በበረሃ ተፈትና የነጠረች ህይወት

በበረሃ ተፈትና የነጠረች ህይወት

 

ወይዘሮ ዘነበች አብረሃ፤

ዛሬ ከትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ ሶሎዳ ተራራ ጥግ ጀምረን በዓረቡ ዓለም ዱባይ፣ ወደ ስልጣኔ ጥግ ሄደን አሜሪካ፣ ከአፍሪካ በምጣኔ ሀብት ምጡቅ ወደተባለችው ደቡብ አፍሪካ፣ በኦሮሚያ ክልል አዳማ፣ አፋር ክልል ደግሞ ሰመራና ሎጊያ ከተሞችን እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎችን እንቃኛለን። በጣታችን ላይ ምራቅ እንትፍ እንትፍ ብለን በቅፅበት ከምንቆጥራት ሦስት ሺህ ብር ጀመረን በማሽን ለመቁጠር እንኳን ረጅም ሰዓት የሚወስደውን 30 ሚሊዮን ብር አብረን እንቆጥራለን በዓይነ ህሊና። የዛሬው የ«ህይወት እንዲህ ናት» አምድ በአዲግራት ከሚገኘው ቀዝቃዛው ሶሎዳ ተራራ ወደ ሞቃታማው አፋር ክልል ሎጊያ ከተማ በሃሳብ እንጓዛለን። እንግዳችን ጥቂት ጥሪት ይዘው ከአድዋ፣ አዳማ፣ ሰመራ ከዚያም አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ምልልስ ያደርጋሉ። ወዲህ ደግሞ በሌላኛው ህይወታቸው ከአገር ወጣ ይሉና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ በአሜሪካና ደቡብ አፍሪካ ያስቀኙናል። ወዲህም ለሥራ ጉዳይ ወደ ዱባይ አድርሰው ይመልሱናል። በድህነት ጉስቁልናና በንግድ ስኬት ውስጥም ያመላልሰናል የእንግዳችን ወይዘሮ ዘነበች አብረሃ ህይወት።

ከሶሎዳ ተራራ ሥር

ወይዘሮ ዘነበች አብረሃ ይባላሉ። 1958 ዓ.ም በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ ነው የተወለዱት። ትምህርታቸውንም ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ በንግስተ ሳባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከዚያም በወቅቱ የንግድ ትምህርትን በዚያው ንግስተ ሳባ ተከታትለዋል። ከዚያን በዘለለ ግን በትምህርታቻው አልገፉበትም። ምክንያቱም ደግሞ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ አመቺ አልነበረም። ወቅቱ ደርግ ከስልጣን ሊወርድ በመንገዳገድ ላይ በመሆኑ ሠላም የደፈረሰ በመሆኑ በዚያ ላይ ለመማር የሚያስችሏቸው ዕድሎች ተዘግተው ነበርና። እንግዳችን እናት አባታቸው በህይወት ባይኖሩም ጠንካራ ሆነው እንዲያድጉ መሰረት ጥለውላቸው አልፈዋል። በገንዘብ ሳይሆን በጠንካራ ሥነ ልቦና እና ከማንም ጋር መግባባትና መሥራት እንዲችሉ አደርገው፤ ለችግሮች እጅ መስጠት ሳይሆን የመፍትሔ አካል መሆን እንዲችሉ ነው ቤተሰቦቻችው ያሳደጓቸው።

እንጀራን ፍለጋ

ወይዘሮ ዘነበች 1979ዓ.ም የንግድ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ከዚያን በኋላ ያሉ ሁኔታዎች ምቹ አልነበሩም። 1980 ዓ.ም በአካባቢው የደርግ ሥርዓት ያደርስ የነበረውን ግፍ መጋፈጥ ግድ ሆነ። በተለይም ከህወሓት ጋር በመወገን የአካባቢውን ሠላም እና ፀጥታ ለመጠበቅ1980 ዓ.ም እስከ 1982 ዓ.ም በአድዋ አካባቢ በሚሊሻነት አገልግለዋል። ሁሉንም ነገሮች አልፈው የደርግ ሥርዓትም ተወግዶ አዲስ መንግሥት ተመሠረተ። በ1983 ዓ.ም የአደጉባትን አካባቢ የኋሊት እያዩ ወደ ኦሮሚያ ክልል በወቅቱ አጠራር ናዝሬት ወደ አሁኗ አዳማ መጡ። ከዚያም ሸቀጥና ንግድ ሌሎች ግብይቶችን ጀመሩ። ከአርሲ፣ ከአሰላ፣ ከበቆጂና ከሌሎች አካባቢዎች እህል በማምጣት በአዳማ ከተማ በችርቻሮ ይሸጡ ነበር። ይሁንና በዚህ አካባቢ የጠበቁትን ለውጥ ባለማግኘታቸው 1987 ዓ.ም ወደ አፋር ክልል ሎጊያ ከተማ አቀኑ። በዚህ መስመር በርካታ ተሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚመላለሱበት ኮሪደር ነው። አጋጣሚውን ተጠቅመው ኮንትሮባንድ ንግድ ለመነገድ ሞከሩ። ይሁንና ይህ ሥራ በመንግሥትም የተጠላ በአገርም የተወገዘ መሆኑን በማመናቸው ወደ ሌላ የሥራ መስክ ቀየሩ።

