Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት 3 ዞኖች መካከል አንዱ ነው፡፡

የካማሺ ዞን

 

 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት 3 ዞኖች መካከል አንዱ ነው፡፡ የዞኑ ዋና ከተማም ካማሽ ትባላለች፡፡ የክልሉ ርዕሰ ከተማ ከሆነችው አሶሳ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በ246 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ በ512 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

 

ጀሎ ተራራ ካማሽ ወረዳ ጀሎ ሌቃ ቀበሌ

የዞኑ ህዝብ ቁጥር 128,632 ሲሆን በአምስት ወረዳዎችና በ65 ቀበሌዎች የተደራጀ ነው፡፡ ዞኑን በደቡብ እና በምስራቅ ኦሮሚያ ክልል በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ከአሶሳና ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሰሜን ከመተከል ዞንና ከአማራ ክልሎች ጋር ይዋሰናል፡፡ የአየር ንብረቱ ቆላማ ሲሆን በዞኑ በብዛት ሰፍሮ የሚገኘው የጉሙዝ ብሄረሰብ ነው፡፡

 

ዞኑ በርካታ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች ያሉት ቢሆንም መስህብ ሀብቶቹ ለብዙ ዓመታት ሳይታዩ፣ ሳይጠኑ እና በተገቢው መንገድ ለህዝብ ሳይተዋወቁ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከመስህብ ሃብቶቹ ማግኘት የነበረበትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

 

የመስህብ ሀብቶቹ

በዞኑ በስተምዕራብ አቅጣጫ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው የአጋሎ ሜጢ ወረዳ ሲሆን በውስጡ በሚገኙ 14 ቀበሌዎች ውስጥ የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ቂልጡ ፍል ውሃ ከወረዳው 5 ኪ.ሜ. ገባ ብሎ የሚገኝ መስህብ ሲሆን ቂልጡ ዋሻም በተመሳሳይ በቂልጡ አባ ዲንሳ ቀበሌ በ3 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ግሽ ዲልባ ታሪካዊ ድንጋይም ከአጋሎ ሜጢ በምዕራብ በኩል በ3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡ ካምፑ ቃሊሴ (የጣሊያን ካምፕ)፣ ሰልባጀንጋራ ፍል ውሃ፣ አባ ጎምቦሎና ቦር ተራራ ይገኛሉ፡፡

 

በካማሽ ወረዳ ደግሞ ጊልጊላ ፍል ውሃ፣ ከካማሽ በ9 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጀሎ ተራራ፣ ኮቢ ጥብቅ ደንን እንዲሁም ቅድስት አርሴማ ገዳም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በያሶ ወረዳም የደዲሳ ወንዝ እና በዙሪያው ያለ ጥቅጥቅ ደን አይምሮን የመቆጣጠር መሳጭ ሀይል አላቸው፡፡

 

በሰዳል ወረዳ የፋጵሮ ሚሊኒየም ፓርክ፣ ሰማያዊ እብነ በረድ፣ የአባይ ወንዝና በዙሪያው ያሉ ጥቅጥቅ ተፈጥሮአዊ ደን እና በየዓመቱ ጥርና ሚያዚያ ላይ ብዛት ያለው ሰው የሚገኝበት ለተለያዩ ህመምተኞች በፈዋሽነቱ የሚታወቀው የፀበላ ጋንቲ ፍል ውሃ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በበሎጂጋንፎይ ወረዳ ከሚገኙት መስህቦች ደግሞ የሳይ ዳለቻ ፏፏቴ፣ ቦሎይዳ ዋሻ፣ ሰኒ ጊዮርጊስ ፍል ውሃ ይጠቀሳሉ፡፡

 

ሽ ዲልባ /ክቡር ድንጋይ/ ታሪካዊ ድንጋይ

 

ግሽ ዲልባ /ታሪካዊ/ ክቡር ድንጋይ

ጊሽ ዲልባ ማለት ጉሙዝኛ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ክቡር ድንጋይ የሚለውን የአማርኛ አቻ ትርጉም ይይዛል፡፡ ይህ ክቡር ድንጋይ የሚገኘው ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በካማሽ ዞን በአጋሎ ሜጢ ወረዳ በቂልጡ አባ ዲንሳ ቀበሌ አባ ጫሊ ወንዝ በሚባለው ልዩ ስፍራ ነው፡፡

