ሀገራችን አስቀድሞ በመከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ እንዳላት

የስኳር በሽታ ለአይን ህመም እንዴት ያጋልጣል?

 

የስኳር በሽታ ለአይን ህመም እንዴት ያጋልጣል?

 

አስቀድሞ በመታከም አይነስውርነትን እንከላከል፤

 

ሀገራችን አስቀድሞ በመከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ እንዳላት ይታወቃል፡፡ በመሆኑም መከላከልን መሰረት ያደረገው አሰራር የዘርፉን ስኬት አጋዥ የሆኑ ውጤቶች ለማስመዝገብ አስችሏል። የህክምና ባለሙያዎችም ሰዎች በተወሰነ ጊዜ ያሉበትን የጤና ሁኔታ በሀኪም የመታየት ባህል ቢያዳበሩ ለክፉ የጤና ችግር ሳይጋለጡ እራሳቸውን ማዳን እንደሚችሉ መምከራቸውን ተያይዘውታል፡፡ ይሁን እንጂ ምክሩን ተቀብሎ በተግባር የሚያውለው እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ነው ከባለሙያዎቹ ለመረዳት የሚቻለው፡፡ይህም የሆነው ማህበረሰባችን ጤናማ ሆኖ የጤና ምርመራ የማድረግ ባህል ባለማዳበሩ እንደሆነ ይታመናል፡፡

«ታሞ ከመሟቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ» የሚለውን ብሂል በመዘንጋት ካልባሰበትና አልጋ ላይ ካልወደቀ በቀር ወደጤና ተቋም የሚሄደው የማህበረሰብ ክፍል ዝቅተኛ መሆኑ አይካድም፡፡ እንዲህ ያለው ልማድ መቅረት እንዳለበት አሁን አሁን እያጋጠሙ ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮች ምልክት እያሳዩ ነው፡፡ ባለሙያዎቹም « ታሞ ከመማቀቅ...» የሚለው ሀገረኛ ብሂል ጊዜው አሁን መሆኑን በአንክሮ እየተናገሩ ነው። ምክንያቱም መከላከል ላይ የተመሰረተው የጤና ፖሊሲ ስኬታማ የሚሆነው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የራሱን ጤና በራሱ ማምረት ሲችል ነው። ህበረተሰቡ ጤናውን በራሱ የሚጠብቀው ደግሞ ከማንኛውም በሽታ አስቀድሞ መከላከል ሲችል እንደሆነ ልብ ይሏል። በመሆኑ ያለበትን የጤና ሁኔታ ቀድሞ ማወቁ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሚሆን ነው ባለሙያዎቹ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚናገሩት።

ብዙ ሰዎች የጤንነታቸውን ሁኔታ አስቀድመው ለመከታተል ጥረት ባለማድረጋቸውና ታመውም በወቅቱ ባለመታከማቸው ለከፋ የጤና ችግር እየተዳረጉ ነው፡፡በተለይ ለውስብስብ የጤና ችግር የሚያጋልጠውን ህመም ለመከላከል በተወሰነ ጊዜ በሀኪም መታየት፣እንዲሁም ለተለያየ የጤና ችግር ከተጋለጡ በኋላም ሙሉ ምርመራ ማድረግ ችግሩ ህመሙ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ መፍትሄ ለማበጅት ያግዛል፡፡

ለውስብ ወይም ለተጓዳኝ የጤና ችግር ከሚዳርጉ የበሽታ አይነቶች አንዱ የስኳር ህመም በመሆኑ ህሙማን የህክምና ክትትላቸው ስኳሩን ለመቆጣጠር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በሽታው በሌላ አካላቸው ላይ ጉዳት ማስከተልና አለማስከተሉንም በህክምና ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ነው የህክምና ባለሙያዎች የሚመክሩት፡፡ የስኳር ህመም በተጓዳኝ ከሚያሰከትለው በርካታ የጤና ችግሮች መካከል በአይን ላይ የሚያሰከትለውን ጉዳት ትኩረት አድርገን ከባለሙያ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

የኢትዮጵያ የአይን ሀኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንትና የአይን ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ፍጹም በቀለ ይባላሉ። ከስኳር ህመም ጋር በተያያዘ የአይን የጤና ችግር እንዴት እንደሚከሰትና የችግሩንም አሳሳቢነት በምን ደረጃላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ በተፈጥሮ ለሰውነታችን የሚያሰፈልገው ኢንሱሊን የሚባለው ንጥረ ነገር ከሚፈለገው መጠን በላይ ሲሆን ለስኳር በሽታ እንጋለጣለን፡፡ የስኳር በሽታ አንዱ በህጻንነት ዕድሜ የሚጀምረው ሲሆን ሌላው ደግሞ ከጊዜ በኋላ በሰውነት ክብደት መጨመር ወይም በሌላ ምክንያት የሚከሰተው ነው፡፡የስኳር በሽታውም የአንዱ ከሌላው ይለያል፡፡በመሆኑም የሚያስከትለው የጤና ችግር ውስብስብነትም የዛኑ ያህል ይለያያል፡፡

