በ16ኛው ክ/ዘመን እንደተመሰረተ የሚነገርለት የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ

 

የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ አደረጃጀት

 

Image result for የጉራጌ

 

 

የሰው ልጅ የእለት ተዕለት ህይወቱን በሰላም ለመምራት በየሚኖርበት አካባቢ እንደየባህሉ የሚተዳደርባቸው ማህበራዊ

 

የመተዳደሪያ ደንቦች(social norms) እንዳሉት ይታወቃል፡፡ በእነኚህ ይሁንታውን በሰጣቸው ማህበራዊ ደንቦች ሰው

 

ህይወቱንና ሀብቱን ከአደጋ ጠብቆባቸው ለአያሌ ዓመታት ህልውናውን ከሚፈታተኑት የተለያዩ ጥፋቶች እየተከላከለባቸው

 

መኖሩን የማህበረሰብ ታሪክ አጥኚዎች በጥናት ጽሁፎቻቸው ላይ አስፍረውታል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ማህበራዊ

 

ተቀባይነትን አግኝተው ለማህበራዊው ህይወት ይበጃሉ ተብለው ሲተገበሩ የቆዩት ደንቦች ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና

 

ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

 

በ16ኛው ክ/ዘመን እንደተመሰረተ የሚነገርለት የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎም ለአመሰራረቱ መንስኤ ይኸው የሸንጎው ባለቤት

 

የሆነው የጉራጌ ብሄር ማህበራዊ ህይወቱን በሰላም ለመምራት እንደሆነ የሚያስረዱ የተለያዩ የጽሁፍና የቃል መስረጃዎች

 

ይገኛሉ፡፡ የጉራጌ ብሔር ጤናማ የሆነ ማህበራዊ ህይወትን ለመምራት ከጥንት ጀምሮ የታገዘው በባህላዊ ሸንጎው ሲሆን

 

ጉልበተኛው ደካማውን እንዳያጠቃ፣ህይወት እንዳይጠፋ፣ በአጠቃላይ የአካባቢው ሰላም እንዳይደፈርስ የመከላከል ብቃቱ

 

እጅግ በጣም ከፍተኛ ሲሆን ከዚህ ሌላ በአካባቢው ልማት እንዲስፋፋ ተወላጁን የማስተባበር አቅሙም እንዲሁ ጠንካራ

 

እንደሆነ የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ፡፡

 

የጉራጌ ብሄረሰብ እንዲህ ከዕለት ተዕለት ህይወቱ ጀምሮ እስከ ዘለቄታው ያለውን ቤተሰባዊ አካባቢያዊና ማህበራዊ

 

ህይወቱን መልክ ለማስያዝ የታገዘበትና የሚታገዝበት ባህላዊ ሸንጎ የሚተዳደርበት ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንብ (ህግ) ያለው

 

ሲሆን ይህ ደንብ ከቀደምቱ ትውልድ በመለስ ሰፊ ተቀባይነትን አግኝቶ ለፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እየዋለ

 

የተለያዩ ግልጋሎቶችን ሲሰጥ እንደቆየ የሸንጎው አባላት ያረጋግጣሉ፡፡

 

ምንም እንኳ ጉራጌ የሚተዳደርበት ደንብ (ህግ) እንደየ አካባቢው ዘዬ መጠነኛ የስም አጠራር ልዩነት ቢታይበትም

 

በአፈፃፀም ግን ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የጉራጌ ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንቦች ናቸው

 

ተብለው በዋናነት ህዝቡ የሚተዳደርባቸው አራት ሲሆኑ እነርሱም፡-

 

 የሰባት ቤት ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ

 

 (የኧጆካ ቕጫ)

 

 የክስታኔ እና የወለኔ ቤተ-ጉራጌዎች ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንብ

 

 (የጎርደና ሴራ)

 

 የመስቃን ቤተ-ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ

 

 (የፈር አገዘኘ ሴራ)

 

 የዶቢ ቤተ-ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ (የዶቢ ጎጎት ስናኖ ሴራ) ሲሆኑ እነዚህ ዋና

 

ባህላዊ መተዳደሪያ ደንቦች(ህጎች) በውስጣቸው የተለያዩ ንኡሳን ርዕሰ ጉዳዮችን ያዘሉ ሲሆን አሁን የምናተኩረው በዋና

 

መተዳደሪያ ደንቦቹ አደረጃጀት ላይ ይሆናል፡፡

 

11

 

1.1. የሰባት ቤት ጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ(የኧጆካ)

 

የኧጆካ ቕጫ/ባህላዊመተዳደሪያ ህግ/ አፈፃፀም እንደ ጉዳዩ ባህሪና ደረጃ በተለያዩ ማህበረሰባዊ ተቋማት የሚከናወን ሲሆን

 

የማህበረሰባዊ ተቋማቱ አደረጃጀትም እንደሚከተለው ነው፡-

 

 የሴራ ገነ መተዳደሪያ ቕጫ

 

 የሙራ ገነ መተዳደሪያ ቕጫ

 

 የጥብ መተዳደሪ ቕጫ

 

 የክፍል ህዝብ ቕጫና

 

 የጉራጌ የቕጫ ምክር ቤት ናቸው፡፡

 

የሴራ ገነ መተዳደሪያ ቕጫ

 

የሴራ ገነ መተዳደሪያ ቕጫ በመተዳደሪያነት ተፈፃሚ የሚሆነው በተወሰነ መንደር /ሰፈር/ ባሉት ማህበረሰቦች ውስጥ ሲሆን

 

የሚያካትታቸው የከብት ጥበቃ ሴራ/ህግ/፣ የቀብር ስነስርዓት ሴራ/ህግ/፣ የሟች ቤት እራት እድር ሴራ የተስካር ሴራ

 

የመንደር /የሰፈር/ ቀራት/ዘብ/ ሴራና የንብረት ጥበቃ ሴራ ለምሳሌ፡- /ክልክል ሳር፣ የጋራ የሆኑ የዛፍ ክልሎች/ የመሳሰሉት

 

ሲሆኑ በዚህ ረገድ ከአካባቢው የቕጫ ስርዓትና፣ ደንብ ውጪ የሆነ ተግባር የፈፀሙ የማህበረሰቡ አባላት የሚዳኙበትም ሆነ

 

ችግሮቹ የሚፈቱት የሴራ ዳነ/ዳኛ/ ተብለው በተሾሙት የሸንጎ አካላት ነው፡፡

 

የሙራ ገነ መተዳደሪያ ቕጫ

 

የሙራ ገነ መተዳደሪያ ቕጫ የሴራ ዳነ ከሚያስተዳድረው ማህበረሰባዊ ተቋም የሰፋና ከአንድና ከሁለት በላይ የሆኑ የሴራ

 

ገነ ያካለለ ሲሆን የተፈጠሩ አወዛጋቢ ወይም ቕጫን የተላለፉ ጉዳዩች በቕጫ መሰረት የሚፈቱበት የማህበራዊ ሸንጎ ተቋም

 

