ተስፋዬ ገብረአብ ከሚበጀው የሚፈጀው

 

ተስፋዬ ገብረአብ ከሚበጀው የሚፈጀው

 

Image result for ተስፋዬ ገብረአብ

 

ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ሰሞኑን የኖህን ልጅ ካምን ሆኖ ከረመ ማለት ይቻላል። አባቱ ኖህ በወይን ጠጅ ሰክሮ እራሱን በማይቆጣጠርበት ጊዜ እራቁትነቱን (ነውሩን) ያየውን ካምን… አይቶ ያልበቃውን፣ ወንድሞቹም የአባታቸውን እራቁትነት አይተው እንዲሳለቁ የጋበዘውን ካምን… ይህን በማድረጉም ዘር ማንዘሩ በአባቱ የተረገመውን ካምን… ተስፋዬ ሆኖ ከረመ። ካምን ለመሆን ህሊና ቢስነት እንጂ ሌላ ችሎታ አለመጠየቁን ተስፋዬ የተረዳው አይመስልም። ድፍረት እንጂ ብልሃት ግድ እንደማይል የገባው አይመስልም። ይህም በሚያቀርባቸው ቁንፅል ታሪኮች ላይ በጉልህ ይነበባል።

ተስፋዬ ገብረአብ ሰሞኑን ካምን የሆነው እንዲህ ነው። ባትወልደውም ያሳደገችውን አገር የታሪክ ጉንፍ እየገላለጠ እራቁትነት ለማየት እጅግ በመጣር ላይ ይገኛል። ለማየት መጣሩ ሳይበቃው ሌሎችም እንዲሳለቁ ‹‹የቅዳሜ ማስታወሻ›› ብሎ በሰየመው ብሎጉ በመጋበዝ ላይ ነው። በተለይ አፄ ምኒልክን፣ አፄ ኃይለሥላሴን፣ እቴጌ ጣይቱ እና እቴጌ መነን የቀጥታ ተጠቂ ለማድረግ ፍላጐት እንዳለው በጉልህ ይታያል። ከእነሱ በሰተጀርባ ደግሞ እኛን ኢላማ አድርጓል፡፡ ‹‹የንጉሠ-ነገሥቱ እናት››፣ ‹‹የጎጃም ልዕልት›› እና ‹‹የመነን አራተኛ ባል›› በተሰኘ ፅሁፉ እነዚህ አጤዎችና ንግሥቶች ላይ ቦጫቂ የንሥር ጥፍር የመሰለ ብዕሩ ሲያንዣብብ በገሃድ ይስተዋላል። እንዴት? ለምን? ምን ፍለጋ? ምን ለማትረፍ? ይሄን ከመፈተሻችን በፊት ተስፋዬ ገብረአብን በጥቂቱ ለማየት እንሞክር። የማይታበለው ነገር ተስፋዬ ገብረአብ ለአማርኛ ሥነ-ፅሁፍ ባለውለታ ነው። ‹‹ያልተመለሰው ባቡር››፣ ‹‹የቢሾፍቱ ቆሪጦች›› እና ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› የተሰኙ ልቦለዶቹ እንደውርዴ ከወላጆቻቸው የወረሱት የዘር ጠባይ ቢኖርባቸውም የትረካ ጥበባቸው ቅርሳችን መሆኑን መካድ አይቻልም። እንዲሁም ሁለት ‹‹ባለቅፅ›› መጽሐፎችንም አበርክቶልናል።

