በየዘመኑ የሚመጡ ወይም የሚከሰቱ ልበል

 

ፋሽን እና የሰውነት ልክ!

 

 Image result for ፋሽን

 

በየዘመኑ የሚመጡ ወይም የሚከሰቱ ልበል? የልብስ፤ የጫማ፤ የፀጉር ወዘተ ፋሽኖች በሚገርም ሁኔታ ከውጭው ዓለም ወደ አገራችን ገብተው እግራቸውን ሲዘረጉ ጊዜ አይፈጅባቸውም፡፡ ከወጣት እስከ ጎልማሳ፤ አዲስ ነው የተባለውን አለባበስ፤የፀጉር አሰራርና አቆራረጥ ፤አፈሻሸን ወዘተ ወንዱም ሴቱም እያሳደደ ለራሱ ያደርገዋል፡፡ አንዳንዴ ፋሽን ተከታዮቹ የልብስ ሞዴል ( ፋሽን) ከዕድሜ፤ ከፆታ፤ ከባህልና ወግ እናም ማህበራዊ እሴት አንፃር ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? ብሎ ጥያቄና ሀሳብ፤ ጥቂትም ይሉኝታ ያላቸው አይመስልም፡፡

የምን ይሉኝታ፤ የምን ወግና ሥርዓት፤ ደግሞም ባህልና ልማድ? ከቶም ስለነዚህ ሀሳበ - ነገሮች፤ ማንም ምንም አይመስለውም፡፡ ብቻ አንዱ የአንዱን ያያል እናም ገበያ ይወጣል አዲሱን ፋሽን ልብስም ሆነ ጫማ ይገዛል ፤ ይለብሳል፡፡ አንዱ የአንዱን ያያል እናም ፀጉሩን ያጎፍራል ወይ ይላጫል ወይ ሹሩባ ይሰራል ወዘተ፡፡ ሴቶችም በተመሳሳይ መንገድ እንዲሁ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም በእዩልኝ ዐይነት አረማመድ በከተማ መሀል ግራና ቀኝ መንጎራደድ ነው፡፡ ማን ማንን ይታዘባል? አይታሰብም፡፡ ሁሉም በራሱ ፋሽን ውስጥ የራሱን ስሜት ያስተናግዳል፡፡

አሁን በዚያን ሰሞን በርካታ ወጣት ሴቶች «እምብርታቸውን» ለአደባባይ አጋልጠው በየጎዳናው ላይ ይንቀሳቀሱ ነበር፤ አሁንም አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡ከእምብርት በላይ አንዲት ትንሽ ጥብቆ ጣል አድርገው፡፡ እምብርት ታዬ አልታዬ «ኬረዳሽ!!» ዋናው ነገር ፋሽኑ ነዋ!! እና ብዙ ነገር ትታዘባላቸሁ፡፡

እንግዲህ ይህንን ፋሽን ጉድ እያልን ሳለን፤ በዚህ ሰሞን ደግሞ ከታች እስከ ጭን መጋጠሚያ ድረስ ግራ ቀኙ፤ አልፎ አልፎ ከታች ወደ ላይ በደረጃ የተቦተረፈ ጂንስ ሱሪ ሴቶች እህቶቻችን እየለበሱ በየአደ ባባዩ ይሄው እንትናን ተመልከቷት እያለ ይዞልን ቀርቧል፡፡ እኛም እምብርት ስናይ እንደከረምነው ይህን የተረገመ ሱሪ እና የሚያሳየውን እያየን ነው፡፡ ይህንን ጂንስ የለበሰች ሁሉ አታፍርም ማለት ነው!! ለምን ታፍራለች?! ፋሽን ነዋ!! ስለምንስ ባህልና ወግ ትላለች ?!! አዲሱ የፋሽን ውጤት የቸራት ጂንስ ነዋ!!

መቼም አለባበስ የግል እና የግል መብት ቢሆንም የሕብረተሰብን የቆየ እና መልካም የሆነውን ልማድና እሴት የሚጋፋ ሲሆን አደጋ አለው፡፡ እጅግ መልካም የሆነውን ማህበራዊ እሴት የሚንድ አካሄድ እና አደራረግ መከተል ውሎ አድሮ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