ከዚያም ከባለቤታቸው ጋር ሆነው በአስፋልት ዳር ሸራ ወጥረው በአስፋልት ዳር ጥብስ መጥበስ፤ እንጀራ መጋገርና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት አካባቢውን ተለማመዱት። በወቅቱ ወደ ጅቡቲ ከሚዘለቀው ዋናው አስፋልት በስተቀር ሎጊያ ሌሎች መሠረተ ልማቶች አልነበሯትም። የአፋር ክልል ዋና ከተማም አሳይታ ነበረች። ከክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሎጊያ እንደአሁኑ ደማቅ የንግድ ከተማ ከመሆኗ በፊት ፖሊስ ጣቢያ፣ ትምህርት ቤትም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ያልተሟሉላት ነበረች። ይሁንና በሠላምና ፀጥታ ጉዳይ በጋራ ይሠራሉ። በወቅቱ ቋሚ ቤት አልነበራችውም። ሥራቸውም ሆነ ቤታቸው ጎዳና ላይ ነው። አካባቢው ሰላማዊ በመሆኑ የቅጠል ኮሽታ እንኳን አልነበረም። በሂደት ከአስፋልት ዳር ትንሽ ፈቅ ብለው ሦስት ክፍል ቤት ሠርተው ገቡ።

በረሃን ያለመለሙ ችግኞች

ከአዳማ ከተማ በ1993 ዓ.ም ሲመጡ አምስት ችግኞችን ይዘው ነበር ወደ ሎጊያ የመጡት። እነዚህንም ችግኞች ተክለው አሳደጓቸው። የሚገርመው አፈሩ ጭምር የመጣው ከሌላ አካባቢ ነው። ብቻ ጥዋትና ማታ እንደ ሕፃን ልጅ እያባበሉ ችግኞቹን ወደ ዛፍነት ቀየሯቸው። በሰዎችም ዘንድ መደመምንም ፈጠረ። ምክንያቱም አካባቢው በረሃ ከመሆኑ ባሻገር ውሃ በሌለበት ችግኝ ማብቀልና ወደ ዛፍነት እንዲቀየሩ መትጋት የሚያስከፍለው ዋጋ እጅግ ትልቅ መሆኑ የሚታውቅ ነበርና።

እኚህ ሴት በአረንጓዴ ልማት ፍቅር የነሆለሉ ናቸው። «በበረሃ ላይ አንድ ዛፍ ተክሎ በጥላው ሥር እንደ መጠለል ትልቅ ደስታ የለም» ይላሉ። ብቻ ለእፅዋት ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው። በግቢያቸው ውስጥ ያሉትን ዛፎች ጥዋትና ማታ ይንከባከቧቸዋል፤ ስለ ጤንነታቸው ይጨነቃሉ። ባለሙያም እያመጡ ክትትል ያደርጉላቸዋል። በረሃ በመሆኑ ከሰው ባልተናነሰ ውሃ ያስፈልጋቸዋልም ይላሉ። አምስቱ ችግኞች ተተክለው የነበረው በሎጊያ ከተማ በገነቡት ናዝሬት ቁጥር አንድ ሆቴል ነበር።

በወቅቱ አንድ ከውጭ የመጡ ባለሙያ «አፋርን እናልማ» የሚል ሃሳብ አንግበው ነበር። በአጋጣሚ በናዝሬት ቁጥር አንድ ያሉትን ዛፎች ከተመለከቱ በኋላ አገራሞት ፈጠረባቸው። ከወይዘሮ ዘነበች ጋርም እንዴት ዛፎቹን ማፅደቅ እንደቻሉ ጠየቋቸው። ባለሙያው አክለው እገዛ ብናደርግሎትስ ምን ይሠራሉ ሲሉ ጠየቋቸው። እርሳቸውም «እኔ አምስቱን ሃምሳ አደረጋለሁ» ሲሉ መለሱላቸው። ሰውዬው ሙያዊ እገዛ አደረጉላቸው።