‹‹ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ›› እና ‹‹እፍታ›› የተሰኙት እነዚህ ‹‹ባለቅፅ›› መጽሐፎች ተስፋዬ የጡት አባት ሆኗቸው በጉዲፈቻነት ባያሳድጋቸው ኖሮ ምናልባትም የሥነ- ፅሁፍ አፀድ ውስጥ የማይቀበሩ በጨቅላነት የተቀጠፉ በሆኑ ነበር። ከእነዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ ሁለቱ ‹‹የጋዜጠኛው›› እና ‹‹የደራሲው›› ማስታወሻዎች ተከትለዋል። የዘር በሽታው ካንዱ ሥራ አንዱ የማይሻል ቢሆንም በሁለቱ ‹‹ማስታወሻዎች›› ላይ ተስፋዬ ለጋነቱን አጥቶ፣ እንደዛፍ ተንጋዶ መብቀሉ በጉልህ የሚስተዋልባቸው ሆነዋል።

 የተስፋዬ ገብረአብ አብዛኞቹ ሥራዎች (ብሎጉን ጨምሮ) እንደ ገጠር ሴትወይዘሮ መኳኳያቸው ‹‹ጥላሸት›› ነው። ‹‹ጥላሸቱ›› ደግሞ ከስም ማጥፋት ጥቀርሻ የሚገኝ ነው። ይሁንና ሥራዎቹ ገና በፈገግታ ሲቀርቡን ጉራማይሌአቸው የጥላሸት እንዳልሆነ ሁሉ በውበት ይጠልፉናል። ተስፋዬ ‹‹የሚነቅስበት›› የራሱ የሆነ የቋንቋ እሾህም አለው። እየጠቀጠቀ ከሚያደማው ‹‹ድድ›› ሆነ ‹‹አንገት›› ውስጥ ከማዝጐርጐር የሚመነጭ ውበት ያፈልቃል። ይሄንን ደግሞ ተስፋዬ ያውቃልና የስም ማጥፋት ጥቀርሻውን ሆነ መጠቅጠቂያ እሾሁን አይጥልም። ‹‹የጋዜጠኛው ማስታወሻ›› ላይ ስለመኳኳያ ‹‹ጥላሸቱ›› እንዲህ ይላል። ‹‹በዚህ መጽሐፍ ባልተለመደ ሁኔታ እውነተኛ ስማችሁን ለተጠቀምኩ ሁሉ ባለማስፈቀዴ ይቅርታ እየጠየቅሁ፤ አትቀየሙኝም ብዬ በመገመቴ ደግሞ አመሰግናለሁ።›› ከእጅ ያፈተለከ የጫካ እርግብ ይመስል መጽሐፍን ያህል የረጅም ዘመን ነዋሪ በዘፈቀደ መልቀቅ ከባድ ጥፋት ነው።

ተስፋዬ ገብረአብ ሆን ብሎ ለሰራው ጥፋት ይቅርታውን የጥፋቱ አባሪ አድርጐ መልቀቁ ደግሞ ትልቅ ሹፈት ይሆንብናል። ተስፋዬ የጥፋቱን ጥፋትነት ቀድሞ ቢረዳውም እራሱን ገስፆ መተው የሚችል አይመስልም። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። የተጋባበትን ሳይሆን የለማበትን አንጡራ ባህርይ ስለሚያስተናግድ ብቻ ነው። ልጅ ሆኖ በእናቱ ላይ ያደረገውን ‹‹የደራሲው ማስታወሻ›› ላይ እንዲህ ይተርክልናል። ንዑስ ርዕሱ ‹‹የልጅነት ተራሮች›› ነው። የጓደኛው የነብዩ አባት ኢሬቻን ለማክበር ወደሆራ እየወሰዱአቸው ነው። መንገድ ላይ ስለክብረ በዓሉ መልካም መልካም ነገር ይነግሯቸዋል። ተስፋዬ በጨዋታው መካከል ገብቶ ‹‹እናቴ ግን እንዲህ አልነገረችኝም›› በማለት ክብረ- በዓሉን የሚያጥላላ ነገር ይዘበዝባል። የነብዩ አባት ይሄን በሆዳቸው ይዘው ወደ ተስፋዬ እናት ይሄዳሉ። በነገሩም ላይ ይነጋገራሉ። ሰውዬው ገና እግራቸው ከቤት እንደወጣ እናት ከጉማሬ ቆዳ የተሰራውን አለንጋ አንስተው ተስፋዬ ላይ ይወርዱበታል።

