ከ«ዙምባራ» እስከ «ጎዳ ዞኮ» የሸመነው ጥበበኛ

 

ድምፃዊ አስናቀ አባተ(አስኔ)

 

ከ«ዙምባራ» እስከ «ጎዳ ዞኮ» የሸመነው ጥበበኛ

 

 ከ«ዙምባራ» እስከ «ጎዳ ዞኮ» የሸመነው ጥበበኛ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በውቢቷ ሀዋሳ ከተማ ነው የተወለደው። ኮረም ውቅሮ ሰፈር ከዕድሜ አኩዮቹ ጋር እየተጫወተ አድጓል፡፡ ከኮረም ውቅሮ ሰፈር ብዙ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የወጡበት፣ የሰፈሩንም ስም ያስጠሩበት ነበር። እርሱም በሙያው የሰፈሩ መከበሪያና መጠሪያ ለመሆን በቅቷል። ብዙ ጊዜ ኮረም ሰፈር «ሰነፍ የለም» ይባላል፡፡ ሁሉም የኮረም ሰፈር ልጆች ታታሪና ለሥራ ያላቸው ተነሳሽነት የተለየ ነው፡፡ እርሱም በዚህ ያምናል። በሰፈሩ ሰነፍ እንዲኖርም አይፈልግም። የሚፈጠሩ መሰናክሎችን በመጋፈጥ አሸንፎ መውጣት የልጅነት ህልሙ ነው።

ድምፃዊ አስናቀ አባተ(አስኔ) ይባላል። ትምህርቱን «ሀ» ብሎ የጀመረው ታቦር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍል ኢትዮጵያ ትቅደም ትምህርት ቤት ቀጥሎ፤ በመጨረሻ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍልን አጠናቋል፡፡ በትምህርት ሂደቱ ውስጥ የመማሪያ ጠረጴዛውን እንደ ከበሮ በመደብደብ ሙዚቃ መጫወት ያዘወትር ስለነበር በበጥባጭነት ይታወቅ ነበር፡፡ ማንኛውም ነገር የሚያወጣው ድምጽ ለእርሱ የተለየ ትርጉም ይሰጠው እንደነበር ያስታውሳል፡፡ እንደዚያም ሆኖ በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ነበር፡፡

አባቱ በ1952ዓ.ም የተመሠረተውና የኢትዮጵያ እርሻ ምርምር እየተባለ በሚጠራው መስሪያ ቤት ሲሰሩ ጎበዝና ታታሪ በመሆናቸው ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ተሸላሚ ነበሩ። በወቅቱ አባቱ የተሸለሙት ፊሊፕስ ሬዲዮ፣ ባንዲራና አቡጀዲ ጨርቅ ታሪካዊ ሽልማት ሆነው በቤተሰቡ ዘንድ ዘወትር ይታወሳሉ፡፡ በተለይ ሰንደቅ ዓላማው አሁንም ድረስ ለቤተሰቡ ትልቅ የክብር መገለጫ ሆኗል። ይህ ባንዲራ ለአስናቀ ህሊና በተለየ መንገድ ገዘፈና ልዩ ስሜት የሚፈጥርበትም ሆነ፡፡ ባንዲራውን ከመውደዱ የተነሳም ወደ ሬጌ ሙዚቃ መሳብ ጀመረ፡፡

ሻሸመኔ ካሉ የጃማይካ ማህበረሰቦች ጋር በመሄድም ለሙዚቃው ያለውን ተሰጥኦ አዳበረ። ከዚያም በሞሊየር የቴአትርና ሰርከስ ቡድን በመግባት የሬጌ ሙዚቃዎችን በመዝፈን ብቃቱን አሳደገ፡፡ በዚያው ከሬጌ ሙዚቃ ጋር ተዋዶ ቀረ። ይህም የሆነው ለአረንጋዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራ ባለው ፍቅር እንደሆነ ዛሬም ድረስ በኩራት ይናገራል፡፡ ዛሬም ድረስ ያ ፍቅሩ እያየለ ሄዶ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ፤ ብሔር ብሔረሰቦች ባህሎች ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን በመስራት ላይ ነው።

ገና በልጅነቱ ነበር ኢትዮጵያዊ ቀለም ያላቸውን ሥራዎች ለመስራት ለራሱ ቃል የገባው፡፡ በአንድ ወቅት ለጓደኞቹ «ታዋቂ ሙዚቀኛ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ» በማለት የወደፊት ህልሙን እንደሚያሳካ ይነግራቸው እንደነበር የሚያስታውሰው አስናቀ፤ ህልሙን ለማሳካት ብዙ ጥሯል። ብዙም ተፈትኗልም፡፡

