Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 174

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 176

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 216

Notice: Undefined index: title in /home/hawassao/public_html/subpage_articles.php on line 218

ሱስ ስንል ማንኛውም ነገር በሰዎች ላይ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት ስ??

ሱሰኝነትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

 

ሱሰኝነትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

 

ሱስ ስንል ማንኛውም ነገር በሰዎች ላይ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት ስሜት በመፍጠር ሰዎች ለመነቃቃት ፤ ድብርትን ለማስወገድ ፤ ጀብዱ ለመስራት፤ ህመምን ለማስታገስና ከፍተኛ የደስታ (Euphoria) ስሜትን ለመጎናጸፍ ብለው የሚያጨሷቸው፤ የሚቅሟቸው በአፍንጫ የሚስቧቸውንና በደም ስር የሚወስዷቸውን ነገሮች በሙሉ ሲያካትት ያለ እነኚህ ሱሶች/ዕፆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴአቸውን ማከናወን ሲሳናቸው ሱስ ወይም የሱሰኝነት ጠባይ እንዳለባቸው ይገለጻል፡፡

ሰዎች ምንም እንኳን ሱስ የሚያሲዙ ነገሮችን በመጀመሪያዎቹ አካባቢ በራሳቸው ተነሳሽነት የሚወስዱና የሚጠቀሙ ቢሆንም እየዋለ ሲያድር ግን በሚያስከትለው ጥገኝነት ሱስ የሚያሲዙ ንጥረ ነገሮችንና አደንዛዥ ዕጾችን መጠቀም የግድ እየሆነ ይመጣባቸዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ በሱስ መጠመድና ተጋላጭ መሆን የአእምሮ ጉዳት ፤ የማስታወስ ክህሎት ማሽቆልቆል ፤ ተስፋ መቁረጥ ፤ እራስን መቆጣጠር አለመቻልና ሌሎች ተጓዳኝ የአካልና የስነ-ልቦና ቀውሶችንና ብሎም ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሱስና በአደንዛዥ ዕፅ ጥገኝነት የሚመጡት የጤና እክሎች በሱስ የተጠመዱ ሰዎች ሱሰኝነትን ማቆም እንዳልቻሉ የሚያመለክቱ ሲሆን ይህንን የጤና እክል ለማስወገድ የሚደረገው ህክምና አካልና አእምሮን ከሱስ ከማጽዳት አንጻር ትልቅ ጥረትና ክትትልን ይጠይቃል፡፡ ሱስና አደንዛዥ ዕፅ በሰዎች አካል ፤ አእምሮና ስነ-ልቦና ላይ ትልቅ ተጽእኖ ስለሚኖረው የሚሰጠው ዕርዳታና ህክምና በሱስ ምክንያት የተከሰቱ አሉታዊ ተጽእኖዎችን በሙሉ ያካተተ መሆን እንዳለበት ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በማስከተል ሱሰኝነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን እንመለከታለን፡፡

 

የመድኃኒት ህክምና

 

በአደንዛዥ ዕፅና ነጥረ ነገሮች ሱስ የተያዙ ሰዎች ሱሰኝነትን እንዲያቆሙና ከሱስ የጸዳ ህይወት እንዲመሩ ለማስቻል ከሚሰጡ ዕርዳታዎች መካከል አንዱ የመድኃኒት ህክምና ሲሆን ይህም የተለያዩ መድኃኒቶቸን በመጠቀም በሱስ የተያዙ ሰዎች ሰውነት ውስጥ የተከማቹትን መርዛማ ኬሚካሎችን ማስወገድን ያካትታል፡፡ ከሱሰኝነት ጋር በተያያዘ አብዛኛውን ጊዜ የመድኃኒት ህክምናዎች ለብቻቸው ዘላቂ መፍትሄ የመስጠት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡

 

ስነ-ልቦናዊ ህክምና (Psychotherapy)

 

ሰዎች ሱስና ሱሰኝነትን ከሚያሲዙ ድርጊቶች እንዲላቀቁ የስነ-ልቦና ህክምና ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ከሱስ አካላዊ ጥገኝነት ይልቅ ስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት ስለሚበልጥ ሰዎች በመጀመሪያ ከሱስ ነጻ መውጣት እንደሚችሉ እራሳቸውን ማሳመን ካልቻሉ ሌሎች የሚደረጉ ህክምናዎችና ዕርዳታዎች ውጤታማ መሆን አይችሉም፡፡ ማንኛውም ለውጥ ከአእምሮ ይጀምራል እንደሚባለው በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች በምክር አገልግሎት ሰጪ ባለሙያ(counselor) በመታገዝ ከሱስ ለመውጣት ስነ-ልቦናዊና አእምሮአዊ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰዎች የመንፈስ ጥንካሬ አእምሯቸውን ለማዘዝ የሚያስችል አቅም ሲሰጣቸው በአንጻሩ የአልችልም ባይነትን ስነ-ልቦና ከተላበሱ አእምሮአቸው ያለመቻልን ስሜት በውስጣቸው ይዘው እንዲዘልቁ ያስገድዳቸዋል፡፡ ስለዚህ ስነ-ልቦናዊ ህክምና በሱስ የተያዙ ሰዎችን ስነ-ልቦና በማጠንከር የሱስ ጥገኝነትን ለማስወገድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡

 

መጠንን መቀነስ (Reducing dosage)

 

በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሱሰኝነትን ቀስ በቀስ ወይም በሂደት ለመተው እንዲችሉ የሚወስዱትን ሱስ የሚያሲዙ ነገሮችን መጠን መቀነስ ይኖርባቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ሱሰኝነትን ለመተው ያስቡና ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማቆም ይሞክራሉ፡፡ ይህ እርምጃ ምንአልባት ለአንድና ለሁለት ቀን ያገለግል እንደሆን እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሄን ማምጣት አይችልም፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱሰኝነት በሰውነት አካል ውስጥ በደንብ የተሰራጨ ከሆነ በአንድ ጊዜ ለመተው ማሰብ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ ስለዚህ ሱሰኝነትን በአንድ ጊዜ ወይም በቅጽበት ለመተው ከማሰብ ይልቅ መጠንን እየቀነሱ ለዘለቄታው እስከመተው መድረስን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሌሎች አማራጮችን መጠቀም

ሱሰኝነት በሰዎች አካላት ውስጥ አንዴ ከተሰራጨ መጠንን በመቀነስ ብቻ በቀላሉ ማስይወገድ ስለማይቻል መጠንን በመቀነስ ለመተው በሚደረገው ጥረት ከዚህ ቀደም ሰውነት የተላመደውን መጠን መጠቀም ስለሚፈልግ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ሱሰኝነትን በአወንታዊ መልኩ በትክክል የሚተካው ባይኖርም ሱሰኝነትን ለመተው በሚደረገው ጥረት የሚከሰቱትን (withdrawal symptoms) እንደ ድብት ፤ ማቅለሽለሽ ፤ ትኩረት ማጣት፤ ራስ ምታት ፤ አለመረጋጋት ፤ የእንቅልፍ ሰዓት መዛባትና እንቅልፍ ማጣትን ለማስተካከል የማነቃቃት ባህርያ ያላቸውን ትኩስ ነገሮችን መውሰድ ፤ ማስቲካ ማኘክና እንደየአስፈላጊነቱ በተደጋጋሚ ጸጉርን መታጠብ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

 

ውጫዊ ተጽንኦዎችን መቋቋም

ሱሰኝነት በተለያዩ ውጫዊ ተጽእኖዎች ሊባባስ ይችላል፡፡ እነዚህን ተጽእኖዎች ለመቋቋም ሱስ ከሚያሲዙ አካባቢዎች መራቅ አንዱ መፍትሄ ሲሆን ይህ የማይቻል ከሆነ ዳግመኛ በሱስ ተጽእኖ ስር ላለመውደቅ አመለካከትን መቀየር ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ ሱሰኝነትን ለማስወገድ የሚደረጉ ዕርዳታዎች ሰዎች ከአካላዊና ስነ-ልቦናዊ የሱስ ጥገኝነት ተላቀው ጤናማ ህይወት እንዲኖሩ ማስቻል ነው፡፡ በሱስ ለተያዙ ሰዎች ከሌሎች የሚደረግላቸውን እንክብካቤና ድጋፍ ማስተናገድ ቀላል ቢሆንም ከሌሎች ዕርዳታ ተላቀው እራሳቸውን ከሱሰኝነት ለማላቀቅ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ትልቅ ተግዳሮት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም ከሱስ የሚያገግሙ ሰዎች የሱስን አካላዊ ፤ ስነ-ልቦናዊና የውስጠ ስሜት (emotional) ቁርኝነት ከልብ በመረዳት የሱሰኝነትን ስሜት በአወንታዊ መልኩ ለመግታት መታገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰዎች ሱሰኝነትን ካቆሙ በኋላ የድብርት ፤ የንዴትና የብስጭት ስሜት በሚሰማቸው ወቅት ከእነዚህ ስሜቶች ለመውጣት ወደ ተዉት የሱስ ህይወት ለመመለስ ያላቸው ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህን አጋጣሚዎች በብልሃት ማስተናገድ ይኖርባቸዋል፡፡

ምንጭ :  ZePsychologist