በድልድዩና በወንዙ መካከል ያለው ርቀት ከፍተኛ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ አ

አደገኛ አትክልቶች

 

Image result for አደገኛ አትክልቶች

 

በድልድዩና በወንዙ መካከል ያለው ርቀት ከፍተኛ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ አባ ወራዎች ከድልድዩ ሥር በወንዙ ዙሪያ ሰፍረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ከመኖሪያ ቤቶቹ ፊት ለፊት በሚገኘውና መጠነኛ ስፋት ባለው ቦታ ላይ እንደ ቆስጣ፣ ሠላጣ፣ ጥቅል ጐመን፣ የሀበሻ ጐመን፣ ቃሪያ፣ ቲማቲም ያሉ የጓሮ አትክልቶችን ያለማሉ፡፡ የወንዙ ስያሜ ቡልቡላ ይባላል፡፡

 

የቡልቡላ ወንዝ እንደ አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ወንዞች ከየኢንዱስትሪውና ከየመኖሪያ ቤቱ በሚለቀቁ ፍሳሾች ተበክሏል፡፡ በውስጡ ደረቅ ቆሻሻ፣ ላስቲክና ሌሎችንም ይዟል፡፡ ተፈጥሯዊ ቀለሙም በጥቁር ተተክቷል፡፡ መጠፎ ጠረንም አለው፡፡ በዙሪያው የሠፈሩት አባ ወራዎች ሁኔታው ብዙም የሚያስጨንቃቸው አይመስሉም፡፡ እንዲያውም ከወንዙ ጎን ባለው ቦታ ላይ የሚያለሟቸውን አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ውኃ የሚያጠጡት ከወንዙ እየቀዱ ነው፡፡ የሚያመርቷቸውን አትክልቶች በኪሎ ከአምስት እስከ 11 ብር በማስከፈል ለቸርቻሪዎች ያስረክባሉ፡፡ በዚህ መልኩ ኑሯቸውን ሲገፉ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ነገ ግን ዋጋ ያስከፍላቸው ጀምሯል፡፡ የሚጠቀሙበት የወንዝ ውኃ በቆዳቸው ላይ የጤና ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በሚያለሙት አትክልት ላይም ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ጠርጥረዋል፡፡ ነገር ግን የወንዙን ውኃ ከመጠቀም ሉቦዝኑ አልቻሉም፡፡    

 

ትንንሽና ትልልቆቹን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ከ70 በላይ ወንዞች እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንደ ቡልቡላ ያሉ እነዚህ ወንዞች ለተለያዩ ግልጋሎቶች መዋል ሲችሉ በተገቢው መንገድ ንጽሕናቸው ባለመጠበቁ ግን ለአካባቢና ለሰዎች ጤና ጠንቅ አድርጓቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ወንዞች ከፋብሪካዎችና ከተለያዩ ተቋማት በሚወጡ ኬሚካሎች የተበከሉ ናቸው፡፡ ከየቤቱ የሚወጣ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ወደ ወንዞች መቀላቀሉም አደገኛነታቸውን አባብሶታል፡፡ ይሁንና በከተማው ባለው የቦታ ጥበት ምክንያት አማራጭ ያጡ ብዙዎች በወንዞቹ ዙሪያ ሰፍረው የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬም ያለማሉ፡፡ ይህ ተግባር ግን በነዋሪዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ድርጅቶችም የግብርናው አካል ናቸው፡፡ ከቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በተገኘ መረጃ መሠረት፣ በከተማዋ 112 ፈቃድ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬ አልሚዎች ይገኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹም በእነዚህ በተበከሉ ወንዞች አካባቢ የሚያለሙ ናቸው፡፡

 

‹‹ወንዞቹ ከመጠን ባለፈ ተበክለዋል፡፡ ለእርሻም ሆነ ለሌሎች አገልግሎቶች መዋል አይችሉም፤›› በማለት ከዚህ ቀደም አስተያየታቸውን የገለጹት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰርና በአዲስ አበባ ወንዞችና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የብክለትና ሳኒቴሽን ፕሮግራም መሪ ዶ/ር ሥዩም ለታ ናቸው፡፡

 