ወይዘሮ ዘነበችም ወዲያውኑ 70 ችግኞችን ተከሉ። አንዷም ሳትደርቅ ሁሉም ፀደቀ። ይኸው ዛሬ በሞቃታማው ከተማ በተገነቡት ናዝሬት ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ሆቴሎች ተጠቃሚዎች በጥላው ስር ተጠልለው እፎይ እያሉ ምስጋናም እያቀረቡ ወደ መጡበት ይመለሳሉ። «ከምንም በላይ ከአስር ማቀዝቀዣ አንድ ችግኝ ምን ያክል ጥቅም እንዳለው እኔ ተረድቻለሁ። በተለይ በበረሃ ላይ ችግኝ ማለት ከምንም በላይ ነው። እኔ ከራሴ አልፎ በርካቶችን አስተምራለሁ። ከሁሉም ሥራዬ በበለጠ ትኩረት የማደርገው ለችግኞች ነው» ሲሉም ለእፅዋት ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ።

የሎጊያ ባለውለታ

ወይዘሮ ዘነበች 1987 ዓ.ም በሎጊያ ከተማ ናዝሬት ቁጥር አንድ ሆቴልን መሰረቱ። እያደር ሆቴሉ ታዋቂ ሆነ። በ2003 ዓ.ም ደግሞ በ10ሺ ካሬሜትር ላይ ያረፈ ናዘሬት ቁጥር ሁለት የሚባለውን ሆቴል አጠናቀቁ። ወይዘሮ ዘነበችም እንግዶች ወደ ከተማዋ እየመጡ የሚስተናገዱበት ሆቴል በመገንባታቸው በተዳጋጋሚ ምስጋና ተችረዋል። ሥራቸውን እያስፋፉ በሄዱ ቁጥር ገቢያቸውም እያደገ ሄደ። ነገር ግን ቀን ያለ ዕረፍት ሲሠሩ የዋሉትን ገንዘብ ማታ የሚያስቀምጡበት አስተማማኝ ሥፍራ አሊያም አደራ የሚሰጡበት ተቋም ያስፈልጋቸው ነበር። ግን ይህ ሐሳብ እንጂ በተግባር ሊያገኙት አልቻሉም። ባለ አደራ በማጣታቸው ምክንያት ከእንቅልፋቸው ይባንናሉ። ታዲያ የችግሩ ሰላባ ከሆኑ የመፍትሔም አካል መሆን እንደሚችሉ አሰቡ። በሎጊያ ከተማ ባንክ እንደሚያስፈልግ አመኑ። በእርግጥ ይህ የእርሳቸው ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ነዋሪ ፍላጎትም ነበር። የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችም ይህንኑ ሃሳብ ይደግፉ ነበር።

አሁን ደግሞ ለከተማዋ አስታማማኝ የባንክ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ በማመን ለባንክ አገልግሎት የሚመጥን ሕንፃ አስገነቡ። ወዲያውም ንግድ ባንክ በሎጊያ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፈተ። ሌላም ሕንፃ ጨምረው ገነቡ። ሕብረት ባንክ ሥራውን ጀመረ። ከዚያም ሌሎች ባንኮች በተከታታይ ተከፈቱ። እርሳቸውም ሆኑ መሰሎቻቸው ሲሠሩ የዋሉትን ብር ትራስ ስር ከማስቀመጥ ወደ ባንክ ካዝና በመክተት ከጭንቀት ተገላገሉ። እኚህ ጠንካራ እንስት ሎጊያ ከተማ ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ሕንፃዎች በመገንባት ለከተማዋ ውበት የራሳቸውን ሚና እየተወጡ ነው። በዚያው ልክ ለመንግሥታዊ ተቋማት አመቺ የሆኑ ሕንፃዎችን በመገንባት ባንክና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲስፋፉ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው። ለከተማዋ ባለ ውለታ መሆናቸው በከተማው ነዋሪዎችም ሆነ ወደ ሎጊያ በሚዘልቁ እንግዶች ዘንድ የተገለጠ ሆነ። የአፋር ክልልም ባለውለታውን አልዘነጋም። በሥራቸው ልክ ምስጋናን በሽልማት እያጀበ አበረታታቸው ለተሻለ ሥራም አነሳሳቸው። በምላሹም በአንድ ጊዜ እስከ 800 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል አዳራሽና የሆቴል አገልግሎትት በመስጠት በከተማዋ የተለያዩ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኑ።

