ ትስስር ድረስ የዘለቀ ከመሆኑ ባሻገር፤ ከሀገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከልም አንዱ በመሆኑ “እገዳ” የሚለው ጉዳይ በአንድ ጊዜ እንደማይሆን የገለፁ ተሳታፊዎችም ነበሩ። በሌላ አቅጣጫ አሜሪካውያን ሳይቀሩ የሜክሲኮን የአደንዛዥ እፅን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ገንዘብ መድበው ስርጭቱን ለማዳከም ለብዙ ጊዜያት ጥረት ቢያደርጉም የተፈለገው ውጤት ሊመጣ አለመቻሉን የገለፁ አንዳንድ ተሳታፊዎች፤ በጫት ላይ እገዳን ለመጣል ቀላል ፈተና እንደማይሆን ገልፀዋል። ከእገዳ በመለስ ግን ሌሎች መሰራት የሚገባቸው ስራዎች ያሉ መሆኑንም የገለፁ ተሳታፊዎች ነበሩ። እነዚህ ተሳታፊዎች የጫት ግብይትና ዝውውር ላይ የራሱ የሆነ የቁጥጥር ስርአት (Regulation) ሊኖር ያስፈልጋል ያሉ ናቸው።

 

     በአልኮሎች መጠጦች ላይ ምርቶቹን ማን መጠቀም እንደሚገባው የእድሜ ገደብ የሚቀመጥበት አሰራር ያለ በመሆኑና የሲጋራና ሌሎች የትምባሆ ምርቶች ላይም ጎጂነታቸው በግልፅ የሚቀመጥበት ሁኔታ ስላለ በጫት የግብይት ቁጥጥር ውስጥም መሰል አሰራሮች ተግባራዊ ቢደረጉ፤ ከእድሜ በታች ያሉ ህፃናት ምርቱን እንዳይጠቀሙ ለመከላከል ይረዳል በማለት አስረድተዋል። በሌላ አቅጣጫ ምርቱ ለሀገሪቱ ቀላል የማይባል የውጪ ምንዛሬን የሚያስገኝ በመሆኑ በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ ሊደረግ የሚገባው ቁጥጥርና ክትትል ቢኖርም እንኳን ወደ ውጪ የመላኩ ስራ ግን ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት የገለፁም ነበሩ። ከዚሁ በተቃራኒ “እኛ ላለመጠቀም ከፈለግን ሌሎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ከሞራልም አንፃር አግባብነት የሌለው በመሆኑ ኤክስፖርቱም ጭምር ቀስ በቀስ በሌላ በመተካት መቅረት መቻል አለበት” ያሉም ነበሩ።

 

     ከዚህም በተጨማሪ ጫት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ እያደረሰ ካለው ማህበራዊና ጤንነታዊ ጉዳት አኳያ በኤክሰፖርት የሚገኘው ገቢ ተመልሶ በእዳ መልክ የሚከፈል በመሆኑ ተገኘ የሚባለው ገቢ ትርጉም የለውም ያሉ ነበሩ። በሀረር አካባቢ ጫት ቅመው በሚሰሩና ጫት ሳይቅሙ በሚሰሩ ገበሬዎች መካከል ያለውን ልዩነት ምሳሌ በመስጠት ማብራሪያ የሠጡት አንድ አስተያየት ሰጪ፤ ጫት በአነቃቂነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ስራን ለመስራት የሚያግዝበት ሁኔታ ቢኖርም፤ ጫትን ቅሞ የሚሰራው ሰው አዲስ ሀይል ፈጥሮ ሳይሆን ያለውን ሀይል ከመጠን በላይ እያቃጠለ በመሆኑ ከወደፊት ሃይሉ ተበድሮ የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ይህም በመሆኑ አንድ ጫት ቅሞ የጉልበት ስራ የሚሰራ ገበሬ ጫት ቅሞ ከማይሰራው ገበሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ስራን የሚሰራበት ሁኔታ ቢኖርም በሂደት ማውጣት ከሚገባው ተፈጥሯዊ ሀይል በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለሚያወጣ፤ ከእድሜ እኩዮቹ አንፃር ሲታይም ፈጥኖ የመውደቅና የእርጅና ምልክቶች የሚታዩበት ሁኔታ ያለ መሆኑንም ተሳታፊው ገልፀዋል።

 