 

ክቡር ድንጋይ /ግሽ ዲልባ /፡- የሚገኘው ከካማሽ ዞን በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በአጋሎ ሜጢ እና በቂልጡ አባ ዲንሳ ቀበሌ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ድንጋይ የቂልጡ ወንዝን እንዳለፍን በቦር ተራራ እና በአባ ጫሊ ወንዝ ተከቦ እናገኘዋለን፡፡

 

ክቡር ድንጋዩ በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን እንደዛሬው ብቻውን ሳይሆን ሁለት ሆኖ ከሰማይ እንደወረደ እና ድንጋዩ በወረደበት ጊዜ ቀንና ሌቱን ለመለየት የሚያስቸግር ከፍተኛ የሆነ ጭስ የመሰለ ጭጋግ አካባቢውን አፍኖት ለተወሰነ ጊዜ እንደቆየ ይነገራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደም መሰል ነገር ከሰማይ እንደወረደ እና በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ጩኽት እንደተሰማ የመሬት መንቀጥቀጥም እንደተከሰተ በአካባቢው የነበሩ አዛውንት ይናገራሉ፡፡ ክቡር ድንጋዩ ከሰማይ ወርዶ አሁን ባረፈበት ቦታ በወቅቱ በዙሪያው ሰፍረው ይኖሩ የነበሩ ድንጋዩ በወደቀበት ጊዜ ከ1000 በላይ የሚሆኑ የአጋሎ፣ ሜንዲያና ጀሞዋ ጎሳዎች እንደሞቱም አዛውንቱ ይናገራሉ፡፡

 

ግሽ ዲልባውን ልዩ እና ታሪካዊ የሚያደርገው ነገር በየዓመቱ በራሱ ጊዜ ቦታ መቀያየሩ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በዝናብ ጊዜ መብረቅ /ነጎድጓድ/ በሚሰማበት ጊዜ ድንጋዩም አብሮ መንቀሳቀሱ ነው፡፡ ታሪካዊ ድንጋዩ በግምት ከ85-100 ኪሎ ግራም ክብደት የሚኖረው ሲሆን ክብ እና ለስላሳ በተጨማሪም ከፊል ጥቁርና ቡራቡሬ መልክ አለው፡፡

 

ሌላ በአካባቢው የሚኖሩ አዛውንትም እንደገለፁት ድንጋዮቹ  ከሰማይ ሲወርዱ በቁጥር 2 መሆናቸውንና ጠቆር ያለ መልክ ያለውና በመጠን ከፍ የሚለው ድንጋይ አሁን ያለው ሲሆን ሌላኛው እና በመልክ ነጣ ያለ ቀለም እንዲሁም በመጠን አነስ ያለው ድንጋይ ወደ ሰማይ ተመልሶ እንዲሄዱ አክለው ገልፀውልናል፡፡ ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪም ሲገልፁ ክቡር ድንጋዩ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ማንሳት የሚቻለው ከመሬት እስከ ቀበቶ መታጠቂያ ብቻ ሲሆን ወደ ግሽ ዲልባው /ክብር ደንጋዩ ሲሄዱ ድምፅ እየተሰማ ከሆነ ግን እስክ ቀበቶ መታጠቂያ ድረስም ማንሳት እንደማይቻል ጠቁመውናል፡፡

 

ይህ ክቡር ድንጋይ ከሰማይ ወደ ምድር በወረደበት ጊዜ ከሞቱት ከ1000 በላይ የአጋሎ፣ ሚንዲያና ጀሙዋ ጎሳዎች በተጨማሪ ከኦሮሚያ ደጋማ አካባቢ ወደ ስፍራው መጥቶ ይሰራ የነበረ ልጅ ታሪካዊ /ክቡር ድንጋዩን/ በጠጠር ከመታውና በላዩ ላይ ሽንቱን ከሸናበት በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ታሞ ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ደም ሸንቶ እንደሞተ ከታሪክ አዋቂዎች አንደበት ለመረዳት ችለናል፡፡