ሀዋሳ ውስጥ ያልሰራበት ክበብ የለም። ለአብነትም የቤተሰብ መምሪያ፣ የሞሊየር የቴአትርና የሰርከስ ክበብ ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የባህል ኪነት ቡድን አባል ሆኖ ለሁለት ዓመታት ሰርቷል። በዚህ ትልቅ የባህል ቡድን ውስጥ መስራቱ ደግሞ ወደ ብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃና ባህል እንዲሳብና ብቃቱን እንዲያሳድግ አግዞታል፡፡ ከሃያ በላይ የባህል ድምጻውያን ባሉበት የባህል ቡድን ውስጥ ከአርባ በላይ የብሔር ብሔረሰቦች ዜማዎች ይቀነቀኑ ስለነበርም ለእርሱ ምቹ ሆነ። ይህ ሁኔታ ከምንም ነገር በላይ ለብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥም አነሳሳው።

አስናቀ ሁለገብ ሙዚቀኛ ነው። ድምፃዊ ነው፤ ኪቦርድና ቤዝ ጊታርን በሚገባ ይጫወታል፤ ግጥም ይሰራል፤ ዜማ ይፈጥራል፤ ሙዚቃ ያቀናብ ራልም፡፡ ይህን ብቃት ይዞ ሁለገብ ሙዚቀኛነቱን ማሳደግ እንዳለበት አመነ። እናም በባህል ቡድኑ ውስጥ ያካበተውን የሁለት ዓመት ልምድ ይዞ በ20 ዓመቱ አልበም ለመስራት ወደ አዲስ አበባ አቀና፡፡

ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የሁለት ወር ደመወዙን ብቻ ይዞ ነበር፡፡ የቤት ኪራይ ለመክፈል እንኳን ከፍተኛ ችግር ነበር የገጠመው፡፡ ችግሮች ሊገጥሙት እንደሚችሉ አምኖ ከችግሮቹ ጋር ለመጋፈጥ ራሱን አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የዓላማ ፅናቱ ለፈተናዎቹ እጅ እንዳይሰጥ ብርታት ሆኖት ነበርና ብዙም ሳይቸገር «ጃንግል ክሩ» ከሚባል የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ተቀላለቀ። ሁለት የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ቴዲ ዮ፣ ጃሉድና ሌሎችም በሚሰሩበት የሙዚቃ ቡድን ውስጥ በመቀላቀሉ ሀዋሳ ላይ ያካበተውን እውቀት የሚመነዝርበት አጋጣሚ ተፈጠረ።

ድምጻዊ አስናቀ በሥራ አጋጣሚ ከሙዚቃ አቀናባሪው ካሙዙ ካሳ ጋር ተዋወቀ፡፡ ካሙዙም በወቅቱ ለእውቅና የሚያበቃ ሥራ ባይኖረውም ትልቅ ሙዚቀኛ እንደሚሆን አስቀድሞ ተንብዮለት ነበር፡፡ ካሙዙንም ለማሳወቅ የበቁ ሥራዎችንም አብረው ለመስራት ቻሉ፡፡ የማርታ አዱኛ «ወሃለያቤ» የሚለው ሱማልኛ ሙዚቃ አንዱ መታወቂያው ሆነ። ይህ ሙዚቃ በዱርዱር ባንድ በተደጋጋሚ የተዘፈነ ቢሆንም፤ አስናቀ ከአማርኛ ጋር አቀላቅሎ ጥሩ አድርጎ ሲሰራው ግን ከቋንቋው ተናጋሪዎች ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንንም ስሜት የሳበ ሆነ፡፡ ከሰርከስ ቡድኑ ጋር አብራው ስትሰራ የነበረችው ዳይመንድ መልካሙ ጋር የሰራው «ዙምባራ» የተሰኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሙዚቃም ሌላው ለእውቀና ያበቃው ሥራ ሆነ፡፡ እነዚህ ሥራዎች ነበሩ አስናቀን በትክክልም ብቃት እንዳለው እርግጠኛ እንዲሆን ያደረጉት።