ነው፡፡ የዚህ ባህላዊ ሸንጎ የዳኝነት ስርዓት አካላቱ የሚመሩት በሙራ ገነ (በአካባቢው፣በአገሬው/ በመልካም ተግባራቸው፣

 

በፍትህ አሰጣጣቸውና፣ በአስተዋይነታቸው የተመረጡ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡

 

የጥብ/የጎሳ/ መተዳደሪያ ቕጫ

 

የጥብ መተዳደሪያ ቕጫ የሚባለው በአራቱም ማእዘናት በተለያዩ አካባቢዎች ከሌሎች ጥቦች/ጎሳዎች/ ጋር ተሰበጣጥረውና

 

ተደበላልቀው የሚኖሩ የጥብ /የጎሳ/ አባላትን በአንድ ማእከል በመጥራት በመሃከላቸው የተፈጠሩ አለመግባባቶችም ሆኑ

 

ከቕጫ ስርዓት ውጭ የተፈፀሙ ድርጊቶች ሲኖሩ በመልካም ስራቸውና ተግባራቸው እንዲሁም በአስተዋይነታቸው

 

በተመሰከረላቸውና በተመረጡ የጎሳው አበቃጥ/አውራ/ ሽማግሌዎች አማካኝነት የሚፈታበት ስርዓት ነው፡፡

 

ይኸውበጎሳው አባላት በራሳቸው መሃል የተከሰተም ችግር ሆነ ከሌላ ጎሳ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ለመፍታት

 

ከተሰበሰበው የጎሳ ሽማግሌዎች በጉባኤ ሰብሳቢነት የሚመረጠው ሰው የጥብ ዳነ ወይም /የጎሳ መሪ/ በመባል ይታወቃል፡፡

 

ይህ በባህላዊ የሸንጎ ኣካል በጎሳው አባላት ውስጥ የሚከሰቱ የቤት ቃጠሎዎች የንብረት ጥፋት፣ ከሌላ ጎሳ ጋር የተፈጠሩ

 

ማህበራዊ ችግሮች ከበድ ያሉ የመሬት ይዞታ ክርክሮችና በዛው ጥብ/ጎሳ/ መሃል የሚከሰቱ ግጭቶች ሲኖሩ በጋራ በመምከር

 

የሚፈቱበትና አስፈላጊ የእርምት እርምጃ የሚወሰድበት ማህበረሰባዊ ተቋም ሲሆን በመላ ጥብ /ጎሳ/ አባላት ይሁንታ

 

ያገኘው የጥብ ዳነ ወይም አበቃጥ/የጎሳ ዳኛ/ የጥብ መተዳደሪያ ቕጫን የባህላዊ ዳኝነት ስርዓቱን በማስፈፀም አስፈላጊውን

 

ሁሉ ያደርጋል፡፡ ይህ ሰው በጎሳው አባላት ዘንድም ተገቢው ስፍራና ክብር ይሰጠዋል፡፡

 

12

 

የክፍለ ህዝብ ምክር ቤት /ሸንጎ/

 

የክፍለ ህዝብ ምክር ቤት ሰፋ ያለና አንድን ቤተ ጉራጌ የሚወከል ሲሆን ከባህላዊ ሸንጎ አካላት ውጭ በሸንጎው የሚሾሙ

 

የተለያየ የዳኝነት አካላት የሚያማክል ሲሆን እነሱም የቕጫ ዳነ፣የጉርዳ ዳነ፣ የሳሞር ዳነ፣ ያንቂት ዳነ፣ የዥር ዳነ፣ የጎንደር

 

ንጉሱ፣ አበቋና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ የክፍለ ህዝብ የኧጆካ አካላት የክፍለ ህዝቡን ልማታዊና ሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች

 

በባለቤትነት የሚከታተሉና ለክፍለ ህዝቡ የጋራ ልማት ያለመታከት የሚሰሩ ሲሆን በዋናነት ግን በክፍለ ህዝቡ የሚከሰቱ

 

የደም ጉዳዮች፣ የቤት ቃጠሎ፣ የአካል ማጉደል ወንጀል፣ የድንበር ግጭቶች፣የንብረት ዘረፋና፣የአካባቢውን ሰላም የሚያውኩ

 

ሁኔታዎች ሲከሰቱ የሚሸመግልና፣ ፍትህ የሚሰጥ አካል ነው፡፡

 

የክፍለ ህዝብ የኧጆካ ሸንጎ ከሌሎች ክፍለ ህዝብ የኧጆካ ተወካዮች ጋር በጋራ በመምከር የጉራጌ የጋራ ጉዳዮችን ለምሳሌ

 

ከአገር ህለውና ጋር ተያይዞ የክተት ጥሪ ሲደረግ፣ የእንደራሴዎች ምርጫ ሲኖር፣ ለሌሎች ሁሉን አቀፍ የመንገድ ስራ ልማት

 

ሲኖርና ተመሳሳይ አገራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የጠቅላላ ጉራጌ ሸንጎ አካላት እንዲሰበሰቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት

 

ለምክር ቤቱ አባላት ሁሉ ጥሪ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡

 

የጉራጌ ቕጫ ምክር ቤት

 

የጉራጌ ቕጫ ምክር ቤት ከላይ የተጠቀሱት የዳኝነት ስርዓት አካላት /የቕጫ አስፈፃሚ/ ሁሉ የበላይና የመጨረሻ ይግባኝ

 

ሰሚ አካል ሲሆን አመሰራረቱም ከሁሉም ክፍለ ህዝቦች በመልካም ስራቸውና በአርአያነታቸው በፍትህ አሰጣታቸውና

 

በአስተዋይነታቸው ተመስክሮላቸው ተመርጠው የሚወከሉ ታዋቂ ሰዎች ነው፡፡ የአመራረጣቸው መስፈርት ሰፋ ያሉ ጎሳዎች

 

ያማከለና ከዚህም ባለፈ አያት አባታቸው ለክፍለ ህዝቡም ሆነ ለጉራጌ የበረከቱት መልካም ተግባር መሰረት ያደረገም

 

ጭምር ነው፡፡

 

በየትኛውም የቕጫ ደረጃና አካባቢ የተወሰኑ ባህላዊ ውሳኔዎች ይግባኝ ሲጠየቅ የመጨረሻው ይግባኝ ሰሚው የጉራጌ

 

ባህላዊ ምክር ቤት ሲሆን በተለያዩ ክፍለ ህዝቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶች የደም ጉዳይ፣ የጉራጌ ጉዳዮችና ቕጫው ውስጥ

 

የሚያጋጥሙ የትርጉም ችግሮች ከሚነሱት ጉዳዮች ዋናውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ምክር ቤቱን በሁለት

 

የከፈለ የውሳኔ ሃሳብ ሲያጋጥም ጉዳዩ የቕጫ ምክር ቤት ሰብሳቢው በሚያሰይሟቸው ሽማግሌዎች አማካኝነት እንዲወሰን

 

ይደረጋል፡፡

 

የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ የቕጫ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሚሰየመው በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚደረገው

 

