ባለሁለት ሻኛ ግመል (ባክቴሪያን ካሜል) ከቀሩት ሁለት የግመል ዝርያዎች አ

ባለሁለት ሻኛ ግመል

 

 

ባለሁለት ሻኛ ግመል (ባክቴሪያን ካሜል) ከቀሩት ሁለት የግመል ዝርያዎች አንዱ ሲሆን፣ መገኛውም ሰሜን እስያ ነው፡፡ ኤቱዜድ አኒማል ድረ ገጽ እንዳሰፈረው፣ በሚልዮን የሚቆጠሩ እነዚሁ ዝርያዎች ከሰሜን እስያ ባለፈ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ይገኛሉ፡፡ ምድባቸው ከቤት እንስሳ ሲሆን፣ ለሰዎችና ዕቃ ማጓጓዣ ያገለግላሉ፡፡ ለምግብነትም ይውላሉ፡፡

 

ነጠላ ሻኛ እንዳላቸው የግመል ዝርያዎች፣ ባለሁለት ሻኛዎቹም ለረዥም ጊዜ ውኃ ሳይጠጡ መቆየት፣ በረሃ ማቋረጥም ሆነ ተራራና ቁልቁለት መውጣትና መውረድ ይችላሉ፡፡

 

በቡናማ ቀለም ፀጉራቸውም የሚለዩት እነዚሁ ግመሎች፣ ከ1.7 ሜትር እስከ 2.1 ሜትር ይረዝማሉ፡፡ ክብደታቸው ከ600 ኪሎ ግራም እስከ 816 ኪሎ ግራም ይደርሳል፡፡ በሰዓት እስከ 64 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላሉ፡፡ የመኖር ዘመናቸውም ከ35 እስከ 50 ዓመት ነው፡፡

 

ጥራጥሬና ቅጠላቅጠል የሚመገቡ ሲሆን፣ ምግብ ባጡ ጊዜ አጥንትና የሞቱ እንስሳትን ሊመገቡ ይችላሉ፡፡ ረሃብ ከጠናባቸው ገመድ፣ ጫማና እንደ ድንኳን ያሉ ጨርቆችን ይመገባሉ፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