 

የጉሙዝ ብሄረሰብ ባህላዊ ዳኝነት  (የግጭት አፈታት ሥነ-ስርዓት) ደመንጋሀቻ ጳጋ

 

የግድያ ወንጀል ሲፈፀም የሚደረግ የእርቅ ስነ ስርዓት

በብሄረሰቡ ዘንድ የህይወት ማጥፋት ወንጀል ሲከሰት ታላላቅ የጉሙዝ አባቶች (የሀገር ሽማግሌዎች ) እና የሀይማኖት  አባቶች ከሀገር በቀል እውቀቶች መካከል አንዱ የሆነውን የብሄረሰቡን ባህላዊ የዳኝነት ስነ-ስርዓት ተጠቅመው የተፈጠረው ችግር ሳይባባስ እና የከፋ አዳጋ ሳይደርስ ጥረት ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ከቦታው ማንም ሰው ሳይደርስ ሶስትና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ሶስት ነገሮች ማለትም ከእህል ዘር፣ ለምለም ሳር እና አጥንት ይዘው ከገዳይ ወደ ሟች ቤት ይላካሉ፡፡

 

ይህ ሲደረግ ግን ገዳዩ ከአካባቢው እንዲርቅ ይደረጋል፡፡ ምክኒያቱም የባሰ ችግር እንዳይመጣ በማለት ነው፡፡ ከዚያ ከገዳይ ወደ ሟች ቤት የተላኩት ሴቶች የያዙትን ለምለም ሳር፣ የእህል ዘር እና አጥንት ለማቹ ቤተሰብ ይሰጣሉ፡፡ በመቀጠል የሟቹ ቤተሰብ የሆነው ከለምለም ሳርና ከእህል ዘር በአፍ ይቀመሳል፡፡ አጥንቱም በእጁ ነክቶ መሬት በማስቀመጥና ከእርሱ ጎሳም  ሰዎችን ጠርቶ ያማክርና ለመታረቅ ፈቃደኛ መሆኑን ለተላኩት ሴቶች ምላሽ ይሰጣል፡፡

 

ከገዳይ ቤተሰብ የተላኩት ሴቶችም የሟች ቤተሰብን ምላሽ ይዘው ወደ ገዳይ ቤተሰብ ይመለሳሉ፡፡ የገዳይ ቤተሰብም በተመሳሳይ ከጎሳው ሰዎች ይመርጡና ለእርቁ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማለትም የትና መቼ እንደሚገናኙ እንዲሁም ምን ምን እንደሚያስፈልግ የሚወስኑ የሀገር ሽማግሌዎች ከገዳይ ወደ ሟች ቤት ይላካሉ፡፡

 

የተላኩት ሽማግሌዎች ወደ ሟች ሰፈር መቅረብ የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ሽማግሌዎች ከሟቹ ቤተሰብ በኩል ከታዩ ጸቡ ሊባባስ ስለሚችል ማለት ነው፡፡ ይህ ከተደረገ በኋላ ከሁለቱም በኩል የተመረጡት ሽማግሌዎች ከሟቹና ከገዳዩ ሰፈር መካከል ላይ እና ሰው በማይበዛበት ቦታ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሁለቱም ቤተሰብ ሽማግሌዎች ጋር ተወያይተው የደረሱበትን  ስምምነት እና ለእርቁ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለይተው ለላካቸው ቤተሰብ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ በዚህም መሰረት የእርቁ ሠዓት  ክረምት በሚገባበት ጊዜ እና ጎርፍ መጥፎ ነገሮችን ጠራርጎ ከሰፈር ወደ ወንዝ በሚያስገባበት ጊዜ ይሆናል፡፡

 