     ይሄንኑ ሃሳብ በማጠናከር ሀገሪቱ አሁን በጫት ኤክስፖርት ገቢ እያገኘች መሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ጎልቶ እየተነገረ ቢሆንም በሌላ መልኩ ደግሞ ጫት በህብረተሰቡ ጤንነትና ማህበራዊ ህይወት ላይ እያደረሰ ባለው መጠነ ሰፊ ጉዳት ሀገሪቱ ዋጋ እየከፈለች በመሆኑ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሰፋ መሆኑን ያመለከቱ ተሣታፊዎችም ነበሩ። ከጫት ጋር በተያያዘ የሚባክነው የስራ ሰአት፣ለሌሎች ተያያዥ ሱሶች የመጋለጥ ሁኔታ፤ እንደዚሁም ለአዕምሮ ህመም ሳይቀር የመጋለጥ ሁኔታዎች በገንዘብ ብቻ ተተምነው ሊቀመጡ የማይችሉ ማህበራዊ ቀውሶች መሆናቸውም ተመልክቷል። መሰል ዘርፈ ብዙ ችገሮች ከመታየት ባለፈ ጫት በመላ ሀገሪቱ አድማሱን እያሰፋ መሄዱ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጫት ያልተለመደባቸው አካባቢዎች ሳይቀሩ ጫት አብቃይ የሆኑበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑን አንዳንድ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

 

     የንግድ ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ጫት በውጪ ገበያ የሚያስገኘው የውጪ ምንዛሬ መጠን በአመት በአማካኝ እስከ 270 ሚሊዮን ዶላር ነው። የዚህ በጀት አመት የስድስት ወራት የጫት የወጪ ንግድ አፈፃፀምንም ከንግድ ሚኒስቴር ያገኘን ሲሆን፤ በዚሁ የሁለት ሺ ሰባት የስድሰት ወራት የወጪ ንግድ ሪፖርት መሰረት የጫት የውጪ ምንዛሪ ገቢ መጠን 149 ሚሊዮን 751 ሺ ዶላር ነው። በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የንግድ ሚኒስቴር ባለሙያ፤ ጫት በውጪ ምንዛሪ ደረጃ ለሀገሪቱ ቀላል የማይባል ገቢን የሚያስገኝ መሆኑን ገልፀው፤ ይሁንና ምርቱን ገበሬዎች በማሳቸው ላይ እንዳያመርቱ የሚከለክልበት እንደዚሁም በግብርናው ዘርፍም ምርታማነታቸው ከፍ እንዲል ክትትል ከሚደረግባቸው የምርት አይነቶች ውስጥም ጫት የተካተተበት ሁኔታ አለመኖሩም ጨምረው ገልፀውልናል።

 

     ቡና አምራች ገበሬው የቡና ምርት ፍላጎት በአለም አቀፍ ገበያ በሚወደቅበት ወቅት የቡና ተክሉን በመንቀል ወደ ጫት የሚዞርበት ሁኔታ እንዳለም ባለሙያው ጨምረው ገልፀውልናል። የጫት ኤክስፖርት ገቢ በአስተማማኝ ገቢነትም ሊያዝ ስለማይችል በሂደት የሀገሪቱ የኤክስፖርት የምርት አይነትና ብዛት እየጎለበተ ሲሄድ የጫት ገቢ መጠን የሚኖረው ተፅዕኖ የሚወርድ መሆኑን ባለሙያው አመልክተዋል። ያገኘናቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጫትን በተመለከተ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተገኙበት በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም ለማካሄድ እንቅስቃሴዎች የተጀመሩበት ሁኔታ አለ። ሲምፖዚየሙን ቀደም ባሉት ጊዜያት ለማካሄድ ታቅዶ በተለያዩ ምክንያቶች ሊራዘም ችሏል። የጫት ዘርፈ ብዙ ጉዳት በተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ ተጠናክሮ እየተነሳ ቢሆንም በኢኮኖሚ በኩል የብዙዎች እንጀራ መሆኑና የሀገሪቱም የውጪ ምንዛሪ ገቢ ማስገኛ የመሆኑ ጉዳይ በርካቶች ጎራ ከፍለው እንዲከራከሩ እያደረጋቸው ነው። ከዚህ በኋላም በጫት ዙሪያ በርካታ የሚነሱ አነጋጋሪ ጉዳዮች የሚኖሩ ሲሆን በቅርቡ ሊካሄድ የታሰበው የጫት ሲምፖዚየምና የፍትህ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ተከታታይ መነጋገሪያ አጀንዳዎችን የሚያስነሱ ናቸው።

ምንጭ፡- ቆንጆ  ህዳር 2004