በምክር ቤቱ ስብሰባ ወቅት ከሚገኙት ሽማግሌዎች መካከል ጥበብና መስተዋል የሞላባቸው ነገር አዋቂ ሽማግሌ በማቅረብ

 

በሰብሳቢነት በአንድ ድምፅየሚመረጥ ሲሆን የመሪነት ዘመኑም የሚቆየው በተሰየመበት ወቅት በዋለው ሸንጎ የተነሱ ጉዳዮች

 

ተጠናቀው እልባት እስካገኙበት ጊዜ ድረስ ሲሆን አንዳንዴም ለረዥም ጊዜ እንደሚቀጥል ይታወቃል ይህም አሰራር ባህላዊ

 

ምክር ቤቱ በውስጡ ያሉትን ብልህና ነገር አዋቂ ሽማግሌዎችን አቅም በተገቢው መጠቀም እንዳስቻላቸው የቕጫ ምክር

 

ቤት አባላት ይገልፃሉ፡፡

 

 በጉራጌ ቕጫ /ባህላዊ ህግ/ የግድያ ወንጀል/ደም/ አጨራረስ ስርዓት

 

ጉራጌ በባህሉ የደም ብቀላ /መገዳደል/ የሚያስከትለው ጥፋት አደገኛ መሆኑና ዘርን እንደሚጨርስ ያምናል፡፡ ይጠየፋልም

 

ስለሆነም ግድያ እንዳይፈፀም ከፍተኛ የመከላከል ጥረት ያደርጋል፡፡ ግድያ ከተፈፀመም በርቸ ሆኖ እንዳይቀጥል /በትውልድ

 

እንዳይደጋገም/ ደም በቕጫ ስርዓት መሰረት እንዲያልቅ ይደረጋል፡፡ በቕጫ መሰረት እንዲያልቅ ካልተደረገ ግን

 

የሚያስከትለው መዘዝ መጥፎ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ስለሆነም ዕያንዳንዱ የደም ጉዳይ መንስኤውና አገዳደሉን መሰረት

 

13

 

በማድረግ በቕጫ ስርዓት እንዲያልቅ ይደረጋል፡፡ በዚህ መልክ በጉራጌ ቕጫ መሰረት የተወሰነውን ውሳኔ በመተግበር ወግ

 

የሚፈፅመውን ባህላዊ ሥርዓት ጨርሶ ካጠናቀቀ ደሙ በዚሁ ያልቅለታል፡፡ በገዳዩና በሟች ዘመዶች መሃል የነበረው

 

መፈላለግና ቁርሾ አብቅቶ ሠላም ወርዶ እንደማንኛውም ሰው ሠላማዊ ህይወት መምራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

 

በኧጆካ ቒጫ/በባህላዊ ህግ/ መሰረት የደም አይነቶች በሶስት ደረጃ የሚፈረጁ ሲሆን እነሱም፡-

 

 ሙራ ደም/የግፍ አገዳደል/

 

በጉራጌ ባህላዊ ህግ መሰረት ሰውን ሆን ብሎ በግፍ የገደለ በሙራ ደም ስርዓት ብር 30,000/ሰላሳ ሺህ ብር/ የደም ካሳ

 

እንዲከፍል የጉራጌ ባህላዊ ህግ/ቒጫ/ ይደነግጋል፡፡

 

 መዳራ/በስህተት የተፈፀመ/ ግድያ

 

መዳራ/በስህተት የተፈፀመ ግድያ ሲሆን ገዳይ ብር 15,000/አስራ አምስት ሺህ ብር/ የደም ካሳ ይከፍላል፡፡

 

 የመዳራ መዳራ/በፍፁም ስህተት የተፈፀመ ግድያ/

 

ግድያው የመዳራ መዳራ(በፍፁም ስህተት የተፈፀመ) ሲሆን ገዳይ ብር 7,500(ሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር) የደም ካሳ

 

ይከፍላል፡፡

 

1.2. የክስታኔና የወለኔ ቤተ-ጉራጌዎች ባህላዊ ሸንጎ(የጎርደና ሴራ)

 

የጎርደና ሴራ አፈፃፀም እንደ ጉዳዩ ባህሪና ደረጃ በተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት የሚከናወን ሲሆን የማህበራዊ ተቋማቱ

 

አደረጃጀትም፡-

 

 የአጥቢያ እድር /ሳቡኘት/

 

 የጥብ /የጎሳ/ ሴራ

 

 የሀገር ሴራ

 

 የወማኖ /የጉታቸ/ ሴራ

 

 የጎርደና ሴራ /ሸንጎ/

 

የአጥቢያ እድር /ሳቡኘት/

 

የአጥቢያ ዕድር /ሳቡኘት/ በጎርደና ሴራ መዋቅር ውስጥ በመንደር ደረጃ የሚቋቋም ትንሹ ተቋም ነው፡፡ በአንድ የክስታኔ

 

አካባቢ ውስጥ አያሌ ሳቡኘቶች ያሉ ሲሆን አባላቱ በመንደሩ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ሳቡኘት የሚመራው በሳቡኘት

 

ዳኛ ነው፡፡

 

የሳቡኘት ዋነኛ ዓላማ በአባላት ላይ የሚደርሱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ ለመረዳዳት ሲሆን በተጨማሪም

 

የአጥቢያ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለመለየት እንዲሁም የአገሬው ሴራ /ሸንጎ/ ውሳኔዎችን ለማስፈፀም ሳቡኘት ዋነኛ የጎርደና

 

ሴራ መዋቅር ነው፡፡ በየአመቱ መስቀል በአል በደመራ ማግስት የሳቡኘት አባላት በሙሉ ተሰብስበው በአመዱ ዙሪያ ቆመው

 

ቃልኪዳናቸውን ያድሳሉ፡፡ በእለቱ ያለ በቂ ምክንያት በቦታው የማይገኝ ወይንም በሌብነት የተሰማራ ግለሰብ‹‹አረሽ››

 

/ሰላቢ/ በማለት የመለየት ስራ ይሰራሉ ሌላው በሳቡኘት የሚታዩ ማህበራዊ ጉዳዮች የከብት ጥበቃ ሴራ፣ የእድር ሴራ፣

 

የለሊት የአካባቢ ጥበቃ /ዘብ/፣ክልክል ሀብቶች የማስከበር ስራ ሲሆን ከተቀመጠው የአካባቢ ሴራ ውጭ የሚንቀሳቀሱም

 

ሆነ ህጉን የሚተላለፉ አካሎች ለተቀመጠው ባህላዊ ሴራ /ህግ/ እንዲገዙ ሰፊ ክትትል በማድረግ የማስፈፀም ስራ ይሰራል፡፡

 

 

 

14

 

 

 

የጥብ/የጎሳ/ ሴራ

 

በጎርደና ሴራ የጥብ /ጎሳ/ በዝምድና ሃረግ ትስስር ላይ የተመሰረተ ብቸኛው የጎርደና ሴራ መዋቅር ነው የጥብ /የጎሳ/ ሸንጎ

 

አስተዳደራዊና ሶሺዮኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሸንጎው በጎሳው አባላት መሀከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የሚፈታ

