ከአራት ሴቶች አንዷ የልብ ህመም ተጠቂ እንደሆነች ጥናቶች ያሳያሉ።

የልብ ጤናን ለመጠበቅ የሚረዱ 10 ምግቦች!

 

የልብ ጤናን ለመጠበቅ የሚረዱ 10 ምግቦች!

 

ከአራት ሴቶች አንዷ የልብ ህመም ተጠቂ እንደሆነች ጥናቶች ያሳያሉ።

የልብ ህመም ከጡት ካንሰር ህመም በሶስት እጥፍ የከፋ አደጋ እንደሚያደርስም ነው የሚነገረው።

እናም የልብ ጤናን በመጠበቅ ህመሙን አስቀድሞ መከላከልና የከፋ አደጋ ሳያደርስ መቆጣጠር ይቻላል።

የልብንም ሆነ መላው ጤንነታችን ለመጠበቅ የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ ተገቢ መሆኑ አያጠያይቅም።

የስነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ሳራህ ፍላወር በተፈጥሯዊ መንገድ የልባችንን ጤና ለመጠበቅ የሚረዱ ያሏቸውን 10 ምግቦች ከዚህ በታች ዘርዝረዋል።

መጠነኛ ለውጥ ትልቅ ልዩነት መፍጠር ይችላልና የሳራህን ጥቆማዎች ከማዕዳችን እየቀላቀልን ብንወስዳቸው መልካም ነው።

 

በባለሙያዋ ለልብ ጤና ይበጃሉ የተባሉት 10 ምግቦች እነዚህ ናቸው፦

 

1. ነጭ ሽንኩርት

በርካታ ቫይታሚኖች እና አንቲኦክሲደንትስ የያዘው ነጭ ሽንኩርት ለልብ ጤንነት ወሳኝ ነው።

በነጭ ሽንኩርት ውስጥ የሚገኘው አሊሲን የተሰኘ ንጥረ ነገር ጠቃሚ ያልሆነ የኮሊስትሮል መጠን እና የደም ግፊትን በመቀነስ የልብ ህመምን ይከላከላል።

አንዳንድ የካንሰር አይነቶችን እና ከፍተኛ የመርሳት በሽታን ለመከላከልም ይረዳል።

 

2. ቲማቲም

ቲማቲም ከፍተኛ የደም ግፊትን ለመቀነስ በሚረዱ ላይኮፔን የተሰኙ አንቲኦክሲደንትስ የተሞላ ነው።

በዚህም የደም ግፊትን፣ የልብ ህመምን እና የማይጠቅም ኮሊስትሮልን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተረጋግጧል።

ከፍተኛ የላይኮፔን ይዘትን ለማግኘት ቲማቲምን በመቀቀል አልያም የስብ ይዘት ካላቸው እንደ አሳ ዘይት ጋር አዋህዶ መመገብ ያስፈልጋል።

 

3. ዘይታማ አሳ

በኦሜጋ 3 የበለፀጉ የአሳ አይነቶች የሴለኒየም፣ ቫይታሚን ዲ እና ፕሮቲን ሁነኛ መገኛ ናቸው።

አሳ የልብ ህመምን ከመከላከል ባለፈ የደም መርጋትን ለመቀነስም ያግዛል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የኦሜጋ 3 ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ አሳዎችን የሚመገቡ ሰዎች ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው።

የብሪታንያ የልብ ህመምተኞች ማህበር በልብ ህመም የተጠቁ ሰዎች በሳምንት ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ በኦሜጋ 3 የበለፀጉ ምግቦችን እንዲወስዱ ይመክራል።

 

4. ቀረፋ

ቀረፋ በደም ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር እና የስኳር በሽታ ለመከላከል ይረዳል።

የደም ግፊትን እና ጠቃሚ ያልሆነ ኮሊስትሮልን ለመቀነስ እንዲሁም እንደ ካንሰር እና ከፍተኛ የመርሳት በሽታ (አልዛይመር) ያሉ በሽታዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስም ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።

 

5. አረንጓዴ ሻይ

አረንጓዴ ሻይ በስፋት በሚጠጣባት ጃፓን በተደረገ ጥናት አረንጓዴ ሻይ መጠጣት በልብ ህመም ምክንያት የሴቶች የመሞት እድልን በ31 በመቶ፤ የወንዶችን ደግሞ በ22 በመቶ መቀነስ ያስችላል።

 

6. የወይን ፍሬ

የወይን ፍሬ ሌላኛው በቫይታሚን ሲ፣ ፋይበር፣ ኮሊን እና ላይኮፔን የተሞላ ፍራፍሬ ነው።

የወይን ፍሬ በትልቁ የደም ስር ተከማችተው የደም ዝውውርን የሚገቱ ጠጣር ነገሮችን መጠን ለመቆጣጠርም ያግዛል።

በተለይም ቀይ የወይን ፍሬዎች ከፍተኛ የላይኮፔን ይዘት ስላላቸው የማይጠቅም ኮሊስትሮል መጠንን ለመቀነስ ይጠቅማሉ።

 

7. አቮካዶ

በርካታ የጤና በረከቶች ያሉት አቮካዶ በቫይታሚን ቢ6 የበለፀገ በመሆኑ ሆርሞኖችን ለመቆጣጠር ይረዳል።

አቮካዶ የቫይታሚን ኢ እና ሞኖሳቹሬትድ ፋት ይዘት ስላለውም አላስፈላጊ ኮሊስትሮልን ለማውረድ ከፍተኛ ሚና አለው።

የደም ቧንቧዎች መዘጋትን በመከላከል ረገድም ጠቀሜታው የጎላ ነው።

 

8. ጥቁር ቼኮሌት

ጥቁር ቼኮሌት በፍቅር ስንወድቅ በአዕምሯችን ውስጥ የምናመነጨውን ፌኔታይላሚን የተሰኘ ኬሚካል ይዟል።

በፍላቭኖድስ የተሞላው ጥቁር ቼኮሌት ከፍተኛ የደም ግፊትን ለመቀነስ እና የምግብ መፈጨትን ለማቀላጠፍ ብሎም ስብን ለማቃጠል ይረዳል።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጥቁር ቼኮሌት ውስጥ የምናገኘው አንቲኦክሲደንትስ በትልቁ ደም ቧንቧ ስር የሚጣበቅ ጎጂ ኮሊስትሮልን ይከላከላል።

 

9. የአጃ ሾርባ

ቤታ ግሉካን በተሰኘ ፋይበር የበለፀገው አጃ ጠቃሚ ያልሆነ የኮሊስትሮል መጠንን ይቀንሳል። በዚህም የልብ ህመምን ለመከላከል ፋይዳ ይኖረዋል።

 

10. የጨው ፍጆታን መቀነስ

ጨው የበዛባቸውን ምግቦች እና መጠጦች መውሰድ ለከፍተኛ የደም ግፊት እና የልብ ህመም የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።

በየቀኑ ከምንጠቀመው የጨው ፍጆታ 1 ግራም ብንቀንስ በየአመቱ በልብ ህመም እና ስትሮክ ከሚሞቱት መካከል የ6 ሺህ ሰዎችን ነብስ ማዳን ይቻላል ነው የተባለው።

 

 

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk/

 

 

 

  

Related Topics