እንደ ዶ/ር ሥዩም ገለጻ፣ የከተማዋ የላይኛው ተፋሰሶች በመጠን አነስተኛ ናቸው፡፡ በተለይም በበጋ ወቅት የተፋሰሶቹ መጠን የለም ለማለት በሚያስደፍር መጠን ይቀንሳሉ፡፡ የታችኛው ተፋሰሶች በተቃራኒው ሙሉ ይሆናሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ከየቤቱና ከየተቋማቱ የሚለቀቁ ፍሳሾች ወደየተፋሰሶቹ ስለሚገቡ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ የሚመስሉት ወንዞች አደገኛ የሚባሉ ቢሆኑም በታችኛው ተፋሰስ በተለይም በትንሹ አቃቂ እና በፒኮክ ወንዝ አካባቢ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ በስፋት ሲለማ ይታያል፡፡

 

በዚህ መልኩ የሚለሙት አትክልትና ፍራፍሬዎች ‹‹ሄቪሜታልስ››፣ የተለያዩ ኬሚካሎችና ለጤና ጐጂ ተህዋስያንን በውስጣቸው ይይዛሉ፡፡ ይህም በተመጋቢዎች ላይ ከፍተኛ የጤና ቀውስ ይፈጥራል፡፡ ‹‹እኛው ብክለቱን ስንልክ እነሱ ተቀብለው በምርት መልሰው ይልኩልናል፤›› የሚሉት ዶክተር ሥዩም፣ ሦስት አራተኛ የሚሆነው የከተማው የአትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት ከዚህ እንደሚገኝ በመግለጽ ጉዳዩ የተለየ ትኩረት እንደሚሻ አሳስበዋል፡፡

 

ለጤና ካላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በበርካቶች ለምግብነት የሚመርጧቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች በአገሪቱ በስፋት ይገኛሉ፡፡ በተለይም በአፅዋማት ወቅት በስፋት ለምግብነት ስለሚውሉ፣ የሚኖራቸው ገበያም የደራ ነው፡፡ በየፍራፍሬ መደብሩ ለሽያጭ የሚቀርቡ የአትክልቶችና ፍራፍሬዎች ዓይነትና መጠንም ከወትሮው በተለየ ይጨምራል፡፡ አትክልት ብቻ የሚመገቡ (ቬጂቴሪያን) ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያው እንደ ፆሙ ወቅት ባይሆንም ሞቅ እንዲል አድርጐታል፡፡

 

ሰለሞን ይባላል (ስሙ ተቀይሯል)፡፡ ከዚህ በፊት የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያዘወትር ነበር፡፡ ይህም ተክለ ሰውነቱ የተስተካከለ እንዲሆን ረድቶታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከሥራ ጋር ስላልተመቸው ስፖርቱን አቋርጧል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሰውነት ክብደቱ እይጨመረ ሄደ፡፡ ክብደቱም በአንድ ጊዜ ከ73 ኪሎ ወደ 90 ኪሎ ደረሰ፡፡

 

ሁኔታው ያሳሰበው ሰለሞን፣ ክብደቱን ለመቆጣጠር በእግር መጓዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብን የዕለት ተግባሩ አደረገ፡፡ የሀበሻ ጐመን፣ ቆስጣ፣ ሠላጣ፣ ቲማቲም፣ አቮካዶ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ገዝቶ የሚመገበው በሰፈሩ ከሚገኝ የአትክልትና ፍራፍሬ መደብር ነው፡፡ ‹‹ከገጠር አምጥተው ለቸርቻሪዎቹ የሚሸጡት ገበሬዎች ናቸው፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ዙሪያ እንደሚመረትም አውቃለሁ፤›› በማለት አብዛኛዎቹ በከተማ ውስጥ የሚለሙት ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በተበከሉ ወንዞች ውኃ መሆኑ አሳስቦት እንደማያውቅ በሚያመለክት ስሜት ይናገራል፡፡

 