 

ሲሆን ከሌሎች ጎሳዎች ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ዙሪያም ይመክራል፡፡ የጎሳ ሸንጎ አባላቱ ከስርቆት፣ ግድያና አካል ማጉደል

 

ወንጀሎች እንዲቆጠቡ አጠንክሮ ይሰራል፡፡ በአባቶች እንደሚነገረው ጥንት የታወቁ ወንጀለኞች /ሽፍቶች/ የጎሳውን ስም

 

አረከሳችሁ በማለት የራሳቸው ጎሳ አባላት አስረው ገደል አፋፍ ላይ በማድረስ ገደል ወርውረን እንግደልህ ወይስ ትታረማለህ

 

በማለት ለመመለስ ቃል የማይገቡትን ገደል ይጨምሯቸው እንደነበር ሲገለፅ ይህም የሚደረገው በጥቂት ወንጀለኛ ምክንያት

 

ከሌሎች ጎሳዎች ጋር መቃቃርና ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ሲባል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

 

የሀገር ሴራ

 

በክስታኔና በወለኔ ቤተ-ጉራጌ ውስጥ ሀገር የሚባሉ አካባቢዎች በተለያዩ መልክአ ምድራዊና ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች

 

ለምሳሌ ወንዞች፣ ኮረብታዎች፣ ለእርሻ በማይሆኑ መሬቶች ወዘተ… የተፈጠሩ ናቸው፡፡ የክስታኔና የወለኔ የሀገር ሴራ

 

አስተዳደራዊ ሶሺዮኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚያይ ሲሆን በዋነኛነት ወንጀለኞችን በተለይም ሌቦችን የሚቀጣ

 

የጎርደና ሴራ አካል ነው፡፡ የሀገር ሴራ የሸንጎ አባላት ከጎሰኝነት ነፃ የሆኑና በአካባቢው ታዋቂና የተከበሩ ሽማግሌዎች

 

ናቸው፡፡

 

ሸንጎው በወር አንድ ጊዜ በሚያደርገው ስብሰባ ወቅት በሌብነት የተጠረጠሩ ሰዎች ጉዳይ ይመለከታል፡፡ አንድ ሰው

 

በሌብነት ተጠርጥሮ ካለበት ሳቡኘት /አጥቢያ/ ተይዞ ለአገሬ ሴራ ሸንጎ ቀርቦ እንደጥፋተኛ ተቆጥሮ ቢቀጣ ጌፈቼ /ይግባኝ/

 

የመጠየቅ መብት አለው፡፡ ጌፈቼ ከሀገር ሸንጎ ውስጥ የሚዋቀር የይግባኝ ሰሚ አካል ነው፡፡ ጌፈቼ ከደም ጉዳይ ውጪ

 

በሌብነት በሌሎች ወንጀሎችና በማንኛውም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የበላይ ውሳኔ ሰጪ አካል ነው፡፡ የጌፈቼ አባላት ከሀገር

 

ሸንጎ ውስጥ እጅግ የታመኑ ጥቂት ነገር አዋቂ ሽማግሌዎች /ስናቻዎች/ ናቸው፡፡ ጌፈቼ የመጀመሪያ ደረጃ የሀገር ሸንጎ

 

ውሳኔዎችን በይግባኝ ሲያይ በተጨማሪም የሀገር ሸንጎ ለውሳኔ የተቸገረባቸው ነገሮች ለምሳሌ ተጠርጣሪው ወንጀለኛ

 

ለንፅህናው እንዲምሉለት ከመረጣቸው ሰዎች መሃል በከፊል ብቻ ቢምሉለት የነሱ መሃላ በቂ መሆን አለመሆኑን

 

ይመለከታል፡፡ ውሳኔም ይሰጥበታል፡፡

 

ጌፈቼ ጠያቂው ወገን ስነቻዎችን መምረጥ ይችላል፡፡ ይህም በፍርድ ሂደቱ ላይ አድልዎ እንዳይደረግበት ሲሆን ከመጀመሪያ

 

ፍርድ ሰጪዎች መሃል አንድ ሰው በአስረጂነት ይገኛል፡፡ የጌፈቼ ሰሚ ሽማግሌዎች የቀድሞ ዳኞች ውሳኔ ከአጠቃላይ

 

የጎርደና ሸንጎ ህግጋት የተጣጣመ መሆን አለመሆኑን በማጣራት የቀድሞውን ውሳኔ ያፀድቃሉ አሊያም ውድቅ ያደርጋሉ፡፡

 

የክስታኔና የወለኔ የሀገር ሴራ ማንም ለግል ይዞታነት የማያውለው የጎርደና ሞጨ እየተባለ የሚጠራ መንገድ፣ለአንዳንድ

 

ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲውሉ የሚቆረጡ ዛፎች ያለበት የጥብቅ ደን ስፍራዎች የጋራ የግጦሽ ስፍራዎችና ለቤተክርስቲያን

 

አገልግሎት ብቻ የሚውል መሬት ያካልላል፡፡ እነዚህን ይዞታዎች የሚያስተዳድር የሀገር ሸንጎው ሲሆን ማንም ለግል ጥቅም

 

ቢያውል ግለሰቡ በሳቡኘት /በአጥቢያ ሴራ/ ይቀጣል፡፡

 

የወማኖ /የጉታቸ/ ሴራ

 

የወማኖ /የጉታቻ/ ሴራ ከነፍስ ማጥፋት ወይም አካል ማጉደል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከፍተኛ ፍርድ ሰጪ አካል ነው፡፡

 

የወማኖ /የጉታቻ/ ሴራ ፍርድ ሰጪዎች በመላ ክስታኔና ወለኔ በነገር አዋቂነታቸው የሚታመንባቸው ዛሬ ኑረና ሃገር

 

15

 

የሚኖሩት የአምስቱ የገንዛደም ጎሳ ተወላጆች ናቸው፡፡ የወማኖ/ጉተቻ/ ፍርድ ሰጪዎች ስልጣን ከዘር ወደ ዘር የሚተላለፍ

 

ሲሆን ፍርዳቸውም በመላው ክስታኔ ተቀባይነት አለው፡፡

 

በወማኖ /ጉታቻ/ ሴራ አንድ ሰው የግድያ ወንጀል ቢፈፅም ላልተወሰነ ጊዜ አካባቢውን ለቆ መሰደድ ይኖርበታል፡፡

 

ቤተሰቡም ይበታተናሉ፡፡ ምክንያቱም በአካባቢው ከቆየና ቤተሰቡም ካልተበተነ ‹‹ደም አይደርቅም›› በሚል ስለሚታመንና

 

ገዳዩና ጎሳው ጡር ስለሚፈሩ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ የሚታወቁ ሽማግሌዎች ካህናትና ዲያቆናት ጋር

 

በመሆን በቀንበር ያልተጠመዱ ሰባት ልጃገረዶችና ጎረምሶች በማስከተል የቤተክርስቲያን መረዋ እየተደወለ ቃጭል

 