ቆራጣ ቀሚስ ለብሶ ገመናን እያሳዩ በጎዳና ላይ መውረግረግ ሥልጣኔና መሰልጠን አይመስለኝም፡፡ ደግሞስ የዚህ ዐይነቱ አለባበስ መልዕክቱ ምንድን ነው? በእርግጥ ቀደም ብዬ እንዳልኩት አለባበስ ይሁን ሌላ፤ ሌላ ነገር የግለሰብ ግላዊ መብት ቢሆንም ራስን ለተለያዩ ችግሮች አሳልፎ የሚሰጥን ነገር የሙጥኝ ማለትና በአብዛኛውም በብዙሃኑ ዐይን ውስጥ አስገብቶ ትዝብት ላይ የሚጥልን ድርጊት መኮናተር ተገቢነት ያለው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ይህ የአንዳንድ ወጣት ሴቶች የፋሽን ተከታይነት ድርጊት በአንዳንድ ወጣት ወይም ጎልማሳ ወንዶችም ላይ ይታያል፡፡ መቀመጫ ላይ ያረፈ ሱሪ ለብሶ፤ የውስጥ ሱሪን እያሳዩ፤ አንዳንዴም ወደታች እንዳይወርድ ወደላይ እየሳቡ በየመንገዱ እና በየታክሲው ውስጥ የሚታዩት ወንዶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ደግሞም አንዳንድ ወንዶች ድንገት በጎዳና ላይ ስታይዋቸው ወንድነታቸውን በመጠራጠር «ሴት ወይስ ወንድ» ብላችሁ እንድትጠይቁና እንድትጠራጠሩ ያደርጋችኋል፡፡ «በሚገባ የተሸረበ ሹሩባ፤ መሀሉ ቅቤ መቀባት የቀረው፤ ረዘም ያለ የጆሮ ጌጥ፤( ሎቲ ) ባለ ትልቅ መስቀል ሀብል፤ ሶስት ወይም አራት የመዳብ አምባር በቀኝ እና በግራ እጅ ተጠልቆ ማየት አጃኢብ! ነው የሚያሰኘው፡፡ ትልቁ የክርስትና መጽሐፍ እንዲህ ይላል «ክብራቸው በነውራቸው፤ … ነው» ነውር እና አሳፋሪ የሆነን ነገር አንዳንዶች እንደ ክብር እና ጌጥ ቆጥረውት፤ ማወቅ እና መሰልጠን አድርገውት ሲታይ ያሳዝናል!!

እምብርትን እርቃን አድርጎ መሄድ፤ ዕቃ ቢወድቅ ጎንበስ ብሎ ለማንሳት የሚያስቸግር ብጣቂት ቀሚስ ተብዬ መልበስ፤ መቀመጫ ደንደስ ላይ የሚቀር ሱሪ ተብዬ አጣብቂኝ ለብሶ ገመናን ለአደባባይ ዓይን እየቸረቸሩ መሄድ ምን የሚሉት የአለባበስ ወግ ነው? መቼም ይህ ጥያቄ ሥልጣኔ ያልዘለቀው ጥያቄ ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ቢባልም ግድየለም፡፡ በትዝብት ዓይን የታየ አጓጉልና ተገቢ ያልሆነን ነገር መሄስ፤ ማረቅና ከማህበረሰቡ መልካም ባህልና ልማድ ጋር እንዲታረቅ ማድረግ ተገቢ ነውና!!

በአጉል የፋሽን ወረራ የተማረኩ አንዳንድ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ይህንን የትዝብት ሀሳብ ላይቀበሉት ይችላሉ- በተለይ ሴቶች፡፡ በእርግጥ ሴቶች የብዙ ነገር ኃላፊነት ያለባቸው ፤ቤተሰብን በሙሉ ኃላፊነት የሚያስተዳድሩ፤ እጅግ የሚከበር ማንነትና ስብዕና ያላቸው ናቸው፡፡ በሕብረተሰቡም ውስጥ የማይተካ ሚና ባለቤቶቸ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ደግሞም በሁሉም አገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እኩል መሳተፍ የሚችሉና የሕብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች ይህን ዐይነቱን ማንነታቸውን የሚንድ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ ሊገኙ አይገባም። ስለሆነም መልካም ማህበራዊ እሴትንና ልማድን የሚፃረር ሁነት ውስጥ የሚገቡ አንዳንድ የአጉል ፋሽን ተከታይ ሴቶችን እንዲሁም ወንዶችን በየአጋጣሚው ሁሉ ማውገዝና ድርጊታቸውን መቃወም ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