ልጅ ሳለች እናቷ ስለሞተችባት እንዴት የመከራ ጊዜ እንደገፋች ያጫውተናል። በመጨረሻ ወታደር አግብታ ሐረር ስትኖር የአባቷ ስም ማተቧ ላይ ተፅፎ በመገኘቱ ባሏ ወደቤተመንግሥት ያመጣታል። አጤ ምኒልክ ከልጃገረዶች መካከል ይለይዋታል፣ ለራስ አሊም ይድሯታል። በ1888 ዓ.ም. ልጅ እያሱ የተወለደው ከሸዋረጋ እንደሆነ ይነግረናል። እዚህ የተስፋዬ ትርክት ውስጥ ፅሁፉን ወደ ውሸትነት ሊለውጥ የሚችል ከፍተኛ የዘመን ዝንፈት ይታያል። ሸዋረጋ ስትረገዝ እናቷን ከቤተመንግሥት ያባረሯት እቴጌ ጣይቱ እንደሆኑ በገደምዳሜ ተነግሮናል። እንዲያ ከሆነ ጉዳዩ የተፈፀመው ከ1876 ዓ.ም. ወዲህ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም እቴጌ ጣይቱና አጤ ምኒልክ ተገናኝተው የተጋቡት በዚህ ዘመን በመሆኑ ነው። ሸዋረጋ እንደው ከአመት በኋላ ተወለደች ቢባል እንኳን ከ1877 ልጅ ኢያሱን እስከወለደች ጊዜ (1888 ዓ.ም) ያለው ዕድሜ ገና አስራ አንድ ዓመት ብቻ ይሆናል። ተስፋዬ፣ ሸዋረጋ ወታደሩን ያገባችው ለአቅመ ሔዋን ደርሳ መሆኑን ደግሞ ነግሮናል። ታዲያ እንዴት በአስራ አንድ አመት ዕድሜዋ ልትወልድ ቻለች? ድሎት በዝቶ የሴት ወጓን ቀድማ አየች እንዳይባል ሸዋረጋ በችግር ተቆራምዳ ያደገች ናት። ታዲያስ? እንዴት? በምን?... ሙግት እንጂ ስድብ በመረጃ አይደገፍም። ተስፋዬ ገብረአብ ከዘመኑ አፋትቶና አፍኖ እዚህ ዘመን ያመጣው ታሪክ ለዚህ ትውልድ ነውር የሚመስል ጥቃቅን ነገር ስላለበት ብቻ ሙሉ ትኩረቱን የሰጠው ታሪኩን አቅርቦ አንጡራ ኢትዮጵያውያኑን ማሸማቀቁ ላይ ነው። ከዚያም ኢትዮጵያዊ ኩራትን ሰብሮ ሀገር ተከላካይነትን ማዳከም። ከዚያስ? ተስፋዬ ገብረአብ ታሪካችንን ከክብሩ አውርዶ የሴትና የወንድ ‹‹ሎሚ ውርወራ›› ብቻ ለማስመሰል የጣረው ተደጋጋሚና አንድ አይነት ቁመና ያላቸውን ታሪክ ነክ ፅሁፎች በማቅረብ ነው። ‹‹የጎጃም ልዕልት›› የተሰኘው ፅሁፉ በንጉሥ ተክለኃይማኖት ልጅ የተነሳው መኳንንታዊ የጋብቻ ውርክብ እንዴት ለአጠቃላይ ጦርነት አስግቶ እንደነበር ይተርክልናል። በመጨረሻ አጤ ምኒልክ እንዴት እንደቋጩት ይነግረናል። ከቁመታቸውም፣ ከወርዳቸውም ቀናንሶለመፍጠር የፈለጋቸውን አጤ ምኒሊክ በዘዴ ያስተዋውቀናል። ‹‹የመነን 4ኛ ባል›› የተሰኘ ፅሁፉ ደግሞ ያነጣጠረው አጼ ኃይለሥላሴ ላይ ነው። መነን በፊት ሁለት አግብተው ፈትተዋል ይለናል። ልጆችም አሏቸው። በኋላ ሦስተኛ ትዳራቸው ላይ ሳሉ ነው ልጅ ኢያሱ አፋትቶ ለራስ ተፈሪ ሲድራቸው የምንመለከተው ‹‹አምላክ በዚሁ በቃሽ ይበለኝ›› በማለት አራተኛ ትዳራቸውን የተቀበሉት እቴጌ መነን ዘመኑና ዘመነኞቹ ያደረሱባቸው ‹‹ጥቃት›› አጥንታችንን ሰርስሮ ይገባል።