እየተቃጨለ ወደ ሟች ቤተ ዘመዶች በመሄድ ከተደጋጋሚ ልመና በኋላ ለእርቁ የእሺታ መልሳቸውን ይሰጣሉ፡፡

 

የእርቅ ስነ-ስርአት የሚከናወነው በአገሬ ሸንጎ በሚመረጡና የሁለቱን ወገን ስምምነት ባገኙ የአገሬው ሽማግሌዎች ነው፡፡

 

የአገሬው ሸንጎ ግድያው ድንገተኛ ወይም ሳይታሰብ የተፈጠረ /የሳቸ/ መሆኑን አሊያም በቂም በቀል መሆን አለመሆኑን

 

አጣርቶ በገዳይ ወገን የሚከፈል የደም ካሳ /ጉማ/ በመወሰን የእርቅ ስርዓት እንዲፈፀም ያደርጋሉ፡፡ የእርቁ ስነ-ስርዓት

 

ከመፈፀሙ በፊት የሟችና የገዳይ ወገኖች ከጥቂት የአገሬው ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ወደ ወማኖ /ጉታቻ/ ፍርድ ሰጪዎች

 

በመሄድ ውሳኔው የፀና ይሆናል፡፡

 

የእርቁ ስነ-ስርዓት በሁለቱም ወገኖች ቤት ውስጥ በየተራ የሚፈፀም ሲሆን ገዳይ ከስደት ኑሮ ተመልሶ እንዲገባ

 

ይፈቀድለታል፡፡ የማስታረቁን ስነ-ስርዓት የሚያስፈፅሙት የማሊማ ጎሳ አባላት ናቸው፡፡ የዚህ ጎሳ አባላት ከማስታረቅ ስነ-

 

ስርዓቱ በተጨማሪ የጉዳ ስነ-ስርዓት የሚያስፈፅሙ ናቸው፡፡

 

የእርቅ ስነ-ስርዓት ከተከናወነ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ፍፁም ቂም እንዳይዙ ጉዳ መፈፀም የተለመደ ሲሆን በጉዳው ስነ-ስርዓት

 

ላይ ጥቁር ፍየል ታርዶ ከሁለቱም ወገኖች አንዳንድ ሰዎች ተመርጠው አውራ ጣቶቻቸው በፍየሉ አንጀት ታስሮ

 

ይቋጠራል፡፡ ይህም ጉዳ የተያያዙ ሰዎች የጠላትንት ስሜትን አስወግደው በመሃላቸው ሰላም ያሰፍናል ተብሎ ስለሚታመን

 

ነው፡፡

 

 የጎርደና ሴራ /ሸንጎ/

 

የጎርደና ሸንጎ የተወሰነ ወቅትና ቋሚ ቦታ የለውም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከክስታኔና ከወለኔ ቤተ-ጉራጌ በሚመረጡ

 

ስነቻዎች /ነገር አዋቂ ሽማግሌዎች/ በተመረጠ ስፍራ ላይ ይካሄዳል፡፡ በአጠቃላይ የጎርደና ሸንጎ ከሚጠራባቸው

 

አጋጣሚዎች መሃል ዋነኛው በሌላ ብሄረሰብ የሚሰነዘር ጥቃት በሚኖርበት ጊዜ የሌሎችም ቤተ-ጉራጌዎች ህብረት

 

ለማቋቋም የሚሰበሰበው ሸንጎ ዋነኛው ነው፡፡

 

1.3. የመስቃን ቤተ-ጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ/የፈራገዘኘ ሴራ/

 

የመስቃን ቤተ-ጉራጌ ማህበረሰብ ባህላዊ አስተዳደር ስያሜ ‹‹የሲናኖሴራ›› ይባላል አንድ ሰው ጥፋት በሚያጠፋበት ጊዜ

 

በዚህ ሴራ አማካኝነት በአካባቢው ሽማገሌዎች ማለትም ‹‹በማጋዎች›› ጉዳዩ ታይቶ የፍርድ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ምናልባት

 

ደግሞ ጉዳያቸው ከማጋዎች በላይ ከሆነ ወደ በላይ ዳኞች እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ እነዚህም ‹‹ራጋዎቹ›› ይባላሉ፡፡ ራጋዎች

 

የመጨረሻ ፍርድ ሰጪ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ራጋዎች የሼህ ዑስማን አስረኛው ትውልድ ላይ ያሉ ሲሆኑ

 

የሚኖሩትም ፈራገዘኘ ነው፡፡

 

በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ /ጎሳዎች/ የነዚህ ትውልድ ሃረጎች ናቸው፡፡ ፍርድ ሰጪዎችም ከጎሳው መሃከል የተመረጡ

 

ሶስት አንጋፋ ራጋዎች ሲሆኑ ፍርድ የሚሰጡት በጎሳው መሃከል ተቀምጠው ነው፡፡ እነሱጋ ፍርድ የሚሰጠው ጥፋተኞቹ

 

በአካባቢያቸው በተመረጡ የጉዳ ሽማግሌዎች ጉዳያቸው አልቆ በመጨረሻ በጉዳ ዳኛቸው አማካኝነት ተያይዘው ከመጡ

 

16

 

በኋላ ነው፡፡ እነሱን የሚዳኙ ሰዎች ፍርድ የሚሰጡት እነሱ ባሉበት ፈራገዘኘ መንደር ካልሆነ በስተቀር በምንም አይነት ሌላ

 

ቦታ ተቀምጠው አይወስኑም ለምሳሌ፡- አንድ ሰው የሌላ ሰው ህይወት አውቆም ሆነ ሳያውቅ ቢያጠፋ ከነበረበት መንደር

 

ይሰወራል፡፡ ቤተሰብም ካለው ዘመድ ወዳለበት ስፍራ መንደራቸውን ለቀው ይሄዳሉ በመጨረሻግን ገዳዩ ደም

 

እነዲያልቅለት በመጀመሪያ በአካባቢ ሽማግሌዎች /ማጋ/ እንዲጨረስ ይደረጋል፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ሁለቱም የጉዳ

 

ሽማግሌዎች ይይዛሉ፡፡ የጉዳ ሽማግሌ የሚያስፈልግበት ምክንያት ሁለቱም ወገኖች በተንኮል እንዳይፈላለጉና ቃልኪዳን

 

ማክበራቸውን ይቆጣጠራል፡፡ ምናልባት መሃላው ፈርሶ ድርጊቱ ተፈፅሞ ቢገኝ በራሱም ሆነ በልጅ ልጆቹ ላይ ጥፋት

 

ስለሚደርስ በባህሉ ረገድ በጣም ይፈራል ለጊዜው የመሃላው ተፈፃሚነት ቢዘገይም ከአንድና ከሁለት ትውልድ በኋላ

 

ሊደርስ ስለሚችል ተሳስቶም ቢሆን ላድርግ ቢል ጥሩ አይሆንለትም ገዳዩ ቢኖርም ባይኖርም አባት የልጁን ሀጢያት በእርቅ

 

ማውጣት አለበትማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መሃላው ቤተሰብን ጭምር ስለሚመለከት ነው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ራጋዎች

 