ከተማዋ ውስጥም የውሃ እጥረት ሲከሰት በራሳቸው «ቦቴ መኪና» ውሃ እየቀዱ ለሰዎች ያከፋፍላሉ። በተለይ የአርብቶ አደሩ ከብት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ውሃ እየቀዱ ግመሎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን በማጠጣት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸው ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ አጠናከረላቸው። ለችግረኞች ፈጥነው በመድረሳቸውም የአካባቢው ነዋሪዎች የተለየ ክብር ይሰጧቸዋል። የውሃ ጉድጓድም በመቆፈር ሰዎች ውሃ እንዲጠቀሙ የራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም በቀድሞ አጠራር ከውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ወደ አዲስ የሥራ ዘርፍ

የከብት አርባታው 12ሺ ካሬ ላይ ያረፈ ሌላኛው ኢንቨስትመንት ነው። በአፋር ክልል እንስሳትን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ እንጂ አንድ ቦታ ማድለብ ብዙም አልተለመደም። እርሳቸው ግን ያልተደፈረውን ነገር ጀምረውታል። ከሻወር የሚወገደው ውሃ ዝም ብሎ አይባክንም። የፈሰሰውን ውሃ ሳር እንዲያበቅል መስመር ተበጅቶለት አስራ ሁለት ሺ ካሬ መሬት ላይ ያለውን መሬት እንዲያጠጣ ይደረጋል። እናም በአሁኑ ወቅት ለከብቶቹ መኖ እያበቀለ አካባቢውንም አረንጓዴ እያደረገ ነው ፍሳሹ። ከሳር በተጨማሪ ፍሩሽካ እና ሌሎች መኖዎች ለከብቶቹ ቀለብ ይውላሉ። አንድ በሬ እስከ ሰባት ሺህ ብር ገዝተው በወራት ልዩነት 20ሺህ በሚጠጋ ብር ይሸጣሉ። በእርግጥ በሬ ማድለብ ከፍተኛ ትግል እንደሚጠይቅ ይናገራሉ። ሆኖም ቁርጠኝነት ካለ በአፋር የከብት ማድለብም ሌላው አዋጭና ያለተነካ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደሆነ ይመክራሉ።

ከ3ሺህ ወደ 30 ሚሊዮን

የወይዘሮ ዘነበች የንግድ እንቅስቃሴ በጥረት ታጅቦ ስኬት ላይ ደርሷል። ከ3ሺህ ወደ 30 ሚሊዮን አድጓል። ይህ ቁጥር ከትግራይ ክልል ጀምሮ ኦሮሚያና አፋር ክልል አሊያም ባህር አሻግሮ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ(ዱባይ) ሊወስዳችሁ ይችላል። በሌላ መንገድ በዕድሜ ስሌትም ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ይህን ፅሑፍ እያነባበችሁ እስካላችሁበት 2008 ዓ.ም ድረስ ሊያስጉዛችሁ ይችላል። በእርግጥ በዚህ አሃዙ ውስጥ እጅግ ፈታኝ የህይወት ግብግብ ታገኛላችሁ። ወይዘሮ ዘነበችና ቤተሰቦቻቸው በ18 ዓመታት ጉዞ በትጋት ያፈሩት ሀብት ነው። ሥራ ሲጀምሩ በእጃቸው ላይ ያለችውን ሦስት ሺህ ብር እየሠሩበት ሌላ ሰውም እያሠሩ ዛሬ ካፒታላቸው 30 ሚሊዮን ደርሷል። ይህ ገንዘብ በብርታት መንገድ ከድህነት ወደ ሚሊየነርነት የተሸጋገሩ ጠንካራ እጆች ህያው ምስክር ነው። ለድህነት እጅ የማይሰጥ በትግል የተሞላና የስኬታማ ቤተሰብ ድምር ውጤት መሆኑን ያመላክታል።