«ዙምባራ የሚባለውን የሙዚቃ መሣሪያ ያወቅኩት አንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተላለፈ የብሔረሰቡ አንድ ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም «ዙምባራ» ስለሚባለው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ የተላለፈውን መረጃ በሚገባ ያዝኩት፡፡ የሙዚቃውን ርዕስም ያኔ ነበር ያወጣሁት፡፡ ለዳይመንድ የሚስማማ ሙዚቃ በመሆኑ መረጥኩላት፡፡ በአምስት ቀን ነው የጨረስነው፡፡ ሥራችንን ለካሙዙ ካሳ አሳየነው፡፡ ዳይመንድ ከቤኒሻንጉል የመጣች ነበር የመሰለችውና ቅድሚያ ሰጠን፡፡ ካሙዙም ʻበትክክልም እንዲህ ዓይነት ዜማ አልሰማሁም ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ታዋቂ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝʼ ነበር ያለው፡፡ እንዳለውም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላ ሀገሪቷ ተወዳጅ ሆነ፡፡ ተወዳጅነቱን አስጠብቆም አምስት ዓመት ለመደመጥ የበቃ ሙዚቃ ሆነ፡፡ በዚያ ልክ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር። የእኔ እምነት ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያውን እንደማስተዋውቅ ነበር እርግጠኛ የነበርኩት፡፡ በወቅቱ በሦስት ራዲዮ ጣቢያ ብቻ ነበር የተደመጠው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉም ተቀባበሉት።»

ዙምባራ ድምፃዊ አስናቀንና ድምፃዊት ዳይመንድን ያሳወቀ የሙዚቃ መሣሪያውንም ያስተዋወቀ አነጋጋሪ ሥራ ሆነ። ያልተለመደ ሥራ ይዞ በመጀመሪያ ሥራው ከፍተኛ የእውቀና ማማ ላይ የወጣው ድምፃዊ ዝናውን ተከትለው የመጡትን ሁሉ በአግባቡ ለመስተናገድ ጥንቃቄ አድርጓል። በጭብጨባ ወጥቶ ፈጥኖ ለመውደቅ የመጣበት ስብዕና አልፈቀደለትምና በመጀመሪያ ሥራው ያገኘውን ዝና ለማስጥበቅ የተለየ ትኩረት ማድረጉን ያስታውሳል።

የዙምባራ ሙዚቃ በሬዲዮ እንደተሰማ የሙዚቃ ቪዲዮውን (ክሊፕ) ከሚሰራለት ሰው ጋር በአጋጣሚ ተዋወቀ፡፡ ይህንኑ ሲገልጽ «ቴዲ የሚባል ልጅ በአጋጣሚ ከሚስቱ ጋር ለመዝናናት ሲወጣ ወደ አሶሳ አብርን እንድንሄድ ጠየቀኝ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አብረን ሄድን «በኤምዲ ካሜራ» ቀረፅነው። የቀረጸውን ምስል ራሱ ድምጽና ምስሉን አቀናጅቶ (Edit) አድርጎ በራሱ ወጪ ነበር የሰራው፡፡ በወቅቱ ክሊፑን ለመስራት ቀርቶ ድምጹ ብቻ ለጋዜጠኞች የማከፋፈል አቅም አልነበረንም፡፡ እግዚአብሔር ስለፈቀደ ነው ሁሉም ነገር የሆነው» ይላል። ከዚያም እውቅናው መጣ። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ላይ የመሬት ሽልማት ተበረከተለት፡፡ እውቅናው ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጀምሮ ብዙ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መቀራረብ ተፈጠረለት፡፡

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል «የሸህ ዎጅሌ» ዜማን አበረከተ። ለጋምቤላ «ኦሊሮ ሊሮ» የተሰኘ ሙዚቃ ሰራ «ማለማለ» አስከተለ። ወደ ወላይታ በመጓዝም ጁሊ ከሚባል ልጅ ጋር «ሎሚየ» የተሰኘ ዜማውን አበረከተ፡፡ ከመቅደስ ኃይሉ ጋር «አፋ ወላ ሲዳ» አፋርኛ ሙዚቃ፣ ከትርሃስ ታረቀኝ ጋር «አመጌ» የተሰኘ ሱማልኛ፣ «ቡርሳሜ» ሲዳምኛ ሙዚቃ፣ «ፉራ» የሲዳማ ንግሥት ፉራን ታሪክ፣ የጋሞ «ድንጉዛዬ»፣ ሐረር «አሹራ»፣ «ጎዳ ዞኮ» የእግዚአብሔር ድልድይ የሚል በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ የተሰራ ሙዚቃ መታወቂያዎቹ ናቸው፡፡ ለአሶሳም ተጨማሪ «ማንጎ» የተሰኘ ሙዚቃ አበርክቷል፡፡ ያልወጡም ብዙ ሥራዎች አሉት።