በከተማዋ አብላጫው የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ የሚካሄድበት አትክልት ተራም አብዛኛውን ምርት የሚቀርብለት እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚያለሙ አርሶ አደሮችና ተቋማት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ በከተማው 112 ፈቃድ ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ጅምላ አከፋፋዮችና 9,488 በችርቻሮ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ በአትክልት ተራ የሚነግዱ ናቸው፡፡ በከተማው የሚካሄደው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በተበከሉ ወንዞች ዙሪያ መሆኑ ከሚፈጥረው የጤና ቀውስ ባለፈ በጣዕምም ሆነ በመልክ በሌላ አካባቢ ከሚመረቱ አትክልቶች በቀላሉ እንደሚለይ የአትክልት ተራ ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ልዩነቱን ነገሬ የሚሉ በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ አትራፊ እስከሆነ ድረስ ከየትም ቢመጣ ግድ ያላቸው አይመስሉም፡፡

 

‹‹አትክልትና ፍሬፍሬ በከተማዋ በአራቱም ማዕዘን ይመጣል፡፡ ነገር ግን በትክክል ከየት ቦታ እንደሚመጣ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚመረት አላውቅም፤›› የሚለው የአትክልት ተራው ነጋዴ በዓሉ ሠይፈ ነው፡፡ መደብሩ በማንጐ፣ በብርትኳን፣ በፓፓያ፣ በቲማቲም፣ በቆስጣ፣ በሠላጣ፣ በአናናስ እና በሌሎችም የአትክልና ፍራፍሬ ዘሮች ተሞልቷል፡፡ መደብሩ አይጓደል እንጂ ምርቱ ከየትም ቢመጣ አያሳስበውም፡፡ የተመረተበትን ቦታ ጠይቆና አጣርቶ የሚሸምት ደንበኛም አጋጥሞት አያውቅም፡፡

 

ከጅምላ ነጋዴዎች ማንጐ በኪሎ 8 ብር ተቀብሎ እስከ 10 ብር ይሸጣል፡፡ ፓፓዬም በኪሎ 12 ብር በመግዛት 14 ብር እንደሚሸጥ ይናገራል፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ከተሠማራ ዓመት ሆኖታል፡፡ አካባቢው ለንግድ ዓይነተኛ ቦታ በመሆኑ፣ በቀን የሚያገኘው ገቢ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በቀን እስከ 10,000 ብር ያገኛል፡፡

 

በአትክልት ተራ መነገድ ከጀመረ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው ቴዎድሮስ ታረቀኝ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ከበዓሉ በተለየ የፍራፍሬና የአትክልት ምርቶች ከየት አካባቢ እንደሚመጡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የሀበሻ ጐመን፣ ቆስጣና ሠላጣ ከዚሁ ከአዲስ አበባ በተለይም ከአቃቂና ከቡልቡላ እንደሚመጡ ይናገራል፡፡ ምርቱን አትክልት ተራ ድረስ የሚያቀርቡት ገበሬዎች በመሆናቸው ዋጋቸው ቅናሽ እንዳለው ይናገራል፡፡

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሌላ አማራጭ መጠቀም ጀምሯል፡፡ ‹‹ከአዲስ አበባ ዙሪያ የሚመጡ ምርቶች በተበከሉ ወንዞች ዳር ስለሚመረቱ የተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚያስከትሉ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ደግሞም እኛ በራሳችን የምናያቸው ልዩነቶች አሉ፡፡ እዚህ የሚመረቱት ጣዕማቸው ደስ አይልም፡፡ ለምሳሌ እዚህ የሚመረተው ሠላጣ ቀጫጫና ተባዮች የበዙበት ነው፡፡ ገበያ ላይ የሚቀርበውም ከነሥሩ ተነቅሎ ነው፤›› የሚለው ቴዎድሮስ፣ አልፎ አልፎ ሠላጣ ከኮምቦልቻ፣ የሀበሻ ጐመን ከአሠላ እንደሚያስመጣ ይናገራል፡፡ ሌሎች እንደ ካሮት፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች ያሉ ምርቶችን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚያመጡላቸው ጅምላ አከፋፋዮች አሉ፡፡

 