በጐነት

ሚሊየነሯ እንስት በህይወት ስንክሳር ውስጥ ብዙ ነገሮችን አይተዋል። ማጣትን፣ ከተወለዱበት አካባቢ መሰደድን፣ ከማያውቁት ሰፈርና ባህል ጋር ለመላመድ ግብግብ መግጠሙን አልፈውበታል። ህይወትን ለማሸነፍ ሌላ ህይወት ለመላመድ ተገደዋል። ይሁንና እርሳቸው ያሳለፉትን መራራ ህይወት ሌሎች እንዲያልፉበት አይፈልጉም። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ 40 የሚጠጉ ወላጆቻቸውን በኤች አይ ቪ እና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ በሞት የተነጠቁ ሕፃናትን በማስተማር ላይ ይገኛሉ። እነዚህም ልጆች በተለያዩ ቦታዎች እያተማሩ ነው። የተወሰኑት ሥራ ጀምረዋል።

ልጆቹ ከቤተክርስቲያንና ከመስጊድ አካባቢ የመጡ ናቸው። ልጆቹ አንዳንድ ሰዎች ለልመና ይጠቀሙባቸው ነበር። ነገር ግን ነገ የተሻለ ህይወት የሚኖራቸውና አገር መደገፍ የሚችሉ መሆናቸውን በመገንዘብ ከልመና ወደ ትምህርት ቤት እንዲያቀኑ አድርገዋል። ልጆቹ ሁሌም ህክምናና ክትትል ይደረግላቸዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ አስር አቅመ ደካሞችን ደግሞ ቤተክርስቲያን አካባቢ መጠለያሠርተው ልብስ እያላበሱ ቀለብም እየሰፈሩ ይረዷቸዋል። ወይዘሮ ዘነበች «ይህንንም በማድረጌም ሁሌም የሚሰማኝ ደስታ ወደር የለውም» ይላሉ። በቀጣይም ቢሆን ከዚህ በበለጠ ችግረኞችን መርዳትና ለዚህች አገር የተሻለ ለውጥ ማመጣት የሚችሉ ዜጎችን ለማፍራት እተጋለሁ ይላሉ።

ሶሎዳን በድጋሜ

ወይዘሮ ዘነበች የተወለዱበትን አካባቢ አልዘነጓትም። ሶሎዳ ተራራና አካባቢው ማርያም ሸዊቶና በሚሊሻነት ያገለገሏትን አድዋን መቼም አይረሷትም። እናም ደርግ ሊወድቅ ሲል በነበረው ከፍተኛ ጦርነት አረንጓዴነቱን በከባድ መሳሪያ እሩምታ ያጣውና ወደ ሐሩር የተቀየረውን አካባቢ ችግኝ በመተከል ተፈጥሮ መልሳ እንድታገግም እያደረጉ ነው። ከሌሎች የአካባቢው ተወላጆች ጋር በመሆንም ትምህርት ቤቶችና ግብአቶች እንዲሟሉ ጥረት አድርገዋል። አድዋ የመኖሪያ ቤት አላቸው። መቼም በህይወት ምህዋር ውስጥ አካባቢውን የማያስታውስ የለምና በትውልድ አካባቢያቸው የበለጠ ልማት እሠራለሁ የሚል ውጥንም አላቸው።

ሶሎዳ ተራራን በድጋሜ ልምላሜው እንዲመለስ እየሠሩ ነው። በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሳ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የነበሩት ልጆች በዳስ ውስጥ ይማሩ ከነበረበት «ከዳስ ወደ ክላስ» በሚል መርህ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ወንበርና ሌሎች ግበዓቶችን በማሟላት ተማሪዎች በተደላደለ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ አደርገዋል፤ ከሌሎች የክልሉ ተወላጆች ጋር በመመካከር። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገነባው ህዳሴ ግድብ ፍፃሜውን እስኪያገኝ ድረስ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑንም ይናገራሉ።

በትዝታ መነፅር

ብዙ ትዝታ በልባቸው ውስጥ ይመላለሳል። ከበረሃማው እስከ ደጋ ጫፍ ወሰድ መለስ የሚያደርግ፤ ከማጣት እስከ ማግኘት የሚያደርስ። ጎዳና ላይ ከመተኛት አስከ ዘመናዊ ቤት መገንባት ያለው ህይወታቸው በትዝታ በሁሉም አቅጣጫ ጭልጥ አድርጎ ይወስዳቸዋል ወይዘሮ ዘነበችን። ገና አሃዱ ብለው ሥራ ሲጀምሩ በእጃቸው ላይ የነበረችው 3ሺህ ብርም ሌላ ትዝታ አላት። ያቺን ብር ይዘውም በተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የሠሯቸው ተግባራትና የገጠሟቸው ፈተናዎች ዛሬም ደረስ ከፊታቸው ድቅን እያሉ በትዝታ ማዕበል ይወስዷቸዋል። በትዝታ ማዕበል በሁሉም አቅጣጫ ይነጉዳሉ። ክፉና በጎውን በትዝታ መነፅር ይቃኛሉ።