«የብሔር ብሔረሰብ አድናቂ ብሆንም በፈለኩት ልክ ሰርቻለሁ ብዬ አላስብም» የሚለው ድምጻዊ አስናቀ፤ አሁን አሁን ድካም እየተሰማው እንደሆነ አልደበቀም፡፡ አንዳንድ ቢሮዎች ያለው ቢሮክራሲ ለመስራት አበረታች አልሆነለትም፡፡ ይህንኑ ሲናገርም «የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሲመጣ ብቻ ሁሉ ለባህሉ ተቆርቋሪ ይሆናል፡፡ በዓሉ ሲደርስ ቲሸርትና ኮፍያ በመልበስ ማክበር በቂ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ገና ብዙ ያልተነካ ታሪክና ባህል አለ። እርሱን ለማስተዋወቅ አይፈልጉም፡፡ እኔም እንደ ሌሎቹ ዘፋኞች ሎቲ አድርጌ ዓይኗ ጥርሷ እያልኩኝ ብዘፍን ዱባይ እየተመላለስኩ ገንዘብ መሰብሰብ እችል ነበር፡፡ ነገር ግን የእኔ ፍላጎት የተመሠረተው በማንነት ላይ ነው፡፡ በአሁኑ አልበሜ ኦሮምኛ፣ ስልጥኛ፣ ኩናምኛ እና ሌሎችም የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎች አካትቻለሁ፡፡ በዓሉን አንድ ቀን ጠብቆ ማክበር በቂ አይደለም፡፡ ዓመቱን ሙሉ ሁሉም ብሔሩን ማስተዋወቅ አለበት፡፡ ሁሉም ክልሎች ለባህላቸው ትኩረት ሊሰጡ ይገባል» የቅሬታው መነሻ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል ለማስተዋወቅ ካለው ቀናኢነት እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። በርግጥም ክልሎችም በዓል በማክበር ብቻ ባህልን ማስተዋወቅ እንደማይቻል ሊረዱት ይገባል።

አስናቀ ወደ አዲስ አበባ የመጣው አልበም ለመስራት ቢሆንም፤ ትኩረቱን የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ ላይ በማድረጉ13 የተለያዩ የባህል ሙዚቃዎችን በክሊፕ ለኅብረተሰቡ አድርሷል። አሁን ግን የቆረጠ ይመስላል። በአልበሙ የተካተቱ 13 የሙዚቃ ክሊፖች ተዘጋጅተው ተቀምጠዋል፡፡ በቅርቡ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አስናቀን ልዩ የሚያደርገው ሁለገብነቱ ነው። እስከዛሬ ከሰራቸው ሥራዎች ገንዘብ ከፍሎ በሌሎች ባለሙያዎች ያሰራቸው ሥራዎች የሉም፡፡ ሁሉንም ነገር ራሱ ነው የሚሰራው ክሊፑንም «ሲክስቲን ፕሮዳክሽን» የሚባል ስቱዲዮ ከጓደኞቹና ወንድሞቹ ጋር በመተባበር ነው የሰራው፡፡

«የሙዚቃ ክሊፕ የሚባለው መስማት የተሳነው ሰው በማየት ብቻ ሙዚቃውን ሊረዳው የሚችል ሲሆን ነው፡፡ ሙዚቃውና ምስሉ የሚግባባ ሲሆን ነው፡፡ እኔም ለዚሁ ትኩረት ሰጥቼ ነው የምሰራው» የሚለው ድምፃዊ አስናቀ፤ ዋናው ነገር ኢትዮጵያን እወዳለሁ ብሎ በቃል ብቻ መናገር በቂ አለመሆኑን ይናገራል፡፡ በሥራውም የሀገሩን ጓዳ ጎድጓዳዎቿን ለማስተዋወቅ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ነው ፍቅሩን የሚገልጸው፡፡ እርሱ የሚሰራው የማይሞተውንና የማይረሳውን ባህል ነው፡፡ ማንነቱን ያልወደደ ይጥላው እንጂ ትክክለኛውን ነገር ነው ለማስተላለፍ የሚፈ ልገው። ይህ የማንነት ጉዳይ በመሆኑ መቼም እንደማያፍርበት ይናገራል፡፡

በሥራው እጅግ አስቸጋሪ የሚባሉ ፈተናዎችን አሳልፏል፡፡ በቀረጻ ወቅት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ከማሽ አካባቢ ከሁለት ነብሮች ጋር መፋጠጡን መቼም አይዘነጋውም። ዘንዶም ተፈታትኖታል፣ በጎርፍ የተወሰደበት አጋጣሚም ነበር። ፈተናዎቹ ይበልጥ እንዲበረታ አደረጉት እንጂ ወደ ኋላ አልመለሱትም፡፡