እንደ ቴዎድሮስ ገለጻ፣ በአትክልት ተራ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ለገበያ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች የሚያስመጡት ከሌሎች ከተሞች ነው፡፡ ከሌላ ቦታ የሚመጡት ምርቶችም እዚህ ከሚመረቱት በጥራት የተሻሉ በመሆናቸው ዋጋቸው ወደድ ይላል፡፡ የተጠየቁትን ዋጋ የመክፈል አቅሙ ያላቸው ጥቂት ነጋዴዎች ብቻ ይገበዩዋቸዋል፡፡ የተቀሩት ገበያ ለሚያቀርቡት ምርት ብዙም ግድ የሌላቸው በብዛት ሕገወጥ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ሙሉ ለሙሉ የሚያቀርቡት ምርት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚመረቱትን ነው፡፡

 

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚመረቱ አትክልትና ፍራፍሬዎች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አመዝኗል፡፡ በጤና ላይ በማያደርሱት ቀውስ አደገኛ የሚባሉት ሄቪ ሜታልስ የሚባሉት ናቸው፡፡ ሶዲየም፣ ማግኒዚየም፣ ፖታሲየም፣ ካልሲየም፣ ክሮሚየም፣ አርሴኒክ፣ ካድሚየም፣ ኮፐር፣ ሊድ፣ ኒኬል፣ ዚንክ፣ ሜርኩሪ፣ ኮባልት፣ ሊድ ከሄቪሜታልስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 

እነዚህ ንጥረ ነገሮች በተወሰነ መጠን በሰውነት ውስጥ እንዲኖሩ ይገባል፡፡ ከመጠን በላይ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ለጤና አደገኛ ይሆናሉ፡፡ የአፈር መሸርሸር፣ ጐርፍ፣ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ኬሚካል አዘል ፍሳሾችና ሌሎችም ንጥረ ነገሮቹ ከመጠን በላይ እንዲከሰቱ ምክንያት ናቸው፡፡ አርሴኒክ፣ ካድሚየም፣ ክሮሚየም፣ ኮፐር፣ ሊድ፣ ኒኬልና ዚንክ በፍሳሽ ውስጥ በስፋት ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች መካከል ይመደባሉ፡፡ የንጥረ ነገሮቹ ከመጠን ያለፈ ክምችት በሣንባ፣ በኩላሊት፣ በጉበት በጭንቅላት ላይ ጉዳት ይፈጥራል፡፡ አቅም ማነስ፣ የደም ችግርና ሌሎችም የጤና ቀውሶች በእነዚህ ንጥረ ነገሮች የሚከሰቱ ናቸው፡፡

 

እ.ኤ.አ. በ2007 የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በቄራ፣ በፒኮክ፣ በአቃቂ፣ በመካኒሳ እንዲሁም በቡልቡላ አካባቢ በሚበቅሉ አትክልቶች ማለትም በጥቅል ጐመን፣ በካሮት፣ በሀበሻ ጐመን፣ በድንች፣ በሠላጣ እና በቆስጣ ውስጥ የንጥረ ነገሮቹ ከፍተኛ ክምችት ታይቷል፡፡ በተለይም በአቃቂ ወንዝ አካባቢ የሚበቅሉ አትክልቶች ላይ ከፍተኛ የኮባልት ክምችት መኖሩን፣ በቄራ አካባቢ የሚመረቱት ላይ ደግሞ ከፍተኛ የኒኬል፣ የኮፐር፣ የዚንክ፣ የማንጋኔዝና የአይረን ክምችት ታይቷል፡፡ አቃቂ አካባቢ በሚለሙ አትክልቶች ላይም እንዲሁ ከመጠን ያለፈ የማንጋኔዝና የሊድ ንጥረ ነገር ክምችት ተመዝግቧል፡፡ ይህም ለበርካታ አዲስ አበቤዎች የጤና ሥጋት መሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

 

በምርት ላይ ሳሉ ከሚያጋጥመው ብክለት በተጨማሪ ተመጋቢው ጋር እስኪደርስ ባለው ሒደት ውስጥ በሚፈጠር የአያያዝ ችግርም በተመጋቢው ላይ ሌላ የጤና ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ችግሩ በብዛት የሚታየውም የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ሆኗል፡፡

 

ከአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በተገኘው መረጃ መሠረት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማራ አንድ ድርጅት በቂ የደንበኞች ማስተናገጃ ቦታ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ማጠቢያ ክፍልና ሌሎችንም መሥፈርቶች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ የድርጅቱን አካባቢያዊ ሁኔታ በተመለከተም ዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ አንድ የፍራፍሬና አትክልት መነገጃ ተቋም ለጐርፍና ለናዳ ተጋላጭ ባልሆነ ቦታ ላይ እንዲቋቋም፣ ከቆሻሻ መጣያ ሥፍራ የራቀ እንዲሆን፣ ከመጥፎ ሽታና ከኬሚካል በፀዱ ቦታዎች እንዲሠራ ይጠበቃል፡፡ በአጠቃላይ ተቋማቱ በሰው ጤናና ደኅንነት ላይ አደጋ ከሚያስከትሉ ነገሮች የራቁ እንዲሆኑ ግድ ይላል፡፡

 

ይሁንና ይህ ድንጋጌ ከወረቀት ባለፈ ምን ያህል ተፈጻሚ መሆን እንደተሳነው ለማየት የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ በስፋት የሚከናወንበት አትክልት ተራን መቃኘት በቂ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ካወጣው መሥፈርት በተቃራኒ አጠቃላይ ቦታው በከተማው ከሚገኙ ለጐርፍ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ አካባቢው ረግረጋማ ባይሆንም ከፍተኛ የቆሻሻ ክምችት የማይለየው ነው፡፡ የተበላሹ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ሌሎች ተረፈ ምርቶች ያለገደብ ይጣሉበታል፡፡ በመጥፎ ጠረኑም ይታወቃል፡፡

 

ሳይሸጡ ቆይተው እንደ መበስበስ ያሉ ፍራፍሬዎችን ለጁስ መሥሪያነት የሚሸጡ፣ የተጣሉና የወዳደቁ ፍራፍሬና አትክልቶችን ሰብስበው የሚሸጡ ‹‹ጐርጓሪዎች››ም ችግሩን ይበልጥ አደገኛ አድርጐታል፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ በተበከሉ ወንዞች ዙሪያ የሚመረቱ አትክልትና ፍራፍሬዎች ጥቅም ላይ ሳይውሉ በቆዩ መጠን መርዛማነታቸው ይጨምራል፡፡ በተለይ በጥሬያቸው የሚበሉት ለከፋ የጤና ችግር ይዳርጋሉ፡፡

 

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የኅብረተሰብ ጤና ምርምርና አደጋዎች ቁጥጥር ዋና የሥራ ሒደት ኃላፊ አቶ አብርሃም ተስፋዬ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

 

‹‹በወንዞች ዳር ማምረት መልካም ቢሆንም ወንዞቹ ከየቤቱና ከየኢንዱስትሪው በሚወጡ ፍሳሾች የተበከሉ በመሆናቸው በአካባቢው የሚለሙ አትክልትና ፍራፍሬዎች ለጤና አደገኛ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ አብርሃም፣ እስካሁን በዚህ ምክንያት የተከሰተ ወረርሽኝ አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በከተማው ውስጥ ለተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል እንደሚገመት፣ ለዚህም በአትክልት ተራና በሌሎች አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን በክሎሪን ታክመው እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ንግድ ቤቶችም በክሎሪን አጽድተው እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህኛው ሳምንትም አትክልት ተራን ለማጽዳት ተችሏል፡፡       

 

በጊዜያዊነት ከተወሰደው ዕርምጃ ባሻገር ፋብሪካዎች ወደ ወንዞች የሚለቀቁትን ፍሳሽ እንዲያክሙ፣ ከወንዝ ጋር የተያያዙ የመፀዳጃ ቤት ቱቦዎችም ሌላ አማራጭ እንዲፈጠርላቸው በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

 

‹‹ወንዞቻችን ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ ብክለቱን ከምንጩ መቆጣጠር ያስፈልጋል፤›› የሚሉት የብክለትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት መሪው ዶ/ር ሥዩም፣ ችግሩን ለመቅረፍ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ሥራዎች ለመሥራት ማቀዱን ይናገራሉ፡፡ ወደ ወንዞቹ ከየአቀጣጫው የሚለቀቁ ፍሳሾች በየምንጫቸው እንዲጣሩ ማድረግ የፕሮጀክቱ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም የተበከሉትን ወንዞች የሚያፀዱ ተክሎችን በወንዞች ዙሪያ ማልማት ያስፈልጋል፡፡

 

 

ምንጭ ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