በሁለተኛው ቀን ከምሳ በኋላ የጉብኝት መርሃ ግብር ነበር የተያዘልን።

ቱሉ ዲምቱ – የሰማይ ጥግ

 

Image result for ቱሉ ዲምቱ – የሰማይ ጥግ

 

በሁለተኛው ቀን ከምሳ በኋላ የጉብኝት መርሃ ግብር ነበር የተያዘልን። ወደ “ሳነቴ” ወይም ወደ ቱሉዲምቱ ተራራ በሶስት መካከለኛ አውቶቡሶች ጉዞው ተጀመረ። ባሌ ሮቤ ከአዲስ አበባ 430 ኪሎ ሜትር አካባቢ ላይ ነው ሚገኘው። ከአስራ አምስት ኪሎ ሜትር በኋላ ጥንታዊቷ ጎባ ከተማ ላይ እንደርሳለን።

መስመሩ በነገሌ ቦረና አድረጎ ወደ ሞያሌ ከዚያም ወደ ኬኒያ ያደርሳል። በዶሎመና አድርገን የአስፋልቱን መንገድ ጨርሰን ወደ ግራ ስንታጠፍ በጥቅጥቅ ደን ውስጥ ገባን። እድሜ ጠገብ አገር በቀል ዛፎች፤ በሰው እቅፍ የማይሞሉ ወፋፍራም ባህር ዛፎች፤ እንዲሁም የፈረንጅ ጽዶች አካባቢውን አረንጓዴ አልብሰውታል። በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ሁሉ ጉዟቸው በፈረስ ነው። ፈረሶቹ ደግሞ በቀይ ኮርቻ የተዋቡና የሚያማምሩ ናቸው።

በኮረኮንቹ መንገድ እየነጠርንና እየተንገራገጭን 30 ኪሎ ሜትሮችን ተጓዝን። በአስፋልት መንገድ መጓዝ ለለመደ አእምሮ 30 ኪሎሜትሩ እጥፍ ይሆንበታል። ከመንገራገጩ ይልቅ የአካባቢው መልከዓ ምድር ነው ስሜትን ሰቅዞ የሚይዘው።

የቅዝቃዜውም መጠን ይበልጥ እየጨመረ ነው። በግራና ቀኝ የሚታዩት ትላልቅ ዛፎች እየጠፉ እጅግ ለአይን ማራኪ ከሆኑ ነጫጭ ደን ውስጥ ደርሰናል። እዚህ ላይ አካባቢውን ልዩ የሚያደርገው ከደኑ በቁመት የምንበልጠው እኛ ሰዎች መሆናችን ነው። ደን ውስጥ ገብቶ ከዛፉ በላይ መሆን የተለመደ አይደለምና እነዚያ ነጫጭ መሬት ላይ የተነጠፉት ሳር መሰል ነገሮች እጅግ በጣም ብዙ የእጽዋት ስብጥር እንደያዙ ተነገረን። ምክንያቱም የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ከሌሎቹ ልዩ የሚያደርጉት በውስጡ የሚገኙት የደን አይነቶች እጅግ በጣም ብዙና በከፍተኛ ደረጃ ተለያይነት ያላቸው መሆናቸው ነው።

እኔ ባለሁበት አውቶቡስ ውስጥ ያሉት አስጎብኛችን አቶ ሙስጠፋ ዱሌ ይባላሉ። ሕይወታቸውን በሙሉ ከቀይ ቀበሮ ጋር ነው ያሳለፉት። የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ቅጥር ግቢ የእርሳቸው መኖሪያ ማለት ነው። በፓርኩ ውስጥ ሲገኙ ነው መንፈሳቸው ተማርኮ ደስታና ሰላም የሚሰማቸው። በተለይ በኢትዮጵያ ብቻ ስለምትገኘው ቀይ ቀበሮ የተለየ ፍቅር አላቸው ስለ ቀይ ቀበሮ አውርተውም አይጠግቡ።

አስጎብኛችን አቶ ሙስጠፋ በቀኝና በግራ እያየን ለምንደነቅበት ሁሉ በቂ ማብራሪያ እየሰጡን ጉዟችንን ፍሬያማ አድርገውታል። አሁን ሙሉ በሙሉ ባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ነን። የአቶ ሙስጠፋም ማብራሪያ እንደቀጠለ ነው። የቱሉ ዲምቱ መገንጠያ በስተግራ ትተን ሽቅብ ወደላይ እየወጣን ነው።

በነገራችን ላይ በአፍሪካ በተሸከርካሪ ወደ ከፍተኛ ቦታ የሚያስወጣ መንገድ ያለው ቱሉ ዲምቱ ሁለተኛው ቦታ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን በከፍታው በቀዳሚነት የሚታወቀው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ቢሆንም በተሸከርካሪ አይወጣበትም። ለዚህም ነው የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ልዩ የሚያደርገው።

አስጎብኛችን አቶ ሙስጠፋ እንደነገሩኝ ከሆነ ፓርኩ በ1962 ዓ.ም ነው የተመሠረተው። ስለአመሠራረቱም እንዲህ አጫወቱኝ፥ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተመሠረተው በፓርኩ ውስጥ የሚገኘውና ከ40 ዓመት በፊት የተቋቋመው የዲንሾ ሎጂን ምክንያት አድርጎ ነበር። በወቅቱ አንድ የውጭ ሀገር ባለሀብት ቦታውን በጎች እያረባ እንደ ቢሮና ማደሪያ ይገለገልበት ነበር። በአጋጣሚ በግ አርቢው የደጋ አጋዘን፣ የምኒልክ ድኩላንና ሌሎችም ብርቅዬ እንስሳትን በማየቱ “ይሄ ነገር ፓርክ ሊሆን ይችላል” በማለት ለመንግስት ሪፖርት አደረገ። መንግስትም የተባለውን በማጣራት በ1962 ዓ.ም በፓርክነት ከለለው።