«በውዝዋዜያችን ውስጥ ባህል ዘመናዊ የሚባል ነገር ያናድደኛል፡፡ በእኔ እምነት ባህል ዘመናዊ የሚባል ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ዘመናዊ ባህል የሚመስል ነገር ነው የሚታየው፡፡ አገውኛን ብንወስድ ሁሉ ነገሩ ተደበላልቆበት ግራ እያጋባን ነው፡፡ የወሎ ባህላዊ ሙዚቃ ቱባነቱን ስቶ ምን እንደመሰለ ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ ከቀጠለ ባህል መቀለጃ ሊሆን ነው፡፡ ይሄ አሳፋሪ ነው» በማለት በባህል መበረዝ የሚበ ሳጨው ድምፃዊ አስናቀ፤ እርሱ የሚሰራው በባህሉ ባለቤቶች የተረጋገጠና የተደገፈ ሲሆን ብቻ መሆኑን ይናገራል። መጀመሪያ ዘፈኑን ካስደመጠ በኋላ ነው እንዲቀርጽ ሲፈቀድለት በጥንቃቄ የሚሰራው፡፡ ሁሉ ነገር ከተጠናቀቀ በኋላም አምነውበት ነው ለእይታ የሚበቃው፡፡ ለዚህ ነው በየክልሉ ተወላጆችም ሆነ በሌላው ማህበረሰብ ዘንድ ሥራዎቹ ተወደው የሚደመጡት።

ድምፃዊ አስናቀ ወደፊትም የባህል መገለጫ መሆን ነው የሚፈልገው፡፡ በተለይ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል መከበሩ ትልቅ ግብአት እንደሆነለት ይናገራል፡፡ ባህላዊ አለባበሶችን፣ ባህላዊ አጨፋፈርና ክዋኔዎችን ያገኝበታል፡፡ ከእነርሱ ጋር ሲሆን የተለየ ስሜት እንደሚሰ ማው ይናገራል፡፡ ከዙምባራ ሙዚቃ በኋላ ባሉት የብሔር ብሔረሰቦች በዓላት በሁሉም ላይ ተገኝቷል፡፡

በሥራዎቹ ነዋይ ባያካብትም፣ ቁሳዊ ለውጥ ባያመጣም በክልሉና በብሔሩ ደስታ ነው እርካታውን የሚለካው፡፡ እስካሁን የሰራቸው ሙዚቃዎች በሙሉ በሽያጭ አይደለም የቀረቡት፡፡ አሁን የትኛውም ክልል ቢሄድ የሚያገኘው ክብር የተለየ ነው። ማሳያውም እስካሁን ሦስትና አራት አካባቢ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተበርክቶለታል።

ሁለገቡ ሙዚቀኛ አስናቀ ከባለቤቱ ጋር የተዋወቀው መንገድ ላይ ነው። ተያዩና ተዋደዱ፤ ከዚያም ተግባቡና ተጋቡ። «አየሁት ምኞቴን» የተሰኘውን ሙዚቃ ነበር የሠርጋቸው ዕለት የዘፈነላት፡፡ ባለቤቱ ሙያውን ስለምትወድለትና ስለምትደግፈው የሚሰራቸውን ዜማዎች ትመርጥለታለች፡፡ የመድረክ አልባሳቱንም የምትመርጠው እርሷ ናት፡፡ በሙዚቃ ውስጥ ባትኖርም ጥሩ ሙዚቃን የመስማት ችሎታ እንዳላት አረጋግጧል፡፡ ለዚህም ውለታዋ ይመስላል አዲስ በሚያወጣው አልበሙ ላይ ስለእርሷ ሙሉ ዜማ ያዜመላት፡፡

ለድምፃዊ አስናቀ ሕዝቡ ምዕራባውያን አፍቃሪ መሆኑ ያሳስበዋል፡፡ ብዙ ዘፈኖች ባህልና ትውፊት የሌላቸውም ጩኸት ብቻ መሆናቸው ያናድደዋል። በሙዚቃው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለማግኘታችን ጉዳይ ያስቆጨዋል፡፡ ከ«ዙምባራ» እስከ «ቦዳ ዞኮ» የተሸመነ ባህላዊ ጥበብን የተጠበበው ይህ ከያኒ በመጨረሻም «የየብሔረሰቡ የሥራ ኃላፊዎች የብሔር ብሔረሰብ ቀንን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ ባህላችሁንና ማንነታችሁን ለማስተዋወቅ ዝግጁ ሁኑ፡፡ በራችሁን ክፍት አድርጉ፤ ቢሮክራሲውን አሳጥሩት፤ ተባብረን የባህል ሙዚቃችንን እናሳድግ። ባህላችንን ለሌሎች እናስተዋውቅ» ሲል ነው የአጽንኦት መልዕክቱን ያስተላለፈው።

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ

 

 

 



 

Related Topics