ከሁለቱም  ቤተሰብ በተውጣጣ ገንዘብ የተገዛ በግም ይቀርባል፡፡ በጉ በገዳዩ ቤት ይታረድና ደም ነክተው ጠላ ጠምቀው የሚታረድ ከብት ተዘጋጅቶ የእርቁ ቀን ይጠበቃል፡፡ ቀኑ ሲደርስም ከሁለቱም በኩል ሴቶች በአጃቢነት እና ግንባር ቀደም ሆነው  ይቆያሉ፡፡ በዕርቁ ላይም እንደ ወላጅ ሆነው በመምከርና በማሰማማት ሚናቸውን ይወጣሉ፡፡ በእርቁ ዕለትም በተመረጠው ወንዝ ይገናኛሉ፡፡ ወንዝ እንደደረሱ ተሸፍነው ይቆያሉ፡፡ በመጀመሪያ የገዳዩና የሟቹ ዘመዶች ይታረቃሉ፡፡ በመቀጠልም ገዳይ ለብዙ ዓመታት ተደብቆ ከቆየበት ቦታ ተፈልጎ እንዲመጣ ይደረጋል፡፡ ከዚያም የሟችና የገዳይ ቤተሰቦች በተመረጠው ወንዝ ይገናኙና ከወዲያና ወዲህ ማዶ በመሆን ሁለቱም እስክ ውሃ ግማሽ ድረስ ይገባሉ፡፡ ውሃው ውስጥ ከገቡት የሁለቱ ቤተሰቦች በስተቀኝ አራት ሴት እና አምስት ወንድ በስተግራም አምስት ሴትና አራት ወንድ በአጠቃላይ አስራ ስምንት ሁነው ይቆማሉ፡፡ ፀብን ያበርዳል ተብሎ ስለሚታሰብ ቀዝቃዛ የዶቅማ ቅጠል በመቁረጥ ወንዙ ውስጥ በገቡት የሁለቱ ቤተሰቦች መካከል በመጋረድ እንደ ጫካ አይነት ነገር ይፈጥራሉ፡፡

 

ከዚያም በኋላ በግ ያስመጡና በጉን በዶቅማ ቅጠሉ ላይ ያስተኛሉ፤ ካስተኙት በኋላ በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል ምንም አይነት መተያየት አይኖርም፤ የሚያዩት በበጉ አንገት ላይ የሚያርፈውን ቢላዋ ብቻ ነው፡፡ በጉ ከታረደ በኋላ ከመካከላቸው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች ከእንግዲህ በመካከላችሁ እርቅ ወርዷል፤ የሚል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ማዶና ማዶ ተሸፍነው የነበሩ የሟችና የገዳይ ቤተሰቦች የተሸፈኑበትን ልብስ ከራሳቸውና ከፊታቸው ላይ ያነሳሉ፤ ይተያያሉ፤ ይሳሳማሉ፡፡ በመቀጠልም ከታረደው በግ ደም ነክተው ይጨባበጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ወዲህ ማዶ የነበሩ ሰዎች ወዲያ ማዶ ከወዲያ ማዶ የነበሩ ሰዎች ደግሞ ወዲህ ማዶ ይሻገራሉ፡፡ ሰዎችም ለጋ ቀርቀሃ፣ ለንቋጣና ዘንባባ ሰንጥቀው ከታረደው በግ ጋር በውሃው መውረጃ ላይ ይለቃሉ፡፡ የታረደው በግ አይገፈፍም፣ አይበላም ከዚያም የሟች ቤተሰብ ወደ ገዳይ ቤት ይሄዱና መታረቃቸውን ያሳያሉ፡፡

 

በገዳይ ቤት ከደረሱ በኋላ ከብት ታርዶ የሟች ቤተሰብ የታረደውን ከብት ደም በጣታቸው በመንካት በደም ገዳዩን እንብርቱንና ግንባሩን ያስነኩታል፤ በመቀጠልም ለእርቁ የተዘጋጀ ጠላ በምሶሶ ስር ይቀመጥና በብርጭቆ ተደርጎ ለገዳዩ ይሰጣል፡፡

 