ፓርኩ ከአዲስ አበባ በ430 ኪሎሜትር ርቀት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይገኛል። ስፋቱ ወደ 2ሺ2መቶ ኪሎ ሜትር ስኩዌር የሚደርስ ሲሆን ከሰሜን ወደ ደቡብ 74 ኪሎሜትር ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ደግሞ 53 ኪሎሜትር ይሸፍናል። ፓርኩ ከባህር ወለል በላይ ከ1ሺ450 እስከ 4ሺ377 ጫማ ባለ ልዩነት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን ያካትታል።

አሁን እኛም በከፍታው በሀገራችን ሁለተኛ ወደሆነው የቱሉ ዲምቱ ተራራ አናት ላይ እየተቃረብን ነው። 4ሺ377 ጫማ የሚረዝመው የቱሉ ዲምቱ ተራራ በሁሉም አቅጣጫ ለአይን እስኪታክት ድረስ አሻግረው ቢያዩት በተለያዩ የደን አይነቶች የተሸፈነ ነው። ቅዝቃዜውን ለመግለጽ እጅግ በጣም ያስቸግራል። ምክንያቱም የተራራው አናት ላይ ሲደረስ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 9 (-9ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ) ይደርሳል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የኦክስጅን እጥረት ቢኖርም ያልተለመደና መንፈስን የሚማርክ ልዩ ስሜት ይሰማዎታል። ምክንያቱም በሁሉም አቅጣጫዎች የሚያስተውሉት ተፈጥሮን ብቻ ነውና። ምንም ሰው የሰራው ነገር የለም። ከመሬት ብዙም ከፍ በማይሉት ጥቅጥቅ ደኖች ውስጥ እንደሆኑ ሲያስቡ ደግሞ በርግጥም ሰው ከደን ቁመት በላይ ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ይሆናሉ።

በአጫጭር እጽዋት የተሸፈነው የቱሉ ዲምቱ ተራራን እንዲያስውቡ ከተፈቀደላቸው መካከል የ«ጅብራ» እጽዋት ዋነኞቹ ናቸው። ይህን ዕጽዋት በስም ብቻ የምናውቀው ብዙዎች ነን። ይሁን እንጅ «እንደ ጅብራ አትገተርብኝ» ተብለን ይሆናል። ጅብራ ምን እንደሆነ ባናውቅም ግዙፍ ነገር ሊሆን እንደሚችል ገምተን ይሆናል። አንዳንዶች እንስሳ ይመስላቸው እንደነበር በመደነቅ ነግረውኛል። ዛሬ ግን ከጅብራ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠናል። በእጃችን እየዳሰስንም አድናቆታችንን ገልጸንለታል።

በስም ብቻ የምናውቀው ጅብራ በቁመት ያን ያህል የሚወራለት ባይሆንም በነዚያ አጫጭር እጽዋት ውስጥ በመገኘቱ ነበር የግዙፍነት ባህሪ ተሰጥቶት “አትገተርብኝ፣ አትከልለኝ” የተባለው። የቱሉ ዲምቱን ተራራ ቅዝቃዜ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ለማነጻጸር አይሞከርም። ምክንያቱም በቦታው የተገኘ ብቻ ነው ስሜቱን ሊረዳው የሚችለውና።

ገና ከአዲስ አበባ ስነሳ ብርድ ስለሆነ አለባበሴን እንዳስተካክል ተነገሮኝ ነበርና ተዘጋጅቼ ነው የሄድኩት። በርግጥም የኔን ያህል ለቦታው ተዘጋጅቶ የሄደ ያለ አይመስለኝም። ምክንያቱም የበረዶ ተንሽራታች መስየ በመሄዴ ጓደኞቼ ስቀውብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ከተራራው አናት ላይ ያሳለፍነው ጊዜ 30 ደቂቃ መሙላቱን እጠራጠራለሁ። ይሁን እንጅ በዚች አጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ነገሮችን አስተውያለሁ። ታሪኩን በምስልና በድምጽ ለማስቀረት ከሚሯሯጡት ጎብኝዎች ውስጥ ደስታውን በቃላት ለመግለጽ የቻለ እርሱ እድለኛ እንደሆነም አስባለሁ። ምክንያቱም ቅዝቃዜው ጥርስን እያንገራገጨ ድምጽን የመስለብ አቅም ነበረውና። ሲጀምር እጆችን፣ ከዛም አካልን ሲቀጥል ደግሞ አንድበትን አሳስሮ በአይን እንባ ሲወርድ ማየት ለቱሉ ዲምቱ ተራራ ብርቅ አይደለም። አስደሳች ጊዜ በቱሉ ዲምቱ አለፈ። የማይረሳ ታሪክ በምስልና በድምጽ ተሰናዳ።

በወቅቱ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሥራ ኃላፊዎች ለባህልና ቱሪዝም ያበረከቱት ሌላው አስደናቂ ስጦታ ነበር። ምክንያቱም በጉዟችን ሁሉ ከአይናችን ተሰውራ የነበረችውን ቀይ ቀበሮን በአሻንጉሊት ምስልና የቀይ ቀበሮን አጠቃላይ ታሪክ የያዘውን መጽሄት ነበር። በእርግጥ የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ፈርጥ የሆነችውን ቀይ ቀበሮ የሄድንበት ጊዜ ምቹ ባለመሆኑ ባለማየታችን ቅር ብንሰኝም ያየነው በሙሉ ለህሊና የማይረሳ በመሆኑ ደስታችንን ጎዶሎ አላደረገውም።

ምንጭ፡-አዲስ ዘመን ጋዜጣ