ያገዳደሉን ሁኔታ በደንብ ካጠኑ በኋላ ለተገደለበት አባትና እናትቡሉኮ፣የወተት ላም፣ወይፈን… ወዘተ ይሰጥ ይባላል፡፡ ይህም

 

‹‹ወርከፈና›› ይሉታል፡፡ ወርከፈና ማለት ካሳ ነው ይህ ሁሉ ከተከናወነ በኋላ የገንዘብ ደም ካሳ ወይም ጉማ እንዲከፈል

 

ይደረጋል ገዳይ የመክፈል አቅም ቢኖረውም ከኪሱ አውጥቶ ብቻውን መክፈል የለበትም የግድ የእናቱና የአባቱ ወገኖች

 

ባሉበት ቦታ ፈልጎ እየዞረ እርዳታ ጠይቆ ካልሞላለትም ከራሱ ጨምሮ ይከፍላል እግረ መንገዱንም በእጁ የሰው ህይወት

 

ስለማጥፋቱ ራሱን ማጋለጡ ነው፡፡

 

ስለዚህ እንደዚህ ካላደረገ ደም አልወጣም ወይም ከሃጢያት አልነዓም ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከተከናወኑ በኋላ

 

ሟች ቤት የገዳዩ ቤተሰቦችና የተገደለባቸው ቤተሰቦች የጉዳ ዳኛ ፊት እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ዓይናቸው በነጠላ

 

ይሸፈኑና የእግር አውራ ጣታቸውን ያቀብላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ጥቁር ፍየል ታርዶ አንጀቱን በማውጣት ዙርያ ቀለበት ሰርተው

 

እንዲታሰሩ ከተደረገ በኋላ የጉዳ ዳኛው የታሰረውን አንጀት ተራበተራ ሲቆርጥ እንደዚህ ይቁረጠኝ ብላችሁ ማሉ ብሎ

 

ያስምላቸዋል የተቆረጠው አንጀት ተሰብስቦ እንዲቀበር ይደረጋል ይህም ሁለተኛ መሃላውን አፍርሼ ብገኝ እንደዚህ ልቀበር

 

ማለታቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከተከናወነ በኋላ አንዱ የገዳይ ቤተሰብ የሆነች ሴት በሳህን ወተት አድርጋ በእርጥብ ሳር

 

እየነከረች ከውጭ ጀምራ በመርጨት እገዳዩ ቤት ትገባለች የተገደለበትም ቤተሰብ የሆነች እንደዚሁ እያደረገች ትገባለች

 

ይህም ማለት ሰላም ሰፍኖ እርቅ ወርዷል ማለት ነው ቀጥሎ ያለው ማሳረጊያ እንግዲህ የሁለቱም ቤተሰቦች በመሰባሰብ

 

ከብት ይታረድና ፈንጠዝያ ይሆናል እርቅ ወርዶ አንድ ማእድ ላይ ተሰብስበው ከበሉ ቤተሰብ ሆኑ ማለት ነው፡፡

 

እንዲያውም ከመቀራረባቸው የተነሳ አይጋቡም፡፡

 

1.4. የዶቢ ቤተ-ጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ /የስናኖ ሴራ/

 

የዶቢ ህዝብ እንደሌሎቹ ቤተ-ጉራጌ ህዝቦች ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንብ ያለው ሲሆን ይህ ደንብ ‹‹የዶቢ ጎጎት ሴራ›› ተብሎ

 

ይጠራል፡፡ ሆኖም የሰባት ጎጎት ክፍል የሆነው ህዝብ የሚተዳደረው በመስቃኑ የስናኖ ሴራ ነው፡፡ የዶቢ ጎጎትም ሆነ የሰባት

 

ጎጎት የስናኖ ሴራዎች /ደንቦች/ ጉባኤ ማከናወኛ በየአካባቢያቸው የተመረጡ አማካኝ ስፍራዎች ቢኖሩዋቸውም የይግባኝ

 

አደባባያቸው ወይም የሴራዎቹ / ደንቦቹ/ ከፍተኛ ጉዳዮች የሚታይባቸው ስፍራ የመስቃኑ ‹‹ፈራገዘኘ›› በመባል

 

የሚታወቀው ባህላዊ የፍርድ አደባባይ ነው፡፡ ፈራገዘኘ የሁለቱ ቤተ-ጉራጌዎች /የመስቃንና የዶቢ ከፍተኛ ባህላዊ ፍርዶችና

 

ውሳኔዎች የሚፀኑበት ችሎት ነው፡፡

 

ይህ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ /ሴራ/ የእርስ በእርስ ግጭትና ጥል የሚገታ አንዱ ሀይሉንና ወገኑን ተመክቶደካማውንና

 

ባይተዋሩን እንዳይጎዳ የሚከላከል፣አንዱ በሌላው ግፍና በደል እንዳያደርስ የሚገድብ በአጠቃላይ ህዝብ በመፈቃቀር

 

በመከባበር በመቻቸል እንዲኖር የማስቻል ሀይል የነበረውና አሁንም በማገልገል ላይ እንዳለ ለዚህ ጥናት በመረጃ አሰባሰብ

 

ሂደት የተሳተፉት ሽማግሌዎችና የባህላዊ ደንብ አስፈፃሚዎች አስረድተዋል፡፡

 

17

 

በዶቢ ህዝብ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ከፍተኛ ጉዳዮችን የሚዳኙ ውሳኔዎችን የሚያፀኑና የሚያስፈፅሙ ‹‹ራጋ›› በመባል

 

ሲታወቁ በህዝብ ዘንድ በባህላዊ አስተዳደራቸው የተመሰገኑ አክብሮትን ያተረፉ አረጋውያን ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ቀደም

 

ሲል ጀምሮ እስካሁን ህዝቡ በባህላዊ ደንቦችና ድንጋጌዎች ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የጎሳ መሪዎችን ይመረጥ ነበር፡፡

 

አሁንም እየመረጡ ነው፡፡ እነዚህ የሚመረጡ እጩ የጎሳ መሪዎች በዶቢ ዘዬ ‹‹ወዳቦ›› ተብሎ ሲጠሩ ከዕጩነት አልፈው

 

አመራሩን ሲረከቡ ‹‹አበጋዝ›› ወይም ‹‹አዝማች›› ተብሎ ይጠራሉ፡፡ የአንድ አበጋዝ ወይም አዝማች የስልጣን ዘመን ሁለት

 

አመት ብቻ ነው፡፡ ይህ የአበጋዝነት /የአዝማችነት/ ስልጣን እንደ ምእራቡ ቤተ-ጉራጌ የጎሳ መሪዎች የጎንደር ንጉስ/አዝማች/

 

የዘር ሀረግን እየተከተለ የሚተላለፍ ሳይሆን በአመራር ችሎታና በህዝብ ዘንድ ያለው ተደማጭነት እየታየ ለሚመረጥ

 

የማንኛውም ጎሳ አባል የሚሰጥ ስልጣን ነው፡፡ የጎሳው መሪ /አዝማቹ/ ሁለት አመት ካገለገለ በኋላ የማእረግ ስሙን /አበጋዝ

 