ከምንም ነገር በላይ ግን በሎጊያ ያሳለፉት ህይወት መቼም ከህሊናቸው ላይፋቅ ታትሟል። በወቅቱ ከ50 ሰው በማይበልጥበት ከተማ ኑሮን ለማሸነፍ ከባለቤታቸው ጋር በርካታ አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ ሥራዎችን ይሠሩ ነበር። ወይዘሮ ዘነበች ሌሊት ሙሉ እንጀራ ሲጋግሩ አድረው፤ ሲነጋጋ ደግሞ እንጀራውን ወደ መሸጥ ይሸጋገራሉ። እንቅልፍ የሚባል ፈፅሞ አይታሰብም። አሳዛኙ ነገር ደግሞ በአካባቢው ውሃ ስላልነበር ለመጠጥም ሆነ ለሌላ ተግባር የሚውል ውሃ በጣም ርቀት ተጉዘው ከአዋሽ ወንዝ ነበር የሚቀዱት። ቀን ሲሠሩ የዋሉትንም ብር በጨርቅ ጠቅልለው ነበር ከትራሳቸው የሚያሳድሩት።

ዛሬ ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ የትዝታ እዳ ጥለው ላይመለሱ አልፈዋል። በአካባቢው ባንኮች ተስፋፍተዋል። የማገዶ እንጨት ለቀማ ቀርቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ናቸው። ሌሊት በጋማ ከብት አሊያም በጀርባቸው ውሃ ለመቅዳት ወደ አዋሽ ወንዝ የሚመላለሱበት ጊዜ አልፎ ዛሬ በግቢያቸው ውስጥ ባለው ቧንቧ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም ተርፈዋል። እርሳቸውና ባለቤታቸው ብቻ ያከናውኑት የነበረውን ሥራ በአሁኑ ወቅት ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረው በመቶች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። በከተማዋ ምንም ዓይነት የስብሰባ አዳራሽ አልነበረም። ዛሬ ግን ለአካባቢው ነዋሪዎች ስብሰባ አዳራሽ በነፃ ይሰጣሉ። ግብረሰናይ ድርጅቶችና የልማት ድርጅቶች ደግሞ በተመጣጣኝ ክፍያ አዳራሹን ያከራያሉ። እነዚህን ሁሉ በማግኘትና በማጣት መካከል ያሉትን፤ የደስታና ትካዜ ድንበር እየሠሩላቸው ወይዘሮ ዘነበችን በትዝታ ምዕራፎች ውስጥ ያመላልሷቸዋል።

በምክክር የተመሰረተ ቤተሰብ

በሁሉም የሥራ እንቅስቃሰዎች ውስጥ ሁሌም ምክክር አለ። ከባለቤታቸው ጋር እያንዳንዷ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ይመካከራሉ። ይህም ደግሞ ወደ ስኬት ማማ ከፍ አድርጓቸዋል። ቀደም ሲልም ልጆቻቸው በአጠገባቸው እያሉ በርበሬ፣ ሽሮ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብቶችን በማዘጋጀት ያግዟቸው ነበር። አሁን ደግሞ በደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ ከሚኖሩት ልጆቻቸው ስለ አዳዲስ የሥራ ፈጠራና በቀጣይ መሆን ስለሚገባው ነገር በስልክ ይመካከራሉ። ስህተቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለና ዘመናዊ አሠራር በመቀየስ ለሰዎችም ሆነ ለራሳቸው እርካታ ለመስጠት ይተጋሉ።

ከልጆቻቸው ጋር ወደ ውጭ ለተሻለ ትምህርት ከመሄዳቸው በፊት የነበረው ትስስር ጠንካራ ነው። በአሁኑ ወቅት አብሯቸው የሚኖረው አንደኛው ልጃቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው። በዕረፍት ጊዜው ወደ ዱባይና ሌሎች አካባቢዎች ይዘውት ይሄዳሉ። ይህም የሥራውን ባህሪ እንዲያውቅና በኑሮ ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ ከወዲሁ በመገንዘብ የተሻለ የንግድ ክህሎት እንዲፈፅም ያበረታቱታል፤ ይመክሩታል። በአሜሪካ ያለችውና የአካውንቲንግ ምሩቅ የሆነችው ልጃቸው ደግሞ ከገንዘብ አያያዝ ጋር ሰፊ ሙያዊ እገዛ ታደግላቸዋለች። ምን መሠራት እንዳለበትም ትመክራለች። ደቡብ አፍሪካ እየተማሩም የሚገኙት ሁለት ልጆቻቸውም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሌላ ቢዝነስ ጀምረዋል። ምክንያቱም እራሳቸውን ችለው መማርና ጠንካራ ሠራተኛ መሆን ስላለባቸው ከወዲሁ ሥራን መልመድ አለባቸው ይላሉ ወይዘሮ ዘነበች።