እውነት ነው፤ ወጣት ሴቶችና ወንዶች የብዙ አዳዲስ ነገሮች ተቀባይና ለአዲስም ነገር ጉጉ ናቸው። ይህ ለአዲስ ነገር ጉጉ መሆናቸው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን አሳልፈው ለአደጋ እንዲያጋልጡ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ «ዛፍን በለጋነቱ፤ ልጅን በልጅነቱ» እንዲሉ እናት እና አባት፤ ዘመድ፤ ወዳጅ በታዳጊነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆቻቸውን፤ ዘመዶቻቸውን መልካሙን ማህበራዊ እሴት፤ ወግና ልማድ እንዲጠብቁ፤ የመልካም ማህበራዊ ኑሮ መገለጫዎችን እንዲያከብሩ በማስተማር በኩል የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንም በዚህ ረገድ ኃላፊነት አለባቸው- በሁለት አቅጣጫ፡፡ አንደኛ በየሚዲያው ወጣቶችን አስመልክቶ በሚቀርቡ ፕሮግራሞች ላይ መልካሙን አገራዊ ባህልና ልማድ፤ ወግና እሴት፤ ማስገንዘብ፡፡ ሁለተኛ በየሚዲያው የሚተላለፉ በተለይም በቴሌቪዥን በሚቀርቡ ፕሮግራሞች ላይ ወጣቶች ወደተሳሳተ አቅጣጫ እንዲያመሩ የሚያደርጉ ዝግጅቶች እንዳይተላለፉ፤ በመዝናኛ ስም የሚቀርቡ አሼሼ ገዳሜዎች፣ የዳንስ ዐይነቶች እና ለወሲብና ለዝሙት የሚያነሳሱ እንቅስቃሴዎች ላይ ማዕቀብ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶቻችን ስብዕና እንዳይረክስብን ለመከላከል ያግዘናል። በቴሌቪዥን መስኮት ለሚቀርቡ ፕሮግራሞች ከፍተኛ ትኩረት መስጠትና ጥንቃቄ ማድረግ አንድ ትልቅ ጉዳይ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

ፀሐፊው የአዳዲስ ነገር ተቃዋሚና ፋሽን ጠል አይደለም፡፡ ነገር ግን ከመስመር የወጣና አገራዊ እና ማህበራዊ መልካም እሴትና ባህልን የሚንድ መሆን እንደሌለበት ያምናል። የወጣቶቻችንን ስብዕና የሚያጎድፍና የሚያረክስ አደገኛ ባህላዊ ወረራን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ ፀሐፊው ወግ አጥባቂም አይደለም፡፡ ይሁንና በፋሽን ስም የሚቀርበውን የሌሎችን ባዕዳን የአፍዝ አደንግዝ ሥራና ማህበራዊ እሴትን ወደ ገደል እንዲገባ የሚያደርግ እንቅስቃሴን ግን በእጅጉ ያወግዛል፡፡

በፋሽንና በዘመናዊነት ስም፤ አንዳንድ ወጣቶቻችን «ማን አለኝ ከልካይ ያሻኝን ባይ» በሚል እሳቤ መልካሙን አገራዊ ልማድና እሴት ለመስበር መሞከር አደጋ አለው ነው- የፀሐፊው ሃሳብ፡፡ ማህበራዊውን የቆየ መልካም ልማድና እሴት መጣስ ውሎ አድሮ ችግር ነው የሚያስከትለው። ማን ምን ያመጣል ይሉ አስተሳሰብ፤ በገዛ ማንነቴ ማን ይገደዋል ብሎ «የአስረሽ ምቺውን» ፀረ መልካም እሴት እና ልማድ የሆነውን ከበሮ ለመደለቅ መሞከር ብዙ የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡

በየዘመኑ መልኩን እየለዋወጠ ከአውሮፓ፣ አሜሪካና ኤሽያ በእነርሱው ንፋስ ታጅቦ ምድራችን ላይ ዱብ የሚለው ፋሽን አብዛኛው አቅሉን አጥቶ አቅል የሚያሳጣ፤ ቀዳዳንና ጨምዳዳን ውበት እና ጌጥ አድርጎ የሰውን ልጅ ክብር የሚያቃልለውን፣ ዝቅ አድርጎ የሚያሳይን ነገር ክቡር ንዑድ ነው እያለ የሚያቀርበውን፤ ነውርን ክብር አድርጎ የሚያውጀውን ተግባሩን ጭምር እምቢኝ ማለት ከወጣት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ይጠበቃል ብዬ አስባለሁ፡፡

የፋሽን ገመድ አንገታችን ላይ እያሰሩ ወደ አልተገባ መንገድ የሚስቡንን በየትኛውም የዓለም ጎራ ያሉ ነጋዴዎችን ሀሳብና ፈቃድ አውቀን አሁንም እምቢ ማለት መቻል አለብን፡፡ በፋሽን ወረራ እጃችንን ወደ ላይ ሰቅለን የሰውነታችንን ልክ አዋርደን ገመናችንን ሜዳ ላይ ጥለን ምርኮኞች ልንሆን በፍፁም የተገባ አይደለም፡፡

የፋሽን ዐይነት አለው፡፡ ሰውም ልክ አለው፡፡ የሚሰፋውን ከሚጠበው፤ የሚያምርበትን ከማያምርበት የመለየት የዕውቀትና የማንነት አቅምና ልክ አለው፡፡ ማህበራዊ እሴትንና ኑሮን የሚያከብር ልክ! የአጉል ፋሽን ወረራን የሚከላከል የሰውነት ልክ!! ዘወትር ይህ ልክ ተፈላጊና አስፈላጊ ነው !

Source: addisadmassnews