ከአድማስ ባሻገር ያለ የቅርብ ሩቅ አድርገን እንስለዋለን።

ህይወትን በአዲስ እይታ

 

Image result for ህይወትን በአዲስ እይታ

 

ብዙዎቻችን ህይወትን የምንደርስበት ግብ አድርገን ፣ነገ የምናገኘው፣ ከልፋት በኋላ የምንቀዳጀው፣ ከአድማስ ባሻገር ያለ የቅርብ ሩቅ አድርገን እንስለዋለን። ይህ ግን ዛሬን እንደ መራራው ኮሶ መድኃኒት እየተጋትን ነገን በሰማይ እናዳለችው ወተቷን እንደማናየው ላም እየናፈቅን የቅዠት ኑሮ፣ በተስፋ መቁረጥ የታጨቀ፣ መፍጨርጨር የተሞላበት ግቡን ቀና ብሎ የሚያይ ግን የችግሮች እንቅፋት የሚያገላድፈው እይታችን ነው። ይህንን እይታ የኑሮ መሰረታቸው አድርገው የትዳር አጋራቸውን ያለፍቃዳቸው የራቁ፣ ልጆቻቸውን የማይንከባከቡ፣ ለእራሳቸው በቂ ጊዜ የማይሰጡ፣ ነፍሳቸው የወደደችውን ነገር ማድረግ እንደ ቅንጦት የሚቆጥሩ ሞልተዋል። ይህ ደግሞ በስተመጨረሻ ቁሳዊ የሆነ ማንነት አሳቅፎ ብቻችንን ያስቀረናል።

ግን እስኪ ደግሞ በዚህ በኩል እንመልከተው! ህይወት ግብ ሳይሆን መንገድ ነው። እራሳችንን እያወቅን የምንጓዝበት፣ በመኖራችን ለውጥ የምናመጣበት፣ በስህተታችን ተምረን የምንቀየርበት፣ በገጠመኞች የተሞላ ወደ ተሻለ ማንነት የሚደረግ ጉዞ። ይህን እይታ ከያዝን ለነገ መኖርን እናቆማለን ማለት ሳይሆን ነገን እያሰብን ዛሬን እስከነ ጭራሹ ከመዘንጋት እንላቀቃለን። ግለኝነትን ያተኮረ የራሴ ጥቅም ብቻ እያልን በሰዎች ጫንቃ ላይ በመወጣጣት እኔን ብቻ ላኑር ከሚል ርካሽ አስተሳሰብ ከላያችን ላይ አራግፈን በዛሬ ውስጥ እራሳችንን ማግኘት ያስችለናል።

ዛሬ ጊዜ ያልሰጠናቸው ቤተሰቦቻችን ነገ “እንደዛ ስለፋ የነበረው አንተ የሻለ ኑሮ እንድትኖር በማሰብ ነው” “እንዲህ እንድትንደላቀቂ ብዬ ነው ቀን ከለሊት ስለፋ የነበረው” የሚል የየዋህነት አስተሳሰብ ያሳጣናቸውን ፍቅር እና አብሮነት አይተካም። ገንዘብ ለልጆቻችን ጃኬትን እንጂ ማቀፍ የሚሰጠውን የደህነትን ስሜት አይገዛም። ገንዘብ ውድ የሆነ ስጦታን እንጂ ከትዳር አጋራችን ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ አይገዛም፣ ገንዘብ አልጋን እንጂ እንቅልፍን አይገዛም፣ ገንዘብ ምግብን እንጂ የምግብ ፍላጎትን አይገዛም። ስለዚህ በእኛነታችን የምንሰጣቸውን፣ የገንዘብ ቁልል የማይገዛቸውን፣ የመኖር ሃብቶች፣ የህይወት ስጦታዎች የሆኑትን እኚህን የዛሬ ውጤቶችን አሳጥተናቸው ነገ ገንዘብ ብንሰጣቸው ዋጋው ምንም ነው።

ህይወታችንን ግብ አድርገን ከምንስለው በዕለትተዕለት ኑሮዋችን ውስጥ የምናደርጋቸው ማናቸውም ቁርኝቶች ድምር መሆኑን ብናምን ይህ አዲስ እይታ የብርሃን ጮራ በህይወታችን ላይ ይፈነጥቅልናል።

ምንጭ :  ZePsychologist

 

  

Related Topics