ሽልማቶች

ሴትየዋ እንደ ብረት አሎሎ የጠነከሩ ስለመሆናቸው አጠገባቸው ያሉ ሠራተኞች ይናገራሉ። ጥዋትና ማታ ዕረፍት የላቸውም፤ ሁሌም ሥራ ላይ ናቸው ይላሉ። አንዲት ደቂቃ እንድትባክን አይሹም። ሁሌም በተግባር ማሳየት ነው የሚፈልጉት። ሠራተኞችም ሠርተው እንዲለወጡና የራሳቸውን «ቢዝነስ» እንዲጀምሩ ያበራታታሉ። ስለ ብርታታቸው ሠራተኞቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አካላት መስክረውላቸዋል።

በተለያዩ ወቅቶች የሚካሄዱ ገባኤዎችን በተሟላ መስተንግዶ በማካሄዳቸው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአርብቶ አደሮች ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከክልሉ መንግሥትና ከተለያዩ ቢሮዎች የምስጋና የምስክር ወረቀቶች ተበርክተውላቸዋል።

እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ በመጓዝ ውሃ እያመላለሱ ዛፎችን ተንከባክበው ወደ ዛፍነት እንዲቀየሩ በማድረጋቸው በአረንጓዴ ልማት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ከቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እጅ ሜዳሊያ ተቀብለዋል። ይህ አረንጓዴ ልማት ወዳድነታቸው ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ ሆኖ የውጭዎችን (ነጮቹን) ቀልብ መሳብ ችሏል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ኖርዌይ አምባሳደር የነበሩት እንስትም አንድ ችግኝ ታስቦ ከአንድ ግቢ ላይ 70 ችግኞች በመገኘቱ ድንቅ ነው ብለው አምባሳደሯ 1997 ዓ.ም ዋንጫ አበርክተውላቸዋል። በዚሁ በአረንጓዴ ልማት ቁርጥኝነታቸው ሌሎች በርካታ ሽልማቶችን ተቀበለዋል።

የማይሞት ህልም

«ገና ብዙ እሠራለሁ፤ ይህ ጅማሮ ነው። ድርጅቱ የእኔ ብቻ አይደለም። የልጆቼም የአገርም ሀብት ነው። በበለጠ የሚሠራበት እንጂ ሙሽሽ ብሎ እንደ እፉዬ ገላ እንዲጠፋ አልፈልግም። ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል አሠራር እየተከተልኩ ነው» ይላሉ። ወይዘሮ ዘነበች ሥራዎችን ከመጀመራቸው ቀደመው ከባለሙያዎችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ምክክር ያደርጋሉ። ከዚያም አዋጭ የሆኑ ሥራዎች ያከናውናሉ። በእያንዳንዷ ቅፅበት የሚሠሯት ሥራ በረጅም እና አጭር ጊዜ እቅድ ውስጥ የተካተተ ነው። ካልሆነ ግን «ወደ አዝቅት መውረድን ያመጣል» የሚል አስተሳሰብም አላቸው። በደመ ነፍስ የሚጀምሩት ሥራ የለም። «ይህ ሀብት እያደገ በሄደ ቁጥር ተጠቃሚነታቸው የሁላችንም ነው» የሚል ፅኑ እምነት አላቸው።

ከአገልግሎት ወደ ኢንዱስትሪ

ወይዘሮ ዘነበች ለበርካታ ዓመታት በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ሲሠሩ ቆየተው ውጤታማ ሆነዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከዚህ ሥራ በዘለለ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚያስፈልገውና በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የጎላ ሚና የሚኖረው ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ያምናሉ። በእርግጥ ይህ የእርሳቸው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱም ፍላጎት እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከአገልግሎት ወደ ኢንዱስትሪው ዓለም መግባት ይፈልጋሉ። ለዚህም በቂ ዝግጅት አደርገዋል። መንግሥት ለዚህ ሃሳብ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው በከፍተኛ ደረጃ ይተማመናሉ። በኢንዱስተሪው ዘረፍ ተሰማርተው የተሻለ ውጤት ማስመዘገብ ይፈልጋሉ። ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጣሪ መሆን ይሻሉ። ሚሊየነር ብቻ ሳይሆን ቢሊየነር መሆንም ህልማቸው ነው።