ወይም አዝማች/ የሚለውን መጠሪያውን ብቻ በመያዝ ስልጣኑን ለባለ ተረኛው እጩ /ወዳቦ/ ያስረክባል፡፡

 

2. የኧጆካ ማዕከል አመሰራረት

 

በምዕራብ በኩል ያለው ቤተ ጉራጌ የሚተዳደርበት የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ የኧጆካ ቕጫ ይባላል፡፡ ይህ መተዳደሪያ

 

ደንብ አሃዱ ተብሎ የተመሰረተበትና የፀደቀበት ሥፍራ ኧጆካ በመባል ይታወቃል፡፡ የመተዳደሪያ ደምቡም ስያሜውን

 

ያገኘው ከዚህ እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡

 

የኧጆካ ቕጫ ከመመስረቱ በፊት ጉራጌ ይተዳደር የነበረው በአካባቢው በነበሩት የተሸለ አቅም በነበራቸው ግለሰቦች፣

 

ሀይለኞች ወይም ቤተሰባዊ አቋማቸው ጠንካራና በህዝቡ ተደማጭ በሆኑ ቡድኖች እንደነበረ በርካታ ማስረጃዎች ይቀርባሉ

 

በዘመኑ በነበሩት ጉልበተኞች ወይም ሀይለኞች በሚደርስ በደል በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ጉዳት ላይ ወድቀዋል፣

 

ልጆቻቸው ተሽጠዋል፣ሚስቶቻቸው ተቀምተዋል ቤቶቻቸው ተቃጥለዋል፣አቅመ ደካሞች መሬት ተነጥቀዋል፣

 

ልጃገረዶቻቸው ተደፍረዋል፣ንብረት ተዘርፈዋል፣ ያረቡትንም ላም ተቀምተዋል በአጠቃላይ አቅመ ደካሞቹ በእነዚህ

 

ሀይለኞችና ጉልበተኞች እጅግ መጠነ ሰፊ የሆነ አስከፊ በደል ተፈፅሞባቸዋል፡፡

 

ሀይለኞች ወይም ጉልበተኞች በህዝቡ ላይ የሚያደርሱት በደል እጅግ እየከፋ ሲመጣ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የብሔረሰቡ

 

አካሎችና በደሉ ያረፈባቸው ቡድኖች በጋራ ሆነው ፎረፎረማት የተባለ ቅጠል በመልበስ አደባባይ በመውጣት

 

ጩኸታቸውን ለእግዚአብሔርና የህዝቡን በደል ለሚጠየፉ የአገር ሽማግሌዎች በለቅሶ ማሰማት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ

 

በህዝቡ ላይ ሲደርስ የነበረው በደል ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም እንዳሳዘነ የተረዱና የህዝቡን ጥቃት ያስቆጣቸው

 

ስመ ጥር ግለሰቦች እርስ በእርስ መልዕክት በመለዋወጥ መገናኘት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ግንኙነት እያደር

 

እየዋለ አድማሱ እየሰፋ ወደ 5ቱ ቤተ-ጉራጌዎች በመዛመቱ በጉዳዩ ላይ ለመምከርና ቋሚ የሆነ የመገናኛ ስፍራ ሲታሰብ

 

የኧጆካ የተባለው አካባቢ ሁሉንም ለማገናኘት ማዕከላዊ ስፍራ ሆኖ ሊመረጥ እንደቻለ ይነገራል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኧጆካ

 

በቋሚነት የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ቋሚ የመሰብሰቢያ ቦታ እንዲሆን ይወሰናል፡፡

 

አምስቱ ቤተ-ጉራጌዎች የኧጆካ ቋሚ የመሰብሰቢያ ቦታ እንዲሆን ከወሰነ በኋላ ቀጣይ የመነጋገሪያ ርዕስ የነበረው

 

የኧጆካቕጫ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ማውጣት ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት ተደጋጋሚ ውይይቶች ተካሂደው ሲያበቁ

 

በመጨረሻ የኧጆካቕጫ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ሆኖ ይፀድቃል፡፡ ቒጫ በሌላ የጉራግኛ ቃል ሲገለጥ አንቅ ወይም የጜታ

 

ትከ ማለት ሲሆን በአማርኛው እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥበት ስርዓት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ምናልባት አንባቢው ስለ እውነተኛ

 

ፍርድ ሲነሳ በዚያ ሀይማኖቶች ባልተስፋፉበትና ሰው የሀይማኖት ትምህርት ባልተማረበት ዘመን እውነተኛ የፍርድ

 

አስተሳሰብ ከየት መጣ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርበት እንደሚችል ይታሰባል፡፡ ዳሩ ግን ሀይማኖቶች ባልተስፋፉበት ዘመንም

 

ቢሆን እያንዳንዱ ሰው ሲወለድ ጀምሮ ህገ-እግዚአብሔር በልቦናው ስለሚታተም ጥሩና መጥፎውን ለመለየት የሚያስችል

 

የተፈጥሮ ፀጋ ተሰጥቶታል የኧጆካ ቒጫ የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ ሆኖ እስከ ዛሬ እንዲቀጥል ካስቻሉት

 

18

 

ምክንያቶች ትልቁና ዋናው ምንም እንኳ በኧጆካ ቂጫ ላይ በቃለ እግዚአብሔር የሰፈሩት አስርቱ ትዕዛዛት ተጽፈው ለንባብ

 

ባይቀርቡም እያንዳንዱ ሽማግሌ የቂጫ ደንብ ሲያወጣ በልቦናው የታተመው ህገ-እግዚአብሔር ላይ መመስረቱ ነበር፡፡

 

በዚህ ሁኔታ ከየጉራጌው የተውጣጡ አዋቂ ሽማግሌዎች የኧጆካ ማእከል ላይ በመሰብሰብ የህዝቡን አቤቱታዎች በማድመጥ

 

በቂጫ መሰረት ይዳኙ /ፍርድ ይሰጡ/ነበር፡፡

 

የኧጆካ ባህላዊ ሸንጎ በህዝቡ ላይ ሲደርሱ የነበሩ በደሎች እንዲቆሙና የእርስ በእርስ የድንበር ግጭቶችና ማህበራዊ

 

ችግሮችን የእኔ ልግዛ እኔ ልግዛ ሽኩቻዎችን እያስቆመ በጉራጌዎች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት እያገኘ ሲመጣ በመጀመሪያው

 

ዙር ጥሪውን ሰምተው ያልተቀላቀሉ ቤተ-ጉራጌዎች ወደ የኧጆካ መድረክ በመምጣታቸው የምዕራቡ ጉራጌ ከ5 ቤት ወደ

 

ሰባት ቤት እንዳደገ የቀደሙ አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ከተደጋጋሚ የኧጆካ ስብሰባዎች በኋላ ነበር ከየስፍራው የመጡት ሰዎች

 

የመጡበት አቅጣጫ ሲናገሩ ወደ ሰባት ስለደረሱ የምዕራቡ ጉራጌ ሰባት ቤት ጉራጌ የተባለውና እስከ ዛሬም መጠሪያው

 