 ከዚያ ወደ ሟቹ ቤት ለመሄድ ይቀጣጠራሉ፤ ሄደውም በገዳዩ ቤት ያደረጉትን በሙሉ በሟቹ ቤትም ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከተጓዙ በኋላ የሁለቱም ቤተሰቦች ሌላ ነብስ ሳይጠፋና የከፋ አደጋ ሳይደርስ ወደ ዱሮው ፍቅራቸው ይመለሳሉ ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም የሟችና የገዳይ ቤተሰቦች በሃገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ፡፡ በዚህ ሂደትም የገዳይ ቤተሰብ ለሟች ቤተሰብ እንጨት ይቆርጡና እንጨቱን የምታክል ልጅ እንዳለቻቸው እና ወልዳ እንድትተካቸው ለመስጠት ይስማማሉ፤ የሟች ቤተሰብ ከገዳይ ቤተሰብ የተሰጣቸውን እንጨት ከተቀበሉ ልጅቷን ለመቀበል ፍቃደኛ መሆናቸውን ያሳያል፤ ይህ ካልሆነ ግን ልጅቷ ትንሽ በመሆኗ ሊሆን ስለሚችል ሌላ ከፍ ያለ እንጨት ተቆርጦ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ የገዳይ ቤተሰብም ሌላ ከፍ ያለች ልጃገረድ ካለቻቸው ከፍ ያለ እንጨት ቆርጠው በመስጠት ስምምነት ላይ ይደርሳሉ፡፡

 

በመቀጠልም ልጅቷን በማምጣትና በምሶሶ ስር በማስቀመጥ ልጅቷን ያሳያሉ፤ የሟች ቤተሰብም በደስታ ይቀበላሉ፡፡ ልጅቷንም በመያዝ ከብት ያርዱና መኢቻ የሚባል ጌጥ በእጇ ላይ ያስሩላታል፡፡ ከዚህ በኋላ የሟች ቤተሰብ ልጅቷን ልክ እንደ እህትና እንደ ቤተሰብ አባል አድርገው ማንኛውንም አይነት ችግር ሳይፈጥሩ ያሳድጋሉ፡፡ ለማግባትም ሆነ ለሌላ መጥፎ ነገር ፈፅሞ አያስቧትም፡፡ ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ በሌላ ሴት ልጅ ተቀይራ በለውጥ ጋብቻ ስርዓት ለሌላ ወንድ ትዳርና ከቤት ትሄዳለች፤ በእርሷም ምትክ ተቀይራ ወደ ሟች ቤተሰብ የመጣችው ልጅ የምትወልደው ልጅ የሟቹ ምትክ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ በሟች ቤት ቃለ መሀላ ይፈፀማል፡፡ የሟችና የገዳይ ቤተሰብ ድሮም አንድ እንደነበሩና ወደ ፊትም አንድ እንደሚሆኑ ቃል ገብተው  የታረደ በግ አጥንት በጋራ ሰብረው በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ይቀብራሉ፡፡ የገዳይ ወንድም ግን በሟች ቤት በመገኘት  ማንኛውንም ሟቹ ሲያከናውናቸው የነበሩ ስራዎችን ይፈፅማል፡፡ በጉሙዝ ብሄረሰብ ባህል መሰረት የሞተ ሰው የሚተካው  በሰው እንጂ ፈፅሞ በገንዘብ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ ነውርም ይቆጠራል፡፡

 

የዞኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች፤

በዞኑ በግብርናው መስክ ሰሊጥ፣ ቦቤ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎ፣ ነጭ ቦሎቄ፣ እጣን በብዛት ሲመረቱ በማዕድን ውጤቶች ወርቅ፣ አሸዋና ድንጋይ፣ እምነ በረድ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ይሁን እንጂ በእርሻ 35 ኢንቨስተሮች ኢንቨስት ያደረጉ ቢሆንም በእጣን 1 ኢንቨስተር ብቻ ነው እየሰራ ያለው ይህ የሚያሳየን ኢንቨስተሮችን ወደ ዞኑ ጎራ ቢሉ በእጣን ምርት ላይና  በባህላዊ መንገድ እየተሰራ ያለውን የወርቅ ሀብት በዘመናዊ የታገዘ አሰራር በማገዝ ዞኑም ባለሀብችንም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

 

ምንጭ፡-tubamegazine