 ይሄ እንግዲህ ተስፋዬ ገብረአብ ቆንፅሎ እንዳቀረበውሁሉ ነገሩን ከሁኔታዎች ነጥለን ስንመለከተው ነው ሀፍረት እንዲሰማን የምንሆነው። ከዚያ ውጭ ግን ነገሩ ሌላ ነው። የዚያ ዘመን ፖለቲካዊ ሀይል የሚመነጨው ከዘር ብቻ ነበር። በመሆኑም አካባቢዎችና ግዛቶች ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ተሳስረው የሚቆዩት በፍትሃዊ የበጀት ክፍፍል ሳይሆን በሚዛናዊ የትዳር ስርጭት ነበር። ሁሉም አካባቢና ግዛት የጋብቻ ዝምድናንና መዋለድን ለዙፋኑ የነገ ተስፋ በዋስትናነት ከያዙ ብቻ የሰላሙ ተባባሪዎች ናቸው። ስለዚህ በንጉሠ ነገሥቱና በመኳንንቱ አካባቢ የነበሩ ሴቶች እንደ ዋነኛ የፖለቲካ መሣሪያ መታየታቸው ግድ ነበር ይሄ በእኛ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓውያን ታሪክ ውስጥ ቦታ ያለው ክስተት ነበር። የሔነሪ ስምንተኛን ታሪክ ማንበብ በቂ ነው።

 የተስፋዬ ገብረአብ በዚህ ዘመን አስተሳሰብ ለማስዳኘት ከታሪክ ጋር የመካሰስ አዝማሚያ ጅልነት ሳይሆን፣ መሰሪነት እንዳለበት እንድንጠረጥር የሚያደርገን ይሄ ነው። ተስፋዬ ያለጥርጥር ከታሪክ ነቁጥ ኢትዮጵያዊ የስብዕና ነውጥ ለመፍጠር በመሞከር ላይ ነው። በተስፋዬ ገብረአብ መስገር ሁልጊዜም የሚፈልገው ቦታ የሚደርሰው ጀርባውን የተከራየው አካል እንደሆነ ግልፅ ነው። ተስፋዬ የራሱ መዳረሻ የለውም። ተስፋዬን እዚህ ታሪክ የመቅመል ሥራ ውስጥ የከተተው ጀርባን አከራይቶ የመኖር ፈረሳዊ ጣጣ ነው። ጋላቢው መንፈስ በግልፅ እኔ ነኝ ባይልም ከተስፋዬ አሰጋገር አስጋሪውን መለየት የሚያዳግት አይደለም። ግን… ግን ተስፋዬን ያለጋላቢ የማይሰግር ‹‹የጋማ-ከብት›› አድርጐ አጉልኛ የገራው ማን ይሆን? እሱ እንደሚለው ባንወልደውም አሳድገነዋልና ጀርባን አከራይቶ የመኖር ፖለቲካዊ ስብዕናው የእኛም መሰደቢያ ገመና ሳይሆን ይቀራል? ‹‹አሳዳጊ…›› በሚል የገመና ተጋሪዎቹ መሆናችን እርግጥ ነው፡፡

 

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ

 

  

Related Topics