የሆነው፡፡

 

ሌላው ጎይታ ጀኘወ የተባለ የጊዜው ጀግና ሀይለኞች በህዝቡ ላይ የሚያደርሱት በደል አይቶ የኧጆካ በመሄድ ለመጀመሪያ

 

ጊዜ እሳት አቀጣጥሎ ጭስ እንዳጬሰና ከተለያየ ቦታ ሰዎች ጭሱን ተከትለው ወደ ስፍራው እንደተሰባሰቡ ይነገራል፡፡

 

የተሰበሰበውም ህዝብ እንደዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ያነሳው በወገናችን ላይ የሚደርሰው ግፍ ያብቃ፣ጉልበተኛ ደካሞችን

 

መግፋቱን ይተው፣የድንበር ውጊያ ይቁም/ኸተራት/ ይሁን በማለት ያሳስባል፡፡ ተሰብሳቢው ጜይታ ጀፕወ ባቀረበው ሀሳብ

 

ላይ በስፋት ከመከረ በኋላ ቀጠሮ በመያዝ በመጀመሪያው ሸንጎ ያልተሳተፉ ታዋቂ ሰዎች ጥሪው እንዲደርሳቸው እንዳደረጉና

 

ይሄው መልካም ጅምር እየተጠናከረ ሄዶ ኧጆካ የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ መሰብሰቢያ ማዕከል ሆኖ እንደቀረ በቀደሙት

 

የብሔረሰቡ አባቶች አንደበት ይነገራል፡፡ ኧጆካ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓታችን የተመሰረተበት ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ የኧጆካ

 

ሸንጎ ባህላዊ ዳኞች ተጠራርተው በመሰብሰብ መተዳደሪያ ደንብ ያወጡበት ነበር፡፡ ከተለያዩ ቤተ-ጉራጌዎች/ወረዳዎች/

 

የሚመጡ የፍርድ ሂደቶች ይግባኝ ሰሚ የኧጆካ ሸንጎ እንደነበር ይታወቃል በቅርብ ዘመን ከመንገድ ስራ ጋር ተያይዞ

 

የሸንጎው መቀመጫ ሟጨ እንዲሆን ተደርጎ የነበረ ሲሆን አሁን እምድብር ከተማ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም የሆነው

 

ከተለያዩ ቤተ-ጉራጌ አካባቢዎች የሚመጡ የኧጆካ ሸንጎ አካላት የመስተንግዶ አገልግሎት እንዲያገኙና ለትራንስፖርት

 

ምቹነት ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡

 

ሌላው ሁለተኛው ኧጆካ የባህላዊ ዳኝነት ማዕከል ሆኖ ከመመረጡ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው ነገር በቀደሙት የብሔሩ

 

አባቶች የሚነሱ በርካታ አብነቶች አሉ፡፡ በዘመኑ ምሳኮ የሚባል አንድ አዋቂ ጉዳ፣አንቂትና በርቸ ይዞ ብዙ ቦታ ሲመላለስ

 

የሚቀመጥበት ስፍራ ያጣል ምክንያቱም ይዟቸው የሚንቀሳቀሰው "ጉዳ"፣"አንቂትና"፣"በርቸ" በብሔሩ ስለሚፈሩና በጣም

 

ትልቅ ግምት ስለሚሰጣቸው ማንም እኔጋ ገብተህ እረፍ የሚለው ሰው ያጣል፡፡

 

ይኸው የእኖር ተወላጅ የሆነው ምሳኮ ከቤተ-ጉራጌ ቤተ-ጉራጌ ሲዘዋወር አንድ ቦታ ላይ ጡር ያገኘዋል፡፡ ከዚያም ጡር

 

ሞሳኮን እባክህ እኔን መሸከም የሚችል ጥሩ ታጋሽ ሰው ፈልግልኝ ይለዋል፡፡ ምሳኮም ተው ትዋሸኛለህ ይለዋል ጡርም

 

አልዋሸህም ይለዋል፡፡ ሞሳኮም እሺ ሰው እገኛለሁ ብሎ ድፍን ሰባት ቤተ-ጉራጌ በመዞር ሰው ፈልጎ ሳያገኝ ይቀራል፡፡

 

በኋላም ቀጠሮ ይደርስና በተነጋገሩበት ቦታ ለይ ይገናኛሉ፡፡ ምሳኮም ጡርን የሚቀበል ሰው ፈልጎ ባለማግኘቱ ተሸክሞ

 

የኧጆካ ይወስደዋል፡፡ እዛው የኧጆካ ያስቀምጠውና ከቸሃ ዋቅ በቀር አንተን የሚሸከም የለም ይለዋል፡፡ ጡርን ተሸክመው

 

እንዲያኖሩ ያነጋገራቸው የሰባት ቤት ሰዎች እሺ ብለውት ቃል ገብቶላቸው የነበረ ቢሆንም በእርሱ አስተሳሰብ ጡርን

 

የሚሸከሙበት ትዕግስት የላቸውም ብሎ በማሰቡ ነበር ጡርን የቸሃ ዋቅ ባለበት የጆካ ያኖረው፡፡ ቃል የገባላቸውም ሰዎች

 

ሲጠይቁት ከእናንተ ለተሻለ ለቸሃ ዋቅ ሰጥቼዋለሁ ይላቸዋል፡፡ ይህም የኧጆካ የባህላዊ ሸንጎ ማእከል ሆኖ እንዲመረጥ አንድ

 

ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡

 

19

 

የኧጆካ ሸንጎ ዝና እጀግ በናኘበት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀድሞ ሸንጎው ዳኝነት ሳይሰጣቸው በየቤተ-ጉራጌው

 

መንፈሳዊና ማህበራዊ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎችን ወደ ሸንጎ በማስጠራት ለተለያዩ አካላት ሹመት በማፅደቅ እያንዳንዱ

 

ተሿሚ ሹመቱን ለጆካ ሸንጎ ቕጫ ተፈፃሚነት እንዲያውለው ቃል በማስገባት ይሸኛቸዋል፡፡

 

ሹመቶቹም፡-

 

1ኛ. የዥር ዳነ፣

 

2ኛ. የአንቂት ዳነ፣

 

3ኛ. የጉርዳ ዳነ፣

 

4ኛ. የቕጫ ዳነ፣

 

5ኛ. የተየ ዳነ፣

 

6ኛ. የወግ ምስ፣

 

7ኛ. የሳምር ዳነ፣

 

8ኛ. የኦገፐቻ ደማም፣

 

9ኛ. የዋይ ደማም

 

 10ኛ. ይናጋራ ደማም ሲሆኑ የነኚህ የዳኝነት አካላት ሁሉ ጉራጌ በኧጆካ ሸንጎ የሰጣቸውን ባህላዊ ስልጣን ህዝባቸውን

 

በማክበርና እግዚአብሔርን በመፍራት የኧጆካ ሸንጎ ማስፈፀሚያ መሳሪያነታቸው በተግባር በማረጋገጥ ትውልድ እየተፈራረቀ

 

ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

 

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