ወይዘሮ ዘነበች የአገሪቱ ሀብት ያልተነኩ ብዙ ነገሮችን ለመሥራት የሚጋበዝ አሠራር እንዳለ ይናገራሉ። ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ ለመሆንም በሁሉም ዘርፍ ብቁ ሆኖ መገኘትም የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ እንደሆነ ያምናሉ። «ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለመራመድ እያንዳንዷን ደቂቃ በሥራ ላይ ማሳለፍ ደግሞ የስኬት ቁንጮ ላይ ያደርሳል» የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። ስለሆነም ወደ ኢንዱስተሪው መንደር ለመዝለቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እያደረጉ የባለሙያዎችን ሃሳብ እየተቀበሉ ነው። የተሻለ አሠራረና ሥራ ለሎጊያ ከተማና አካባቢዋ ማሳየት ይፈልጋሉ።

ምክር

ወይዘሮ ዘነበች ህይወትን መምከርም መዘከርም ተገቢ እንደሆነ ያምናሉ። ወጣቶች በአገራቸው ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉና ለዚህም የሚያበረታታ ሥርዓት እንዳለ ይናገራሉ። በሃሳብ ብቻ ዶላር እያፈሱ ከመኖር በአገር ውስጥ የተገኘውን ገንዘብ በሥራ ላይ በማዋል የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ስኬት በአንዲት ሌሊት የምትመጣ ሳትሆን የብዙ ቀናትና ዓመታት ጥረትን ውጤት የሚጠይቅ ነው። ሌላው ቀርቶ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት መጀመሪያ ከምንጣፍ ጀምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን መሟላት እንዳለባቸው ይናገራሉ። «ባዶ መሬት ላይ ተኝቶ አፈር እየቆረቆረው ጥሩ እንቅልፍ እንደማይተኛ ሁሉ፤ ስኬትም ችግሮችን በሂደት ሳያልፉ ልትጨበጥ የማትችል ውድ ነገር ናት» ይሏታል። ስለሆነም ወጣቱ ስኬታማ ለመሆን በቅድሚያ ለዓላማ መገዛት አለበት የሚል እምነት አላቸው።

በአሁኑ ወቅት በስደት ወደ ተያዩ አገሮች በመሄድ ህይወታቸው የሚያልፍ ወጣቶች ያሳዝኗቸዋል። «ከማናቸው አገራት ባልተናነሰ የኢትዮጵያ ሀብት ተዘቆ አያልቅምና በአገራቸው ላይ ቢሠሩ የት በደረሱ» በማለት ይቆጫሉ። «ወጣቱ ግን እየነጎደ ያለው ሀብት ወደ ሌለው ምድር ነው፤ ይህ መታረም አለበት። ሌላው ቀርቶ አሁን በምኖርባት ሎጊያ ከተማ ቀላለ ሥራ ሠርቶ አትራፊ መሆን የሚቻልበት ሥፍራ ነው። ዋናው ነገር በአገር ውስጥ ሠርቶ የመለወጥ ሥነ ልቦና መጎናፀፍ ነው። ከውጭ ይልቅ ወደ አገር ውስጥ ማማተር ተገቢ ነው» የሚሉት ወይዘሮ ዘነበች «ማን እንደ ሀገር» ብለው በርካቶችን ከስደት መልሰዋል። በአገራቸው ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉም አስተምረዋል። የሹፌሮችን አልባሳት እንኳን አጥበው የተለወጡ በርካቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። በርካቶች ስደት ሄደው ተመልሰው ሲመጡ አንገት ማስገቢያ አልሠሩም። ሁሌም ተንከራታች ናቸው። ከስደት የበለጠ በአገር ላይ መሥራት የተለየ ደስታ ይሰጣል ባይ ናቸው። ስለሆነም «ከስደት ምንም አይገኝምና በአገር ቤት እንሥራ ሲሉ» ይመክራሉ።

ምንጭ፡-አዲስ አድማስ ጋዜጣ

 

  

Related Topics