የስኳር በሽታ ከሚያጠቃው የተለያዩ የሰውነት ክፍል ውስጥ አንዱ አይን ነው፡፡ስኳር ታማሚው ከሌሎች በተለየ ለጥቃት የሚዳረገው የህመምተኛው የሰውነት መከላከያ ኃይሉ የቀነሰ በመሆኑ ነው፡፡የስኳር ህመም አይንን የሚያጠቃውም ባለቀለሙንና ብርሃን የሚቀበለውን ሬቲና የተባለውን የአይናችንን ክፍል ነው፡፡ጉዳት የሚያሰከትለውም ቀጫጭን የሆኑትን የደም ስሮች በማጥቃት ነው፡፡የደምስሮቹ ሲጎዱ ጥቁሩ የአይን ክፍል ይቆስላል፡፡ አይን ብርሃን ለማየት ይቸገራል ወይም ይፈራል፡፡ ብርሃኑ አንፀባርቆም እንባ እንዲፈስ ያደርጋል፡፡በጥቁሩ ዘሪያ ያለው ነጩ የአይን ክፍልም ይቆስላል፡፡ ከፍተኛ ህመምም ይኖራል፡፡ በእነዚህ የመጀመሪያ ምልክቶች በህክምና መከላከል ካልተቻለ ከፍ ወዳለ የጤና ችግር ሊሸጋገር ይችላል፡፡

ሬቲና የተባለው የአይን የውስጥ ክፍል በጣም ከተጎዳ ችግሩ የማየት ችሎታን እስከመቀነስና ባስ ሲልም አይነስውርነትን እሰከማስከተል ይደርሳል፡፡ በደም ስሮቹ ላይ ጉዳቱ እየበረታ ሲሄድ ሬቲና ላይ የደምስሮች ደም መርጨት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡ በአካባቢውም አዳዲስ የደምስሮች ሊያቆጠቁጡ ይችላሉ፡፡ አዳዲስ የሚያቆጠቁጡት የደም ሰሮች እንደቀድሞ ተፈጥሯዊ ባለመሆናቸው ለአይኑ መጎዳት መንስኤ ይሆናሉ፡፡ይሄ በጣም አደገኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚከሰት መሆኑን ነው ዶክተር ፍፁም የሚናገሩት፡፡ የስኳር በሽታ እንዲህ ያለውን የከፋ የጤና ችግር የሚያስከትለው በአንድጊዜ ክስተት አይደለም፡፡ስኳሩ በጊዜ ሂደት በደምስሮቹ ላይ በሚደርሰው ጉዳት ነው፡፡ደምስሮቹን ሲበጣጥሳቸው ነው ችግሩ የሚከሰተው፡፡

ዶክተር ፍፁም የጉዳቱን መጠን ከጠቀሱ በኋላም የህክምና መፍትሄ እንዳለውም ይገልጻሉ፡፡ ሰዎች ከስኳር በሽታ አጋላጭ ነገሮች መቆጠብ ቀዳሚው መፍትሄ ነው፡፡ ችግሩ ካጋጠመ በኋላ ስኳሩን መቆጣጠር ከቻሉና በሀኪም የሚሰጠውን ምክር ከተገበሩ ስጋቱን መቀነስ ይቻላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአይን ጠብታ መድኃኒ፣በመርፌ፣ በጨረር እና በቀዶ ህክምና ቀድሞ በማከም መርዳት ይቻላል፡፡ ህክምናው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም የህክምና ተቋማት በተሟላ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን ዶክተር ፍጹም ይጠቁማሉ፡፡ በጨረር የሚሰጠው ህክምናን ሲያስረዱም «የሬቲናውን ግድግዳ እንደመበየድ ማለት ነው»ይላሉ ይህ በሚሆንበት ወቅት ለታማሚው ከባድ ይመስላል፡፡ ህክምናው ሲደረግ ሙሉ ለሙሉ ፈውስ እስኪገኝ ድረስ ታማሚው እንደቀድሞው ቶሎ ብርሃን ላያገኝ ይችላል፡፡ አንዳንድ ታማሚዎች ህክምናውን ባለመረዳት የጨረር ወይም የመርፌ ህክምናውን ከወሰዱ በኋላ የአይናቸው ብርሃን እንደቀነሰ አድርገው የሚገምቱ መኖራቸውን አስተውለዋል፡፡ የህክምናው ባህሪ በመሆኑ ችግር እንዳልሆነ በመረዳት በትእግስት ህክምናው አስኪጠናቀቅ ድረስ መከታተል እንደሚገባም ያስርዳሉ፡፡

እንደ ዶክተር ፍፁም ገለጻ ህክምናውን ማቋረጡ የጤና ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ማቋረጡ በአንድ የጨረር ወይም የመርፌ ህክምና ሊድን የሚችለውን አይን ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ህክምና እንዲደረግ መንገድ የሚከፍት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም መክረዋል፡፡የተጀመረውን ትቶ እንደ አዲስ ህክምና መጀመሩም ጉዳት እንዳለው አሳስበዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከስኳር በሽታ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የአይን በሽታ አሳሳቢ መሆኑንና ለአይነስውርነትም እየዳረገ መሆኑን መረጃዎች በስፋት እንደሚያሳዩ በመጠቆም ህብረተሰቡ ትኩረት እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምንጭ፡-  አዲስ ዘመን ጋዜጣ