በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በጋሞ ጎፋ ዞን በ

መስቀልን በደንባ ጎፋ

 

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በጋሞ ጎፋ ዞን በደምባ ጎፋ ወረዳ ተገኝተናል፡፡ ወረዳዋ ከመዲናችን አዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ516 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ወረዳዋን በስተ ምስራቅ የዛላ ወረዳ፣ በደቡብ የገዜ ጎፋና ኦይዳ ወረዳዎች፣ በምዕራብ የመሎ ኮዛ እና በሰሜን የቁጫ ወረዳና የዳውሮ ዞን ያዋስኗታል፡፡ የወረዳው የቆዳ ስፋት 97,900 ሄክታር ሲሆን በ38 ቀበሌያት የተዋቀረ ነው፡፡ የወረዳው አጠቃላይ ህዝብ ብዛት 150,000 የደረሰ ሲሆን የራሱ የሆነ የቋንቋና የባህል እሴቶች ባለቤት ናት፡፡

 

የወረዳው መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ በአብዛኛው ሜዳማ ሲሆን በከፊል ተራራማነትን የያዘ ነው፡፡ ከባህር ጠለል በላይ ከ1900-2400 ሜትር ከፍታ ሲኖረው ዓመታዊ የዝናብ መጠኑ ከ900-1100 ሚ.ሊ የሚደርስ ሆኖ አማካይ የሙቀት መጠኑ ከ32-38 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሷል፡፡

 

የአየር ንብረቱ 75 በመቶ ቆላ 15 በመቶ ወይና ደጋ እና 10 በመቶ ደጋ ነው፡፡ የአብዛኛው ህዝብ ኑሮ የተመሰረተው በግብርና ላይ ሲሆን የተለያዩ ምርቶችን ያመርታሉ፡፡

 

ከአገዳ ሰብሎች በቆሎና ማሽላ ሲሆን በተለይም ወረዳዋ በበቆሎ ምርቱ ታዋቂ በመሆኑ "Maize Belt" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ከብዕር ሰብሎች ስንዴ፣ ገብስና ጤፍ ከጥራጥሬ ሰብሎች ባቄላ አተርና ቦሎቄ እና የተለያዩ ቋሚ ተክሎችና የጓሮ አትክልት ይመረትበታል፡፡ በሀገሪቱ ስመ ጥር የሆነውን የበቆሎ እሸት እና እጅግ ተወዳጅ የሆነውን የለውዝ ምርት ለገበያ በማቅረብ ትታወቃለች፡፡ በእርባታው ደግሞ የዳልጋና የጋማ ከብቶችን ጨምሮ ከ94,256 በላይ የሚሆን የቤት እንስሳት በወረዳው ሲገኙ በሣምንት ከ1000-15000 የደለቡ ሠንጋ በሬና በግ ለገበያ ታቀርባለች፡፡

 

የመስቀል በዓል አከባበር /Meskel Fastival among Gofa’s nations/

 

ይህ በዓል በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበር፤ በጎፋ ብሔረሰብ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ከትንሽ እስከ ትልቅ ደሀውም ሆነ ሀብታሙ በሁሉም ማህበረሰብ፤ ያለውም ሆነ የሌለው በመስቀል በዓል አንድ የሚሆንበት ልዩ በዓል ነው፡፡ አሮጌው ዓመት ማለቁንና ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሩን አረጋግጠው የሚደሰቱበት በዓል ነው፡፡

 

ለመስቀል በዓል ካለው ከበሬታ የተነሣ ገና በዓመቱ እስከሚመጣ ታስቦበት ቅድመ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ለልጆች ልብስ፤ በዕለቱ ለሚዘጋጅ ምግብና መጠጥ በተለይ ለመስቀል ስጋ ተብሎ ዓመቱን ሙሉ በመቆጠብ በእድር ዝግጅት ከመደረጉም ባለፈ ለመስቀል ተብሎ ለሚደረግ ነገር ሁሉ ሳይሰስት ማንም የሚፈጽመው ይሆናል፡፡

 

አካባቢው በአደይ አበባ ሲደምቅ በብሔረሰቡ አጠራር ቤላ ጪሻ /Beella Ciishsha/ ጋራው ሸንተረሩ ሲያሸበርቅ በብሔረሰቡ በስፋት ከሚታወቀው ምርት በዋናነት ጤፍ በጊዜው አርሶ አደሩ ከአረም ነጻ የሚያደርጉበትና አብቦ የሚደምቅበት /Gaashshey Piiliximees/ ወቅት መሆኑን ያሳየዋል፤ ውበት ይሰጣል፡፡

 

ወርሃ መስከረም መግቢያ ለመስቀል በዓል መድረሻ ለመሆኑ መገለጫ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም መስቀል በዓል ሲቃረብ ልጆች በተሠማሩበት የሥራ መስክ ላይ ሆነው ከብቶችን በመጠበቅ ላይ ሳሉ ለእንጨት ለቀማ፣ ውሃ ለመቅዳትና ሣር ለማጨድ ከአንድ በላይ ሆነው በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ያለማንም ቅስቀሳ ሲያዜሙ

 

ሎያ ባይ…ሎያ ባይ….ሎያ

 

ሎያ ማስቀላ ባይ ሎያ

 

ማስቃል ኡፋይስ ባይ ሎያ

 

ሙስ ሁሽ ባይ ሎያ ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ ማለት መስቀል እንኳን መጣህልን፤ የእኛ ደስታ፤ የእኛ መዝናኛ መስቀል እንኳን በደህና መጣህልን በማለት በጉጉት ስለሚጠባበቁት መስቀል በዓል ሲያዜሙ በስፋት ይደመጣል፡፡

 

በጎፋ ብሔረሰብ ለመስቀል በዓል የምግብና መጠጥ አዘገጃጀቱም ሆነ በሌላ የሚሰጠው ትኩረት ከሌሎች በዓላት የተለየና ልዩ የሚያደርገው ሲሆን ለመስቀል ተብሎ የሚወጣው ወጪ የማንንም በር የሚያንኳኳ እና ያለውም የሌለውም ዓመቱን ሙሉ በመቆጠብ ሳይሳሳ የሚዘጋጅበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡

 

በተለይ በመስቀል በዓል ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠውና የቤተሰብ አባል ሆነው ተለያይተው የቆዩ የሚገናኙበት ከአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ርቀው ያሉ በደመራ ዕለት በመገኘት ናፍቆቱን የሚወጣበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ሀዘን ውስጥ የነበረ ሀዘኑን የሚረሳበት፣ የተነፋፈቁ የሚገናኙበት፣የትዳር ጓደኛ የሚመረጥበት፣ ዓይነተኛ ቀንና ጊዜ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

ምንጭ፡-tubamegazine